ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, December 17, 2014

በአዲሱ የአውሮፓውያን 2015 ዓም ዓለም ለአዲስ የፖለቲካዊም ሆነ የምጣኔ ሀብታዊ የቅርፅ እና የይዘት ለውጥ እየተዘጋጀች ይመስላል (የጉዳያችን ጡመራ ምልከታ)



ከፍልስጤም እስከ ኩባ 

ዛሬ ሮብ ታህሳስ 8/2007 ዓም አዲሱ የፈረንጆቹን ዓመት ሊገባ አስራ ሶስት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።በእዚሁ ዕለት ግን ላለፈው ግማሽ ክ/ዘመን ያልተፈቱ የፖለቲካ ውጥረቶች አዲስ ቅርፅ እና ይዘት መያዛቸው ተነግሯል።ከእዚህ ውስጥ የመጀመርያው  የአሜሪካ እና የኩባ ግንኙነታቸውን ሊያድሱ መሆኑ ዛሬ መነገሩ ነው።ይህ ማለት አሜሪካ እና ኩባ ከ1954 ዓም ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይኖራቸዋል ማለት ነው።

ሁለተኛው  በስዊድን የተጀመረው እና ለዓለማችን ትልቁ የፀጥታ ችግር የሆነውን የፍልስጤም  ግዛት በመንግስትነት የመታወቅ ጥያቄ ጉዳይ ነው።ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኃላ የፍልስጤም ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ቢተላለፍበትም ተግባራዊ መሆን ያልቻለው የፍልስጤም የመንግስትነት የመታወቅ ጉዳይ ዛሬ የአውሮፓ ሕብረት ''በመርህ ደረጃ'' የፍልስጤምን  መንግስትነት ማወቁን በመግለፅ ድምፅ ሰጥቷበታል።የሩስያ የመገናኛ ብዙሃን ''ለይምሰል'' (symbolic) በማለት የጠሩት ይህ ውሳኔ ምን ያህል  በመካከለኛው ምሥራቅ የኃይል ሚዛን ላይ ተፅኖ እንደሚኖረው በሂደት የሚታይ ጉዳይ ይሆናል። 

በሌላ በኩል ይህ ዕውቅና የመስጠት ሂደት ከእስራኤል  የሚገጥመው የተግዳሮት ደረጃ የከፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።ከእዚህ ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ለዘመናት አሸባሪ ያለውን ''ሐማስን'' ከአሸባሪነት መዝገብ መፋቁ ሌላው ከፍልስጤም ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዛሬ የተደመጠ አዲስ ዜና ነው።እስራኤል በተለይ የሀማስ ከሽብርተኛ መዝገብ መነሳት ''መውጊያው ባንተ ይብሳል'' የሚል ቃና ያለው ንግግር ተናግራለች።''የሐማስ ችግር ከእስራኤል ይልቅ ለእራሱ ለአውሮፓ ይከፋል'' ነበር እስራኤል ያለችው።

