Tuesday, March 22, 2016

ሰበር ዜና: የወልቃይት ጠገዴ ውጥረት ተባብሷል።አማራ ነኝ ማለት ወንጀል ሆኗል።ዛሬ ከ2000 ሕዝብ በላይ ሰልፍ ወጥቷል።የ16 ዓመት ታዳጊ በጥይት ተገድሏል።የህወሓት ደህንነት የሱዳን ታርጋ በለጠፉ መኪናዎች ይንቀሳቀሳል (ጉዳያችን)


ዛሬ ወልቃይት ጠገዴ ወረዳ ቀራቅር የምትባል ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ነበር።በዛሬው ዕለት ብቻ ከ2000 ሕዝብ በላይ ሰልፍ ወጥቷል።የ16 ዓመት ታዳጊ በጥየት ተገድሏል።የህወሓት ደህንነት የሱዳን ታርጋ በለጠፉ መኪናዎች ይንቀሳቀሳል።
===========================================

የአሜሪካ ድምፅ ራድዮ የአማርኛው አገልግሎት ዛሬ መጋቢት 13/2008 ዓም ከወልቃይት ጠገዴ በቀጥታ በስልክ ያነጋገራቸው እና በሰልፉ የተሳተፉ ነዋሪ እንደተናገሩት:- ''ሰልፉ የተደረገው ዳንሻ ከተማ ላይ አማራ ነን ብለው በጠየቁ ወጣቶች ላይ የግድያ እና እስራት ማዋከብ ተግባር ስለነበር ይህንን በመቃወም መንገድ በመዝጋት እና በመሳሰለው ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ አድርገናል'' ብለዋል።

በዛሬው ሰልፍ ስንት ሕዝብ ተገኘ? ተብሎ ለእኚሁ ነዋሪ ለቀረበላቸው ጥያቄ  ሲመልሱ  ''በቀራቅር ከተማ ብቻ ዛሬ ተማሪዎች  ወደ 800 ተገኝተዋል። ከሕዝቡ ገበሬው ወደ 1200 ሕዝብ ባጠቃላይ በግምት ወደ 2000 ሕዝብ ተሳትፏል ብለን እንገምታለን'' ብለዋል።

ቀሪው ቃለ ምልልስ በቀጥታ እንዲህ ቀጥሏል:-

ቪኦኤ :- ተሰልፋችሁ ወዴት ሄዳችሁ?

''ተሰልፈን ከተማውን ሁለት ጊዜ ዞረነዋል።በኃላ ወደ አስተዳደሩ ቢሮ ነው የሄድነው እሳቸው የዳንሻ መንገድ ስለተዘጋ ከህዝብ ጋር ለመደራደር ሄደዋል ተባልን።ቢሮ ይወከል አይወከል አይታወቅም አንዱ ሰብስቦን ነበር። እኛ ግን እሱን ማዳመጥ አልፈለግንም።ይሄው ሰው ግን ሰልፍ መውጣታችሁ ትክክል አይደለም።የዳንሻን ሕዝብ መወከል አትችሉም፣አማራ ነኝ ለሚል ወገን ብላችሁ መደገፍ አትችሉም የሚል መልስ ነው የሰጠን። እኛም በመልሱ ስላልተደሰትን ሌላ ስሜት ውስጥ እንዳንገባ ብለን ጥለነው ነው  የሄድነው ሰውዬው እዚያው ብቻቸውን ነው የቀሩት ''

ቪኦኤ:- የታሰሩ እና የተገደሉ አሉ ብለው ነበር? የታሰሩ የሚያውቁት አለ? 

''የታሰሩ ብዙ ናቸው። ስማቸውን መዘርዘር አይቻልም ብዙ ናቸው።''

ቪኦኤ:- ስንት ይሆናሉ?

''አሁን ጧት ያለን መረጃ 70 አካባቢ ደርሰዋል ተብሎ ነበር አሁን ግን የቀሩት በረሃ ይብላን ብለው ወደ በረሃ ወርደዋል።አሁን የቀሩት ወደ 40 ይሆናሉ።ሌላው ግን በርካቶች ሰዎች ሚሊሻ ታጣቂ ሁሉ ወገናችንን አንጨፈጭፍም ብለው ወደ በረሃ መውረዳቸውን እየደወሉ እየነገሩን ነው ያሉት''

ቪኦኤ:- የተገደሉት ይታወቃሉ?

''የተገደሉት አይታወቁም ሁለት በረሃ ተገለው ተገኝተዋል።አንዱ አድራሻው ጠፍቶብናል።ሊላይ ብርሃኔ የሚባል ልጅ ታፍኖ ጠፍቶብናል። አድራሻው አይታወቅም።ሁለቱ ግን በእኛ አካባቢ ሞተው ተገኝተዋል።''

ቪኦኤ:- አስከሬናቸውን አይታችኃል?

''አዎን አይተናል ግን ከየት ይምጡ ከየት አይታወቅም ሞተው አይተናቸዋል። አንዱ ግን ሊላይ ብርሃኔ ይሆናል ብለን ገምተናል።''

ቪኦኤ:- እንዴ እናንተ አቶ የላይን አታውቁትም?

''እናውቀዋለን ግን አስከሬኑ መልኩን ቀይሯል''

በመቀጠል ሌላ ተጠያቂ ቀረቡ እና  ስለሁኔታው እንዲህ አሉ:-

''ከጎንደር ወደ ሁመራ የሚወስደው መንገድ ተዘግቷል።ከዳንሻ ወደ 30 ሰው አማራ ነን የሚሉ ታስረዋል።አንድ የ16 ዓመት ልጅ ትናንት ማታ በጥይት ገለውታል። ሌላይ ብርሃኔን ከጎንደር ይዘውት እስከ ሳንጃ ድረስ ይዘው ሲያመጡት ታይቷል ቡሬ የሚባል ቦታ ነው የያዙት ከእዛ አልታየም እሱንም ገድለውታል።''

ቪኦኤ:- የያዘው ማነው?

          ''የትግራይ ደህንነት''

ቪኦኤ:- እንዴት አወቃችሁ የትግራይ ደህንነት መሆናቸውን?

        ''እዚህ ሁለት ታርጋ የሌላቸው እና የሱዳን ታርጋ የለጠፈ መኪናዎች እዚህ ቆመው ሰንብተዋል።እነርሱ ናቸው የወሰዱት''

ቪኦኤ:- የመንግስት ደህንነት መሆናቸውን እንዴት አወቃችሁ?

         ''ይታወቃል እናውቃለን......ብዙ ሰው በረሃ ግብቷል።''

ቪኦኤ:- በረሃ ገብቶ ምን ያደርጋል? 

      ''በረሃ ገብቶ አማራጭ መፈለግ''

ቪኦኤ:- አማራጭ ምን ይደረጋል?

''በቦታው ሰላም ከሌለ በዱር ሆኖ መታገል ይቻላል ''

ቪኦኤ:- አሁን ሰሮቃ ከተማ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች እርስዎ ያሉባት?

