ፎቶ ከጉግል
የሱማሌ ጉዳይ
የሱማሌ ክልል ፖለቲካው ችግር እረዘም ያለ ስር ያለው ነው።ከአስራ ዘጠነኛው ክ/ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ወዲህ ብቻ የጎረቤት ሱማልያን ለመቀራመት ያሰቡት እና የተሳካላቸው የእንግሊዝ እና የጣልያን ቅኝ ገዢዎች ድንበር እየተሻገሩ ኢትዮጵያውያን የሱማልኛ ተናጋሪ ወገኖቻችንን የተለየ ሃሳብ እንዲይዙ ያልተደረገ ሙከራ አልነበረም።በሃያኛው ክ/ዘመን አንስቶ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ አካባቢው የግብፅ እና የሳውዳረብያን ጨምሮ የሌሎች ሃገራትን ትኩረት ስቧል።ይህ ተፈጥሮ የሰጠን ፀጋ ነው።ሲደንቀን የሚኖር ጉዳይ አይደለም።የእዚህ አጭር ማስታወሻ ዓላማ ግን የባዕዳንን ነገር ለመተርክ አይደለም።እኛ የእራሳችንን የቤት ሥራ ሳንሰራ ባዕዳን ላይ እጃችንን መጠቆም አንችልም።እኛ ወገኖቻችንን መንከባከብ፣ኢትዮጵያዊ ስሜታቸውን ማክበር፣የግልም ሆነ የቡድን መብታቸውን ማክበር ይገባናል።አዎን! እነኝህ መብቶች ሁላችንም የተነጠቅናቸው እና ማስመለስ እንዳለብን የምናምናቸው ቁልፍ ጉዳዮቻችን ናቸው።
የመሃል ሀገር እና የሱማልኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ፍቅር
ሱማልኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንንም ሆነ የማዶ ሱማልያውያንን በመሃል ሀገር የኖርን ኢትዮጵያውያን ተቀራርበን መተዋወቅ የቻልነው የዚያድ ባሬ መንግስት ከወደቀ እና ሱማልያ እርስ በርስ ስትዋጋ በርካታ ሱማሌዎች ወደ ሃገራችን መጉረፍ ከጀመሩ ጀምሮ ነው።ቀድም ብለው እነርሱም የመሃል ሀገር ተወላጅን በሙሉ ''ሐበሽ'' እያሉ የመሃል ሃገሩ ህዝብም ''ሱማሌ'' እያለ ልብ ለልብ ሳይተዋወቅ ኖረ።ከሱማሌ መፍረስ በኃላ ግን ሕዝብ ለሕዝብ ተዋወቀ።የመሃል ሃገሩ ኢትዮጵያዊ ምን ያህል ታጋሽ፣ደግ እና ሩህሩህ መሆኑን ሱማልኛ ተናጋሪ ወንድሞቻችን አሁንም ይመሰክራሉ።ዛሬ በመላው ዓለም በስደት የሚገኙ በእርስ በርስ ውግያ የታመሰችው የሱማሌ ተወላጆች ባብዛኛው ከኬንያ ቀጥሎ የረገጧት እና በትዝታ የሚያስቧት ኢትዮጵያ ነች።ብዙዎች አውሮፓ እና አሜሪካ ኖረው ለእረፍት ኢትዮጵያ መምጣት ያስደስታቸዋል።ይህ አዲስ ሚስጥር አይደለም።ሕዝብ ለሕዝብ ከተዋወቀ በኃላ የፈጠረው በጎ ተፅኖ ነው።የምዕራቡን ዓለም መገናኛ ብቻ እየሰማ ለሚኖር አፍሪካዊ ቀርቦ መተዋወቅ የሚለው አባባል ብዙ ማለት እንደሆነ ይረዳል።
