ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, December 6, 2014

''እውነትን እስከያዝን እና በርካቶች ከእኛ ጋር እስከቆሙ ድረስ በእርግጠኝነት አድርባዩን ግንብ ደርምሰን አደባባዩ እንደርሳለን፡፡'' በጌታቸው ሺፈራው ከሰማያዊ ፓርቲ ልሳን 'ነገረ ኢትዮጵያ' ፌስ ቡክ የተገኘ

የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት ከህዳር 27/2007 ዓም ሰልፍ በፊት 

በእርግጠኝነት አደባባዩ ጋ እንደርሳለን!
በጌታቸው ሺፈራው
ትናንት ለሰላማዊ ሰልፉ ዝግጅት ሙሉ ሌሊቱን ነው ስንሰራ ያደርነው፡፡ በተለይ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬና ሳሙኤል አበበ ሌሊቱን ሲለቀቁ ቢሮው ይበልጡን ሞቅ ደመቅ ብሎ አመሸ፡፡ ቢሮ ውስጥ የነበሩት ወጣቶች እስከ አፍንጫቸው አውተማቲክ መሳሪያ የታጠቁ የገዥው ፓርቲ ደህንነትና ፖሊሶች ቢሮውን እንደከበቡት ረስተው ስራቸው ላይ ተጠምደዋል፡፡ ደህንነት ይሁን ፖሊስ ከምንም አይቆጥሩትም፡፡ አቤል፣ ብርሃኑ፣ ወይንሸት፣ እያስፔድ፣ ምኞት፣ በላይ፣ ሜሮን፣ ኃይለማሪያም፣ ሳሙኤል፣ እየሩስ፣ ወሮታው፣ ይልቃል...... ፖሊስ፣ ደህንነት፣ መሳሪያ ቅብጥርጥስ ብሎ የማያስፈራቸው ፍጥረቶች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ከሰማያዊ ፅ/ቤት ውጭ ሰላማዊ ሰልፉን ለመጀመር ሌሎች ደፋር ወጣቶች ተሰማርተዋል፡፡ ቆራጡ ጌታነህ ባልቻ አንዱን ክፍን ይመራዋል፡፡ እየደወሉ አንዳንድ ነገሮችን ይጠይቁናል፡፡ እነሱም እንዲሁ በትንንሽ ሜትሮች ፖሊስና ደህንነት የሚበገርባት አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ አይመስሉም፡፡ ኢህአዴግ አፍነዋለሁ በሚለው ሰላማዊ ሰልፍ ማሰቃያው ማዕከላዊ እስር ቤት ጀርባ ሳይቀር ሌሊቱን ወረቀት እየተለጠፈ እንደሆነ ሲሰሙ የራሳቸውን ቆራጥነት ረስተው ሌሎቹን ያሞካሻሉ፡፡ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በፓልቶክና በመሳሰሉት ድጋፋቸውን ሲሰጡ ሲሰሙ ስራቸውን በደስታ ነበር የሚሰሩት፡፡ የሁሉም ትኩረት በተቻለው ሰላማዊ መንገድ ሁሉ መስቀል አደባባይ መድረስ ነው፡፡ ለዛም ጊዜው የረዘመባቸው ይመስላል፡፡ ደግሞ በበርካታ ስራዎች ተጠምደዋል፡፡
ወጣቶቹ ጠዋት ተነስተው ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙት ጓዶቻቸው ምን ደረጃ ላይ እንደደረሱ፣ መቼ እንደሚጀመር ለማወቅ ቋምጠዋል፡፡ እስከዛው ደግሞ ፌደራልና ደህንነቶች የቆሙበት ድረስ እየሄዱ ፎቶ ግራፍ እያነሱ ያመጣሉ፡፡ የደህንነቶችን ስራ በማህበራዊ ሚዲያዎቸ ያጋልጣሉ፡፡ ብዙዎቹ ምግብ አልቀመሱም፡፡ የእነሱ ትኩረት ወደ መስቀል አደባባይ ማቅናት፣ ከዛም ለኢትዮጵያውያን መብት መጮህ ነው!
እናም ያ ጊዜ ደረሰ፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ቢሮ መቅረት ነበረባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞም አብዮት አደባባይ ላይ ሰልፍ ለመውጣት (ያውም የአዳር ሰልፍ) ሲሞከር ከስርዓቱ የሚመጣው ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል ለወጣቶቹ ግልጽ ነው፡፡ ስርዓቱ ሊደባደብ፣ ሊያስር፣ ከዚህም ሲያልፍ ሊገድል እንደሚችል ያውቃሉ፡፡ ግን ፍርሃትን አላሰቡትም፡፡ እንዲያውም ‹‹ኑ ራሳችን ነጻ በማውጣት አገራችን ነጻ እናውጣ›› የሚሉት ወጣቶቹ ራሳቸውን ከፍርሃት ነጻ አውጥተዋል፡፡ እነሱ የሚታገሉት ሌሎች ከፍርሃታቸው ነጻ ይወጡ ዘንድ ነው፡፡ እናም ፍርሃትን አላሰቡትም፡፡ እነሱ ያሰቡት መስቀል አደባባይ ስለመድረስ ብቻ ነው፡፡ ከዛ ውጭ ያለው መስዋዕትነት የትግሉ አካል ነው፡፡ ስለሆነም ‹‹እኔ ብሄድ ይሻላል፡፡ እንትና ይቀር›› የሚሉት በዙ፡፡ ቢሮ መቅረትን የሚፈልግ ሰው የለም፡፡
እናም ያ ጊዜ ደረሰ፡፡ አመራሮቹ ደግሞ የሚቀያየሩትን ነገሮች ጋር አብረው ለመሄድ በተደጋጋሚ ‹‹ኦረንቴሽን›› ይሰጣሉ፡፡ በተለይ በተለያዩ የአብዮት አደባባይ አካባቢ የነበሩት የሰልፉ አስተባባሪዎች መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ሰማያዊ ጽ/ቤት የነበሩት ወጣቶች ይበልጡን ተቁነጠነጡ፡፡ ምክንያቱም የሚያስመልሱት መብትን ነው፡፡ የሚያስመልሱት ታሪካዊ አደባባይንም ነው፡፡ ደግሞም ሌላ ቦታ ሰልፉን የጀመሩት ጓደኞቻቸው ከፖሊስና ደህንነት ጋር እየተጋፈጡ ነው፡፡ ቆይቶ ግን የእነሱም የተጋድሎ ተራ ደረሰ፡፡
ከአቧሬ በኩል መንገድ ተዘግቶ በርካታ ፖሊሶች ተደርድረዋል፡፡ በካሳንችስ በኩልም እንዲሁ፡፡ ደህንነቶች (ጆሮ ጠቢዎች) ቢሮው በር ድረስ ተኮልኩለዋል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ወጣቶች አብዮት አደባባይ ለመድረስ ይህን ሁሉ አጥር ጥሰው ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነ ብርሃኑ፣ እያስፔድ፣ አቤል፣ ወይኒ፣ እየሩስ፣.......በግንባር ቀደምነት ድምጻቸውን እያሰሙ የፌደራል ፖሊስና ደህንነቶችን ለመጣስ በሚያስችል ፍጥነት ስለ ነጻነት እየጮኹ ወደ አደባባዩ ከነፉ፡፡ ግን እውነትን ስለያዙ እንጅ የእነሱ ቁጥር በየ ቦታው ከተኮለኮለው ደህንነትና መንገድ ዳር ከተዘረገፈው ፌደራል በእጅጉ የሚያንስ ነበር፡፡ እናም እንደራሴ ላይ ስርዓቱን ለመከላከል ቆርጦ ከተነሳ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ግንብ ጋር መላተም ነበረባቸው፡፡ ከእውቀት ይልቅ በጥላቻ የተገነባ ግንብ፡፡ ለለውጥ የቆረጡ እንጅ አድርባይነት የማይታይባቸው ወጣቶች በደቂቃዎች በምክንያት አሳምነው የማያልፉት በጥላቻ የጠጠረ አድር ባይ ግንብ፡፡
ስርዓቱ ግንብ ለሰላማዊ ታጋዮች፣ ለህዝብ ጥቅም የቆሙት ላይ ጥላቻ ያለው እንደሆነ ሁሉ አቤል፣ ወሮታው፣ ይልቃል፣ በላይ፣ ጣይቱዎቹ...ለአድርባይነት፣ ለኢ -ዴሞክራሲያዊነት የጠለቀ ጥላቻ ይዘዋል፡፡ ፖሊስና ደህንነት ከስርዓቱ እንደወገነ ሁሉ እነሱ ስለ እውነት ከኢትዮጵያውያን ጋር ወግነዋል፡፡ እናም ሁለት የተለያዩ (ተቃራኒ) ግንቦች ፊት ለፊት ተፋጠጡ፡፡ ስለ እውነት፣ ህግን መሰረት አድርገው መብት የሚጠይቁት ወጣቶች ስርዓቱን የከለለው ግንብ አልፈው መንጎድን መርጠዋል፡፡ ስርዓቱን ለመመከት የተበገረው ግንብ ደግሞ ከእውነት ይልቅ መሳሪያና ቆመጥ ይዟል፡፡ በተለያዩ ቋንቋዎች ተነጋገሩ፡፡ ወጣቶቹ በሰላማዊ መንገድና በህግ ፖሊስና ደህንነት በኃይል!
በአድርባይነት የቆመው ፖሊስና መከላከያ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ስርዓት በባዶ እጃቸው ነጻነታቸውን እንዲያከብር የሚጠይቁትን ወጣቶች ደበደበ፡፡ አቤል ኤፍሬም፣ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፣ ንግስት ወንዲፍራው፣ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ በላይ ማናዬ፣ ኃይለማሪያም.....ሁሉም በጭካኔ ተደበደቡ፡፡ ድምጽ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን መብታቸው እንዲከበር እጁን ብቻ ወደላይ አንስቶ ‹‹ነጻነት!›› ያለው አቤል በቅልብ ፌደራሎች ተቀጥቅጦ ራሱን ስቶ ወደቀ፣ ንግስት ወንዲፍራውና ሌሎችም በተመሳሳይ፡፡ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በጭካኔ ተደበደበ፣ ሌሎቹም እንደዚሁ፡፡
ግን ሁለቱም የሚገባቸውን አድርገዋል፡፡ ፌደራል ፖሊስና ደህንነት ስልጣናቸውን እንጅ ምክንያት፣ ህግ ተብሎ በማይገባቸው ባለስልጣናት ‹‹ደብድብ!›› ተብሎ የተሰጠውን ‹‹ስራ አከናወነ››፡፡ ህገ ወጥ አቅሙን በህጋዊያን ላይ ተጠቀመ፡፡ ለፖሊስና ደህንነት ይህ አድርባይነት ማደሪያው ነው፡፡ ስለ ነጻነት የቆሙት ደግሞ መጀመሪየም ስርዓቱ እንደሚያስደበድብ ያውቁታል፡፡ እናም ስለእውነት ሲሉ ያለ መሳሪያ መሳሪያ ያነገበው ጋር ተፋጠው ተደበደቡ፡፡ ይህም ለነገው ትግላቸው እርሾ እንደሆነ ያውቁታል፡፡ ፌደራል ፖሊስ ወጣቶቹን ሲደበድብ ራሱን ይደበድባል፡፡ ቢያንስ ይህ ቁስል ዛሬ ባይሰማው ነገ ይጠዘጥዘዋል፡፡ ያመረቅዛልም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት እንዳየሁት የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ስለ መብታቸውን ሊያስከብሩ ሰልፍ ወጥተው ሲደበደቡ ይዘምራሉ፡፡ የዛሬው ዱላ በእጅጉ በርትቶባቸው ራሳቸውን ቢስቱም ቁስሉ ግን ሊሰማቸው አይችልም፡፡ እያንዳንዷ ቁስል፣ ስቃይ፣ መስዋዕትነት ለነጻነት ትግሉ ስንቅ ነች፡፡ እናም የአድር ባዩ ፖሊስና ደህንነት ቆመጥ ለጊዜው እንጅ እንደማይሰማቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡
ዛሬ እነዚህ ቆራጥ ወጣቶች ከጎኔ የሉም፡፡ ለዘገባ እንደምወጣ ስነግረው ‹‹አይሆንም እኔ ነኝ የምወጣው!›› ብሎኝ ምንችክ ያለው በላይ ማናዬን አውቀዋለሁ፡፡ ፖሊስ ከሚያሳርፍበት አጥንት የሚሰብር በትር ይልቅ ቅንጣት እውነት ስትዛባ ያመዋል፡፡ አቤል፣ ብርሃኑ፣ ይልቃል፣ ወሮታው፣ ሳሙኤል... ጣይቱዎቹን አውቃቸዋለሁ፡፡ እውነት ስትዛባ ያንገበግባቸዋል፡፡
ጓደኞቼ ወደ አደባባዩ ሲያቀኑ እንደሚደበደቡ አውቃለሁ፡፡ ከእነሱ ጋር አንድ አይነት ጥያቄ አንግቦ መደብደብ ለጊዜው ካልሆነ በስተቀር አያምምና እኔም ለመሄድ ቋምጬ ነበር፡፡ ግን ቢሮ ሰው መቅረት ነበረበትና ቀርቻለሁ፡፡ ግን ደግሞ ቢሮ ሆኖ እንደቆሰሉ መስማት እንዴት ያማል? ስለ እውነት ጠይቆ መስዋዕትነት መክፈል እንዴት ክብር ነው? ወጣቶቹ እንደትናንትው አብረውኝ ቢሮ ውስጥ ባያድሩም እምነታቸው ግን አብሮኝ ነው፡፡ ከእምነት ወዲያ ምን አለ?
ጓደኞቹ አብዮት አደባባይ (መስቀል አደባባይ) ለመድረስ አማትረው ለጊዜው ጉዟቸው መንገድ ላይ ተገትቷል፡፡ በጭካኔ ተደብድበዋል፣ ቆስለዋል፡፡ ይህ ስለሆነ ግን አሁንም ወደ አደባባዩ ከማማተር አይቆጠቡም፡፡ ራሳቸውን ነጻ ቢያወጡም ሌሎች ነጻ እንዲወጡ ከተለሙት አላማቸው የሚያቆማቸው የለም፡፡ ዛሬ እንደራሴ ላይ ቢቆሙ፣ ነገ ካሳንቺስ ድረስ እንደርሳለን፡፡ አካላዊ ቁስሉ ሳይበግረን ከነገ ወዲያ....እንዲያ እያልን ደግሞ ወደታለመው አደባባይ እናቀናለን፡፡ በእርግጠኝነት የአድርባዩ ጎራ እየሳሳ፣ ስለ እውነት የቆሙት የሚጠነክሩበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ እውነትን እስከያዝን እና በርካቶች ከእኛ ጋር እስከቆሙ ድረስ በእርግጠኝነት አድርባዩን ግንብ ደርምሰን አደባባዩ እንደርሳለን፡፡



No comments:

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)