ጉዳያችን/ Gudayachn
ኅዳር 25/2011 ዓም (ዴሰምበር 4/2018 ዓም)
በሀገራችን ዘመን አቆጣጠር 2011 ዓም ከመጀመሩ ጥቂት ቀናት በፊት ጉዳያችን በያዝነው ዓመት አዳዲስ ሃሳቦች ላይ በማተኮር ሃሳቦችን ለሚመለከተው ማመልከት ላይ እንደምታተኩር ተገልጦ ነበር።በእዚሁ መሰረት የእዚህ ዓመት የመጀመርያውን አዲስ ሀሳብ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ።በጉዳያችን ላይ የሚቀርቡ አዳዲስ ሃሳቦች አጭር እና ጉዳዩን በማሳሰብ ደረጃ የሚቀርብ እንጂ በጥልቅ ጥናት አድርጎ ለማቅረብ ከጊዜ አንፃርም እንደማይቻል አንባቢ ሊገነዘበው ይገባል።
በጉዳያችን አዲስ ሃሳብ ላይ የሚቀርቡ ሃሳቦች፣ ሃሳብ ለመጫር እና በሚቀርበው ሃሳብ ዙርያ የጠለቀ እውቀት ያላቸው እንዲገፉበት፣የበለጠ እንዲሰሩበት እና የሚመለከተው አካል መንግስት፣ግለሰብ ወይንም ድርጅት ጉዳዩን ችላ እንዳይለው ለሚመለከተው አካል በተናጥል ከመላክ ጉዳዩን እንዲህ በድረ ገፅ መግለጡ የራሱ የሆነ ተፅኖ ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ።
ጉዳያችን አዲስ ሀሳብ - በዝቅተኛ ሥራ ተቀጥረው የሚሰሩ ወጣቶችን ኑሮ ለማሻሻል ሕጉ ይሻሻል።
በኢትዮጵያ የልማት ተግባር የሚያስብ ማንኛውም አካል በኢትዮጵያ የከተሞች ኑሮ የተጠቁ ሁለት የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፊቱ ይደቀናሉ።እነርሱም ወጣቶች እና ሴቶች ናቸው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሐምሌ/ 2017 ዓም በዩኤስኤይድ የቀረበ ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ ወጣት ኃይል ለኢትዮጵያ ማደግ ትልቅ ተስፋ መሆኑን ከጠቀሰ በኃላ አንድ መቶ ሚልዮን ከሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 41% የሚሆነው ከ15 ዓመት በታች ሲሆን፣ 28% የሚሆነው በ15 እና 29 ዓመት እድሜ የሚገኝ መሆኑን ያመለክታል። ይህ ማለት 69% የኢትዮጵያ ሕዝብ እድሜው ከ29 ዓመት በታች ነው ማለት ነው።
ከላይ የተጠቀሰው መረጃ ብዙ መለት ነው።ለእዚህ የጉዳያችን ሃሳብ ግን ትኩረት የሚያደርገው ወጣቶችን በተለይ ሴት ወጣቶችን ነው። ጉዳዩ ደግሞ የመንግስትን ሕግ የማሻሻል እና የብዙሃን መገናኛዎች ግፊት ይፈልጋል።ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አስር ዓመታት ከተጎሳቆለባት ሀብት ውስጥ አንዱ ወጣት የሰው ኃይሏ ነው።በ1960ዎቹ መጨረሻ እና '70ዎቹ መጀመርያ በቀይ እና ነጭ ሽብር የጠፋው ትውልድ በዘመነ ህወሓት/ ኢህአዴግ በስደት እና በኑሮ ጉስቁልና ተጎድቷል። ሌላውን ትተን በመካከለኛው ምስራቅ ብቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴት እህቶቻችን የትምህርት እና ቤተሰብ የመመስረቻ ዘመናቸውን በአረብ ሃገራት የልፋት እንጀራ ፍለጋ እያባከኑ ይገኛሉ። ለእዚህ አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የመንግስት ፖሊሲ ጉድለትም ጭምር ነው።