ሕዝብ ከህዝብ ከተዋወቀ በኃላ የመሃል ሀገር ተወላጁም ሱማልኛ ተናጋሪው ኢትዮጵያዊም ሆነ የማዶው ሱማልያዊውን የሚገልፅበት ቃላት ''ቂም የማያውቁ፣ያላቸውን የሚያካፍሉ፣ተንኮል የሌለባቸው'' እያለ ነው።ባጭሩ ሕዝብ ለሕዝብ በታሪካዊ አጋጣሚ ተዋወቀ።የእዚህ ታሪካዊ ክስተት ውጤትን ላስተዋለው አንድን ሕዝብ በጅምላ አንድ ከረጢት ውስጥ ከትቶ በግምት ክፉ ከማውራት አባዜን የሚያላቅቅ አይነተኛ መድሃኒት ነው።ይህ ማለት ግን ሱማልኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊውም ሆነ የመሃል ሀገር ኢትዮጵያዊ ታሪካዊም ሆነ ሕዝብ ለሕዝብ ትውውቅ እና ትስስር አልነበረም ለማለት አይደለም።ይህንን ለታሪክ ሰዎች መተዉ የተሻለ ነው።ኢትዮጵያዊነትን ስናነሳ ከጥንቱ አፄ ካሌብ ጀምሮ ለዘመናት የተሳሰረ እና ትልቅ መልክአ ምድራውም ሆነ ታሪካዊ ትስስር ከኦጋዴን ሱማልኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን ጋር አለን።አባቶቻችን ለኢትዮጵያዊነት የከሰከሱት አጥንት እና ደም በኦጋዴን መሬት ላይ ዛሬም ድረስ ይጣራል።አባቶቻችን የኦጋዴን ተወላጆች ለኢትዮጵያዊነት የከፈሉት መስዋዕትነት ለዛሬ መተሳሰባችን እና አንድነታችን መሰረት ሆኖ ይኖራል።ብዙም እሩቅ አያስኬደን ከሶስት አስርተ ዓመታት በፊትም የእኛ አባቶች ስለፍቅር ሲሉ ደም እና አጥንት የገበሩበት ምድር ነው ዑጋዴን።
በሱማሌ ክልል የተፈፀመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት
በሱማሌ ክልል የተፈፀመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አሳዛኝ ነው።ኢሳት ቴሌቭዥን ባለፈው ማክሰኞ ከመከላከያ ሰራዊት አባላት የደረሰውን ፊልም ለሕዝብ ማሳየቱ ይታወሳል።አንድ ኢትዮጵያዊ ሚድያ ትልቁ ኃላፊነት ደግሞ በየትኛውም የሃጋራችን ጥግ ላይ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀሙ ድርጊቶችን መዘገብ ነው።ኢሳትም ያደረገው ይህንኑ ነው።አንዳንድ ቅን ኢትዮጵያውያን የፊልሙን መለቀቅ የሚያዩበት የተለየ የፍራቻ አይን እንደሚኖር እገምታለሁ።እኔም መጀመርያ ከብዙ ቅን ዕይታዎች ለማየት ዳድቶኝ ነበር።በኃላ ለእራሴ እነኝህን ጥያቄዎች መጠየቅ ጀመርኩ።የፊልሙ መለቀቅ አንደምታ ምንድነው? እንደሀገር ምን ማለት ነው? በሱማልኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ዘንድስ ምን ትርጉም ይሰጣል? የሚሉትን ጥያቄዎች ለእራሴ ሳነሳ የከረምኩት። መልሶቹ ግን እራሴው ለእራሴው ተመለሰለኝ። በእዚህም መሰረት ለእናንተም ለማካፈል ወደድኩ።የፊልሙ ይፋ መሆን ያሉት አራት በጎ ተፅኖዎች
ስለ ፊልሙ ተፅኖ ከማውራት በፊት በፊልሙ ላይ የቀረበው ይዘት በእራሱ የሰብአዊ ይዘት በሀገራችን ምን ያህል ፋሽሽታዊ ደረጃ መድረሱን ማመልከቱ ተገቢ ነው።በሃያ አንደኛው ክ/ዘመን በኢራቅ እና ሌሎች ሃገራት የሚፈፀሙ ፅንፈኛ ፀረ -የሰው ዘር ድርጊቶችን እያየን እንዳላዘንን ዛሬ በሀገራችን በእንዲህ ዓይነት ደረጃ ግፍ ሲፈፀም መመልከት እራስ ያማል።
የፊልሙ ለሕዝብ የመቅረቡን ፋይዳ ስንመለከት ግን ለነገዋ ኢትዮጵያችን ዛሬ የምንሰራው ሥራ ነፀብራቅ መሆኑን እንረዳለን።ለእዚህም ነው ኢሳት ነገሩን ለሕዝብ የመግለጡ ፋይዳ በጎ ተፅኖ ፈጣሪ ነው እንድል ያደረገኝ።ከእነዚህ በጎ ተፅኖዎች ውስጥ አራቱን ብቻ ብጠቅስ -
1/ የመጀመርያው የፊልሙ በጎ ሥራ በሌላው የሀገራችን ክፍል ለሚኖረው ሕዝብ ሱማልኛ ተናጋሪው ወገኑን ስሜት እንዲታመም ያደግርጋል።
2/ ሱማልኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንም የእነርሱን ችግር ሌላው ኢትዮጵያዊ እየተረዳ መሆኑ በራሱ በኢትዮጵያዊነታቸው ላይ እፎይታ ይሰጣቸዋል።ይህ ማለት ችግሩ የአስተዳደር እና የአምባገነንነት እንጂ የኢትዮጵያዊ የመሆን እና ያለመሆን ጉዳይ አለመሆኑን ይረዳሉ።ውሎ አድሮ ኢትዮጵያዊ ሚድያዎች ላይ እንደ ኢሳት ባሉት ላይ እምነታቸው ይጠነክራል።ይህ እምነታቸው ደግሞ ነገ በነፃነት ለምትኖረው ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት መገናኛ ብዙሃንም ላይ ቀጣይ እንዲሆን ይረዳል።
3/ የግፍ ድርጊቱ ነገ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ሊደገም ይችላል እና የእዚህ አይነት ግፍ አድራጊ ባለስልጣናት ከፍርድ እንደማያመልጡ የሚረዱበት በጎ አጋጣሚ ይሆናል።
4/ በዑጋዴን ጉዳይ ከእዚህ በፊት እጃቸውን የከተቱ እንደ ግብፅ ያሉት እና ወደፊትም እጃቸውን ለመክተት ለሚዘጋጁት ባዕዳን ሁሉ የወንድሞቻችን ሱማልኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ እኛው በራሳችን እየጮህንበት መሆኑ ሲመለከቱ የሚናገሩት አዲስ ነገርም ሆነ ጉዳዩን የክልሉን ነዋሪዎች ከሌላው ኢትዮጵያውያን ጋር ለማጋጨት የሚሸርቡት የአጭር ጊዜም ሆነ የእረጅም ጊዜ ስልት ውድቅ ይሆናል።ለሱማልኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን ጥብቅና የምንቆም እኛ እራሳችን ኢትዮጵያውያን እንጂ ባዕዳን አለመሆናቸውን ዓለምም ሆነ ሱማልኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ይረዱልናል።
በመሆኑም የእዚህ ዓይነቱ የምርመራ ጋዜጠኝነት ዘገባ ኢሳት ሊቀጥልበት የሚገባ ሥራ ነው።ሰሞኑን የሱማሌው ጉዳይ ተመለከትን እንጂ በሀገራችን ልዩ ልዩ ክፍሎች ከፍትህ እጦት ሳብያ በግብታዊነት የተወሰዱ በርካታ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ለመኖራቸው አሌ አይባልም።ለምሳሌ የጋምቤላ፣የወልቃይጥ፣የአዋሳ እና የሐውዘን ግልፅ እና ስውር እልቂቶች የሚጠቀሱ ናቸው።
ጉዳያችን
መስከረም 8/2007 ዓም (ሴፕቴምበር 18/2014)
No comments:
Post a Comment