''ዝግ ነው መኪና አይንቀሳቀስም ''

ቪኦኤ :- ለምንድነው መኪና የቆመው?

''አድማ ነው አድማ''

ቪኦኤ:- መኪናዎቹ ናቸው አድማ የመቱት?

''ህዝቡ ነው የአማራ ጥያቄ ይመለስ በሚል ነው''

ቪኦኤ:- የመንግስት አካላት ናቸው መኪና እንዳይተላለፍ ያደረጉት?

      ''ህዝቡ ነው የመንግስት አካላት የሉም።ህዝቡ ነው መንገዱን እንጨት እና ድንጋይ ዘግቶ አማራ እየተደበደበ ነው መብታችንን ብሎ''

ቪኦኤ:- ታድያ እስካሁን መልስ የሰጣችሁ  የለም?

''መልስ ከፌድራልም ከዞንም የለም አራተኛ ቀናችን ነው''

ቪኦኤ:- የሊላይ ብርሃኔ ጉዳይስ እየተከታተላችሁ ነው?

''ወንድምዬው ጧት  መጥቷል  አይቼዋለሁ።ወንድሜ ሞቷል ገለውታል ብሎ ሲያለቅስ አይቼዋለሁ።''

በመጨረሻም ቪኦኤ ከህወሓት በኩል ምላሽ ለማግኘት ጥረት ማድረጉን ግን ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን አክሎ ገልጧል።ከእዚህ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ሕዝብ በውሃ እጦት መቸገሩን እና በርካታ የከተማዋ ክፍሎች እሰከ 20 ቀን ድረስ ውሃ እንደማያዩ ነዋሪዎች አማረው ሲናገሩ አሰምቷል።


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com 
መጋቢት 14/2008 ዓም 

በስድስት ደቂቃዎች ውስጥ የጎንደር አብያተ መንግሥታትን (ቪድዮ) The Palaces and Castles of Gondar, Ethiopia



ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Emperor Fasilidas established Gondar as a capital of Ethiopia in 1636. The castles, palaces and churches from the period are now UNESCO World Heritage Site. In the video, the main Gondar historic sites: Fasil Ghebbi, Fasiladas Bath, Debre Berhan Selassie Church, Kuskuam (Empress Mentewab's Royal compound).


Monday, March 21, 2016

የአቶ አሰፋ ጫቦ ግልፅ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ መንግስት - ''ይህንን የኢህአዴግ የክልል መንግስት፣ የታሪክና የማህበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት ነገ ሲተነትኑት፤ 'ዘመን መሳፍንት ዳግማዊ' የሚሉት ይመስለኛል'' አቶ አሰፋ ጫቦ

