ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, September 29, 2014

አዲስ አበባ የሚታተመው ''አዲስ አድማስ ጋዜጣ'' ቅዳሜ መስከረም 17፣2007ዓም (27 September, 2014) የሰሞኑን የኢህአዲግ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ስልጠና የዳሰሰበት ሊነበብ የሚገባ ፅሁፍ።


 
           በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት የህግ ተማሪ የሆነው አቤል ስሜ መንግስት ካለፈው ነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባዘጋጀው የ15 ቀናት ሥልጠና ላይ ተሳትፏል፡፡ በቴሌቪዥን የተላለፈው ማስታወቂያ በአቅራቢያችሁ በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ተመዝገቡ የሚል ስለነበረ በሚኖርበት ከተማ በሚገኘው አምቦ ዩኒቨርሲቲ መመዝገቡን የገለፀው አቤል፤ ለ15 ቀናት የሚዘልቅ ሥልጠና ላይ እሳተፋለሁ ብሎ እንዳልጠበቀ ይናገራል፡፡ አቤል ለስልጠና የተመደበው አቃቂ በሚገኘው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን አልጋና ቀለብ እንዲሁም ትራንስፖርት በዩኒቨርሲቲው እንደተሸፈነላቸው ለአንዳንድ ወጪዎች ተብሎም 400 ብር እንደተሰጣቸው ጠቁሟል፡፡ የመጀመሪያዎቹ በርካታ ቀናት ስልጠና በኒዮሊበራሊዝም ርዕዮተ - ዓለም ላይ ያተኮረ እንደነበረ ያስታወሰው ተማሪው፤ የኒዮሊበራሊዝም ውድቀት በተለያዩ አገራት ማሳያነት በስፋት እንደተብራራላቸው ይናገራል፡፡

እኔን ጨምሮ በርካታ ተማሪዎች ስለጉዳዩ ምንም ግንዛቤ አልነበረንም ያለው አቤል፤ ከስልጠናው በኋላ በገባን መጠን ጥያቄዎችና አስተያየቶች አቅርበናል ብሏል፡፡ በስልጠናው የተነሳው ሌላ አጀንዳ ልማታዊ መንግስትና አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚል ነበር ያለው ተማሪው፤ በዚህ ስልጠና ከአፄዎቹ ስርአት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ሃገሪቱ የተጓዘችበት ውጣ ውረድ መዳሰሱን ጠቁሟል፡፡ በዚህ ርዕሰጉዳይ መነሻነት በርካታ ፈታኝ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተማሪዎች መነሳታቸውን አቤል ይገልፃል፡፡ ከተነሱት ጠንካራ ጥያቄዎችና አስተያየቶች መካከልም “ልማቱ ስራ አጥነትን በመቅረፍ ረገድ ምን ውጤት አመጣ?” “የተማረው ኃይል ስራ አጥ ሆኗል፣ ሃገሪቷም ጥቅም ማግኘት አልቻለችም፤ ይሄም በአጠቃላይ ሃገሪቱ የምትመራበት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ችግር ያመጣው ነው” የሚሉ ይጠቀሳሉ ብሏል - አስተያየት ሰጪው፡፡ በተለይ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች በስራ አጥነት እንደሚንገላቱ በመጥቀስ መንግስት ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የተጓዘባቸውን መንገዶች አምርረው እንደተቹ አቤል ይናገራል፡፡ ዲግሪ ይዘው ድንጋይ ጠራቢ የሆኑ ተማሪዎች እንዳሉ በመጥቀስም ሃገሪቱ በቂ የተማረ ሰው ኃይል በማፍራቷ ነው ወይ የተማረው ረክሶ በእውቀቱ ሳይሆን እውቀት በማይጠይቅ ሙያ ላይ እንዲሰማራ የተገደደው? የሚሉ ጥያቄዎች መሰንዘራቸውንም አስታውሷል፡፡

