Sunday, December 9, 2018

ከቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ አንድነት በኃላም ከቤተ ክርስቲያን መዋቅር እውቅና ውጪ ቤተ ክርስቲያን በሚከፍቱ ላይ ጳጳሳት ቁጥጥር ሊያደርጉ ይገባል።


ጉዳያችን/Gudayachn
ኅዳር 30/2011 ዓም (ኖቬምበር 9/2018 ዓም)
 ''ያለ ኤጲስቆጶሱ ትእዛዝ ቤተ ክርስቲያንን አይሥሩ። አንድ ሰው ስንኳ ደፍሮ ከዚህ ውጪ ቢሠራ በውስጥዋ እስከ ዘላለም ቁርባን አይቈረብ። ቄሱም ይህን ተላልፎ በውስጥዋ ቁርባንን ቢቈርብ ይሻር።'' (ፍት.ነገ.አን.1፥2፤ በስ.94)።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚታወቁበት አንዱ እና መሰረታዊው መለያ በቅዱስ ሲኖዶሳዊ መዋቅር ውስጥ የሚታዘዙ እና መውቅሩን ተከትሎ በተመደቡላቸው ጳጳሳት አባታዊ ቡራኬ እና መመርያ የመመራታቸው መፅሐፍ ቅዱሳዊ ስርዓት ነው።ይህ የክህነት ስልጣን ተዋረድ ጠብቆ የሚሄደው  የቤተ ክርስቲያን ስርዓት ኦርቶዶክሳዊ አብያተ ክርስቲያናት እምነታቸው እና አምላካዊ ቃል የሆነው መሰረተ እምነት (ዶግማ) በእየዘመኑ በሚነሱ የኃይማኖት ቀሳጮች  በቀላሉ እንዳይበረዙ እና እንዳይሸረሸሩ አንዱ ጠንካራ ግንብ ሆኖ ቆይቷል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክህነትን በአንብሮተዕድ  ሐዋርያትን በክህነት የሾማቸው ገና መንፈስ ቅዱስ ሳይወርድላቸው እርሱም ገና አርጎ በአባቱ ቀኝ ሳይቀመጥ ነበር። /ዮሐ.20፥22-23/  ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ክህነትን ያገኘችው ከክርስቶስ ነው።ይህም በአንብሮተዕድ  (እጅን በመጫን)  ከጌታችን የተገኘች ክህነት ከሐዋርያት ጀምሮ አሁን እስካሉ ጳጳሳት ደርሳ አሁን ላለችው ቤተ ክርስቲያንም እያገለገለ ይገኛል። ክህነት ከእግዚአብሔር የተሰጠች ለመሆኗ ቅዱስ መፅሐፍ በልዩ ልዩ ቦታ ያስተምረናል።ሐዋርያትም የትንሣኤውን ዐዋጅ ለመንገር ወደ ዓለም በገቡ ጊዜ በክህነታቸው ተኣምራት ያደርጉ ነበር፡፡ /ማር.16፥16/ ሐዋርያት በሥልጣናቸው ያስሩ ይፈቱ ነበር፡፡/ማቴ.18፥18፤ 1ቆሮ.4፥1፤ 2ቆሮ.5፥20፤ ማቴ.16፥18/ ለምሳሌ፡- የሐናንያንና የሚስቱን የሰጲራን፤ የሲሞን መሠርይን ታሪክ ይመለከቷል፡፡ /የሐዋ.5፥1-11፤ 8፥24-28/ ቤተ ክርስቲያንን ይመግቡና ያስተዳድሩም ዘንድ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ /ዮሐ.20፥15/

አሁን ባለንበት ዘመን በተለይ ሲኖዶሳዊ አንድነት ከተፈጠረ በኃላ ለቅዱስ ሲኖዶስ ስርዓት ባለመታዘዝ ወይንም በግብር ይውጣ መልክ በቸልተኝነት  ቤተ ክርስቲያን ሳያስባርኩ መግባት፣ክህነት በሊቃነ ጳጳሳት ተይዞ እያለ ሕዝቡን ለመባረክ መውጣት፣ቤተ ክርስቲያንን የግል መተዳደርያ የሆነች ይመስል ተመሳሳይ ታቦታትን በአንድ ከተማ በመደርደር የምመናንን አንድነት መፈታተን እና የመሳሰሉ ጉድለቶች በተለይ በውጭ የሚገኙ አንዳንድ ከተሞች ላይ ይስተዋላል። እነኝህ ችግሮች ከሁለት አቅጣጫ የሚከሰቱ ናቸው። አንዱ የሀገረ ስብከቱ ጳጳሳት ስርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማስከበር አፋጣኝ ማስተካከያዎችን ካለማድረግ እና ህዝቡ ትክክለኛ የቤተ ክርስቲያንን ስርዓት እንዲያውቅ በግልጥ ካለመንገር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከስኖዶሳዊ ፈቃድ ውጭ በራሳቸው የሚሄዱ ካህናት ቤተ ክርስቲያንን ብቸኛ መተዳደርያ እንጂ ምዕመናንን ለማስተማር እና ለሰማያዊ መንግስት ለማብቃት ዓላማን ያላደረገ ተግባር ላይ ሲጠመዱ ነው።

