ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, February 17, 2022

አስከሬን ከብቦ እየዘፈነ፣ሃይማኖት ከፍሎ እየፈነጠዘ እና አጼ ዮሃንስ የሞቱለትን ሰንደቅ ዓላማ እያወረደ እንደጣኦት አምልኩኝ ባዩ ሽብርተኛው ህወሓት እና የካቲት 11


  • ሽብርተኛው ህወሓት በትግራይ በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ፍርሃት ፈጥሯል።ፍርሃቱ የተፈጠረው የትግራይ በህወሓት በግድ መለየት አዲስ ቅስፈት ይዞ ይመጣል የሚል ወሬ በሰፊው በትግራይ እየተዛመተ መምጣቱ መሆኑን  አስተማማኝ መረጃ ያላቸው እየተናገሩ ነው።

ጉዳያችን / Gudayachn

ዓለም ለልማት ይፋጠናል።ህዝቦች ከችግር ለመውጣት ይፍጨረጨራሉ።መሪዎች ህዝባቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሌት ከቀን እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ።ባለፈው ግማሽ ክፍለዘመን ውስጥ ቻይና በሚልዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿን ከድህነት አላቃ ከመካከለኛ ገቢ እስከ ሚልዬነር አድርሳለች። ደቡብ ኮርያ ከድህነት ወጥታለች።ብራዚል እና ህንድ ድንቅ እድገት አሳይተዋል።ይህ ሁሉ የሆነው ህወሓት በደደቢት ከተመሰረተ በኋላ ነው። ዓለም በእዚህ መንገድ ሲራመድ ህወሓት ግን መሬቱን በደም እያጨቀየ፣አጥንት እየቆጠረ የኢትዮጵያውያንን መከራ አርዝሞ 27 ዓመታት ከኖረ በኋላ፣አፋር እና አማራን አጎሳቁሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ህዝብ አርግፎ ዛሬም ደደቢት የገባበትን 47ኛ ዓመት አስከሬን ከቦ በመዝፈን እና ሃይማኖት ከፍሎ በመፈንጠዝ ለማክበር ዓይኑን በጨው አጥቦ መጥቷል።

ህወሓት ግማሽ ክፍለ ዘመን ባለበት ብቻ ሳይሆን ቆሜለታለህ ያለውን የትግራይ ህዝብ በደም ነክሮ፣ልጆቹን አርግፎ እና ወደ የባሰ ረሃብ ውስጥ ከትቶ 47 ኛ ዓመቴን ላከብር ነው ዝፈኑልኝ እያለ ነው። የትግራይ እናቶች የዘመቱት ልጆቻቸው መሞት ምክንያት ትካዜ ላይ ቢሆኑም አስከሬን ከቦ፣ሃይማኖት ከፍሎ፣አጼ ዮሃንስ መተማ ላይ የሞቱላትን ሰንደቅ ዓላማ ከመቀሌ መንገዶች አውርዶ እንደጣኦት አምልኩኝ የሚለው ህወሓት አተርፍ ባይ አጉዳይ የሚለው አባባል የሚያጥረው ሆኗል።

ጥበብ ከመነሻውም አያውቀውም።ድንቁርና በራሱ ላይ እንደሙጃ ሰፍቶበታል። ሽብርተኛው ህወሓት በመጀመርያ ደረጃ የሚጠላው የትግራይን ህዝብ ነው።በስሙ ነግዶበት፣ሃብት አካብቶበት እና ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ጋር አጋጭቶት እና ላለፉት ወራት ደግሞ ወደ ህዝቡ የተላከውን የእርዳታ እህል እንዳያልፍ አፋር ላይ ተኩስ ከፍቶ አቋርጦበት  የካቲት 11 ደደቢት የገባሁበትን አክብር እያለ ህዝቡን እያስገደደው ነው።የሚገርመው አሁን ላይ ሆኖም ህዝቡን የተረፈ ሰው ከቤት ፈልጉ ወደ ጦርነት ልማግደው እያለ እየቀሰቀሰ ነው።ይህንን የሚቀሰቅሱት እነ ጻድቃን ኝ ልጆቻቸውን በአሜሪካ ውድ ዩንቨርስቲዎች እየተማሩ ነው።የጻድቃን ገብረትንሣይ ልጅ በቅርቡ ከታወቀ የአሜሪካ ዩንቨርስቲ መመረቋን በማኅበራዊ ድረ ገጿ ላይ ለቃ ታይታለች። የትግራይ ወጣት ግን የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ለመፈተን የነበረውን ዕድል ሳይቀር ዘግቶበት ዝመት እያለ አስፈጅቶታል።የድንቁርናው ግዝፈት ደግሞ ፊደል ቆጠርን የሚሉት በውጭ የሚኖሩት የሽብርተኛው ህወሓት ደጋፊዎች እና በሃገር ውስጥ ያለው ጀሌውም ሳይቀር የትግራይን ህዝብ ወደየመጨረሻው ገደል ሲከተው እያዩ የቅስቀሳ ዘፈን ከመኝታቤታቸው ሳይወጡ እየለቀቁ ሲቀማጠሉ ማየት ምን ዓይነት የቅዠት ዓለም ውስጥ እንዳሉ መረዳት ይቻላል።አስከሬን ከቦ በመዝፈን፣ሃይማኖት ከፍሎ በመፈንጠዝ እና አጼ ዮሃንስ የሞቱለትን ሰንደቅ ዓላማ አውርዶ እንደጣኦት አምልኩኝ ማለት ወግ ያለው ሞትም ላለመሞት ህወሓት መወሰኗን በግልጥ ያሳያል።

