ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, December 25, 2018

በሻሸመኔ በጋጠ ወጥ ወጣቶች ከተደበደቡ ሙስሊም ወንድሞቻችን ጎን መቆም አለብን።መንግስት በክልል የወረዳ እና ዋና ከተሞች ሕዝብ የመረጣቸው ታጣቂ ሚሊሻዎች ማደራጀት አለበት።

(ጽሁፉ ከጽሁፉ ስር የተለጠፈው፣ የጃኖ ባንድ ሙዚቃ ልዑክ ሀሳብ ጋር አይገናኝም)

ጉዳያችን/ Gudayachn
ታሕሳስ 17/2011 ዓም (ዴሰምበር 26/2018 ዓም)

በኢትዮጵያ ከመጋቢት 24/2010 ዓም የመጣው ለውጥ ተከትሎ፣ ለውጡ እጅግ በርካታ መልካም ዕድሎችን ለኢትዮጵያ የማምጣቱን ያህል በአንዳንድ አክትቪስቶች የሚመሩ እና ከአክትቪስቶቹም ውጭ የሆኑ ፍፁም ጋጠወጥ ወጣቶች በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክፍሎች ሽብር በሰላማዊው ሕዝብ ላይ እየፈፀሙ እንደሆነ ይሰማል።ከአራት ወራት በፊት የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ቴሌቭዥን እራሳቸውን ቄሮ በሚል ስም ያደራጁ ወጣቶች ከከተማው ዳር የእስር ቤት ከፍተው ዜጎችን ሲያሰቃዩ እንደነበር ፖሊስ እንደደረሰበት እና ለሕግ እንዳቀረባቸው የሚያሳይ ዘገባ አስተላልፎ ነበር።

ድሬዳዋ ብቻ አይደለም።በሻሸመኔ ከተማ የሰው ልጅ እንደ በግ ተዘቅዝቆ የተሰቀለው ባሳለፍነው ክረምት ውስጥ ነበር። በቡራዩ አሰቃቂ ግድያም የተከተለው እንዲሁ ወጣቶች ናቸው በተባሉ አውሬያዊ ባህሪ በተላበሱ ሰው የሚል ስም በተሰጣቸው ነው። በሁለቱም ቦታዎች የወንጀሉ ተሳታፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መንግስት ማስታወቁ እና ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ እንዳለም መገለጡ ይታወሳል።በተለይ የቡራዩን እልቂት አስመልክቶ በርካቶች ጉዳዩን ኮንነው የተናገሩትን ያህል '' የቡራዩ ጉዳይ ከሚገባው በላይ ተራገበ፣በጣም ተጮሆለታል፣እኔ ተጋነነ ባይ ነኝ '' የሚል ቃል ባለፈው ሳምንት ውስጥ ለትግራይ ቴሌቭዥን የተናገረው አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ የሻሸመኔውን የሰው መሰቀል ለማውገዝ ቀናት እንደፈጁበት መመልከት እንደ ሰው ለሚያስብ ሁሉ የሚያም ጉዳይ ሆኖ አልፏል።ጉዳዩ አሁንም አክቲቪስቶች የብስለት ደረጃቸው ብዙ የሚቀረው መሆኑን አመላካች ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ጉዳዮች ሕዝብ በአይነ ቁራኛ እንዲከታተል የሚያስገድድ ነው።

ዛሬ ህዳር 16፣2011 ዓም በማኅበራዊ ሚድያ እየተዘዋወረ ያለው በቁልፍ ከተማ ሻሸመኔ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን አዛውንቶች ላይ የብልግና ስድብ እየተሳደቡ የተራገጡ፣የደበደቡ እና የፈነከቱ  ወጣቶች  ድርጊት ነው።ጉዳዩ እንደገና  በሻሸመኔ ከተማ ባሳለፍነው ክረምት ወቅት የተፈፀመውን የሰው መስቀል ወንጀል  እንድናስታውስ ያደርገናል።ሻሸመኔ ከአርሲ፣ባሌ፣ሲዳሞ፣ከአዲስ አበባ  እና ምዕራብ ኢትዮጵያ የመገናኛ ከተማ ነች።በከተማዋ ውስጥ ከእነኝህ ቦታዎች በሙሉ በወንጀል የሚፈለጉ ወጣቶች የሚተራመሱባት ከተማም ነች።ይህ ሁኔታ ደግሞ  በወንጀል እና በሽብር ዓላማቸውን ለማሳካት ለሚፈልጉ አካሎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ከተማዋ እንደመናሃርያነቷ በከተማዋ ውስጥ አድሮ የሚሄደው እና ነዋሪው እስኪያምታታ ድረስ ከፍተኛ መተራመስ እንዳለ ከተማዋን የሚያውቁ ይናገራሉ። ስለሆነም ከተማዋ ቁልፍ ከመሆኗ አንፃር ጥብቅ የፀጥታ ቁጥጥር ያስፈልጋታል።ባለፈው ክረምት ወቅት በሻሸመኔ የተፈፀመውም ሆነ በሌሎች የኦሮምያ ክልሎች የሚፈፀሙት የሽብር ተግባሮች ዋና አላማቸው በአንዳንድ አቅትቪስቶችም እየተደገፈ ያለው ሆን ብሎ በማሸበር ህዝብን እና መንግስትን አንገት የምያስደፉ መስሏቸው ነው።