ስለሆነም  በውጭ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ሲኖዶስ መዋቅር ስር ከሚገኘው አህጉረ ስብከቱ ጳጳስ ውጭ  የሚሄዱ ካህናት ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የምእመናንን አንድነት ለመፈታተን እየሰሩ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምትመራበት መሰረተ ዕምነት የሚያወጣ አደገኛ መጋለጥ ውስጥ እንደሚጥሏት ተገንዝበው ከአህጉረ ስብከት ጳጳሳት ትዕዛዝ ስር ሆነው በክህነት ችግር ያለባቸውን አገልጋዮች ጳጳሳት አባቶች በሚመሯቸው ስርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሰረት ስርዓት መያዝ ይገባቸዋል። እዚህ ላይ ምዕመናን የቤተ ክርስቲያን ባለድርሻ እና ባለ ርስት መሆናቸውን ተገንዝበው በየቦታው የሚከፈቱ አብያተ ክርስቲያናት በአሕጉረ ስብከቱ ጳጳስ ተባርከዋል? የተመደቡት ካህንስ ትክክለኛ ስልጣነ ክህነቱ አላቸው? ወይንስ በራሳቸው ከሕግ ውጭ እየሄዱ ነው? ብለው መጠየቅ አለባቸው። ማንም ካለ ኤጵስቆጶስ ፍቃድ ውጭ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታቦተ ሕጉን ይዞ እንዲገባ አይፈቀድለትም።

 ''ያለ ኤጲስቆጶሱ ትእዛዝ ቤተ ክርስቲያንን አይሥሩ። አንድ ሰው ስንኳ ደፍሮ ከዚህ ውጪ ቢሠራ በውስጥዋ እስከ ዘላለም ቁርባን አይቈረብ። ቄሱም ይህን ተላልፎ በውስጥዋ ቁርባንን ቢቈርብ ይሻር።'' (ፍት.ነገ.አን.1፥2፤ በስ.94)።

ተው ዓለም ተመለስ (መዘምር ኪነጥበብ ወ/ቂርቆስ)

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Tuesday, December 4, 2018

ጉዳያችን አዲስ ሀሳብ - በዝቅተኛ ሥራ ተቀጥረው የሚሰሩ ወጣቶችን ኑሮ ለማሻሻል ሕጉ ይሻሻል።

Bildergebnis für thinking


ጉዳያችን/ Gudayachn
ኅዳር 25/2011 ዓም (ዴሰምበር 4/2018 ዓም)

በሀገራችን ዘመን አቆጣጠር 2011 ዓም ከመጀመሩ ጥቂት ቀናት በፊት ጉዳያችን በያዝነው ዓመት አዳዲስ ሃሳቦች ላይ በማተኮር ሃሳቦችን ለሚመለከተው ማመልከት ላይ እንደምታተኩር ተገልጦ ነበር።በእዚሁ መሰረት የእዚህ ዓመት የመጀመርያውን አዲስ ሀሳብ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ።በጉዳያችን ላይ የሚቀርቡ አዳዲስ ሃሳቦች አጭር እና ጉዳዩን በማሳሰብ ደረጃ የሚቀርብ እንጂ በጥልቅ ጥናት አድርጎ ለማቅረብ ከጊዜ አንፃርም እንደማይቻል አንባቢ ሊገነዘበው ይገባል።

በጉዳያችን አዲስ ሃሳብ ላይ የሚቀርቡ ሃሳቦች፣ ሃሳብ ለመጫር እና በሚቀርበው ሃሳብ ዙርያ የጠለቀ እውቀት ያላቸው እንዲገፉበት፣የበለጠ እንዲሰሩበት  እና የሚመለከተው አካል መንግስት፣ግለሰብ ወይንም ድርጅት ጉዳዩን ችላ እንዳይለው ለሚመለከተው አካል በተናጥል ከመላክ ጉዳዩን እንዲህ በድረ ገፅ መግለጡ የራሱ የሆነ ተፅኖ ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ።

ጉዳያችን አዲስ ሀሳብ - በዝቅተኛ ሥራ ተቀጥረው የሚሰሩ ወጣቶችን ኑሮ ለማሻሻል ሕጉ ይሻሻል።

በኢትዮጵያ የልማት ተግባር የሚያስብ ማንኛውም አካል በኢትዮጵያ የከተሞች ኑሮ የተጠቁ ሁለት የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፊቱ  ይደቀናሉ።እነርሱም ወጣቶች እና  ሴቶች  ናቸው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሐምሌ/ 2017 ዓም በዩኤስኤይድ የቀረበ ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ ወጣት ኃይል ለኢትዮጵያ ማደግ ትልቅ ተስፋ መሆኑን ከጠቀሰ በኃላ አንድ መቶ ሚልዮን ከሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 41% የሚሆነው ከ15 ዓመት በታች ሲሆን፣ 28% የሚሆነው በ15 እና 29 ዓመት እድሜ የሚገኝ መሆኑን ያመለክታል። ይህ ማለት 69% የኢትዮጵያ ሕዝብ እድሜው ከ29 ዓመት በታች ነው ማለት ነው።

ከላይ የተጠቀሰው መረጃ ብዙ መለት ነው።ለእዚህ የጉዳያችን ሃሳብ ግን ትኩረት የሚያደርገው ወጣቶችን በተለይ ሴት ወጣቶችን ነው። ጉዳዩ ደግሞ የመንግስትን ሕግ የማሻሻል እና የብዙሃን መገናኛዎች ግፊት ይፈልጋል።ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አስር ዓመታት ከተጎሳቆለባት ሀብት ውስጥ አንዱ ወጣት የሰው ኃይሏ ነው።በ1960ዎቹ መጨረሻ እና '70ዎቹ መጀመርያ በቀይ እና ነጭ ሽብር የጠፋው ትውልድ በዘመነ ህወሓት/ ኢህአዴግ በስደት እና በኑሮ ጉስቁልና ተጎድቷል። ሌላውን ትተን በመካከለኛው ምስራቅ ብቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ  ሴት እህቶቻችን የትምህርት እና ቤተሰብ የመመስረቻ ዘመናቸውን በአረብ ሃገራት የልፋት እንጀራ ፍለጋ እያባከኑ ይገኛሉ። ለእዚህ አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የመንግስት ፖሊሲ ጉድለትም ጭምር ነው።

በአረብ ሃገራት ሥራ ለመፈለግ የሚሄዱ እህቶቻችን የመጀመርያም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደነገሩ በብዙ ችግር (ብዙዎቹ ቤተሰቦቻቸውን ለማገዝ  ከትርፍ ጊዜ ሥራ ጋር እየሰሩ የሚማሩ ናቸው) ካጠናቀቁ በኃላ ፊታቸው የሚታያቸው ብቸኛ መንገድ ወደ አረብ ሀገሮች ሄዶ ለበለጠ እንግልት መዳረግ ነው። ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ በትርፍ ጊዜያቸው የሰሩበት ሥራም ሆነ በሀገር ውስጥ ተቀጥረው ለመስራት የሚከፈላቸው ክፍያ እጅግ ያነሰ ከመሆኑ በላይ ከቤታቸው ወደ ሥራ ለመመላለስ ለአውቶብስ ሳይቀር የማይበቃ ገንዘብ ነው። የሀገር ውስጥ እድላቸውን ለመሞከር ሴት ወጣቶች ከሚሰማሩባቸው የስራ መስኮች ውስጥ: -
  •  የኬክ ቤት መስተንግዶ፣
  • የልብስ መሸጫ ሱቅ፣
  • የቤት ሰራተኛነት፣
  • የፀጉር ቤት ሰራተኛነት፣
  • የምግብ ቤት መስተንግዶ፣
  • የፎቶ ኮፒ ማሽን እና የፅህፈት አገልግሎት፣
  • የሞግዚትነት ሥራ፣ የመሳሰሉት ሲሆኑ።
በእነኝህ የስራ መስኮች ላይ የሚሰማሩት ገና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያላጠናቀቁ እና በቅርብ ያጠናቀቁትን ሁሉ ይጨምራል። እነኝህ ስራዎች የመካከለኛ እና አነስተኛ  ገቢ ነጋዴዎች ሥራ ቢሆኑም አሰሪዎቹ ወጣቶቹን የሚቀጥሩት በፈለጉት ደሞዝ ብቻ ሳይሆን  እጅግ አሰቃቂ በሚባል ደሞዝ ነው። ለምሳሌ በአንድ የኬክ ቤት መስተንግዶ ላይ የተሰማራች ወጣት የሚከፈላት  ገንዘብ ለምሳ የማይበቃት ስለሆነ አንድ ኬክ በልታ ከመዋል ጀምሮ ሻይ የጠጣው ሰው ጉርሻ ካልሰጣት በአውቶብስ ወደ ቤት  ለመሄድ የማትችልባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ። ስለሆነም በእዚህ እድሜ ያሉ ወጣቶች በአጠገባቸው የሚያገኙት ሥራ ሳይወዱ የግድ በሴተኛ አዳሪነት ሥራ ላይ መሰማራት ይሆናል።በመቀጠል ብቸኛ አማራጫቸው ወደ አረብ ሀገር መሄድ ይሆናል።

 በዝቅተኛ የደሞዝ ጣርያ ላይ የመንግስት አዲስ ሕግ ያስፈልጋል።

መንግስት በመንግስት መስርያ ቤት እና ለግል ድርጅቶች የደሞዝ ወለል ሲያስቀምጥ በአነስተኛ ንግድ ላይ ተሰማርተው ለሚሰሩ ወጣቶች አስገዳጅ  የደሞዝ ወለል መወሰን እና ባለ ሃብቱ ከሚያገኘው ላይ ለተቀጣሪ ወጣቶች እንዲያካፍል የሚያደርግ ሕግ ማፅደቅ አለበት። ይህ ማለት ከሚገባው በላይ ጣርያውን መስቀሉ የስራ አጥ ቁጥር እንዳይጨምር አሁን ካለው በተሻለ ወለሉን ከፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ የአንድ ኬክ ቤት አስተናጋጅ ዝቅተኛ ደሞዝ መቀመጥ ያለበት እና ከወጣው ሕግ በታች ከሆነ መንግስት ባለ ሃብቱን የመቅጣት ሥራ መስራት አለበት።በቅድምያ ግን በባለ ሃብቱም ሆነ በሕዝብ ዘንድ ተገቢው መረዳት እንዲመጣ ማድረግ እና ይህ ጉዳይ ማኅበራዊ ችግርንም ፈቺ መሆኑን ማሳመን ይፈልጋል።

ከእለት ምግብ፣ትራንስፖርት እና የማታ ሙያ ማሻሻያ ትምህርት የሚረዳ ገቢ ያገኙ ወጣቶች በሁለት እና ሶስት አመታት ውስጥ እራሳቸውን አሻሽለው ወደ ተሻለ የስራ ደረጃ ወደ አረብ ሀገሮችም ሆነ ሌላ ማኅበራዊ ችግር ውስጥ ሳይገቡ ሊሻሻሉ ይችላሉ።ተረኛው ታዳጊ ወጣትም  እንዲሁ እየተከተለ ምጣኔ ሃብቱንም ሆነ በራሱ የሚተማመን ትውልድ ማፍራት ይቻላል።ይህ ግን የመንግስት  በተለይ ወጣቶች እና ታዳጊዎች ተቀጥረው  አነስተኛ የስራ መስኮች ላይ የደሞዝ ወለል ማስቀመጥ እና መቆጣጠር ከቻለ ብቻ ነው።


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Monday, November 26, 2018

ግጥም በጠብ-መንጃ (ቪድዮ)

ግጥም በጠብ-መንጃ በአርቲስት ፍቃዱ ከበደ


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Tuesday, November 20, 2018

የዘገየ አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ለውጥ እንደቀረ ይቆጠራል።የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ይመለከታል።

ጉዳያችን GUDAYACHN
ሕዳር 12/2011 ዓም (ኖቬምበር 21/2018 ዓም)

በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚገኙ ሁለት ገዢ  ነጥቦች 



  • ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመታደግ በፍጥነት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ምን ምንድናቸው?
  •  የጎጥ እና የዘረፋ ኃይሉ በታሪክ ያልታየ ግጭት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊፈጥር ይችላል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትባላለች።ከሁለት ሺህ ዓመታት በዓይ ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ፣ማኅበራዊ እና ታሪካዊ ሂደት ጋር ስትወጣ እና ስትወርድ የኖረች ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትሰኛለች።የሶርያ ኦርቶዶክስ የሶርያ ቤተ ክርስቲያን እንደምትባል፣ "ቤተ ክርስቲያኒቱ ሀገር ማለት ነች" እንዳሉት ዶ/ር ዓብይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሰኘቷ በብዙ ዕይታ ጥያቄ ውስጥ አይገባም።

ይህች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሁለት ሺህ ዓመታት ታሪክ ውስጥ ከደረሰባት ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፉት 27 ዓመታት የደረሰባት በቡድን የተደራጁ ዘራፊዎች እና ጎጠኞች ያደረሱባት መቦርቦር እና መጎሳቆል እጅግ ከምንገምተው በላይ የከፋ ነው።የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረት ከቤተ ክህነት እስከ አጥብያ ድረስ የግለሰቦች መጠቀምያ ሆኗል፣ዝርፍያው እንዳይደናቀፍባቸው ዘራፊ የጨለማ ቡድ አባላት  ከጳጳሳት ማስደብደብ፣እስከ አጥብያ አስተዳዳሪ በመኪና ለማስገጨት እስከመሞከር፣ከሀገር ማሰደድ እስከ እስርቤት መወርወር ድረስ በአገልጋይ ካህናት እና ምዕመናን ላይ ፈፅመዋል።ይህ ብቻ አይደለም የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ዘመናዊ መልክ ይዞ ለዝርፍያ እንዳይመች ሆኖ ይዋቀር ብለው በከፍተኛ አማካሪዎች ታግዘው ያቀረቡት የማሻሻያ መዋቅር የአዲስ አበባ አድባራት አስተዳዳሪዎች ከ90% በላይ የደገፉት ቢሆንም አሁንም የዘራፊው እና የጎጥ ቡድን አባላት የማሻሻያ ሃሳብ ባቀረቡት ላይ ከማስፈራራት ጀምሮ እስከ ስም ማጥፋት በፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ጭምር ተደግፈው ፈፅመዋል።

ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመታደግ በፍጥነት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ምን ምንድናቸው?


አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ  የተፈፀመባትን ግፍ የመዘርዘርያ ጊዜ አይደለም።በደረሰባት ግፍ መጠን የግፉ እና የዘረፋውን አካላት የመቁረጫ ጊዜ ግን ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የሚከተሉት ተግባራት በቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት እና በመንግስት መወሰድ አለበት። እነርሱም : -
  • ምእመናንን፣የቤተ ክርስቲያናትን የአገልግሎት አካላት በየደረጃው  እና መንግስትን የሚያነቃ ለተግብራዊነቱ ፍጥነት የሚያሳስብ የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻ እና የቃል ለቃል እንዲሁም ቤት ለቤት የሚሄድ ቅስቀሳ ማድረግ። ቅስቀሳው ሌቦችን፣ዘራፊዎችን እና በጎጥ ብቻ ተጠራርተው የተሿሹሙትን በሙሉ መንጥሮ ለማውጣት ዘመቻ ስለሚጀመር የስነ ልቦና ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን በየደረጃው የመጠበቅ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለሁሉም ማሳሰብንም ይጨምራል።
  • የቤተ ክርስቲያኒቱን የለውጥ ሂደት (አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ለውጥ) የሚያስተባብር ልዩ ግብረ ኃይል ከቅዱስ ሲኖዶስ፣ከምእመናን እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታይ ከሆኑ ከመንግስት አካላት እንዲመሰረት ማድረግ።
  • ግብረ ኃይሉ በመንግስት ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለውን ምዝበራ እና ዝርፍያ የሚያጣራ እና በአጭር ጊዜ ዘራፊዎቹ ከስራ እንዲታገዱ የሚያስደርግ እና ለሕግ (ቤተ ክርስቲያን በፍትሕ መንፈሳውም ልታየው የምትችልበት ልዩ የፍትሕ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ልትዳኘው ወይንም በመደበኛ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለባቸው ለሕግ እንዲቀርቡ የማመቻቸት እና አስፈላጊ ከሆነም ከሕግ አካላት ጋር በመሆን ከምእመናን የሚመጡ ጥያቄዎችን በሕግ አግባብ እንዲፈቱ ወደ ፍርድ ቤት የሚወስድ መሆን ይገባዋል።
  • የቤተ ክርስቲያኒቱ ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀስ ንብረት በሙሉ የማጣራት ተግባር እስኪጠናቀቅ ድረስ ከስራ ማስኬጃ እና የካህናት ደሞዝ በቀር በዝግ ሂሳብ መያዝ።ይህም በግርግር በርካታ ንብረት እንዳይሸሽ ይረዳል።
  • በቀጣይ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር እና የገንዘብ አስተዳደር በዘመናዊ የአሰራር አግባብ እና የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና እና ዶግማ ባላፋለሰ መልክ ማደራጀት።
  • የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ተግባራዊነት መከታተል ፣ ወንጀለኞችን በፍትህ መንፈሳዊም ሆነ  በተደረሰበት ስምምነት መሰረት መቅጣት።
  • የማሻሻያውን ሂደት በሙሉ ምእመናን እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ የሚገዳቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንዲከታተሉት ልዩ የሚድያ አገልግሎት መስጠት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
የማሻሻያ ለውጡ በፍጥነት ካልተጀመረ የሚከተለው አደጋ 