ከተማሪዎቹ ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥ አሰልጣኞች ለአንዳንዶቹ ተገቢ ማብራሪያና ምላሽ እንደሰጡ የተናገረው አቤል፤ ጥቂት የማይባሉ በቸልታ የታለፉ ጥያቄዎች እንደነበሩም አልሸሸገም፡፡ በተለይ ሰፊ የመወያያ አጀንዳ በነበረው በፌደራሊዝም ጉዳይ ላይ ለቀረቡ አንኳር ጥያቄዎች መልስ አልተሰጠም ብሏል፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛው ዙር የተሰጠውን ስልጠና የዲላ ዩኒቨርሲቲ የ1ኛ ዓመት የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ተማሪ ሄለን ጉርሜሳ፣ ስልጠናው በአመዛኙ በጥያቄና አጨቃጫቂ ውይይቶች የተሞላ እንደነበር ትገልፃለች፡፡ በተለይ ያለፉት ስርአቶች ታሪክ እየተመዘዘ በንፅፅር መልክ ሲቀርብ፤ ተማሪዎች ንፅፅሩ ምን ጠቀሜታ አለው? የሃገሪቱን ታሪክ ማበላሸት አይሆንም ወይ? እንዲህ ያለው ጉዳይ የብሄርና ጎሳ እንዲሁም የሃይማኖት ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል፣ ቂም በቀልንስ አይቀሰቅስም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በስፋት እንደቀረቡ ታስታውሳለች፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚከሰቱ ብሄርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች፤ በተማሪዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል የምትለው አስተያየት ሰጪዋ፤ በተለይ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተነስቶ በነበረው ግጭት የሞቱ ተማሪዎችና ሰዎች ጉዳይ መጣራትና ወንጀለኞችም ፍርድ ማግኘት እንዳለባቸው ተማሪዎቹ አጥብቀው ጠይቀዋል ብላለች፡፡ አንዳንድ ተማሪዎችም በመምህራን የትምህርት አሰጣጥ ዘይቤና የፈተና ውጤት አያያዝ ላይ ያላቸውን ቅሬታም እንዳቀረቡ ታስታውሳለች፡፡

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት ተማሪ የሆነው አስቻለው ብርሃኔ በበኩሉ፤ ስልጠናው ሙሉ ለሙሉ ከፖለቲካ አስተሳሰብ ጋር የተገናኘ መሆኑን ባይወደውም በየመሃሉ በዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት አሰጣጥና ከተማሪ ውጤት ነጥብ አያያዝ ጋር በተገናኘ በተማሪዎች የተነሱት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ባይሰጥባቸውም ጠቃሚ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በአንዳንድ የስልጠና መድረኮችም አሰልጣኞች ያልጠበቋቸውና ፈታኝ የሆኑ ጥያቄዎች ከተማሪዎች መቅረባቸውን ምንጮቻችን ጠቁመውናል፡፡ “የፀረ ሽብር አዋጁ ተቃዋሚዎችን ለማፈን ነው የወጣው ይባላል…” “ኢህአዴግ ከስልጣን የሚወርደው መቼ ነው?” የሚሉና ሌሎችም እንደተነሱ ለማወቅ ችለናል፡፡ በአለማያ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ስልጠና በአዲስ አበባ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የቆመውን የምኒልክ ሃውልት በተመለከተ ከተማሪዎች ጥያቄ መነሳቱን የጠቀሱት ምንጮች፤ ምኒልክ የኦሮሞን ህዝብ ጨፍጭፈው ሃውልታቸው መቆሙ ተገቢ አይደለም የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል መንግስት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያዘጋጀውን ሥልጠና በተመለከተ ተቃዋሚዎች በሰጡት አስተያየት የአንድ ፓርቲን አመለካከት ለማስረፅ የተዘጋጀ ነው ሲሉ ተቃውመውታል፡፡ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ፤ ስልጠናው በግዴታ መሆኑ የሰዎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብት የሚጥስ ነው ብሏል፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ጉዳዩን አስመልክቶ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፤ “ስልጠናው ታቅዶበት የተከናወነ ሳይሆን ድንገት ደራሽ ነው፣ በስልጠናው ያልተሳተፉ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርት እንደማይቀጥሉ የሚያስጠነቅቅ፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብትን የሚደፈጥጥ ነው” ብለዋል፡፡ ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚገባው በትምህርት ብቃት እንጂ በዚህ መልኩ ተጣርቶ መሆን የለበትም የሚሉት ኢ/ር ግዛቸው፤ ተማሪዎች ያላቸውን አስተሳሰብና አመለካከት የመያዝ መብታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ መሰሉ ስልጠና የመንግስትን መዋቅርና ንብረት መጠቀም እንደማይገባ የሚናገሩት ኢ/ሩ፤ ይሄ የመንግስትና የህዝብ ሃብት ብክነት ነው ባይ ናቸው፡፡ ስልጠናው ውጤታማ አለመሆኑን ካሰባሰብናቸው መረጃዎች ለመረዳት ችለናል ያሉት ኢ/ር ግዛቸው፤ ስልጠናው ይበልጥ ኢህአዴግን ያስገመገመ እንደነበር ጠቅሰው የግምገማው ውጤትም አስከፊ እንደሆነ ተረድተናል ብለዋል፡፡ የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ በበኩላቸው፤ የስልጠናው መንስኤ “በገዥው ፓርቲ በኩል ያለው ፍርሃትና ጭንቀት ነው” ይላሉ፡፡ ስልጠናው ተማሪዎቹ እንዴት ማጥናትና መማር እንዳለባቸው ቢሆን ኖሮ ሁሉም የሚደግፈው ሰናይ ተግባር ይሆን ነበር የሚሉት አቶ አበባው፤ ከዚህ ይልቅ የአንድን ፓርቲ አመለካከትና አስተሳሰብ አዳምጠው እንዲወጡ ነው የተደረገው፤ ይህ ደግሞ ለሃገር የሚጠቅም አይደለም ሲሉ ተችተዋል፡፡