በአረብ ሃገራት ሥራ ለመፈለግ የሚሄዱ እህቶቻችን የመጀመርያም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደነገሩ በብዙ ችግር (ብዙዎቹ ቤተሰቦቻቸውን ለማገዝ ከትርፍ ጊዜ ሥራ ጋር እየሰሩ የሚማሩ ናቸው) ካጠናቀቁ በኃላ ፊታቸው የሚታያቸው ብቸኛ መንገድ ወደ አረብ ሀገሮች ሄዶ ለበለጠ እንግልት መዳረግ ነው። ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ በትርፍ ጊዜያቸው የሰሩበት ሥራም ሆነ በሀገር ውስጥ ተቀጥረው ለመስራት የሚከፈላቸው ክፍያ እጅግ ያነሰ ከመሆኑ በላይ ከቤታቸው ወደ ሥራ ለመመላለስ ለአውቶብስ ሳይቀር የማይበቃ ገንዘብ ነው። የሀገር ውስጥ እድላቸውን ለመሞከር ሴት ወጣቶች ከሚሰማሩባቸው የስራ መስኮች ውስጥ: -
- የኬክ ቤት መስተንግዶ፣
- የልብስ መሸጫ ሱቅ፣
- የቤት ሰራተኛነት፣
- የፀጉር ቤት ሰራተኛነት፣
- የምግብ ቤት መስተንግዶ፣
- የፎቶ ኮፒ ማሽን እና የፅህፈት አገልግሎት፣
- የሞግዚትነት ሥራ፣ የመሳሰሉት ሲሆኑ።
በዝቅተኛ የደሞዝ ጣርያ ላይ የመንግስት አዲስ ሕግ ያስፈልጋል።
መንግስት በመንግስት መስርያ ቤት እና ለግል ድርጅቶች የደሞዝ ወለል ሲያስቀምጥ በአነስተኛ ንግድ ላይ ተሰማርተው ለሚሰሩ ወጣቶች አስገዳጅ የደሞዝ ወለል መወሰን እና ባለ ሃብቱ ከሚያገኘው ላይ ለተቀጣሪ ወጣቶች እንዲያካፍል የሚያደርግ ሕግ ማፅደቅ አለበት። ይህ ማለት ከሚገባው በላይ ጣርያውን መስቀሉ የስራ አጥ ቁጥር እንዳይጨምር አሁን ካለው በተሻለ ወለሉን ከፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ የአንድ ኬክ ቤት አስተናጋጅ ዝቅተኛ ደሞዝ መቀመጥ ያለበት እና ከወጣው ሕግ በታች ከሆነ መንግስት ባለ ሃብቱን የመቅጣት ሥራ መስራት አለበት።በቅድምያ ግን በባለ ሃብቱም ሆነ በሕዝብ ዘንድ ተገቢው መረዳት እንዲመጣ ማድረግ እና ይህ ጉዳይ ማኅበራዊ ችግርንም ፈቺ መሆኑን ማሳመን ይፈልጋል።
ከእለት ምግብ፣ትራንስፖርት እና የማታ ሙያ ማሻሻያ ትምህርት የሚረዳ ገቢ ያገኙ ወጣቶች በሁለት እና ሶስት አመታት ውስጥ እራሳቸውን አሻሽለው ወደ ተሻለ የስራ ደረጃ ወደ አረብ ሀገሮችም ሆነ ሌላ ማኅበራዊ ችግር ውስጥ ሳይገቡ ሊሻሻሉ ይችላሉ።ተረኛው ታዳጊ ወጣትም እንዲሁ እየተከተለ ምጣኔ ሃብቱንም ሆነ በራሱ የሚተማመን ትውልድ ማፍራት ይቻላል።ይህ ግን የመንግስት በተለይ ወጣቶች እና ታዳጊዎች ተቀጥረው አነስተኛ የስራ መስኮች ላይ የደሞዝ ወለል ማስቀመጥ እና መቆጣጠር ከቻለ ብቻ ነው።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment