ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, December 9, 2018

ከቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ አንድነት በኃላም ከቤተ ክርስቲያን መዋቅር እውቅና ውጪ ቤተ ክርስቲያን በሚከፍቱ ላይ ጳጳሳት ቁጥጥር ሊያደርጉ ይገባል።


ጉዳያችን/Gudayachn
ኅዳር 30/2011 ዓም (ኖቬምበር 9/2018 ዓም)
 ''ያለ ኤጲስቆጶሱ ትእዛዝ ቤተ ክርስቲያንን አይሥሩ። አንድ ሰው ስንኳ ደፍሮ ከዚህ ውጪ ቢሠራ በውስጥዋ እስከ ዘላለም ቁርባን አይቈረብ። ቄሱም ይህን ተላልፎ በውስጥዋ ቁርባንን ቢቈርብ ይሻር።'' (ፍት.ነገ.አን.1፥2፤ በስ.94)።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚታወቁበት አንዱ እና መሰረታዊው መለያ በቅዱስ ሲኖዶሳዊ መዋቅር ውስጥ የሚታዘዙ እና መውቅሩን ተከትሎ በተመደቡላቸው ጳጳሳት አባታዊ ቡራኬ እና መመርያ የመመራታቸው መፅሐፍ ቅዱሳዊ ስርዓት ነው።ይህ የክህነት ስልጣን ተዋረድ ጠብቆ የሚሄደው  የቤተ ክርስቲያን ስርዓት ኦርቶዶክሳዊ አብያተ ክርስቲያናት እምነታቸው እና አምላካዊ ቃል የሆነው መሰረተ እምነት (ዶግማ) በእየዘመኑ በሚነሱ የኃይማኖት ቀሳጮች  በቀላሉ እንዳይበረዙ እና እንዳይሸረሸሩ አንዱ ጠንካራ ግንብ ሆኖ ቆይቷል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክህነትን በአንብሮተዕድ  ሐዋርያትን በክህነት የሾማቸው ገና መንፈስ ቅዱስ ሳይወርድላቸው እርሱም ገና አርጎ በአባቱ ቀኝ ሳይቀመጥ ነበር። /ዮሐ.20፥22-23/  ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ክህነትን ያገኘችው ከክርስቶስ ነው።ይህም በአንብሮተዕድ  (እጅን በመጫን)  ከጌታችን የተገኘች ክህነት ከሐዋርያት ጀምሮ አሁን እስካሉ ጳጳሳት ደርሳ አሁን ላለችው ቤተ ክርስቲያንም እያገለገለ ይገኛል። ክህነት ከእግዚአብሔር የተሰጠች ለመሆኗ ቅዱስ መፅሐፍ በልዩ ልዩ ቦታ ያስተምረናል።ሐዋርያትም የትንሣኤውን ዐዋጅ ለመንገር ወደ ዓለም በገቡ ጊዜ በክህነታቸው ተኣምራት ያደርጉ ነበር፡፡ /ማር.16፥16/ ሐዋርያት በሥልጣናቸው ያስሩ ይፈቱ ነበር፡፡/ማቴ.18፥18፤ 1ቆሮ.4፥1፤ 2ቆሮ.5፥20፤ ማቴ.16፥18/ ለምሳሌ፡- የሐናንያንና የሚስቱን የሰጲራን፤ የሲሞን መሠርይን ታሪክ ይመለከቷል፡፡ /የሐዋ.5፥1-11፤ 8፥24-28/ ቤተ ክርስቲያንን ይመግቡና ያስተዳድሩም ዘንድ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ /ዮሐ.20፥15/

አሁን ባለንበት ዘመን በተለይ ሲኖዶሳዊ አንድነት ከተፈጠረ በኃላ ለቅዱስ ሲኖዶስ ስርዓት ባለመታዘዝ ወይንም በግብር ይውጣ መልክ በቸልተኝነት  ቤተ ክርስቲያን ሳያስባርኩ መግባት፣ክህነት በሊቃነ ጳጳሳት ተይዞ እያለ ሕዝቡን ለመባረክ መውጣት፣ቤተ ክርስቲያንን የግል መተዳደርያ የሆነች ይመስል ተመሳሳይ ታቦታትን በአንድ ከተማ በመደርደር የምመናንን አንድነት መፈታተን እና የመሳሰሉ ጉድለቶች በተለይ በውጭ የሚገኙ አንዳንድ ከተሞች ላይ ይስተዋላል። እነኝህ ችግሮች ከሁለት አቅጣጫ የሚከሰቱ ናቸው። አንዱ የሀገረ ስብከቱ ጳጳሳት ስርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማስከበር አፋጣኝ ማስተካከያዎችን ካለማድረግ እና ህዝቡ ትክክለኛ የቤተ ክርስቲያንን ስርዓት እንዲያውቅ በግልጥ ካለመንገር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከስኖዶሳዊ ፈቃድ ውጭ በራሳቸው የሚሄዱ ካህናት ቤተ ክርስቲያንን ብቸኛ መተዳደርያ እንጂ ምዕመናንን ለማስተማር እና ለሰማያዊ መንግስት ለማብቃት ዓላማን ያላደረገ ተግባር ላይ ሲጠመዱ ነው።

ስለሆነም  በውጭ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ሲኖዶስ መዋቅር ስር ከሚገኘው አህጉረ ስብከቱ ጳጳስ ውጭ  የሚሄዱ ካህናት ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የምእመናንን አንድነት ለመፈታተን እየሰሩ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምትመራበት መሰረተ ዕምነት የሚያወጣ አደገኛ መጋለጥ ውስጥ እንደሚጥሏት ተገንዝበው ከአህጉረ ስብከት ጳጳሳት ትዕዛዝ ስር ሆነው በክህነት ችግር ያለባቸውን አገልጋዮች ጳጳሳት አባቶች በሚመሯቸው ስርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሰረት ስርዓት መያዝ ይገባቸዋል። እዚህ ላይ ምዕመናን የቤተ ክርስቲያን ባለድርሻ እና ባለ ርስት መሆናቸውን ተገንዝበው በየቦታው የሚከፈቱ አብያተ ክርስቲያናት በአሕጉረ ስብከቱ ጳጳስ ተባርከዋል? የተመደቡት ካህንስ ትክክለኛ ስልጣነ ክህነቱ አላቸው? ወይንስ በራሳቸው ከሕግ ውጭ እየሄዱ ነው? ብለው መጠየቅ አለባቸው። ማንም ካለ ኤጵስቆጶስ ፍቃድ ውጭ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታቦተ ሕጉን ይዞ እንዲገባ አይፈቀድለትም

 ''ያለ ኤጲስቆጶሱ ትእዛዝ ቤተ ክርስቲያንን አይሥሩ። አንድ ሰው ስንኳ ደፍሮ ከዚህ ውጪ ቢሠራ በውስጥዋ እስከ ዘላለም ቁርባን አይቈረብ። ቄሱም ይህን ተላልፎ በውስጥዋ ቁርባንን ቢቈርብ ይሻር።'' (ፍት.ነገ.አን.1፥2፤ በስ.94)።

ተው ዓለም ተመለስ (መዘምር ኪነጥበብ ወ/ቂርቆስ)

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...