በስልጠናው ወቅት የሚወጣው ወጪም ህግን የጣሰ ነው የሚሉት አቶ አበባው፤ ህጉ “የመንግስት ንብረትና ሃብት ለምርጫ ቅስቀሳ ወይም ለፖለቲካ ስራ አይውልም” እንደሚል ጠቁመዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ይህን ድንጋጌ ጥሶ የመንግስት ሃብትን ለግል ጥቅሙ እያዋለ ነው ሲሉም ከሰዋል፡፡ “ስልጠናው በተማሪዎች ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ዜጎችን በአጠቃላይ አፍኖ ለመያዝ የሚደረግ ጥረት በመሆኑ ወደ ሌሎች ዜጎችም እየወረደ ነው” ብለዋል አቶ አበባው፡፡ በየስልጠና መድረኩ ያለፉ ታሪኮች እየተመዘዙ ትችት ማቅረቡና ታሪክ ማዛባቱ ተገቢ አይደለም የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እነዚህ ጉዳዮች በየስልጠና መድረኮቹ አከራካሪ ሆነው ጎልተው መውጣታቸውን ካሰባሰቡት መረጃ መረዳታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ተማሪዎቹ ባነሷቸው ጠንካራ ጥያቄዎች ምክንያት ከአሰልጣኞቹ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብተው እንደነበረም አቶ አበባው ይገልፃሉ፡፡

ለተማሪዎቹም ሆነ ለመምህራኑ የተዘጋጀው ስልጠና ሃገሪቱን የሚያስተዳድሩ ሰዎች ለሃገሪቱ በሚገባ የማያስቡ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው የሚሉት የመድረክ አመራር አቶ ገብሩ ገ/ማርያም፤ ለዚህ ጉዳይ በይፋ የተመደበ በጀት ሳይኖር በስልጠና ስም የህዝብ ሃብት ማባከንና የአንድ ወገን አስተሳሰብ ለማስተላለፍ መጠቀም ነውር ነው ብለዋል፡፡ የአንድን ወገን የፖለቲካ አመለካከት በወጣቶች አዕምሮ ውስጥ ለማስረፅ የሚሰጥ ስልጠና ትውልድንም ሃገርንም አጥፊ ነው ያሉት አቶ ገብሩ፤ “እኛ ለዚህች ሃገር እንዲፈጠር የምንፈልገው በራሱ የሚተማመን፣ ራሱ የሚያስብ፣ ራሱ ጠይቆና አንብቦ የሚረዳ፣ ለጠየቀው ጥያቄ ተገቢ መልስ ማግኘቱን የሚያረጋግጥና ሀገር መምራት የሚችል ወጣት ነው፡፡” ሲሉም አስረድተዋል፡፡ “ስልጠናው የታለመለትን ግብ አልመታም” ብለው እንደሚያምኑ የገለፁት አመራሩ፤ በአንዳንድ መድረኮች ባለስልጣናት መልስ መስጠት እስኪያቅታቸው ድረስ በጥያቄ የተፋጠጡበት፣ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህ ይበልጥ የተፈተሸበት፣ መንግስት ከጠበቀው ውጤት የተለየ ተቃራኒ ውጤት የተመዘገበበት የስልጠና ሂደት መሆኑን እንደተረዱ ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይም ስልጠናው አስቀድሞ የታቀደበት አለመሆኑንና ምርጫውን ታሳቢ ያደረገ፣ የግራ መጋባት ውጤት እንደሆነ አቶ ገብሩ ተናግረዋል፡፡ በአሠልጣኝነት ተሣታፊ የነበሩት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ በበኩላቸው፤ ስልጠናው ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ምርጫን ታሳቢ ያደረገ ሳይሆን ታቅዶና ታስቦበት የተካሄደ ነው፡፡ በስልጠናው ሂደትም መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን የተረዳበትና ለቀጣይ የእርምት እርምጃዎች አጋዥ የሆኑ ግብአቶችን ያገኘበት እጅግ ስኬታማ ስልጠና እየተከናወነ ነው ብለዋል - አቶ እውነቱ፡፡ አክለውም ስልጠናው በግዴታ ነው የተካሄደው የሚለው ሃሰት መሆኑንና በሠልጣኞች ውዴታና ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቅዳሜ መስከረም 17፣2007ዓም (27 September, 2014) 

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...