ህወሓት ቀድሞ በህዝብ ህልውና ላይ መጥቷል።ቀጥሎ በሃይማኖት ላይ ዘምቷል።በሰሞኑ ህወሓታዊ የትግራይ ቤተክህነት እና የእስልምና ጉዳዮች ኮሚቴ ከኢትዮጵያ ለይቻለሁ ብሎ አውጇል።ይህ ከቅዱስ ሲኖዶስ እና ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የበላይ አካል ትግራይ እንድትለይ በህወሓት መገድዷ፣ በትግራይ በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ፍርሃት ፈጥሯል።ፍርሃቱ የተፈጠረው የትግራይ በህወሓት በግድ መለየት አዲስ ቅስፈት ይዞ ይመጣል የሚል ወሬ በሰፊው በትግራይ እየተዛመተ መምጣቱ መሆኑን  አስተማማኝ መረጃ ያላቸው እየተናገሩ ነው።እዚህ ላይ እነ ቢቢሲ አማርኛ ጨምሮ ''የትግራይ ክልል ካህናት እና  የእስልምና ጉዳዮች የበላይ አካል ከኢትዮጵያ ተለዩ ''እያለ ዘገባ ሰርቷል።

የቢቢሲ ዘገባ ሁለት ስህተቶች አሉበት።የመጀመርያው የትግራይ ካሕናት የት ተሰብስበው? ተፈራረሙ? ስንት የደብር እና የገዳማት አለቆች ተሰብስበው ወሰኑ? እንደ ቢቢሲ ያሉ የዜና አውታሮች የዜናውን ትክክለኛ ምንጭ ሳያገኙ ጥቂት ጳጳሳት የተሰበሰቡበት ፎቶ እና ቪድዮ ይዞ ማውጣት ነገ ማጣፍያው ያጥራል። በሁለተኛ ደረጃ ዘገባው የተወሰኑ ካሕናት የታዩበት ስብሰባ የተመራው በደብረጽዮን እና አለቃ ጸጋዬ ነው። ይህ ማለት ስብሰባው በካሕናቱ የተጠራ ሳይሆን የፖለቲካ አካሉ የሃይማኖት አባቶችን ጠርቶ መመርያ ነው የሰጣቸው።ቢቢሲ ይህንኑ ስብሰባ ሲዘግብ የደብረ ጽዮንን እና የአለቃ ጸጋዬን ፎቶ ቆርጦታል።ይህ በስህተት የተደረገ አይደለም።ጉዳያችን ላይም ሆነ በራሱ በህወሓት ሚድያዎችም ሁለቱም ጥቂት አባቶችን በመኖርያ ቤት ሰብስበው ሲያወያዩ ለቀዋል።ይህ ታሪክ ወደፊት የሚጠይቀው ነው።በመሆኑም የትግራይ አባቶች፣የደብር አለቆች፣የገዳማት አስተዳዳሪዎች እና ሊቃውንቱ ከቅዱስ ሲኖዶስ ለመለየት የወሰኑበት ስብሰባ ይዘት የለም።በእስልምናም የሆነው ይሄው ነው።ለህወሃት የተወዳደሩ የእስልምና አባት ጨምሮ ሰብሰብ ብለው ቪድዮ ተነስተው ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ማዕከል ተለየን የሚል የሜዳ ላይ መግለጫ ነው የተሰጠው።ባጭሩ ህወሃት መቃብር አፋፍ ላይ ሆና ሃይማኖት ለማገት ሞክራለች።ሃይማኖት በመኖርያ ቤት በሚደረግ ስብሰባ አትታገትም።በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ ጠልቃ የገባች ስለሆነ ደብረጽዮን እና አለቃ ጸጋዬ በስብሰባ አይሸብቧትም።

በመጨረሻም ይሄውም የሽብርተኛው ህወሓት በሃይማኖት ጉዳይ ላይ መቅደስ እና መስጊድ ገብቶ መክፈል ቢያንስ በረከት ይዞ አይመጣም ብቻ ሳይሆን ህወሓትን እንደተክለፈለፈ ወደ መጥፍያው መንገድ እየሄደ መሆኑን ትግራይ ውስጥ በግልጥ እየተነገረ ነው።ለመጠገን መራወጡ ግን ቀጥሏል።ይህ ደግሞ በተጨማሪ የትግራይ ወጣት ደም የሚያስፈስስ ነው።ለእዚህ የትግራይ ህዝብ ፍቃደኛ ነው ወይ? ላለፉት 47 ዓመታት የሞቱት ኢትዮጵያውያን አጥንት ዛሬ እንደ አዲስ ለፍርድ የሚቆምበት ጊዜ ነው።ስለሆነም መደናበሩም ምንም ለውጥ አያመጣም።አስከሬን ከቦ በመዝፈን፣ሃይማኖት ከፍሎ በመፈንጠዝ እና አጼ ዮሃንስ የሞቱለትን ሰንደቅ ዓላማ አውርዶ እንደጣኦት አምልኩኝ ማለት ህዝብ እና ክልሉን አብሮ ይዞ ለመጥፋት ካልሆነ በቀር የሚያመጣው ለውጥ የለም።ህወሓት 47 ዓመት ያላመጣው ብልጽግና የመቃብር አፋፍ ላይ ሆኖ ለትግራይ ህዝብ ይቆማል ብለው መቃብሩ አፋፍ ላይ ቆመው የሚያዩት የበለጠ ደንዝዘዋል።

================////===========

No comments: