ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, December 31, 2018

ከጎጥ አስተሳሰብ የፀዱ ብሔራዊ ስሜት የሚያንፀባርቁ ዩንቨርስቲዎችና ኮሌጆች እንዲኖሩን መወሰድ ያለበት የመጀመርያው መጀመርያ ተግባር (ጉዳያችን ሃሳብ)

 ጉዳያችን / Gudayachn 
ታኅሳስ 22/2011 ዓም (ደሴምበር 31/2018 ዓም)

  • በአሁኑ ወቅት በዩንቨርስቲዎች አካባቢ የሚታዩት የጎሳ ግጭቶች (በጥቂቶች የሚለኮሱ አብዛኛው ተማሪ የማይሳተፍበት) ለመፍታት መንግስት እየሞከረ ያለው የዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች እና ማኅበረሰብ በማወያየት፣የችግሩ ምንጭ እና መፍትሄ በሚል የጥናት ስብሰባ በማብዛት መሆኑ ወደ መፍትሄው አይወስደውም። መፍትሄው ሌላ ነው።


ኢትዮጵያ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በትውልዱ ላይ የተዘራው የጎሳ ፖለቲካ እያደገ መጥቶ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ከሚታዩት የጎሳ ግጭቶች በተጨማሪ በዩንቨርስቲዎች ውስጥ የሚጫሩ ግጭቶች ወደ አላስፈላጊ ጥፋት እያመራ ይገኛል።እንደ ሀገር የጎሳ ግጭቱ ዋነኛ መነሻዎች ሁለት ናቸው። እነርሱም  ኢትዮጵያ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የተሰራችበት የጎሳ-መር ሕገ መንግሥት እና የአስተዳደር መዋቅር መኖር እና በሌላ በኩል ደግሞ ሆን ተብሎ የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ በሚፈልጉ ኃይሎች አማካይነት የሚሸረቡ ሴራዎች ናቸው።በዩንቨርስቲ ተማሪዎች አንፃር  ለምሳሌ ከሃምሳ ሺህ የማይንስ የትምህርቱ ማኅበረሰብ ባለበት እንደ ጅማ  ዩንቨርስቲ ውስጥ ለመበጥበጥ  ከአምስት በማይበልጡ ተማሪዎች የመማር ማስተመሩን ሂደት ለማወክ በቂ ነው።ተማሪዎች ትምህርት እንዳይገቡ ወይንም አንዱን ጎሳ ከሌላው የሚያጋጭ ይዘት ያለው  ወረቀት በማስታወቂያ ቦርድ ላይ በመለጠፍ ሁከት ማስነሳት ቀላል ሆኗል።

በቅርቡ የቡሌ ሆራ  (ሃገረ ማርያም) ዩንቨርስቲ ተማሪዎችን ጨምሮ በሌሎች ዩንቨርስቲዎች እየተከሰቱ ያሉት የጎሳ ግጭቶች ዩንቨርስቲዎች ምቹ የመማርያ ቦታ እንዳይሆኑ ብቻ ሳይሆን በተማሪዎች ስነ ልቦና ላይ ጥቁር ነጥብ ጥለው እንዳይሄዱ ዩንቨርስቲዎችን ሰላማዊ፣አስደሳች እና የመልካም ትዝታ ቦታዎች እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ በቶሎ መከወን ያስፈልጋል።

ከጎጥ አስተሳሰብ የፀዱ ብሔራዊ ስሜት የሚያንፀባርቁ ዩንቨርስቲዎችና ኮሌጆች እንዲኖሩን መወሰድ ያለበት የመጀመርያው መጀመርያ ተግባር 

ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ድርጅቶች አሰራር፣ውጤት እና የእድገት አቅጣጫ አይነተኛ አስተዋፅኦ ከሚያከናውኑት ውስጥ አንዱ እና ዋናው ከዩንቨርስቲ የሚመረቁ ተማሪዎች የሃሳብ፣የፈጠራ እና የክህሎት ውጤት ነው።የፋሽሽት ጣልያን መባረር በኃላ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ለዩንቨርስቲ ትምህርት ትኩረት ሲሰጡ ትምህርቱን ብቻ ሳይሆን አሰራሩን እና የአካዳሚክ ነፃነቱንም ጭምር አብረው ለማስረፅ ጥረዋል።ስለሆነም እስከ 1966 ዓም ድረስ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲን የሃሳብ የመግለጥ እና የተማሪዎች የመደራጀት ነፃነት ስንመለከት በተሻለ ደረጃ ላይ እንደነበር እንመለከታለን።በደርግ ዘመንም ከነበረው አምባገነን አሰራር ጋር የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲም ሆነ ሌሎች ኮሌጆች የተማሪዎች ሕብረት ማኅበር በአደረጃጀትም ሆነ ድምፁን በማሰማት የሚታማ አልነበረም።ለእዚህም የህብረቱ አመራሮች በተለያዩ የሀገር ጉዳዮች ላይ ድምፃቸውን ያሰሙ የነበሩ መሆናቸው አንዱ ማስረጃ ነው።

ዩንቨርስቲዎች ከሚለኩበት አንዱ የጥራት ደረጃዎቻቸው ውስጥ የአካዳሚክ ነፃነት እና የተማሪዎች በነፃ የመደራጀት መብቶች አንዱ የሚለኩበት ነጥብ ነው።የትምህርት አካባቢ ምቹ፣ነፃ እና ሃሳብ አፍላቂ ማኅበረሰብ ፈጣሪ የሚሆነው በነፃነት የተደራጀ የተማሪዎች ኅብረት ሲመሰረት እና በቂ ስልጣን ሲሰጠው ነው። ለኢትዮጵያ የወቅቱ የጎሳ ፖለቲካ መታመስ በተለይ በዩንቨርስቲዎች አካባቢ ላለው ዋናው እና ቁልፉ ጉዳይ  ከጎሳዊ ከፋፋይ አስተሳሰብ የፀዳ ሃገራዊ ርዕይ ያለው የዩንቨርስቲ እና ኮሌጅ ተማሪዎች ኅብረትን በሚገባ ማዋቀር እና ማደራጀት ነው።የዩንቨርስቲ እና ኮሌጆች ተማሪዎች ኅብረት ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም።ይልቁንም የራሱ የሆነ በጎም ሆነ በጎ ያልሆነ ታሪክ ጥሎ ያለፈ ነው።ይህ ማለት ግን ሁል ጊዜ በአፍራሽ መልኩ ልንመለከተው አይገባም።

በአሁኑ ወቅት በዩንቨርስቲዎች አካባቢ የሚታዩት የጎሳ ግጭቶች (በጥቂቶች የሚለኮሱ አብዛኛው ተማሪ የማይሳተፍበት) ለመፍታት መንግስት እየሞከረ ያለው የዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች እና ማኅበረሰብ በማወያየት፣የችግሩ ምንጭ እና መፍትሄ በሚል የጥናት ስብሰባ በማብዛት መሆኑ ወደ መፍትሄው አይወስደውም። መፍትሄው ሌላ ነው። ከእዚህ ይቅል እውነተኛ የሆነ ሀገር አቀፍ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች  ህብረት መመስረት እና አቅሙ እና በተማሪው ዘንድ የሚደነቁ አመራሮች ተመርጠው አመራሩን እንዲይዙ  እና በጎሳ ፖለቲካ ለሚታመሰው ወጣት መፍትሄ አፍላቂዎችን ወደፊት በማምጣት እና ተማሪዎቹን በሀገራዊ አስተሳሰብ እንዲይዙ በማድረግ ነው።

ለማጠቃለል የዩንቨርስቲ እና ኮሌጅ ተማሪዎች ኅብረት መመስረት እና በባለ ብሩህ አዕምሮ ወጣቶች (በተማሪዎች በሃሳብ አፍላቂነታቸው በምደነቁ) እንዲመራ ማድረግ እና የጎሳ ችግሮች በተነሱባቸው ቦታዎች ሁሉ  የተማሪዎቹ ህብረት የማስተማር ሥራ እንዲሰራ እንዲሁም ችግር ከመፈጠሩ በፊት ወደ ጎሳ ግጭቶች የሚመሩ ጉዳዮችን ቀድሞ እያጠና ከዩንቨርስቲ ቦርዶች ጋር በመነጋገር የማንቅያ ሥራ የሚሰራ እንዲሆን ማስቻል ይገባል።ኅብረቱ ደግሞ እውቅና ብቻ ሳይሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እና በተወካዮች ምክር ቤት ሳይቀር ከበሬታ ያለው እና የማስፈፀም አቅሙን ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል። እዚህ ላይ የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮዎች ማንሳቱ ተገቢ ነው። በአውሮፓ እና በአሜሪካ ትተን በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ዩንቨርስቲዎች የተማሪዎች ኅብረቶች ከፍተኛ ተከባሪነት እና የመደመጥ አቅም በሀገራቸው ውስጥ አላቸው።ለምሳሌ በዩጋንዳው የማካረሬ ዩንቨርስቲ የተማሪዎች ኅብረት በፕሬዝዳንት እና በካቢኔ ሚኒስትር ደረጃ የተደራጀ ሲሆን፣ምርጫው በዲሞክራሲ እያንዳንዱ ተማሪ ድምፅ የሚሰጥበት፣የተመረጠው የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝዳንትም ከመንግስት መኪና ከመሰጠት ጀምሮ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እና የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት በቀጠሮ እስከማነጋገር ድረስ መንግስታዊ ስልጣን ተቸሮታል።ይህ የእኛ ሀገር ምን ያህል ወደ ኃላ የቀረ ደረጃ ላይ እንዳለን አመላካች ነው።ተማሪዎቹን ማደራጀት እና እውነተኛ የተማሪዎች ኅብረት በሀገራዊ እሳቤ ላይ መስርቶ እንዲኖር ማድረግ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞችን አደብ ያስገዛል፣ሀገር ያረጋጋል።


የዩጋንዳው ማካረሬ ዩንቨርስቲ የተማሪዎች ፕሬዝዳንት ምርጫ ሲደረግ በአካባቢ ቴሌቭዥን  (አርባን ቲቪ ዩጋንዳ) ሳይቀር የምርጫ ዘመቻ ተደርጎ እንደሆነ ለማሳየት የቀረበ ቪድዮ ከስር ይመልከቱ።


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...