አቶ አሰፋ ጫቦ 

ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርይም ደሳለኝ 

ከአቶ አሰፋ ጫቦ 

         ይህን ደብዳቤ እንድጽፍልዎ ያስገደደኝ፣ ዛሬ አገራችን የገባችበት ማጥ ነዉ። ከፖለቲካነትን ይልቅ የ“ኧረ ምን ይሻላል! ኧረ  ምን ይበጃል !” ደብዳቤ አድርገው ቢያዩልኝ ደስ ይለኛል። እንደ መፍትሔ አፈላላጊ የአገር ሽማግሌ ድምፅ ሆኖ እንዲታይልኝ/ቢታይልኝ እወዳለሁ። ነውም!! ”የጋራ ቤታችን” እንዲህ ማጥ ውስጥ ስትዘፈቅ የሚያይ አገር ወዳድ ሁሉ ድምጹን የመስማት ግዴታ ያለበት ወቅት ላይ ነን ብዬ አምናለሁ። ከፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ይልቅ የአገራችን የኢትዮጵያ መሰንበት፤ ከዚያም “በነጻነትዋ ለዘላለም ትኑር!” ማለት ይቅደም እንደማለት ነው። በደርግ ቋንቋ “ኢትዮጵያ ትቅደም!” እንደማለት!
ታዋቂዉና ዝነኛዉ የጥንቱ የቻይና ሊቅ ሱን ዡ (Sun Tzu) በ “የጦርነት ጥበብ “ (The Art of War) መጽሐፉ ከጻፈው ጠቅሼ ብጀምር የሚሻል መስለኝ፡- 
“..ጠላትህን (ይቃወመኛል የምትለውን) የምታውቅ ከሆነ ፤ደግሞም ራስክን የምታውቅ ከሆነ የግጥሚያ ወጤት ከቶም አያጠራጥርም:: ሆኖም፤ ራስክን ብቻ አውቀህ ጠላት ነው (ተቃዋሚ ነው) የምትለውን የማታውቅ ከሆነ  አሸነፍኩ ባልክ ቁጥር ሽንፈት ያጋጥመሀል። ከዚህ ውጭ ግን ራስክንም ጠላቴ (ተቃዋሚዬ የምትለውን) የማታዉቃቸው ከሆነ በገጠምክ ቁጥር ሽንፈት እጣህ ይሆናል” ይላል፡፡
ከነጉዳንጉዱ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን መንግስት ለማድረግ ሙከራ ያደረገ መንግስት ቢኖር ደርግ ብቻ ነበር  ለማለት የምንችል ይመስለለኛል። የስልጣን መሠረቱ ብሔረሰብ አልነበረም። ያም ሆኖ የብሔረሰብ ጭቆና መኖሩን ተቀብሏል። ተቀብሎም  በመላ- ምት ሳይሆን ጥናት ላይ በተመሠረት መፍትሔ ለመሻት ተንቀሳቅሷል። “የብሔረሰብ ጥናት ተቋም” (Institute)፤ በምርጥ የኢዮጵያ ምሁራን የሚመራ፣ አቋቁሟል። የዚያ ጥናት ውጤት ሰባት የመፍትሔ አማራጮች ያቀፈ ነበር። በጊዜያዊነትም ቢሆን ከነዚህ አማራጮች አንዱን  “የራስ ገዝ”  የሚለውን በስራ አውሎ ኢትዮጵያን በዚያ ለማስተዳደር ሞክሯል። 
ኢሕአዴግ ከዚህ የደርግ ጥናት ውስጥ ሰባተኛ የነበረውን አማራጭ ወስዶ አገሪቱን “ክልል” በሚል  መጠሪያ ክልል አዋቀረ። ክልል ማለት በዚህኛው አገባቡ፣ለኔ፣ “አጥር ታጠረ!” እንደማለት ነው” “ድርሽ ትልና!  ድርሽ ትይና!” እንደማለት። ደርግ ለኃይለሥላሴ  ሲል እንደነበረው፤ “ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረው” ይኸዉ ላለፉት አራት ወራት ቁርጡ ለይቶለት መፈረካከስ ጀመረ። መንግስትዎን ይህ ነገር “ወትሮ ነበር እንጅ መጥኖ መደቆስ፤ አሁን ምን ይባላል ድስትን ጥዶ ማልቀሰ!”ን አስታወሰኝ። በዚህ ላይ መንግስትዎ አሁንም ሐሳብ- ወለድ ጠላቶች ላይ ጣቱን መጠንቆሉን ቀጠለ። ያ የተለምደ ስለሆነ አይገርመኝም። ሆኖም አዲስ ኪዳን ውስጥ ያለ አንድ ነገር ያስታውስኛል።” ሌላው አይን ውስጥ ያለ ትቢያ ከመጠቆምህ በፊት አንተ አይን ውስጥ የተጋረጠውን ግንድ መጀመሪያ አስውግድ!” የሚለው ነው።
በምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር- “ተከለለ” ማለት “ታጠረ” ማለት ነው። ጋሞ “ካሎ” ይለዋል። ማስቃላ ከመድረሱ ወራት በፊት የከብቶች ማስማሪያ  መሐሉ ላይ አንድ እንጨት ይተከላል። ያንን በምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር። ያ ቦታ/መስክ “ካሎ” ሆነ ማለት ነው። ያንን እንጨት መጀመሪያ የተከለው ባለስልጣን  እስኪነቅለው ከብት ድርሽ አይልበትም። ጎሜ/ ኃጢአት ነው የሚሆነው። ወንጀል/ሽብርተኝነት እንድምትሉት! ጋሞ ውስጥ ካሎ አይጣስም። ምክንያቱም ቀላል ነው። ሕዝቡ  የተቀበለው፣ ለዘመናትም ተቀብሎት የኖረው፤ እምነቱ ፤ንብረቱ ስለሆነ ነው።
ዛሬ በአገሬ፤ በኢትዮጵያ፣ ያለው በግሪክ ተረታ-ተረት (Mythology) ያለውን የፓንዶራን ሙዳይ (Pandora Box) ያስታውሰኛል። አማልክት እንደ ምርቃት/ እርግማን ሙዳይዋን በአለም ላይ በሚገኙ ክፋቶችና ተስፋ ሞልቶ ይሀጣታል። ፓንዶራ ቸኩላ ስከፍተው ክፋቶቹ ሁሉ በረው ወጡና እቡይ ስራቸውን ተያያዙት። ወያኔ በዚህ አዲስ የመንግስት አዋቃቀሩንና ሕግ መንግስቱ ያደረገው የፓንዶርን ሙዳይ እንደመክፈት መስሎ ይታየኛል። አንድ የሚያጽናናኝ ነጥብ ቢኖር ሙዳዩ ውስጥ አሁንም ተስፋ አለ። ኢሕአዴግ ብርታትን፣ ቅንነትን፤ “ለጋራ ቤታችን” ዘላቂነትን የሚፈልግ ቢሆን፤ይህችን ሙዳይዋ ውስጥ የተረፈቸውን ተስፋ አውጥቶ ተግባር ላይ ማዋል ብቻ ነው። የዚያን እለት፤ በዚያ ወቅት ፤የኢትዮጵያ ሕዝብ በተቃውሞ ሳይሆን በድጋፍ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ይውጣል ብዬ አምናለሁ።  እኔ  ደግሞ በመሠረቱ ተስፋ መቁረጥ አላውቅበትም። ተስፋ የምቆርጥ ብሆን ይህንን ደብዳቤ ባልጻፍኩም!!
ጠቅላይ ሚኒስቴር ለነበሩት ለአቶ መለስ ዜናዊ፤የዛሬ ስንትና ስንት አመት በጻፍኩት ግልጽ ደብዳቤ አገሪቱን “አያድሩበት ቤት አያመሻሹበት አያፈርጉት!” ብዬ ነበር። እርስዎን ደግሞ “ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም!” ለማለት እፈልጋለሁ። ያለፈው ክረምት ቤቱን ነካካው እንጅ አላፈራረሰውም፤ ወይም ወደማፈራረስ አላቃረበውም ብዬ አምኜ ነው ይህንን ተረት የጠቀስኩት። እዚህ ተረት ውስጥ በውስጠ ታዋቂነት ያለው፤ ወይም አንድምታው “ያለፈው ክረምት ያናጋውን አይነት ቤት ደግመህ አትስራ!” የሚል ይመስለኛል። ማለትም እዚያ፤ ያለፈው ክረምት ቤት አወቃቀር ላይ/ውስጥ የነበረውን ደካማ ጎን አትድግመው ነው። ማለትም  “ካለፈው የግንባታ ስህተት ተማር!” ነው።
ከሆነ ደግሞ የግንባታው ስህተት ምን ነበር? ዙሪያውን ላለመዞር ስህተቱ ሕገ መንግስቱ ነው ! ስህተቱ ኢትዮጵያን በክልል ማዋቀሩ፤በብሔረሰብ ማካለሉ ነው!! 
ኢትዮጵያን በብሔረሰብ ሲዋቅር ወያኔ የመጀመሪያ አልነበረም። በ1928 ኢትዮጵያን የወረረው የጣሊያን፤ የሙሶሉኒ አወቃቀር በብሔረሰብ ላይ የተመሠረተ ነበር። “የጣልያን የምስራቅ አፍሪካ ግዛት! (Africa Orientale Italiana” ይለዋል። ከ19ኛው ምእተ አመት ጀምሮ ብዙ የጣሊያን “ሊቃውንት” ያጠኑት ጥናት ውጤት መሆኑ ነበር። የጥናታቸው ውጤት ኢትዮጵያን በጎሳ በመከፋፈል እርስ በርሳቸው ማናቆርና እነሱ ሲባሉ እኛ አርፈን መግዛት ነው የሚል ነበር። ታሪክ እንደሚነግረን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው ተባብሮ፤ ዱር-ገደል ገብቶ  ጣሊያንን አዋርዶ አባረረው። እንግሊዝም  በሰሜን በኩል የትግራይ- ትግሪኝን፣ በምስራቅ በኩል የታላቂትዋን ሶማሌ መርዝ ቀበረች/ረጨች። ባጭሩ ይህ በብሔረሰብ  መከፋፋል ከጠላቶቻችን የመጣ በመሆኑ ሞዴል አድርገን ልንቀበለው ከቶም አይገባም ለማለት ነው። ይህም ማለት   ለአዲሱ፤ መጭው ክርምት፣ የሚሰራው ቤት በጠላቶቻችን ንድፍ ላይ የተመሠረት ሳይሆን በኢትዮጵያ እሴት፤ በኢትዮጵያ እውነት ላይ መሆን አለበት ለማለት ነው። መሠረቱ፤ ጣሪያ፤ ግርግዳው፤ ታዛው የኛው ይሁን ነው። ዞር-ዞር ብሎ የማየት እንጅ ታሪካዊ እሴት ሞልቶ የተረፈን አገር ነን። ከልቤ ነው የምልዎት!!
ደርግን “ከነጉዳንጉዱ”ብዬ ነበር የገለጽኩት። ለጊዜው ለተነሳሁበት ጉዳይ ሲባል ጉዳንጉዱን ልተወውና በጎ ጎኖቹ ሊባሉ ከሚችሉት ጥቂቱን ልጥቀስ። ከሁሉ ሁሌ  ቁልጭ ብለው ከሚታዩኝ ውስጥ አብዮት አደባባይ ሰልፍ በተደረገ ቁጥር ከደርግ ሊቃናተ መንበሮች በስተቀኝ ፓትሪያርኩ አቡነ ተክለሐይማኖት፤ ከግራ ሐጂ ያሲን የክብር ቦታ ይዘው ተቀመጠው የማየው ነበር። በኢትዮጵያ ምድር የእምነት እኩልነት ለማየት ሲያልም ለነበረ እስልምና እንዲህ የክብር ቦታ አግኝቶ በአደባባይ ከማየት የተሻለ የሚያረካ ወቅት ይኖራል ብዬ አልገምትም። ከዚያም መስከርም 12ትን አረፋ፤ ታህሳስ 13ትን መውሊድ፣ ሰኔ 29ን ረመዳን ብሔራዊ በአል አድርጎ የደነገገዉ ደርግ ነበር።
የካቲቲ 25 ቀን 1967 የገጠር መሬት አዋጅና የትርፍ ቤቶችና የከተማ ቦታ አዋጅ ሌላው የሚጠቀስ ነበር። የነዚህ አዋጆች ትርጉም “መሬት ለአራሽ/ለባለቤቱ፣ የከተማ መኖሪያ ቤትን አናሳ ገቢ ያላቸው ጭምር ተከራይተው እንዲኖሩ ማድረግ ነበር።  ደርግ ወያኔን ጉድፉን አጥርቶ፤መንገዱን ጠራርጎና ዘርግቶ ጠበቀው ልንል የምንችል ይመስለኛል። ወያኔን ከጥቂት ማሻሻል/በስተቀር “ግፋ በለው!” ብቻ ነበር የሚጠበቀው። ታዲያ ምን ሆነ?
ከዚያ የሆነውን እርስዎ ደጋግመው ከተናገሩት አንዱን ብቻ ወስጄ ለመግለጽ እንድሞክር ይፈቀድልኝል። ቃል-በቃል ባልጠቅስዎትም “መንግስታችን የኪራይ ሰብሳቢ መንግስት ሆነ!” አሉ። እኔም ልሁን ማንኛውም ተቃዋሚ ወይም መንግስትዎ አሸባሪ የሚላቸዉም ቢሆኑ ይህንን መንግስት ከዚህ፣ እርስዎ ከገለጹት በተሻለ ሊገልጡት የሚቻላቸው አይመስለኝም።
ለመሆኑ እኒህ ኪራይ ሰብሳቢዎቹ እነማን ናቸዉ? የሚያከራዩት ምንን/ማንን ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። ብቻ የሚያከራዩት ቢኖር ነው አከራይተው ኪራይ የሚሰበስቡት። ይህ ደግሞ ራሱን በራሱ ገላጭ እውነት ነው። ከሆነ ደግሞ የሚያከራዩት ኢትዮጵያን ወይም የኢትዮጵያን መሬትና ቤት መሆኑ ነው። ተሳስቼም ከሆነ ልታረም ፈቃደኛ ነኝ። ልማት በሚባል ታላቅ አሳሳች ቃል ስር ዛሬ ብር ወይም ጉልበት ያለው የፈለገውን ያክል የገጠር መሬትና ቦታ ማግኘት እንደሚችል መንግስትዎ በአደባባይ የሚናገረውና አስፈጻሚ አዋጅም ያወጣለት ነው። በቅርቡ ያነበብኩት አንድ የአፍሪቃ የባለሚሊዮን ዶላር ሀብታሞች ዝርዝር ገርሞኝ ነበር። ባለሚሊዮን ዶላር ሀብታሞች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያዊያን የአንደኝነት  ስፍራ ይዘዋል። አሁን አንደኝነታችን በረዥም ሩጫ ብቻ ሳይሆን በዶላር ጭምር መሆኑ ነዉ/ሆነ።  እንደ ኢትዮጵያዊነቴ በዚህ ልኩራበት ወይስ ልፈርበት? ይህ ሁሉ የተቻለውን ‘በሕጉ’ መሠረት ባለመሬቶቹ ከመሬትና ቤት ንብረታቸው ተነቅለው ተጥለው ነው።  የመሬት ላራሹ አዋጅ፣ መሬት ለኪራይ ሰብሳቢ በሚል አዋጅ የተተካ አይመስልዎትም? የእስልምና ተከታዮችም  ከብዛታቸው የተነሳ ስማቸውን ልጠራ የማልችለውን ወህኒ ቤት ሞልተውታል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ የተሰየመ አነሰም በዛ የመቶ አመት ታሪክ አለ። ይህም ማእከላዊ መንግስት የላላበት፤ የአካባቢ መሳፍንት የነገሱበት ዘመን ማለት ነው። ግዛቱን ለማስፋት፤ ወይም ጉልብቱን ለማሳየት፤ ወይም እኔ ካንተ በናቴም ባባቴም እበልጣለሁ በሚል ሰበብ አስባብ ጦርነት የሚከፋፈቱበት፤ ሚስኪኑ ኢትዮጵያዊ የሚያልቅበት ዘመን ነበር። ያንን ዘመን በር-ቀዳጅ የአድዋው ስሑል ሚካኤል ነበሩ።
ከዚያ ያለው እንደገና የማእከላዊ መንግስት መመስረት፤ ወይም ግዛት ማስፋት ዘመን ነበር። የዚህ አይነት ብሔራዊ መንግስት የመመስረት ሂደት (The Formation of National State) የሰው ልጅ ታሪክ ወጥ አካል ነዉ። ከነክፋቱ!! የአሁንዋ/የዛሬይቱ ኢትዮጵያም የዚያ ወጤት ነች። አሁን ከ120 አመት በላይ ሆኖታል። በዚህም የተነሳ ዛሬ ኢትዮጵያ በሚባለው አገር  ታይቶ ተስምቶ የማይታውቅ የብሔረሰብ አነባበሮ ተፈጥሯል። በዚህም 120 አመታት ውስጥ መጋባት፤ መገባባት፣ መግባባትና መዋለድ ብቻ ሳይሆን  አብሮ የመኖርና የመቻቻል  ስነ ልቦና (Psychological make up) ተፈጥሯል። 
ይህንን የኢህአዴግ የክልል መንግስት፣ የታሪክና የማህበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት ነገ ሲተነትኑት፤ ዘመን መሳፍንት ዳግማዊ የሚሉት ይመስለኛል። በአገር ደረጃ ወደፊት መራመድ ራሱ ከባድ መሆኑን ይሔው የምታዩት ነው። 200 አመት ወደ ኋላ ለመውሰድ መሞከር ግን የጤና አይመስለኝም። ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ ዩጎዝላቪያ ይባል የነበረው አገር ህዝብ አይነት አይደለም። ያ ሕዝብና  መንግስት እንደዚያ የተፈረካከሰው የዛሬ 500 አመት በፊት የሆነ  የታሪክ በደል በማንዠጉና አላምጦ ባለመዋጡ ነበር። ቱርክም፤ ሊባኖስም፤ ሶሪያም፤ ኢራቅም አይደለም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ቂም በቀል ፤የነበረ ያልነበረ የሚያመንዥግ ህዝብ  አይደለም። አላምጦ ውጦ የታሪኩ አካል አድርጎ ወደፊት የሚራመድ ታላቅ “ይቅር ለግዜር!!” ተባባይ ህዝብ ነው።  የታላላቅ እምነቶቹም ሆነ የባሕላዊ እምነቶቹ መሠረቱ ይሔው ነው።
የእስልምና እምነት በአላት በደርግ ዘመን ወደ ብሔራዊው በአልነት መሸጋገራቸውን አንስቼ ነበር። አሁን በኢሕአዴግ ዘመን ደግሞ ምን እንደደረሰባቸውና በመድረስ ላይ እንዳሉ የሚያዉቁትና መላው አለምም የሚያዉቀው ስለሆነ ዝርዘሩ ውስጥ አለገባም። አንድ ነገር ብቻ ላስታውስዎት እወዳለሁ። ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት የመለስ ዜናውን “የመጨረሻ ኑዛዜ” ያንብቡ። ኑዛዜ ያልኩት ከማረፋቸው አንድ ይሁን ሁለት ወር በፊት ያደርጉት የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ስብሰባ ቃለ ጉባዔ ነው። ይህንን ሚስጥራዊ ቃለ ጉባዔ ያነበብኩት ድሕረ ገጾች ላይ ተለጥፎ ነበር። ማመን ነበር ያቃተኝ!! ወይም አንድ ሰው “የመጨረሻው ደውል” እንደተደወለለት ሲያውቅ፤ “እውነቱን ተናግሬ ልሙት!” ያሰኘዋል ይሉናል። በዚያ ስበስባ ላይ የአቶ መለስ አስተያየት ከማውቃቸውና ከሚታውቁበት መለስ ለየት ያሉ ነበር። እውነት ብቻ ሳይሆን የሚስጥር እውነት ነበር። ይህ እውነት የመጀመሪያቸውም የመጨረሻቸውም ነበር ብዬ እገምታለሁ። 
አቶ መለስ ያሉት ቢጨመቅ “ይህንን የእስልምና እምነት ችግር የቀየስነውና የፈጠርነው እኛው (መንግስት) ስለሆንን ከዚህ በኋላ ይወገድ!” የሚል ይሆናል። የተቃወመ ሰው ቢኖር አንድ ዶክተር ሽፈራው ተክለ ማርያም  የሚባሉ ነበሩ። የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ  መደገፍ ብቻ ሳይሆን ድርጊቱን አውግዘውና ይህንን ወሳኔ አድምቀው፤ አክርረው ደግፈዋል። ያም ሆኖ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዛሬም አክራሪ ይሁን አሸባሪ (ልዩነት አልገባኝም፤ የገባውም ሰውም አላገኘሁም) በሚል እንደታጎሩ፤ያልታጎሩትም “ማነህ ባለ ሳምንት!”ን በመጠባበቅ እንደተሳቀቁ ናቸውና እባክዎን የአቶ መለሰን ኑዛዜ ስራ ላይ ያዉሉት። ከዚያ የተሻለ መፍትሔ የለምም!!
ይህንን ደብዳቤ  ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለሰ ዜናዊ አንዴ ከተናገሩት ጠቅሼ ማጠቃለል ፈለግሁ። መለስ፤ በሆነ አጋጣሚ (ረስቸዋለሁ) “በሩም መስኮቱም ከተዘጋ ህዝቡ ግድግዳውን ሰብሮም ቢሆን ይወጣል” ነበር ያሉት። ቃለ በቃል መጥቀሴ ሳይሆን መንፈሱ ይሔው ነበር። ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ የሚታየው ቃል በቃል ይሔው መሆኑ የሚያከራክር አይመስለኝም። በምድር ላይ የሚታየው ማስረጃ ይሔው ነው። በሰነዶች ላይ የሚታየው ይሔው ነው። ተቃዋሚዎች፣ መንግስት ግን አክራሪ ወይም አሸባሪ የሚላቸውም፣ የሚናገሩት ይህንኑ ነው። አገርና አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አካላትም የሚሉት ይህንኑ ነው። እርስዎም በተደጋጋሚ በሚያደርጉት ንግግር የሚሉት መንፈሱ ሲነጠር ይሕንኑ ይመስላል።
ይህ ሁሉ ሲሰባሰብ አንድ እውነት የሚያሳይ ይመስለኛል። ይህንን ኢሕአፈግ “ልማት፣ እድገት” ያለውን ሕዝቡ አልተቀበለውም። ይህንን ኢሕአዴግ መቶ-ከመቶ(100%) ድምጽ አግኝቼ ምርጫ አሸንፌያለሁ ያለው ውሸት መሆኑ ነው። ውሸትም ባይሆን ትላንት መቶ-ከመቶ (100%) የደገፈ በማግስቱ መቶ-ለመቶ ፈንቅሎ አይነሳበትም ነበራ! ወደ ህዝቡ መግቢያ ሽፋን እንዲሆኑ የተፈጠሩት ለምሳሌም እንደ ኦሮሞ  ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት  የተባለውን ሽፋን መስጠት ቀርቶ ራሳቸው የሚሸፈኑበት ያጡ መሆናቸውም እውነት ነው። “አባይ ማደሪያ የለው ግንድ ያገላብጣል”ን አስታወሰኝ። እዚህ ያላነሳሁትን ሌሎች ማስረጃዎች ሰብሰብ አድርገን ብናበራያቸው ይህ ኢሕአዴግ ያመጣው ስርአት አልሰራም ማለት ነው። “ለማንም አልበጀ!” ሆኗል እንደማለት ነው። አድሮ ከዋለ ደግሞ ካደረሰው በላይ ዘላቂና ጠላቂ ጉዳት ያመጣል የሚል ብርቱ ፍርሐት አለኝ።
እንደኔ እንደኔ መፍትሔው፤ መውጫው ችግሩን በድፍረት ፊት ለፊት መጋፈጥ ነው። አውቃለሁ! መጋፈጡ እንዲህ ቀላል አይመስለኝም! ድፍረቱም ብልሐቱም ላይኖር ይችላል። ያም ሆኖ ግን አማራጩ፤ ማለትም አድሮ ውሎ ጊዜ ይፈተዋል   በሚል የሚሰጥ የመተንፈሻ ጊዜ መግዣ ምክንያት መደርደር  የሚጸጽት አማራጭ ይፈጥራል።  
ትላንትና ያደመጥኩትን አንድ ነገር ልጨምር ፈለግሁ:- ከሶቪየት ህብረት ዘመን ጀምሮ ሩሲያን የሚያውቁ፤ አሁን ጡረታ ላይ የሚገኙ ጋዜጠኛ አን ጋረለስ (Anne Garreles) ሰሞኑን Public Broadcasting System (PBS)  በተባለ ራዲዮ ጣቢያ  Fresh Air በሚባል ፕሮግራም ላይ ረዘም ያለ ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር። ለቃለ መጠይቁ ዋንኛ ምክንያት የፑቲን አገር “Putin Country” የሚል መጽሐፍ ደርሰው ስለነበር ነው። 
ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያ የአሁኑ ፕሬዚዳንት ናቸው። ጋረልስ በዚህ ምልልስ በዚያ አገር፣ በሩሲያ፣ ውስጥ የሚታየውን የፖለቲካና ሁሉ ዘርፍ አቀፍ ንቅዘት ይዘርዝራሉ። የፑቲንን ጨምሮ!   “ይህ ሁሉ ጉድ እያለ ሕዝቡ ፑቲንን እንዴት ያያል?” ለሚለው በሰጡት መልስ “ዛሬ በአለም ላይ ከሚገኙት መሪዎች ሁሉ በመላው የሀገሪቱ ህዝብ በጣም ተወዳጅነት ያለው መሪ ቢኖር ፑቲን ናቸዉ”አሉ። ምክንያቱን ሲጠይቁ “ከሳቸው በፊት የነበረው ፕሬዝዳንት፣ ቦሪስ የልሲን፣ ሰካራም ከመሆኑም ሌላዘራፊም ነበር። ዝርፊያው እንደቀጠለ ሆኑ ፑቲን በአገራችን፤ በሩሲያዊነታችን እንድንኮራ፣ እንድንኩራራ፣ አፋችንን ሞልተን ሩሲውያን ነን ለመለት አበቃን!” የሚል መልስ ሰጡ። ቃለ ምልልሱን ከጠቀስኩት ጣቢያ ማድመጥ የሚችሉ ይመስለኛል።
ለኛም የምንኮራባት፤ በጠፍ ጨረቃ ጥለን የማንፈጥጥባት፤ እንደወጣን የማምንቀረርባት፤ ለመመለስ የምንናፍቃት ኢትዮጵያን እንዲያስቡ፤ እንዲያልሙ፣ ወደዚያ የሚወስደውን መንገድ በሙሉ መስራት ባይችሉ እንኳን ጠረግ ጠረግ እንዲያደርጉ ከልብ እመኛለሁ። እመኝሎታለሁም!
ብርታት፤ ብልሐት እመኝላችኋለሁ! ለአገሬም የተሻለውን፤ የሚበጀውን፤ የሚያምረውን፣ የሚዘልቀውን የሚያዘልቀንን እመኝላታለሁ!