ሰው የሚያሸብረውን ኃይል ፈፅሞ ይፈራል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ጅልነትም ነው።በሻሸመኔ ሰው የሰቀሉም ሆኑ ያሰቀሉ፣ በቡራዩ ሕፃናትን የጨፈጨፉም ሆኑ ያስጨፈጨፉ ሁሉ ዓላማቸው የሽብር ተግባራችን ይህንን ያህል ይሄዳል የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው።ይህንን ደግሞ ከአክቲቪስቶቻቸው ገደምዳሜ ንግግሮች መረዳት ይቻላል።ይህ ግን ከከንፈር እስከ አፍንጫ ያለ ደካማ አስተሳሰብ ነው።ማንም ህልውና ላይ ማንም ቆሞ እርቀት መሔድ አይቻልም።ስለሆነም አክትቪስቶች በርካታ በሕግ የሚያስጠይቁ ቃላት ባገኙት ሚድያ ሁሉ ሲረጩ እንደነበር ዘወር ብለው መመልከቻቸው ጊዜ አሁን ነው።የሩዋንዳው እልቂት ከተነሳ በኃላ የጉዳዩ መነሻ ሲመረመር በእየሚድያው ላይ የተነገሩ ግንባር ቀደሞች ቃል ተሰብስቦ ለፍርድ እንደቀረቡ ማስታወስ በቂ ነው።ያለፈው አልፏል።ከአሁን በኃላ መስተካከል እና ሕዝብ መካስ አለብኝ የሚል ውሳኔ በኢትዮጵያውያን ደም በተንሸዋረረ አስተሳሰብ ወጣቱን በመረዙት ሁሉ ውስጥ መጫር ያለበት ጊዜ አሁን ነው።

በወጣት ጋጠ ወጦች ለሚፈፀሙ ሽብሮች መፍትሔው 

በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ የወረዳ ከተሞች እና የክልል ከተሞች ነዋሪዎች ላይ የሽብር ተግባር የሚፈፅሙ ጋጠ ወጥ ወጣቶች  የለውጡን ሂደት ከማይደግፉ ኃይሎች በሚያገኙት የገንዘብ እና የቁሳቁስ እርዳታ ጭምር በንፁሃን ላይ እየደረሰ ያለው ሽብር ስፍር ቁጥር የለውም።አንዳንድ የኦሮምያ ከተሞች ባለ ሀብቶች ገንዘብ እንዲሰጡ በሚስጥር በምደወሉ ስልኮች ይጠየቃሉ።ገንዘቡን ካልሰጡ ንብረታቸው አደጋ ላይ እንደሆነ ይነገራቸዋል።አንዳንድ ቦታዎች ላይ ዜጎች ወንጀለኞችን ለማጋለጥ እስከሚፈሩ ድረስ የውስጥ ለውስጥ ሽብር እንዳለም ይሰማል።ይህ ሁኔታ ባብዛኛው በኦሮምያ ክልል የሚገኝ የሽብር ተግባር ሲሆን ዛሬ በሻሸመኔ ከተማ በሙስሊም አዛውንቶች ላይ የተፈፀመው ድብደባ ሕዝብ በቃ! በማለት በአንድነት በመነሳት የአካባቢውን ፀጥታ ለማስከበር መነሳት ያለበት ጊዜ አሁን ነው።አዛውንቱ ጋር የተፈጠረው ግጭት ምንም ይሁን ምን በሥርዓት አልባ ወጣቶች የተፈፀመው ድርጊት በፅኑ መኮነን ያለበት ነው።ይህ ሁኔታ በአንዳንድ የአዲስ አበባ ዳር  ያሉ መንደሮች ባሉ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ሁሉ ሲፈፀም መመልከት የተለመደ እንደሆነ የእዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ መረጃው እንዳለው ያስታውሳል።ይህ ጉዳይ ሀገር አፍራሽ ነው።በምክር ያልተመለሰ በሕግ እና በኃይል ስርዓት መያዝ ያለበት ጊዜ አሁን ነው።

መንግስት እንደመንግስት በመዋቅሩ መውሰድ ያለበት እርምጃዎች በህዝባዊ የፀጥታ ኃይሎች መደገፍ አለበት።እዚህ ላይ መንግስት የሚጠበቅበት የማደራጀት እና የበጀት፣የስልጠና እና የትጥቅ ድጋፍ ሕዝብ ለሚመርጣቸው አካባቢ ሚሊሻዎች ማደራጀት እና የህዝብ አሸባሪዎችን በራሱ በሕዝቡ አደብ ማስገባት ያስፈልጋል። ምክንያቱም የፈድራል ፖሊስ እና የጦር ኃይሉ ሁሉም ቦታዎች በአንድ ጊዜ መድረስ አይችሉም።ቢያንስ በአሸባሪዎች የሚነሱ ጥፋቶችን በመጀመርያ ሊመክት እና የሚጠፋውን ሕይወት እና ንብረት (የፀጥታው ችግር ከአቅም በላይ ከሆነ የፈድራል ፖሊስ እስኪደርስ ድረስ) ለመግታት የአካባቢ ሚሊሻ ብዙ ተግባራትን ማከናወን ይችላል።እዚህ ላይ የወደቀው ዘረኛ ስርዓት ደጋፊዎች መረዳት የሚገባቸው በእነርሱ ዘመን ከነበርንበት የጥፋት ዘመን እጅግ እጅግ በተሻለ ደረጃ ኢትዮጵያ እንደምትገኝ ነው።አሁን ፍፁም ወደ ሆነ የሕግ መከበር የሚኬድበት ስርዓት እንጂ በቀን በአንድ ከተማ የአጋዚ ወታደሮች እንደሚገድሉን ዘመን አለመሆናችንን ነው።

ጃኖ ባንድ ''ጥቁር አልማዝ'' የተሰኘው አዲስ ዜማ 


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...