Wednesday, March 9, 2016

የኢትዮጵያ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሁኔታ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ትከሻ ላይ ወድቋል።የችግሮቹ የመፍትሄ አካላት እነማን ናቸው? መፍትሄው ምን ይሁን? (የጉዳያችን ወቅታዊ ማስታወሻ)





ስለ አገራችን ፖለቲካ ብዙ ብዙ ተብሏል።ሁሉም ከቆመበት ጥግ እየተነሳ ዕይታውን አካፍሏል።ከእዚህ ሁሉ ጋር ግን ያለንበት ጊዜ ምን ያክል አጣዳፊ እና ኢትዮጵያን የማዳን ሥራ የአንድ ግለሰብ ወይንም መሪ ወይንም የፖለቲካ ድርጅት ጉዳይ አለመሆኑን በምን ያህል ደረጃ ተገንዝበነዋል? የሚለው ጥያቄ  ሁል ጊዜም ወሳኝ ነው።ይህ ጉዳይ የሚመለከተው በኢትዮጵያ ምድር ላይም ሆነ ውጭ  ያለ ማንኛውንም ግለሰብ፣የፖለቲካ ድርጅት፣የጦር ኃይሉን  እና የትኛውንም ማኅበረሰብን ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት አጣብቂኝ ሁኔታ በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ/ህወሓት ስልጣን መንገዳገድ  እና መንገዳገዱን ተከትሎ የሚመጣው የፖለቲካ ትኩሳት ብቻ አይደለም።ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያን እንደ አገር እንዳትቀጥል ለዘመናት የዋተቱ ኃይሎች በከፍተኛ ከበባ ላይ ናቸው።ይህንን አላየንም አልሰማንም ብለን የምናልፈው ጉዳይ አይደለም።ይህንን ያክል የፖለቲካ ጅልነት የሚያጠቃው ኢትዮጵያዊም የለም።ችግሩ ግን እይታችን በየገባንበት ጎጥ እና ጉራጉር ጉዳይ ውስጥ ተከለለና  አጠቃላይ የሆነውን የአገሪቱን ስዕል ማየት ተስኖናል።ይህ ፅሁፍ ባጭሩ ግን አሁን ያለብን ችግር እና መፍትሄዎቹ ምን መሆን ይገባቸዋል የሚለው መሰረታዊ ነጥብ ላይ ብቻ ያተኩራል።ፅሁፉ እይታም ነውና የአንድ ዜጋ ወይንም የሕዝብ ዕይታ አካልም አድርጎ መውሰድ ይቻላል።

አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ችግር 

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ግን ፈታኝ ችግር በአራት ነጥቦች መለየት ይቻላል። እነርሱም:
1/ በከፍተኛ ደረጃ በከፋፋይ ሥራ የተጠመደ መንግስት መኖር 

በውስጥ መንግስታዊ የጎጥ ፖለቲካ ሕዝቡን እና ማንኛውንም የኅብረተሰብ አካል በከፍተኛ ደረጃ በመከፋፈል ሥራ ተጠምዷል።ይህም ስልጣኔን ያስጠብቅልኛል ከሚል ስሌት ነው።በኦሮምያ እና በአማራ ክልል ያሉ ተቃውሞዎችን እንደ አደጋም እንደ በጎ አጋጣሚም  ስርዓቱ ይመለከተዋል።
አደጋው ለስልጣኑ ሲሆን መልካም አጋጣሚው ከመቼውም ጊዜ በባሰ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ በህወሓት ዕዝ ስር ክልሎችን በሙሉ ለማስገባት በማሰብ ነው።የኦሮምያ በስምንት የጦር ቀጠናዎች ስር  መግባት የጋምቤላ አስተዳደር መፍረስ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል የሚሰማው ሁሉ ይህንን ያገራግጣል።

2/ ለውጥ አለመኖሩ 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀዳሚ ችግር በአሁኑ ጊዜ የለውጥ አለመኖር ነው።ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥም ህወሓት ብዙ ጊዜ ሕዝቡን ሊያታልለው ሞክሯል።ስለሆነም በህወሓት ጥገናዊ ለውጥ ኢትዮጵያ ምንም አይነት መሻሻል እንደማታገኝ የሕዝቡ እምነት ነው።
ስርዓቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ገድሎታል፣አሰድዶታል፣ማንነቱን ተጋፍቷል፣አደህይቶታል፣ኑሮ አስወድዶበታል፣ሌላው ቀርቶ በከተሞች ውሃ እና መብራት መጥፋት አስመርሮት ከስርዓቱ መወገድ ጋር እንደሚፈታ የሚያምኑ ታዳጊ ሕፃናት ሁሉ ሆነዋል። ባጠቃላይ የስርዓቱ አለመቀየር የአገሪቱ ቀዳሚ ችግር ሆኖ ቀርቧል።

3/ ባዕዳን ኢትዮጵያን ከመቼውም ጊዜ የመከፋፈል አደጋ አለባት ብለው እየከበቧት ነው

ሱዳን በቀጥታ የደቡብ ሱዳን አጀንዳ ተወት አድርጋ የኢትዮጵያን ድንበር ለመውሰድ ከህወሓት ጋር ውል ጨርሳ ወደ ማካለሉ ላይ ነች።የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ ሱዳን ደርሰው የተመለሱት ትናንት ነው።የሱዳኑ ሱዳን ትሪቡን ጋዜጣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር  ካርቱም የመጡት መሬት ለሱዳን ስለሚሰጥበት ጉዳይ ለመነጋገር መሆኑን በድንበር ማካለል በሚል ስም በመስጠት ዘግቧል።በሌላ በኩል የአረብ መንግስታ ሳውዲ እና ዩናይትድ አረብ ኢምረት የጦር ጀት መንደርደርያ እና የጦር ካምፖችን በአሰብ እና ጂቡቲ ላይ እየገነቡ ነው።አንዳንዶቹን ጨርሰው ሰራዊት እያሰፈሩ ነው።በቅርቡ ሳውዲ አረብያ ለሱዳን ለጦር መሳርያ መግዣ የሰጠችው የገንዘብ መጠን 2 ቢልዮን ዶላር በላይ መሆኑ ከተዘገበ ገና ወራት ማስቆጠሩ ነው።(አል-ሞንተርን ይመልከቱ)

4/ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ የድሕነት ችግር ውስጥ ገብተናል 

አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ በልቶ ማደር ትልቅ ፈተና ሆኖበታል።በዓለም ላይ እጅግ ድሃ ከሚባሉት አገራት ተርታ ነን።የተባበሩት መንግሥታት የድህነት ወለል ብሎ ያስቀመጠው አንድ ሰው በቀን 1 ዶላር 25 ሳንቲም (በቅርቡ 25 ወደ 90 ሳንቲም ጨምሯል) አንፃር ስንታይ ገና ብዙ ይቀረናል።
በእዚህ ሂሳብ ስናሰላው በወር አንድ ሰው በወር ኢትዮጵያ ውስጥ በአማካይ  1600 ብር ማግኘት ማለት ነው።ይህ በአማካይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የወር ገቢ ሆነ ማለት በእራሱ የድህነት ወለል ነው።እኛ ግን የዓለም ባንክ ካስቀመጠው የድህነት ወለል እጅግ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነን። 

ይህ ሁኔታ ከሳሃራ በታች ካሉት የአፍሪካ አገራት ጋርም ሲወዳደር የኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ አሁንም ብዙ ልዩነት እንዳለው ማየት እንችላለን።ይህ በእራሱ ትልቅ አደጋ አለው።የድህነት መስፋፋት የፀጥታ ችግር ያስከትላል።በሌላ በኩል ደግሞ ለነፃነቱ የሚነሳ የቆረጠ ሕዝብም ይበዛል የሚሉም አሉ።ምን ይህል ትክክለኛ መሆኑ ባይረጋገጥም።

ድህነት ሲበዛ መደማመጥ ይጠፋል፣የድህነቱ ምንጭ የማንነት ችግር ተደርጎ ይወሰድ እና ወደሌላ ምስቅልቅል ፖለቲካ ይመራል።በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ በመንግሥትነት የተቀመጠው ስርዓት ይህንን ብሶት እንዲባባስ ከስልጣኑ መጠበቅያ መንገድ አንፃር ብቻ  ስለሚጠቀምበት በእሳት ላይ ነዳጅ የማርከፍከፍ ያክል ችግሩ ይሰፋል።

በእኛ አገር ያለው የድህነት መብዛት ብቻ አይደለም።በሀብት የናጠጡ ጥቂቶች መኖርም የሀብት ክፍፍሉን ጎድቶታል።በጎጥ፣በሙስና እና በሕገ ወጥ መንገድ ሃብታም መሆን የተለመደ የዋልጌ ባለስልጣናት መለያ ሆኗል። 

የችግሮቹ የመፍትሄ አካላት እነማን ናቸው? መፍትሄው ምን ይሁን

የችግሮቹ የመፍትሄ አካላት እነማን ናቸው?

ከላይ በዋናነት የተጠቀሱት ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ችግሮቹ እና አደጋዎቹ የሁሉም መሆናቸውን ማመን ሲቻል ነው።ይህ ማለት አደጋው አንድን ሕብረተሰብ በተለየ የሚያጠቃ ሳይሆን እንደ አገር የመኖር እና አለመኖር ሁኔታዎች ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ነው።በመሆኑም የመፍትሄ አካላት ሊሆኑ የሚችሉት የሚመረጡት እጅግ አግላይ በሆነ መንገድ ሊሆን አይችልም።በመሆኑም የመፍትሄ አካል መሆን የሚገባቸው የሚከተሉት ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሰራዊት ውስጥ ገብተው የሚያገለግሉ የሰራዊቱ አባላት በእየደረጃቸው፣
/ በአሁኑ ስርዓት ስር ሆነው ነገር ግን ሕዝብን እና አገርን ይቅርታ ለመጠየቅ የተዘጋጁ ባለስልጣናት፣የንግድ ሸሪኮች፣የማኅበረሰብ መሪዎች፣ምሁራን ወዘተ፣
/ ከሊቅ እስከ ደቂቅ (ከትንሽ እስከ ትልቅ) ያለ በየትኛውም የኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ ባለ ቦታ የሚኖር ኢትዮጵያዊ፣
/ በኢትዮጵያ ጉዳይ የጋራ እሳቤ ያላቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ስብስቦች በሙሉ ናቸው።

መፍትሄው ምን ይሁን? 