ኢትዮጵያ በሕዝቦችዋ ትብብር በነጻነትዋ ለዘለዓለም ትኑር!
ከአክብሮት ጋር 

ምንጭ - አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቅዳሜ መጋቢት 10/2008 ዓም ዕትም 

Saturday, March 19, 2016

ኢትዮጵያዊ ማንነት! ሳራን ከጀርመን መቱ ድረስ የወሰደ ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑር! (የሳራን ቪድዮ ንግግር ይመለከቱ)


Video Source: TED Ideas worth spreading*


ጉዳያችን GUDAYACHN 

በሳምንቱ ውስጥ የነበሩ አጫጭር ዜናዎች (ጉዳያችን)




አቶ ኃይለማርያም የዓለም ሕዝብ የምግብ ዕርዳታ እንዲለግስ በድጋሚ በይፋ ተማፀኑ 

 ኢትዮጵያ ትናንት ዓርብ ለዓለም ማኅበረሰብ የምግብ እርዳታ እንዲሰጣት በድጋሚ ተማፀነች። ተማፅኖውን ያቀርቡት አቶ ሃይለማርያም ሲሆኑ የምግብ እርዳታው በአፋጣኝ ካልደረሰ አደጋ እንደሚከተል ገልጠዋል። አቶ ኃይለማርያም በምግብ እራሳችንን ችለናል ባሉ በአንድ ዓመት ሳይሞላ ነው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን ለሁለተኛ ጊዜ የተማፀኑት።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በረሃብ ለተጎዱ ወገኖቻቸው መርዳት ቀጥለዋል 

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮያውያን በረሃብ ለተጎዱ ወገኖች መርዳታቸውን ቀጥለዋል ባለፈው ሳምንት አሜሪካ የሚገኘው በአርቲስት ታማኝ እና የሚመራው ''ግሎባል አልያንስ'' (አለማቀፋዊ ህብረት ወይንም ቃል ኪዳን ለኢትዮጵያ) የተሰኘው ድርጅት ከአንድ ሚልዮን ብር በላይ አሰባስቦ ለ'ዎርልድ ቪዥን' አስረክቧል።በአውሮፓ እና ሌሎች አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በማሰባሰብ ላይ ናቸው።

አቶ አርከበ 'ብሉምበርግ' ቀርበው ምን አሉ?

 አቶ አርከበ በእዚህ ሳምንት ለብሉምበርግ ''በምግብ እራሳችንን ችለናል የኦሮምያው ግጭት ምጣኔ ሃብቱን አልጎዳም'' ብለዋል።እዚህ ላይ የቡና አምራች አካባቢ አመፅ ተነስቶ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ቡና ላይ የተመሰረተ ሆኖ ሳለ እንዴት ምጣኔ ሃብቱ አልተጎዳም? ብላ የብሉምበርግ ጋዜጠኛ መጠየቅ ነበረባት።አቶ አርከበ በቃለ ምልልሳቸው ላይ በኢትዮጵያ የሚነሱ ፀረ መንግስት እንቅስቃሴዎች በሙሉ ወጣቱ ሥራ ስላጣ ነው፣ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እንከፍታለን የመሳሰሉትን ይናገሩ እንጂ አገሪቱ ግልፅ የሆነ የምጣኔ ሀብት አቅጣጫ እንደሌላት ለጋዜጠኞቹ ግልፅ ሆኗል።ለእዚህም ነው የብሉምበርግ ጋዜጠኛ ''ወዴት እየሄዳችሁ ነው ምንድነው ቀዳሚ ትኩረታችሁ?''የሚል ጥያቄ የጠየቀው።አቶ አርከበ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ እንደሚመጣ እና በቅርቡ ከዓለም 10ሩ በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ አገራት ውስጥ እንደምትገባ ገልፀው ለመፍትሄነት ያስቀመጡት ግን ግልፅነት የሌለው የአገሪቱን አቅም ያላመላከተ እና ወደፊት ኢንቨስተር ይመጣል የሚል መልስ ነበር።በመሰረቱ አቶ አርከበ በቃለ መጠየቃቸው ላይ የምጣኔ ሀብት ቃላት (terminology) አጠቃቀም ላይ ከሌሎች ባለስልጣናት የተሻለ የእንግሊዝኛ አጠቃቀም ይታይባቸዋል።

''ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች'' ግብፅ በድጋሚ 'የኢትዮጵያን የአየር ክልል በሳተላይት ኢትየጠቆጣጠርኩ ነው 'አለች ህወሓት በዝምታ አበረታቷል። 

- ግብፅ የኢትዮጵያን የአባይ ግድብ ላይ ለ24 ሰዓታት ለመከታተል የቀድሞውን ሳተላይት በሌላ ልመቀየሯን በግልፅ ተናግራለች።የእዚህ አይነት ግልፅ ንግግሮች በግብፅ ባለስልጣናት ሲነገር ኢትዮጵያ እንደ ሉዓላዊ አገር ምላሽ አልሰጠችም።ይህ አንዱ የህወሓት አሳፋሪ ተግባሩ አካል ነው።የእዚህ አይነት ተግባር በግልፅ መነገራቸው ለኢትዮጵያ ያላቸውን ንቀት ለማሳየት ካልሆነ በቀር የአንድ ሉዓላዊት አገርን መሬት ከሳተላይት አያለሁ የሚሉ ንግግሮች በሚንስትር ደረጃ ሲነገሩ የተለመዱ አይደለም።በድብቅ አገራት ቢያደርጉትም በአደባባይ መናገር ግን ንትርክ ስለሚያስከትል አያደርጉትም የህወሓት ኢትዮጵያ ግን  በእዚህ ጉዳይ ላይ የግብፁን አምባሳደር ጠርታ ማብራርያም አጠይቅም።የመንደር አስተሳሰብ ካለህ ስለ ትልቁ አገር ማሰብ ታቆማለህ።ህወሓት ከአገር ይልቅ ለመንደር የሚጨነቅ ድርጅት ስለሆነ የኢትዮጵያን ጉዳይ እንዲህ ያጎሳቁለዋል።

''የኢትዮጵያው ደግ ክርስቲያን ንጉስ  እስልምናን ባይከላከል ኖሮ እስልምና ዛሬ አይኖርም ነበር'' የግብፁ የእስልምና እምነት አባት 

- ''በመጀመርያ እስልምናን ከለላ የሰጠልን ክርስትና ነው።የኢትዮጵያው ደግ ክርስቲያን ንጉስ ባይኖር ኖሮ እስልምና በአሁኑ ሰዓት ላይኖር ይችል ነበር'' ይህንን የተናገሩት የግብፅ የሃይማኖት አባት ለጀርመን ምክርቤት በእዚህ ሳምንት ነው። የሃይማኖት አባቱ እንደገለፁት ደጉ የአብሲንያ ንጉስ የመሐመድ ቤተሰቦችን መንከባከቡ እና በሰላም ማቆየቱ ዛሬ እስልምና ሳይጠፋ እንዲኖር አድርጎታል በማለት በማስረጃ አብራርተዋል።የግብፅ አልሃራም ጋዜጣ ዘግቦታል።ይህ ታሪካዊ ንግግር ነው።በመጀመርያ ደረጃ ንጉሡ ክርስትናውን ጠብቆ መኖሩን እና ኢትዮያ በዓለም ታላላቅ ክስተቶች ላይ አሻራዋ መኖሩ የተገለፀበት ነው።

ኢማሙ ለጀርመን ምክርቤት ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 6/2008 ዓም ቀርበው ያሉት እንዲህ የሚል ነበር።''Christianity was the first to provide sanctuary for Islam; without Abyssinia and its Christian king who protected the first Muslims, Islam would have been destroyed in its cradle,” Grand al-Azhar Imam Sheikh Ahmed al-Tayeb

''እየሰመጠ ካለ መርከብ ራስን የማዳኛ ጊዜ አሁን ነው!'' የአርበኞች ግንቦት 7 ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ሲጠናቀቅ ያወጣው መግለጫ።

በእዚህ ሳምንት ሌላው በድረገፆች የወጣው ዜና የአርበኞች ግንቦት 7 ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ በመጪዎቹ ሶስት ወራት የሚሰሩት ሥራ ላይ መወያይቱን እና ማፅደቁን ''ዘ-ሐበሻ'' ድረ-ገፅ ገልጧል።ድረ-ገፁ እንዳስታወቀው ስብስባው የሚከተሉትን  መልዕክቶች ለአባላቱና ደጋፊዎች፣ለመከላከያ ሰራዊት፣ለለህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴግ እና የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች አባላት እና  ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተላልፏል። መልክቶቹም : -


1. ለአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች
ወሳኝ በሆነ የትግል ወቅት ላይ እንገኛለን፤ በዚህ ወቅት በትጥቅ ትግሉ በቀጥታ ተሰልፈው ያሉት አባሎቻችን፣ በአገር ውስጥ በሕዝባዊ እምቢተኝነት በመሳተፍ ላይ ያሉ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን እና በውጭ አገራት የሚገኙ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ሁሉ በአንድ ልብና መንፈስ ህወሓትን ከስልጣን የማስወገድ ሥራ ላይ እንዲረባረቡ ሥራ አስፈፃሚው ጥሪ ያደርጋል።
2. ለአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለፓሊስና የደህንነት አባላት
ነገ ከሚወድቅ ሥርዓት ጎን ቆማችሁ ወገኖቻችሁን ማጥቃት ተው! የመሳሪያዎቻችሁ አፈሙዝ የሁላችንም ጠላት ወደሆነው አገዛዝ ይዙር! ከወያኔ በኋላ በሚመጣው ሥርዓት የመከላከያ ሠራዊትና ፓሊስ መበተን የለባቸውም ብለን እናምናለን፤ ይህ እንዲሆን ግን ዛሬ ከአምባገነን ሥርዓት ጎን ሳይሆን ከሕዝብ ጎን ቁሙ።
3. ለህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴግ እና የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች አባላት
እየሰመጠ ካለ መርከብ ራሳችሁን አውጡ! አባል የሆናችሁባቸው ድርጅቶች ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለእናንተም በግል የሚበጁ አይደሉም። ቢቻል በግልጽ፤ ካልተቻለም በስውር ድርጅቶቻችሁን በማዳከም የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግልን አግዙ።
4. በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ለሚታገሉ የፓለቲካና ሲቪክ ማኅበራት
በጋራ የምንቆምበት ወቅት አሁን ነው። ዛሬ የምናደርጋቸው ትብብሮች የረዥም ጊዜ ውጤት ያላቸው መሆኑን ተገንዝበን ኃይላችንን እንድናስተባብር ጥሪ እናደርጋለን።
5. ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ
ጥያቄዎቻችን አካባቢ ተኮር ሊሆኑ ይችላሉ፤ ግባችን ግን የጋራ ነው። ከህወሓት አምባገነን አገዛዝ ነፃ የወጣች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትኖረን ሁላችንም በአንድነት እንድንቆም የአርበኞች ግንቦት 7 ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥሪ ያደርጋል። 

የሚሉ ነበሩ።

ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com 

መጋቢት 10/2008 ዓም  (March 19/2016) 

Tuesday, March 15, 2016

ኦኬሎ ይፈታ! ኖርዌይ ኢትዮጵያውያንን በግዳጅ መመለስ ታቁም! ኢትዮጵያውያንን መግደል ይቁም! በሚል በኖርዋይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰልፍ አደረጉ።







ዛሬ መጋቢት 6/2008 ዓም በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ኢትዮጵያውያን የኖርዌይ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያዊው  ኦከሎ አክዋይ ኦቻላ በወያኔ ደቡብ ሱዳን ላይ ተጠልፈው ለእስር መዳረጋቸውን፣ የኖርዌይ መንግስት በግዳጅ ኢትዮጵያውያንን ከአገሩ ለማስወጣት እና ወደ ኢትዮጵያ ለመውሰድ ማቀዱን በመቃወም እና በኦሮምያ እና ልዩ ልዩ የአገራችን ክፍሎች የተፈፀሙትን እና በመፈፀም ላይ ያሉትን ግድያዎች እና እስራቶች በመቃወም  ሰልፍ ወጥተዋል።ሰልፉ የአገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ፅህፈት ቤት ከሚገኝበት እስከ ምክርቤቱ ድረስ የ20 ደቂቃ የእግር ጉዞ በማድረግ የተከናወነ ሲሆን በሰልፉ ወቅት የኖርዌይ ፖሊስ በፈረሰኛ እና በመኪና በመታገዝ ጥበቃ አድርገዋል።

በሰልፉ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ የኖርዌይ ዜጎች ከደቡብ ሱዳን በግዳጅ ታግቶ የተወሰደው የቀድሞ የጋምቤላ አስተዳደር ኦኬሎ በፍጥነት እንዲፈታ የሚጠይቅ መፈክር እና ፎቶ ግራፍ ይዘው ነበር። በሰልፉ ላይ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች፣የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ እና የኖርዌይ እና ዓለም አቀፍ ሰብአዊ እና ፀረ ዘረኝነት ድርጅቶች ተወካዮች የተገኙ እና ንግግር ያደረጉ  ሲሆን የሰልፈኛውን ጥያቄ የያዘ ደብዳቤም ለኖርዌይ ፓርላማ እንዲደርስ  መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።

ከእዚህ በታች በጉዳያችን የተነሱ የሰልፉን ገፅታ የሚያሳዩ ፎቶዎች ይመልከቱ።













ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
መጋቢት 7/2008 ዓም


Saturday, March 12, 2016

''ኩዳድ '' የአማርኛ ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ መፅሐፍ በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ተመረቀ

የኩዳድ የፊት ገፅ 

በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አርአያነት ያለው ተግባር እየፈፀሙ ነው። በአራት ዓመታት ውስጥ ሁለት የአማርኛ መፃህፍት፣አንድ ዳጎስ ያለ የአማርኛ ኖርዌጅኛ መዝገበ ቃላት እና ሰዋሰው (grammar)  ታትመው ገበያ ላይ ውለዋል። ይህ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትልቅ አርአያነት ያለው ተግባር ነው።
ወ/ሮ ዙፋን የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ ሰብሳቢ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ 

ዛሬ መጋቢት 3/2008 ዓም ደግሞ በደራሲ አቶ ማተቤ  መለሰ የተፃፈ ''ኩዳድ'' የተሰኘ ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ መፅሐፍ የምረቃ ስነ-ስርዓት ተከናውኗል።

ይህ 433 ገፆች የያዘ ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ  መፅሐፍ ምረቃ መርሃ ግብር ላይ በርካታ በኦስሎ እና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የታደሙበት ሲሆን የመክፈቻ ስነ-ስርዓቱን የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በኖርዌይ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዙፋን ለምረቃ የተዘጋጀውን ሪባን በመቁረጥ መፅሐፉ መመረቁን አብስረዋል።በመቀጠልም መፅሐፉ በሶስት ምሁራን ተገምግሟል።በመፅሐፍ ግምገማው ላይ በኦስሎ ዩንቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ተክሉ አባተ፣ ዶ/ር ሙሉ ዓለም አዳም እና አቶ ይበልጣል ጋሹ የተሳተፉ ሲሆን ሶስቱም ጥልቅ የሆነ ዕይታቸውን ለታዳሚው  በየተራ አቅርበዋል።
ደራሲው አቶ ማተቤ መለሰ  ከልጆቻቸው ጋር የኬክ ቆረሳ ስነ-ስርዓት ላይ 


ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ተክሉ አባተ ከመፅሐፉ የፊት ገፅ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ የታሪኩን ፍሰት እና ተያያዥነት ከመፅሐፉ እያጣቀሱ እና የገፀ ባህርያቱን የገሃዱ ዓለም ነባራዊ ነፀብራቅ መሆን ላይ አፅንኦት ሰጥተው ያብራሩ ሲሆን ዶ/ር ሙሉ ዓለም በበኩላቸው ከደራሲው ጥረት እና ትጋት ተነስተው እስከ ቃላት አጠቃቀም ጥልቅ ግምገማቸውን አቅርበዋል።አቶ ይበልጣል ጋሹ በሌላ በኩል በመፅሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት ታሪኮች ምን ያህል ከቦታው ባህላዊ መስተጋብር ጋር የተያያዘ መሆኑን እና የሚያካልላቸው ቦታዎች ከጎጃም እስከ ኤርትራ ከዝያም እስከ ሱማሌ ምድር ድረስ  መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ ሰብሳቢ በማኅበረሰቡ ስም ለደራሲው ስጦታ ሲያበረክቱ 

ከመፅሐፉ ግምገማ በኃላ የሻይ እረፍት ተደርጎ ከታዳሚው ለገምጋሚዎች እና ለደራሲው አቶ ማተቤ መለሰ ጥያቄዎች፣አስተያየቶች እና የመልካም ምኞት መግለጫዎች ተሰምተዋል።ለቀረቡት ጥያቄዎች ደራሲው እና የመፅሐፉ ገምጋሚ ምሁራን በቂ መልስ የሰጡ ሲሆን በመጨረሻ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ ለደራሲው ውድ ጊዜያቸውን ሰውተው በስደት አገር ለአገራቸው ይህንን በማበርከታቸው አርአያ ሆነውናል በሚል ልዩ ስጦታ አበርክቶላቸዋል።በመጨረሻም  ደራሲው ከአራት ልጆቻቸው ጋር በመሆን የኬክ መቁረስ ስነ-ስርዓት የተካሄደ ሲሆን የደራሲው አቶ ማተቤ መለሰ  ልጆች በጋር ይህንን የምረቃ ዝግጅት ላዘጋጁ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ አባላት የምስጋና የአበባ ስጦታ አበርክተዋል።

በመፅሐፉ የፊት ገፅ ላይ እንደሚነበበው መፅሐፉን ለማዘዝም ሆነ ደራሲውን ለማግኘት የሚከተሉትን አድራሻዎች መጠቀም ይችላሉ።

ተንቀሳቃሽ ስልክ = (0047) 99850153
ኢ-ሜል = matebemelese@yahoo.com  


ጉዳያችን GUDAYACHN 
www.gudayachn.com
መጋቢት 3/2008 ዓም