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተንሰራፋውን የጎጥ እና የዘረፋ ቡድን በቶሎ እጅግ በፍጥነት የማምከን ሥራ ካልተሰራ አደጋ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ደረጃም ሊከሰት ይችላል።እርሱም : -

 የጎጥ እና የዘረፋ ኃይሉ በታሪክ ያልታየ ግጭት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊፈጥር ይችላል።

አሁን በኢትዮጵያ ያለው የለውጥ ንፋስ ያልተስማማቸው የቀድሞው አረመኔያዊ ዘመን እንዲመለስ የሚመኙ አካላት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ጊዜ እና ወቅት እየጠበቁ ነው።እነኝህ በውሸት ምንኩስና እና ቅስና ተሸፍነው በስለላ እና በዘረፋ በቡድን የሚንቀሳቀሱ አካላት ለተኮላሸው የጎጥ ስርዓት የመጨረሻ ምሽግ እና ታማኝነታቸውን ለመግለጥ እና የለውጥ አሰራሩ እነርሱ ላይ እንደሚያነጣጥር ስለሚረዱ  በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አዲስ ግጭት ለማቀናበር እና ትኩረቱ ሁሉ ወደዚሁ ግጭት እንዲሆን አይሰሩም ብሎ ማሰብ አይቻልም።ይህ ደግሞ አደጋው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን ከሃምሳ ሚልዮን በላይ ምዕመን ለያዘችው ሀገርም ጭምር ነው። የተሸነፈው የጎጥ ቡድን የዶ/ር አብይ የለውጥ ኃይል ወደ ስልጣን ከመጣ ከመጋቢት 24/2010 ዓም ጀምሮ ለውጡን ለመገዳደር የተጠቀመበት መንገድ ህዝብን በጎሳ ማፋጀት ነበር።ይህ ጉዳይ አለማዋጣቱ እየታየ ስለመጣ ቀጣዩ የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ይህንን ከቤተ ክህነት እስከ አጥብያ የተዘረጋውን የጎጥ እና የዘራፍ ቡድን ለግጭት ያለፈው ስርዓት አይጠቀምበትም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።ለእዚህ ነው እጅግ በፈጠነ መልክ ቡድኑን እና አሰራሩን ማምከን እና ቤተ ክርስቲያኒቱን በዘመናዊ አሰራር እና መዋቅር ሃያ አንደኛውን ክ/ዘመን ማሻገር ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ማሻገር መሆኑን መረዳት የሚገባው።

ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዶግማዊ እና ቀኖናዊ ሳይሆን አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ለውጥ ለማድረግ በቅድምያ በውስጧ የተሰገሰጉትን የዘራፊ እና የጎጥ ቡድን ነጥሎ ለሕግ ተገዥ ማድረግ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበራትን የሞራል ልዕልና ለአዲሱ ትውልድ የምታሳይ አድርጎ ማዘጋጀት እጅግ አስፈላጊ ነው።
ለጎጥ እና ዘራፊው የጨለማ ቡድን ቀናት አይደለም ሰዓታት መስጠት እጅግ ውድ ዋጋ ይስከፍላል።

ቤተ ክርስቲያንን አንተውም ከቶ (ኦድዮ መዝሙር)







ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com