ከላይ አሁንም ባጭሩ እንደተቀመጠው ችግሩ ሁሉንም የሚመለከት መፍትሄውም እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ነው።እዚህ ላይ የችግሩ መፍተሄ አካል አሁን ያለውን ስርዓት ሙሉ በሙሉ ማድረግ (እራሳቸውን ከህዝብ ወገን ያደረጉ በይቅርታ ወደ ሕዝብ የሚመለሱትን ሳይጨምር) በእራሱ ችግሩን የበለጠ የምያወሳስበው ነው።

ይህ የጨለመ ወይንም ተስፋ ያጣ  አስተሳሰብ ውጤት አይደለም።ባለፉት 24 ዓመታት ተሞክሮ ስንመለከት ህወሓት የመጀመርያ እና ቀዳሚ ተግባሩ በማናቸውም ወጪ እና የአገር ክስረት ቢሆን ስልጣኑን ማስጠበቅን የመጀመርያ ስራው እንጂ የአገር ጉዳይ ቀዳሚ ጉዳዩ ሆኖ አልታየም።ባህሪው አነሳሱ እና ሂደቱ ሁሉ ያሳየው ይህንኑ ነው።በመሆኑም የስርዓቱን አቀንቃኞች ትቶ ለኢትዮጵያ የሚቆመው እና የማይቆመው በቁርጥ መለየት ተገቢ ነው።ይህንን ከግንዛቤ አስገብተን መፍትሄው ሊሆን የሚችለው አንድ ብቻ ይመስለኛል። ይሄውም ለውጥ እና ለውጥ ብቻ ነው።

አንዳንዶች ለውጥ በእራሱ ይዞት የሚመጣው ምስቅልቅል ሁኔታ ስለሚኖር ወደባሰ ችግር ላይ አገሪቱ ትገባለች ብለው የሚያስቡ አሉ።በእርግጥ ለውጥ ሁሉ ካለምንም መንገጫገጭ አይመጣም።ቁምነገሩ ግን ተንገጫግጮ ቦታው ይገባል የሚለው እሳቤ ነው።አሁን ባለው ሁኔታ መፍትሄ ሲታሰብ ያሉት ሁለት አማራጮች ናቸው።እነኝህን አማራጮች ስናወዳድር ለውጥ መምጣቱ የበለጠ አማራጭ ብቻ መሆኑን እንረዳለን።

አንድኛው፣ ምርጫ ህወሓት በስልጣን ላይ የመቆየቱ አማራጭ ሲሆን ሁለተኛው፣ህወሓት በአዲስ ስርዓት የመለውጥ ሂደት ነው።

ህወሓት በስልጣን ላይ የመቆየቱ አማራጭ

የመጀመርያው አማራጭ ስናየው ለጊዜው ኢትዮጵያ ያለች ይመስለናል እንጂ ''ዱር አልባው ሽፍተኝነት'' ያጠቃው የኢትዮጵያ ሕዝብ በምንም አይነት አገርን የማዳን ሥራ ላይ ከህወሓት ጋር አይሰለፍም።ለእዚህ ብዙ ምክንያቶች ስላሉ መዘርዘሩ አያስፈልግም።ከእዚህ ይልቅ ህወሓት በስልጣን በቆየ ቁጥር ሕዝብ የችግሩ እና የድህነቱ ምክንያት  ከማንነት ጉዳይ ጋር እየያዘው ይሄድና በመጨረሻ አገሪቱ ወደ እርስ በርስ ጦርነት የመግባት አዝማምያ ያሰጋታል።

ሁሉም ለእርስ በርስ ግጭቱ የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ ወያኔን ለማውረድ ነው ስለሚል ጉዳዩ በተለያዩ የባዕዳን እጅ የመግባት አደጋው ይሰፋል።በመጨረሻ ወያኔ እራሱ የጎጥ ፖለቲካውን ያጦዘውና (የትግራይ ሕዝብ ምን ያክል ይተባበረዋል የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ)  ትግራይን ለመነጠል ሙከራ ያደርጋል።ይህ እንግዲህ የአገሪቱ ሀብት በሙሰኛ ባለስልጣናት እና ባዕዳን የመዘረፍ ጉዳይ ሁሉ እንደቀጠለ ማለት ነው።በመጨረሻ ኢትዮጵያን የከበቡት ኃይላት በማናቸውም ጊዜ አገሪቱን በቀላሉ ከፋፍለው የማዳከም  አመቺ ጊዜ እንዳገኙ ያስባሉ። ህወሓት በስልጣን ላይ መቆየት ከቻለ መጪው ጊዜ ከእዚህ ያነሰ አይሆንም።ስርዓቱ የገባበት ቅራኔ በሙሉ ሳይፈታ እና የቅራኔው መነሻ ከስልጣን ሳይወርድ የኢትዮጵያን ህልውና ማስጠበቅ ፈፅሞ አይታሰብም።ሕዝብ እንጂ ግለሰቦች አገር አያድኑም።የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩን በባለቤትነት እንዲያድን ይህ ስርዓት ከስልጣን መውረድ አለበት።ከእዛ መለስ ግን ህወሓት ብሔራዊ ሕብረት የሚያመጣበትም ሆነ ስልጣኑን ሕጋዊ መሰረት ለማስያዝ ምንም የቀረው ጥይት የለም።በሕዝብ ዘንድ የመንግስት ሕጋዊነት (legitimacy) በእዚህ ያህል ደረጃ ከወረደ በኃላ ለመጠገን መሞከር ትርፉ የሚፎረፎተው ፍርስራሽ አይን ውስጥ እየገባ አይን እንዲያጠፋ ከማድረግ በቀር ምንም ትርፍ የለውም።ይህንን ከስርዓቱ ጋር እየሰሩ ያሉ በሙሉ ሊረዱት የሚገባ ሀቅ ነው። 

ባጭሩ የህወሓት በስልጣን ላይ መቆየት በአማራጭነት የማይቀርብ ይልቁንም ኢትዮጵያ በዘመኗ አይታ ወደማታውቀው የእርስ በርስ ግጭት የሚመራት መሆኑ መታወቅ አለበት።ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ አገር ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የማትችል ወደ ማድረግ የሚመራት አሁንም በስልጣን ላይ ያለው ቡድን የታቀደ የመከፋፈል እና የማጋጨት ሥራ ነው።

ለውጥ 

ሁለተኛው እና እንደ እኔ ብቸኛው አማራጭ የምለው በኢትዮጵያ አፋጣኝ ግን የሁሉም ህብረት የታየበት ለውጥ ማምጣት ነው።ለውጥ ጊዝያዊ  የኃይል ክፍተት፣የህዝብ አለመረጋጋት፣ የአካባቢ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች የመደመጥ አቅም መቀነስ ወዘተ ያጋጥሙታል።ለእዚህም ነው ከላይ የመፍትሄ አካላት መሆን የሚገባቸው ተብሎ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል እና ሕዝብ ይቅርታ የጠየቁ የስርዓቱ አካላት የለውጡ አካል እና ኢትዮትጵያን የማዳን ድርሻ አላቸው የተባለው።ስለዚህ የኃይል ክፍተት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥራ ብቻ ሳይሆን የጦር ኃይሉም ተግባር ነው።

ሰራዊቱ ከየትም የመጣ ሳይሆን  አሁንም ከኢትዮጵያ ሕዝብ የወጣ እና በየቦታው የሚነሱ ግጭቶች ሰለባ ስለሆነ  ችግሩ  የአገሪቱ ችግር የሚመነጨው ከመሪዎቹ እንደሆነ ይገነዘባል።ለውጥ መምጣቱ የአገራችን ችግር በጋራ መነጋገር ይስችላል፣ከልዩነታችን ይልቅ ሕብረታችንን የሚያሳዩን የመገናኛ ብዙሃን ይኖሩናል፣ ከሁለት ሚልዮን በላይ የሚገመተው በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ለአገሩ የጋራ ጉዳይ የመስራት ዕድል ይኖረዋል፣የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት በበለጠ ይነቃቃል፣ በኢትዮጵያ ላይ ከባዕዳን ጋር በማበር የሚያሴሩት በግልፅ ለሕዝብ ይጋለጣሉ፣ ሕዝብ በእራሱ የመለያየት ፖለቲካ አራማጆችን ከአገራዊ ፖለቲካ አራማጆች የመለየት ዕድል ስለሚያገኝ የመወሰን አቅሙን ያሳያል።

ይህ ሁሉ ሁኔታ ህወሓት በስልጣን ላይ ሆኖ ህዝቡ በመታፈኑ ሳብያ የሚመጣው አደጋ ጋር ሲነፃፀር ለውጥ የሚያመጣው አንድነት እና ህብረት የበለጠ የአገሪቱን አንድነት የማምጣት አቅም ይኖረዋል። እዚህ ላይ ብዙዎች በሌላ አገር ያሉ ተሞክሮዎችን በማንሳት ከአምባገነን መሪዎች በኃላ መከፋፈል እንደሚኖር ሊሰብኩ ይሞክራሉ።ይህ ግን እንደ ኢትዮጵያ ላለ የእረጅም ጊዜ ማኅበራዊ መስተሳስር ላለው ሕዝብ አይሰራም።እርግጥ ነው ይህ ማለት ማኅበራዊ መስተሳሰር በእራሱ ተአምር አይፈጥርም። ትውልድም ተቀይሯል።ስለሆነም የምሁራን አስተዋፅኦ በጣም ይፈለጋል።በዝምታ የእራስን ኑሮ እየኖሩ ከንፈር መምጠጥ በእራሱ ኢትዮጵያን ከመግደል አይተናነስም።


ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ እንደ ውሃ ጠብታ ቀስ እያለ እየሸረሸራት ነው። ችላ ብሎ ወይንም ዝም ብሎ የሚኖረው ሕዝብ እጣው እና ህይወቱ ከአገሩ ጋር መያያዙን ማመን አለበት።በተለይ ምሑራን ቢያንስ ለአገራቸው እና ለሕዝባቸው አዳዲስ ሃሳቦች ከማፍለቅ አንስቶ የኑሮ መደላድላቸውን ብቻ እየተመለከቱ ከመኖር ባለፈ ለኢትዮጵያ ምን ላድርግ ማለት አለባቸው።ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ማለት በእራሱ በገዛ አገር ላይ የሚፈፀም የፀጥታ አሰቃቂ ወንጀል ነው።ኢትዮጵያ ከሌላ አገር ትለያለች።አምባገነኖች መጥተዋል፣አምባገነኖች ሄደዋል። ኢትዮጵያ ግን በሕዝቧ አስተዋይነት እና በእግዚአብሔር መሪነት ከብዙ ፈተና ድናለች።ወደፊትም ትድናለች። ለአገር ብዙ ሃሳብ እና አቅም ያላችሁ ግን ከእየተደበቃችሁበት የምትወጡበት ጊዜ አሁን ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሁኔታ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ትከሻ ላይ  ወድቋል።እያንዳንዷ ቀን ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነችና።

ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
የካቲት 30/2008 ዓም 

Tuesday, March 8, 2016

በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ ነው።100 ሺህ ሕፃናት በአዲስ አበባ፣በሌሎች ከተሞች ደግሞ 600ሺህ ሕፃናት የጎዳና ተዳዳሪ ናቸው።150ሺህ መንግስት ያመነው ቁጥር ነው።(ጉዳያችን)

በአዲስ አበባ የነገ ትውልድ ተረካቢዎች የትምህርት ጊዜያቸው እንዲህ እየባከነ ነው
 በኢትዮጵያ ምን ያህል ማኅበራዊ ቀውስ እየደረሰ መሆኑን እና ለእዚህም መንግስት ምንም የአጭር እና የእረጅም ጊዜ የመፍትሄ ሃሳብ የሌለው ነገር ግን በድንገት የጎዳና ተዳዳሪዎችን በሙያ አሰለጠንኩ እያለ መልሶ ወደ ጎዳና  እያወጣቸው መሆኑን የምናውቅ ብዙ አይመስለኝም። በተለይ ቁጥር ብዙ ነገርን ያመላክታል እና የችግሩ ግዝፈት ምን ያህል እንደሆነ ለማየት የዩኒሴፍ እና የኢሪን ሪፖርት መሰረተ በማድረግ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ።
ከጥቂት አመታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት አድን ድርጅት (UNICEF)፣ 4.6 ሚልዮን ሕፃናት ወላጅ አልባ መሆናቸውን እና በአዲስ አበባ ብቻ 30% የሚሆኑ እድሜያቸው በ10 እና 14 መካከል ያሉ ልጃገረዶች ከወላጆቻቸው ውጭ ይኖራሉ ይላል። በእዚህ ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ቀዳሚ ከሚባሉት የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት የበዛባቸው አገሮች ተርታ መሆኗንም ይሄው ሪፖርት አክሎ ያብራራል። ይህ አስደንጋጭ ሪፖርት ነው።
የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት የዜና ወኪል (ኢሪን (IRIN) (ካለፈው ዓመት ወዲህ ከተባበሩት መንግሥታት ጥገኝነት ወጥቶ በመላው ዓለም ከ200 በላይ ወኪሎቹ አማካይነት በግል የዜና ወኪልነት ቀጥሏል) ቀደም ባሉ አመታት እንደዘገበው በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር እራሱ የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያመነው 150 ሺህ ሲሆን የእርዳታ ድርጅቶች ግን በአዲስ አበባ ብቻ ቁጥሩን 100ሺህ ሲያደርሱት በሌሎች ከተሞች የሚገኙትን ሲጨምር ከግማሽ ሚልዮን በላይ ማለትም 600 ሺህ እንደሚደርስ በጥናታቸው እንደገለፁ ያብራራል።ይህ የሁሉም ሕብረተሰብ ኃላፊነት ቢሆንም በቀዳሚነት ግን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ቀዳሚ ኃላፊነት ነው። ከላይ የተጠቀሱት ሪፖርቶች ወዲህ በርካታ መፈናቀሎች እና የድህነት መጠኑም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ይታወቃል።ይህ ማለት በአሁኑ ጊዜ ከላይ በዩኒሴፍም ሆነ በኢሪን የቀረቡት ቁጥሮች የበለጠ እንደሚሆኑ ይታመናል።ከእዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ በሆነ አንድ ጥናት ላይ የኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር እስከ 2030 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 40% እንደሚሄድ ያብራራል።ይህ እንግዲህ የአገልግሎት ዘርፉ እንጂ በርካታ ሰው የሚቀጥር ኢንዱስትሪ የሌላት አገር አሁንም መጪውን የከፋ ያደርገዋል። ይህ ማለት ደግሞ አንዳችም የረባ የድህነት ቅነሳ ስልትም ሆነ ፖሊሲ የሌለው ይልቁንም የአገሪቱን ሀብት ባብዛኛው ስልጣኑን ለማስጠበቅ የምታትር አምባገነን ህወሓት በስልጣን ላይ መኖሩ የችግሩ ዋና ምንጭ ሆኖ ይታያል።
በመጀመርያ ደረጃ ለጎዳና ተዳዳሪነት የሚዳረጉት ሕፃናት አንዱ ምክንያት የስርዓቱ አምባገነናዊ ፖሊሲ ውስጥ አንዱ ከእየቦታው በግድ የሚፈናቀሉ ነዋሪዎች ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።በአዲስ አበባ ብቻ በርካታ ሰው በግድ መሬቱን እንዲለቅ እየተደረገ ልጆቹን ለጎዳና ተዳርገዋል።ይህ እንግዲህ ከከተሞች አጎራባች ወረዳዎች ያለውን ሁኔታ ሁሉ ይጨምራል።
ሌላው እና ዋናው የችግሩ መነሻ የድህነት መጠን መጨመር ነው።ኢህአዴግ/ህወሓት ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የውሸት ቁጥር እየሰጠ አገሪቱ አድጋለች ድህነት ቀንሷል ይበል እንጂ በመሬት ያለው እውነታ ግን የተለየ ነው።ድህነት ለመቀነስ የተቀመጠ ስልትም ሆነ ባለሙያ በሌለበት ጥቂት የስርዓቱ ታዛዦች ብቻ እንደፈለጉ በሀብት ማማ ላይ በምንጠላጠሉባት አገር ውስጥ አብዛኛው ሕዝብ የበይ ተመልካች ሆኗል።ከእዚህ ሁሉ ግን አንዳንድ ሪፖርቶች ከመውጣታቸው በፊት በመንግስት ለይስሙላ የሚሰጡት  የማታለያ ዜናዎች የበለጠ የሚያሳዝኑ ናቸው። 
ሰሞኑን የፋና ድረ ገፅ የጎዳና ተዳዳሪዎች በሹፍርና፣በኤሌክትሪክ ሙያ አሰለጠንኩ ብሎ ለፎቶ እና ለፕሮፓጋንዳ የሚጠቀምበት መንገድ አሳዛኝነቱን ስንመለከት ምን ያህል በችግሩ ሰለባ ወገኖች ላይ እየተቀለደ መሆኑን ያሳያል።በመጀመርያ ደረጃ የጎዳና ተዳዳሪዎች ችግር የመሰልጠን እና ያለመሰልጠን ብቻ አይደለም።ችግሩ ከአገሪቱ ፖለቲካዊ ስር የሰደደ ችግር እና የተሳሳተ ፖሊሲ የመጣም ጭምር ነው። ሁለተኛ መንግስት ስጋት ባደረበት ጊዜ ሁሉ እየተነሳ የጎዳና ተዳዳሪዎች ማጎር እና ስልጠና እየሰጠሁ ነው ማለት በእራሱ ስልት የጎደለው ድህነትን የሚያህል ነገር በሺ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ፎቶ በማሳየት የችግሩ ምንጭ እራሱ መንግስት እና ፖሊሲው መሆኑን ለመሸፋፈን የሚደረገው ሙከራ አካል ነው።ይህ ደግሞ የትም የማያደርስ እና ችግሩ ገዝፎ የሚመጣ ቀን ማጣፍያው እንደሚያጥር ለማወቅ ብዙም ምርምር አይፈልግም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአገሪቱ ገንዘብ በአራቱም ማዕዘናት በሙሰኛ ባለስልጣናት እየተዘረፈ፣ህወሓት ለድርጅቶቹ በዓል ማክበርያ ፣በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ለመሰለል፣ ኢሳትን እና ሌሎች ወደ አገርቤት የሚተላለፉ ሚድያዎችን ለማፈን ወዘተ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየከሰከሰ  መሆኑን ማሰብ እና በአንፃሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከግማሽ ሚልዮን በላይ መናራቸውን መመልከት በእራሱ ኢትዮጵያ ትውልዷን እያጣች ያለችው እና ለእዚህም ዋና ምክንያቱ የመጥፎ አስተዳደር ሰለባነት መሆኑ በግልፅ ይታያል።አሁን የሚታየው እውነታ ይሄው ነው።ኢትዮጵያ በጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናቷ ከአለም ቀደምቶቹ ውስጥ ገብታለች።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com 
የካቲት 29/2008 ዓም (ማርች 8/2016)