የሩስያ ጉዳይ 

ሌላው ከላይ ከተጠቀሱት የዛሬው የሃገራት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ለውጦች ጋር በቀጥታ ግንኙነት የሌለው የሚመስለው ግን የቀዝቃዛው ጦርነት መፋፋም አመላካች የሆነው እና በክረምያ ጉዳይ ሳብያ በሩስያ ላይ እቀባ ያወጀው የምዕራቡ ዓለም የሩስያ ገንዘብ ሩብል መውረዱን በመገናኛ ብዙሃኑ ደጋግሞ እየተናገረ ነው።የሩስያ ቲቪ (አር ቲ) በተቃራኒው የሩብል መውረድ ''የሩብልን ትክክለኛ ዋጋ አያሳይም።ጊዜያዊ 'ንዝረት' ነው'' እያለ ነው።ነገ ሐሙስ ታህሳስ 9/2007 ዓም  የሩስያው ፕሬዝዳንት ፑቲን  በጉዳዩ ላይ የቀጥታ ንግግር  ለህዝባቸው ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ዛሬ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ''ሩስያ ከዓለም ኢኮኖሚ እየተገለለች ነው።ይህም ለዓለም ሕግ ያለመገዛቷ ውጤት ነው'' ሲሉ ለፓርላማ ተሰብሳቢዎቻቸው ተናግረዋል።ሁኔታውን ለተመለከተ ግን ሩስያ ከምዕራቡ ገበያ በእቀባ ስምም ይሁን በሌላ መራቋ የበለጠ የማጠንከር ከእዚያም አልፎ ከደቡብ እስያ ሃገራት ጋር ልትመሰርት ካለችው የገበያ ቀጠና ጋር ከምዕራቡ ምጣኔ ሀብት ያላትን ትስስር እያላላ ወደ እስያ አድማሷን ያሰፋላት እንደሆነ እንጂ ትልቅ ንዝረት ይፈጥራል ተብሎ ማሰብ ይከብዳል።ይልቁንም ሩስያ ከምዕራቡ  ገበያ በተገለለች ቁጥር የእራሷን የንግድ ቀጠና ለመፍጠር እና ወደ ባልካን ሀገሮች መስፋፋቷ ልትቀጥል ትችላለች።ከእዚህ ሁሉ ጋር ግን የዓለማችን ትልቁን የመሬት የቆዳ ስፋት የያዘች ባለ 146,300,000  ሕዝብ (የአለምን 2.03%) የያዘች ሀገርን ማግለሉ እና ትንሿን ኩባ ማቅረቡ ውጤቱ  ምን እንደሚሆን ወደፊት የምናየው ነው።

ለእዚህም ይመልሳል ጅም ዮንግ ኪም የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዛሬ ''ለሲ ኤን ኤን'' ቴሌቭዥን  እንዳሉት ''የሩስያ ኢኮኖሚ ግዙፍ ኢኮኖሚ ነው በአለማችን ምጣኔ ሀብት ላይም ተፅኖ አለው'' በማለት በጉዳዩ አሳሳቢነት ላይ አፅንኦት የሰጡት።

የነገሮች መፍጠን ግን ዓለም በ2015 እ አውሮፓውያን አቆጣጠር ለሆነ ነገር እየተዘጋጀች ይመስላል።ለሆነ ነገር።ለምን?  የሚለውን አሁን መግለፅ አይቻል ይሆናል።ነገር ግን ለግማሽ ክ/ዘመን የቆዩ ጉዳዮች በውስጥ ድርድር አልቀው አዲስ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ይዘው ብቅ የሚሉት ከመጪው ዓመት የሀገራት ስልታዊ አካሄድ ጋር የትዛመደ እንደሚሆን መገመት ይቻላል።እርግጥ የፍልስጤም ጉዳይ የምዕራቡ ዓለም ከመካከለኛው ምስራቅ በተደጋጋሚ የሚነሳው የሽብርተኝነት ትንኮሳ አንዱ መነሻ የሚያደረገው የፍልስጤምን ጉዳይ በመሆኑ ጉዳዩን ለማስተንፈስ አይነተኛ መልስ መስጠት አስፈላጊነቱ ታምኖበት ይሆናል።ሆኖም ግን ጉዳዩ ከእስራኤል አንፃር የሚኖረው ምላሽ እና ከአሜሪካ ጋር ያላት የጠበቀ ግንኙነት ያለው ተፅኖ ገና አልተለካም።በተለይ በሐማስ አንፃር ያለው ጉዳይ ትልቅ የዓለማችን ትኩሳት መሆኑ አይቀርም።