Saturday, March 5, 2016

ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኖርዌጅያን ኦከሎ አክዋይ ኦቻላ ከደቡብ ሱዳን በወያኔ ታፍኖ ከተወሰደ ሁለተኛ ዓመቱ።Norge, hvor er statsborger Okello Akway Ochalla?

Norge hvor er statsborger Okello Akway Ochalla? 
Det er nøyaktig to år siden Okello Akway Ochalla har blitt kapret fra Sør-Sudan Etiopia dagens regime.

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የኖርዌይ ዜግነት ያለው  ኦከሎ አክዋይ ኦቻላ ከደቡብ ሱዳን በወያኔ ታፍኖ  ከተወሰደ  መጋቢት/2008 ዓም  ሁለተኛ ዓመቱ።  


Ochalla i Norge ኦቻላ (Photo Dagbladet News paper)
Ochalla with his childrens
 ኦቻላ ከልጆቹ ጋር ኖርዌይ (Photo Dagbladet News paper)



የ10 ዓመቱ የኦቻላ ልጅ ማርሆ አባቱ በወያኔ እንደሚገደል ሰምቶ ተክዟል። (ፎቶ የኖርዌይ ጋዜጣ ''ዳግብላደ'') Papuan oil Marho (10) for i Trondheim, men riskier dødsstraff i Ethiopia. .(Dagbladet Publisert 


ጉዳያችን GUDAYACHN 
www.gudayachn.com 

Friday, March 4, 2016

ሰበር ዜና- አዲስ አበባ ቅዱስ ሲኖዶስ ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ ዛሬ ከሰዓት በኃላ ተቀምጧል።አቡነ ማትያስ ስብሰባው ሲጀመር ነው ያወቁት።



አዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ የካቲት 25/2008 ዓም ድንገተኛ ስብሰባ ጠርቷል።ሐራ ዘተዋሕዶ የተሰኘው በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙርያ መረጃ የሚሰጠው ድረ-ገፅ እንደገለፀው ስብሰባው የተጠራው በቋሚ ሲኖዶስ ሲሆን አጀንዳዎቹ ውስጥ: 
  • ስለ ሰላም እና ስለ ተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት፤
  • በድርቁ ምክንያት ለተጎዱት ወገኖች እየተደረገ ስላለው ርዳታና ጸሎተ ምሕላ፤
  • ማዕከላዊነትን ስላልጠበቁ አሠራሮችና ስላስከተሏቸው ችግሮች፤
  • ከልዩ ጽ/ቤት ስለሚወጡ ደብዳቤዎችና መጻጻፎች በተመለከተ፤
  • የፓትርያርኩን የውጭ ጉዞዎች በተመለከተ፤ 
  • በፓትርያርኩና በማኅበረ ቅዱሳን ውዝግብ፣
  • በዐቢይ ጾም የጸሎተ ምሕላ ጉዳይ 
የሚሉት እንደሚጠቀሱ ድረ-ገፁ ያብራራል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፓትርያርኩ በበለጠ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል ከመንፈስ ቅዱስ በታች ቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑ ይታወቃል።ዛሬ አቡነ ማትያስ ስብሰባ እንደሚደረግ አለማወቃቸው እና በመጪው ሰኞ ስለምጀመረው አቢይ ፆም መግለጫ ሰጥተው እንደጨረሱ ተነስተው ለመውጣት ሲሉ ተመልሰው እንዲቀመጡ እና ሲኖዶሱ ድንገተኛ ስብሰባ እንደሚያደርግ በዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ማትያስ እንደተነገራቸው ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ1984 ዓም ጅምሮ ፓትርያሪክ አቡነ መርቆርዮስ እና ሌሎች ብፁዓን አባቶች ከአገራቸው ተሰደው እንደሚገኙ እና በአገር ቤት እና በውጭ ''ሲኖዶስ'' በሚል አባቶች መለያየታቸው ይታወቃል። ሆኖም ግን ይህ ልዩነት ሃይማኖታዊ ወይንም ዶግማዊ ሳይሆን የሥርዓት መሆኑን እና በአገር ቤት ያለው የአምባገነን ስርዓት ለውጥ ከመጣ ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነቷን እንደምትጠብቅ የብዙዎች ተስፋ ነው።

አቡነ መርቆርዮስ ከአገር ሲሰደዱ መንበረ ጵጵስናውን የያዙት እና ከእዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አቡነ ጳውሎስ በዘመናቸው በአባቶች መካከል ፍሬ ያፈራ የአንድነት ሥራ ሳይሰራ መኖሩ እና ይብሱንም ቤተ ክርስቲያኒቱ በዘመኗ አይታ የማታውቀው የለየለት የሙስና፣የገንዘብ ብክነት እና  ጎጣዊ አሰራሮች ሰፍነው ቆይተዋል።አቡነ ጳውሎስን የተኩት አቡነ ማትያስ በመንበራቸው በቆዩባቸው ሁለት አመታት ውስጥ ምንም አይነት የአሰራር መሻሻል ሳይታይ የቆየ ከመሆኑም በላይ ይብሱንም አቡነ ማትያስ የነገሮች አያያዝ አቅማቸው እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ግንኙነት እንዲሁም በተለያየ ጊዜ የሚፈጥሯቸው አዳዲስ የግጭት ሜዳዎች ብዙዎችን እጅግ ሲያሳዝን የከረመ ጉዳይ ነው።

በሌላ በኩል ከአራት ቀናት በፊት  አቡነ ማትያስ ከካቶሊክ ፓፓ ፍራንሲስ ጋር በቫቲካን ተገናኝተው መምከራቸው ይታወሳል።የዛሬው የቅዱስ ሲኖዶስ ድንገተኛ የስብሰባ አጀንዳ ውስጥ አንዱ የፓትራሪኩን የውጭ ጉዞዎች የሚፈትሽ እንደሚሆን ተሰምቷል።

ባለፈ ሰኞ የካቲት 21/2008 ዓም አቡነ ማትያስ እና ፖፕ ፍራንሲስ በባቲካን ሲገናኙ 

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ውስጥ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕዝቡን አንድነት እና ሰላም በመጠበቅ ረገድ የተጫወተችው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው።በአገር ውስጥ የሚነሱ ማናቸውም ከቁጥጥር ውጭ የሚሆኑ እና አገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ እንደ ትልቅ ጉድለት የሚጠቀሰው አንድ ማዕከላዊ፣ገለልተኛ እና ተአማኒ አካል አለመኖር ነው።በተለይ ባለፉት 24 ዓመታት እንደ አገር ካጣናቸው እሴቶች አንዱ እና ትልቁ ይህ መሆኑ ይታወቃል።ይህንን ክፍተት ለመሙላት ደግሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ መንበር ላይ የሚቀመጡ አባቶች ሚና ትልቅ ድርሻ አለው። 

ይህ እንዳይሆን ግን የቤተ ክርስቲያን አሰራር በሙሰኞች እና በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ጣልቃ ገብነት ቤተ ክርስቲያን የእራሷን የመልካም ስነ-ምግባር እና መንፈሳዊ ስርዓት የመምራት አቅም በየጊዜው እንዲዳከም እየተደረገ ነው።ይህ ሁኔታ ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው እንደ አገር ኢትዮጵያን መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።የኢትዮጵይ ቤተ ክርስቲያን ግን ኢትዮጵያ በ18 ኛው ክ/ዘመን ተነስቶ እስከ 19ኛው አጋማሽ ድረስ የዘለቀው እና የአገሪቱን አንድነት በተፈታተነው ''የዘመነ መሳፍንት'' ወቅትም ብቸኛ የህዝብ አገናኝ ድልድይ እና ገላጋይ ሆና ቆይታለች።ለእዚህ ነው ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማጥፋት የሚነሱ ኃይሎች ሁሉ በመጀመርያ ኢላማቸውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የሚያደርጉት።

ጉዳያችን GUDAYACHN 

የካቲት 25/2008 ዓም 

Wednesday, March 2, 2016

ገጣሚና ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ዛሬ ምሽት በማኅበራዊ ድረ-ገፁ የለቀቀው ግጥም አስተማሪ ነው።

ገጣሚና ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ)  

እንደምን አመሻችሁ ውዱ ወዳጆቼ ፥ቆየት ካሉ ግጥሞቼ አንዱን እነሆ ፦

ጎራው ያለ እደሆን ባራምባራስ ደስታ
ዛራፍ ያለ እንደሆን ባራምባራስ ደስታ
ጠላት ይጠፋዋል መደበቂያ ቦታ።
ፊት አውራሪ ፍላቴ
ግራ አዝማች በሃፍቴ
አዛዥ ለጥ ይበሉ
ቀኝ አዝማች በአካሉ
ዣንጥራር ባያለው
ደጃዝማች እንዳለው
እንዲህ ነው ካልቀረ አንጀት አርስ ሹመት
ለድል የሚያበቃ ጦር ይዞ ቢዘመት።
የጣልያን ጄኔራል ኮኮቡን ደርድሮ
በሊጋባሞ ዜር ስንት አሳሩን ቆጥሮ
ድል አድርጎት የኛ ሰው ፎክረን በኩራት እንደተመለስን
ስልጣኔ መስሎን የሱን ስም ወረስን።
ማቹ ጄኔራል ነው ገዳይ ፊት አውራሪ
ስም እንዴት ይዋሳል ደፋር ሰው ከፈሪ
በጠላት ሬሳ ላይ ቆመን እያቅራራን
በድላችን ማግስት የኛን ሹመት ንቀን ከ ሆንን ኔተራል
ባናውቀው ነው እንጂ የዛን ቀን ሙተናል።
ኮኔሬል አይበሉን ያገሩን አርበኛ
ጄኔራል አይበሉን ያገሩን አርበኛ
ፈረንጅ አደለንም ሀበሻ ነን እኛ።
የሞች ስም አደለም የገዳይ ሰው ምሱ
በደም ተበላሽተዋል ባለ ኮከብ ልብሱ
ገድየው ሳበቃ ባስታጠቁኝ ወኔ
በሱ ስም አይጥሩኝ ቆሞ እንዲሄድ በኔ
ጄኔራል ድል ሆኖ ስላለፈች ነፍሱ
ይበሉ ጃንሆይ ሹመቴን መልሱ።
ፊት አውራሪ ካታካምቦ
ሊጋባ ዴሊቦ
አዛዥ ለጥ ይበሉ
ቀኝ አዝማች አካሉ
ዣንጥራር አበጋዝ
እንዲህ ነው አንጀት አርስ ሹመት
ለድል የሚያበቃ ጦር ይዞ ቢዘመት
ፍቃድዎ ከሆነ ግርማዊ ተፈሪ
እንዳገሬ ሹመት በሉኝ ፊት አውራሪ
በሞች ከመጠራት ስለ ሚሻል እሱ
ይበሉ ጃንሆይ ሹመቴን መልሱ።




ጉዳያችን GUDAYACHN 

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ፣ የአፈጀው የአዛውንቶች ክበብ፣ ''ፅንዶ'' እና ቅምጥሎቹ ''ባንዳ'' ዩቱበሮች በአውሮፓና አሜሪካ።

+++++++++++++ ጉዳያችን ወቅታዊ ምጥን +++++++++++++ መንደርደርያ ኢትዮጵያ በዘመን አቆጣጠሯ ስንሔድ የሐያ አንደኛውን ክ/ዘመን የመዠመርያ ሩብ ክፍለዘመን ለማጠናቀቅ ሰባት ዓመታት ብቻ ቀርተዋታል። ያለፈው ሐ...