ዓለም አቀፍ ሕግ  ከዓለም አቀፍ ተቋማት እጅ መውጣት 

በእዚህ ሁሉ መካከል የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ስልታዊ ተፈላጊነት እና የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው ሀገሮች የውስጥ ቅራኔዎቻቸውን ተከትሎ የዓለም አቀፉ የምጣኔ ሀብት ጦርነትም ሆነ ፖለቲካዊ ግፍያ ሳይነካካቸው ማለፍ አይችልም።ለእዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት የሚሆነው ዓለም አቀፍ ሕግ ቀስ በቀስ እንደ ተባበሩት መንግሥታት ካሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት እጅ እየተንሸራተተ መምጣቱ ነው።ከ1982 ዓም ከሩስያው  ሚካኤል ጎርባቾቭ ''ግልፅነት ወይንም ግላስኖስ'' ፖሊስ ወዲህ በዓለም አቀፍ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ከተባበሩት መንግሥታት ይልቅ ቀድማ አሜሪካ እና የጦር ሸሪኮቿ ''ናቶ'' በአለማችን ላይ የተነሱትን የፀጥታ ችግሮች  መፍትሄ ጉዳይ  ላይ መክረው ከጨረሱ በኃላ  ወደ  ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክርቤት የሚወስዱበት አግባብ ተለምዷል።ለእዚህ ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል።የኔቶ ወረራ በኢራቅ (አንደኛ እና ሁለተኛው)፣በቀድሞዋ ዩጎዝላቭያ ላይ የኔቶ ጣልቃ መግባት ፣በአፍጋኒስታን ላይ እና በሊብያ ላይ የተደረጉት ዘመቻዎች ሁሉ ከተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውይይት ይልቅ የኔቶ ቁርጠኝነት ተጠብቆበታል።

ሆኖም ግን ሩስያ ዘግይታም ቢሆን የምዕራቡን ዓለም የተገዳደረችው ፕሬዝዳንት ፑቲን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ ያውም በሶርያ ጉዳይ ላይ ሩስያ የፀጥታው ምክር ቤትን ውሳኔ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷ ውድቅ አድርጋ ''ሶርያ ሊብያ እንድትሆን አልፈቅድም'' ብለው ፕሬዝዳንት ፑቲን ከተናገሩ በኃላ ነበር።ፕሬዝዳንት ኦባማ ደጋግመው ፕሬዝዳንት ፑቲንን ለማግባባት ሞከሩ ፑቲን ይብሱን ''ከአልቃይዳ የባሱ አሸባሪ ሰው በላዎች'' ያሏቸውን የሶርያ ፅንፈኛ አማፅያንን ''የምዕራቡ ዓለም መደገፉ ምን ያህል ሰዋዊ አስተሳሰብ እንደራቀው ያሳያል'' ሲሉ በግልፅ ተናገሩ።የምዕራቡ ዓለም ሩስያን ማግለል ጀመረ።በቡድን ስምንት ጉባኤ ላይ ሩስያ ለመጀመርያ ጊዜ ወደኃላ ቀረች።በቅርቡ በተደረገው የቡድን 20 ስብሰባ ላይ እንደ አልጀዝራ ጋዜጠኛ አባባል ''ፑቲን ምሳ ሲበሉም እንዲገለሉ ተደረጉ'' ካለ በኃላ ጋዜጠኛው ''ግን ፑቲንን አጥብቀው የምፈልገው ማን ነው የምዕራቡ ዓለም ነው ወይስ? እና ያገለለው ማነው ፑቲን የምዕራቡን ዓለም አገለሉ ወይስ ምዕራባውያን ሩስያን አገለሉ?'' ብሎ ይጠይቃል።

ከሶርያ ጉዳይ በኃላ የሩስያ ዳግም ''ለአቅመ ልዕለ ኃያልነት'' ሰውነቷን እያሟሟቀች መሆኑን ምዕራቡ ዓለም አወቀ።ትንሽ ዘግይቶ ቅርቡ በዩክሬን ጉዳይ የክሬምያን ጉዳይ ሩስያ የያዘችበት አግባብ የምዕራቡን ዓለም የበለጠ አስደነገጠው።የኢኮኖሚ እቀባ ታወጀ፣የሩስያ የጋዝ ሽያጭ የሚያሳስባት ጀርመንም እያቅማማችም ቢሆን ገባችበት። ሩስያ ባንፃሩ ከአውሮፓ እና አሜሪካ ምንም አይነት የእርሻ ምርት ላለመግዛት ወሰነች።በተለይ ይህ ውሳኔዋ የአሳ ምርት እና የእርሻ ምርት ለሩስያ ያቀርቡ የነበሩ የአውሮፓ ሃገራት የገበያ ቀውስ መፈጠሩ አልቀረም ለአውሮፓዊው ግን አሳ እና አትክልት  አንፃራዊ በሆነ መልክም ቢሆን ከቀድሞው ረከስ ባለ ዋጋ መግዛት ቻለ።

አዲሱ የአውሮፓውያን 2015 ዓም

መጪው 2015 የዓለማችን ሃያላን የበለጠ የገበያ እና የፖለቲካ ፍትግያ ውስጥ የሚገቡበት፣የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የህዝብ ብዛት፣ሥራ አጥነት የፅንፈኛ ኃይሎች ወደ ስልጣን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መቅረብ እና ከነዳጅ ቀውስ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ወደ በለጠ ቀውስ ሊያመሩ የሚችሉበት ዓመት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይችላል።ለእዚህም ማሳያ የሚሆነው እነኚሁ የመካከለኛ ምስራቅ ሃገራት የመንግስት ስሪታቸው በፍፁም ፈላጭ ቆራጭነት ላይ የተመሰረተ የቤተሰብ ስልጣን ስለሆነ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት በሆነ አጋጣሚ ከስልጣኑ ዘወር ሲሉ ቀውስ እና የጎሳ ግጭት መከተሉ የተለመደ ነው።ለእዚህ ምሳሌ የምትሆነን የጋዳፊዋ   ሊብያ ነች።የሊብያ የአሁኑ ጥያቄ የአንድነት እና የሰላም ጉዳይ ነው።የምዕራቡ ዓለም ደግሞ ጋዳፊ ከወረዱ በኃላ የሊብያን ጉዳይ ከዜና ርዕስነትም ጭምር አውጥቷቷል።

ተመሳሳይ ጉዳይ ለአፍሪካ ሀገራትም ሊገጥማቸው ይችላል።ሆኖም ግን የአፍሪካ ሃገራት ሙስናን ቀንሰው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እና ጠንካራ የመንግስት ስርዓትን መመስረት ከቻሉ ከሁኔታዎች የሚጠቀሙበት ዕድል ቀላል አይደለም።ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ኢህአዲግ/ወያኔን የሚገዳደር ጠንካራ ተቃዋሚ ነጥሮ መውጣቱ የግድ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ነው።ይህ ተቃዋሚም የኢትዮጵያን አንድነት ላይ የማያወላውል አቋም ያለው መሆኑ እና ከጎሳ ፖለቲካ የራቀ መሆኑ ነገ ከኢህአዲግ/ወያኔ በኃላ ለምትኖረው ኢትዮጵያ ብቸኛ ዋስትና ነው።ለሁሉም ግን 2015 የፈረንጆቹ ዓመት አጀማመሩ በአለማችን የፖለቲካም ሆነ የምጣኔ ሀብት ጉዳይ ላይ ብዙ የይዘትም ሆነ ይቅርፅ ለውጦች ይዞ እንደሚመጣ ከወዲሁ እየጠቆመ ነው። በአካባብያችንም ያላለቁ ብዙ አጀንዳዎች አሉ።የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ከዑጋንዳ እና ኢትዮጵያ ጉዳይ ጋር መያያዙ፣የሱማልያ ጉዳይ፣ከኤርትራ ጋር ያለው ሁኔታ እና የግብፅ የፍላጎት ትኩረት ከፍተኛ መሆን የሚጠቀሱ ናቸው።

ጉዳያችን (ታህሳስ 7/2007 ዓም (ደሴምበር 17/2014)


No comments: