ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, February 2, 2022

ጠልነት ወቅታዊ የሃገራችን ችግር ነው።ከዘረኝነት እኩል አደገኛ ነው።መገናኛ ብዙሃን ሊዘምቱበት ይገባል።

===============

ጉዳያችን / Gudayachn

==============

በሽታ ህመሙ የሚሰማ እና ህመሙ በቀላሉ የማይሰማ በሚል መክፈል እንችላለን።በአካላችን ላይ የሚደርስ በሽታ ውስጣዊ በሽታችንንም ሆነ ላይኛውን አካላችንን ቢያመን የቱ ጋር ህመሙ እንዳለ ስለምናውቀው ወደ ሃኪም ዘንድ ሄደን በመታከም እንድናለን። ህመማቸው በአካላችን ላይ የማይታዩ ውስጣዊ የስሜት ችግሮች ግን አደገኛ የሚያደርጋቸው ታማሚው በራሱ እንደታመመ አለማወቁ ነው።

በሃገራችን አሁን የሚታየው አንዱ ችግር የጠልነት ችግር ነው።የጠልነት ችግር ምክንያታዊነት የሌለው በአብዛኛው የጠልነት ችግር ያለበት ሰው በራሱ የታመመ የማይመስለው ወይንም ለጠልነቱ የራሱን ምክንያት ያለውን ሰጥቶ በጥላቻ ላይ ሌላ ጥላቻ እየደረበ በእራሱ አዕምሮ ላይ በጠልነት የተለወሰ መርዝ እያኖረ እራሱን የሚጎዳ እና ሌሎችም እንደርሱ ጠል እንዲሆኑ እያወቀ ወይንም ሳያውቅ የሚያዛምት ሰው ነው።በተለይ በአሁኑ ጊዜ ዘረኝነት ምክንያታዊ አለመሆኑ እየታወቀበት ሲመጣ ጠልነት በሰፊው እየተንሰራፋ ነው።

ጠልነት ከእኛ ጎሳ ውጭ የሆነ ሰው ወይንም የተለየ እምነት ያለው አልያም ከእኛ አስተሳሰብ ውጭ ነው የምንለውን ሰው፣ማንነቱን ሳናውቅ፣ደግ ይሁን ክፉ፣የተማረ ይሁን ያልተማረ ገጠር ይሁን ከተማ ማንነቱን ሳናውቅ በአዕምሯችን ውስጥ በፈጠርነው ምናባዊ ፍረጃ ብቻ ያንን ሰው የመጥላት ክፉ በሽታ ነው። ባብዛኛው ጠልነቱን የሚፈጥሩ ሰዎች በራሳቸው የሚዛናዊነት ዕይታ ችግር ያለባቸው ሲሆኑ በአስተዳደጋቸውም ነገሮችን የመመርመር፣የማድመጥ እና የትዕግስት ክህሎትን ከአደጉበት ውጭያዊ አካባቢ ለማግኘት ያልታደሉ ወይንም በህይወት ልምዳቸውም ይህንኑ ማዳበር ያልቻሉ ናቸው። እገሌን ለምን ጠላህ/ሽ? ተብለው ሲጠየቁ የሚመልሱት የተሟላ መልስ እንደሌለ የሚያውቁት በራሱ ሲጠየቁ እንጂ ቀድሞም ምክንያት የላቸውም። ለእራስ ማታለያ ግን የሚሰጥ ምክንያት አላቸውም።እነኝህ ምክኛቶች ግን መልሰው ሲመለከቱት ለራሳቸው አስደንጋጭ መሆናቸውን በእርጋታ ቢመለከቱት ጥሩ ነበር።

አንድ ሰው በራሱ መርጦ ባልተወለደበት ቦታ ምክንያት መጥላት፣ አንድ ሰው በሚያምነው ዕምነት ምክንያት መጥላት፣ አንድን ሰው በሚወደው ነገር ወይንም በግል የኑሮ ዘይቤው ምክንያት ከእኛ ጋር ስላልተመሳሰለ ብቻ መጥላት እና የመሳሰሉት ሁሉ አደገኛ የጥላቻ ምክንያት ሆነው ሲቀርቡ መመልከት አሳዛኝ ነው።ጠልነት በተለይ ከሚዛናዊነት እና ሁሉን ለማገልገል ወይንም ለመርዳት ካለ ፍላጎት ጋር ስለሚጋጭ በራሱ አድሏዊነትን ይፈጥራል።ስለሆነም ጠልነት የሚያራምድ ሰው ለጊዜው ለራሱ ጥሩ እና ፍትሃዊ ነገር እየሰራ ያለ ይምሰለው እንጂ ውሎ አድሮ ትክክል አለመሆኑን ይረዳዋል። የጠልነት በሽታ አለብኝ? ወይንስ የለብኝም? ብሎ መመርመር ያስፈልጋል። ህመሙም መድሃኒቱም ያለው እራሳችን ውስጣችን ነው። ለሃገር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ምሁራን በተደረገባቸው የጠልነት ዘመቻ እነርሱ የተናገሩት ሁሉ ጥፋት መስሎን እራሳችንን የምናታልል፣በራሳችን የእምነት አባቶች ላይ የጠልነት ስሜት የምናስተናግድ፣በማኅበራዊ ሚድያ የጠልነት ዘመቻ የተደረገበት ሰው ምን አንዳለ ሳናውቅ በውስጣችን የጠል ስሜት አብቅለን በአዚያው ደምድመን የምንኖር አንጠፋም። 

ጠልነት የትኛውም እምነት አይቀበለውም።ነገር ግን በእምነት ድርጅቶች ውስጥ ሳይቀር ሰርጾ የሚገኝ አደገኛ ስሜት ነው።ሰውን ያህል ቡር ፍጥረት ጠልቶ ጽድቅ የለም።መርዛማ ጠልነትን ይዞ ውስጣዊ መረጋጋት አይኖርም።ሰዎች ሊጠሉን ይችላሉ።ይህ በእኛ የሚወሰን አይደለም።የመውደድም ሆነ የመጥላት መብታቸው ይከበራል።ነገር ግን የጥላቻ ስሜት በጠል አራማጁ ግለሰብ ውስጥ የሚገኝ መርዝ በመሆኑ ለጠል አራማጁ ቀሪ እና አደገኛ ውስጣዊ ቅሪት ሆኖ ይጎዳዋል እንጂ የሚያተርፈው ነገር የለም።ስለሆነም ሌሎች የጥላቻ ባህር ውስጥ ሲገቡ እራስን ከእዚህ የጥፋት ባህር አትርፎ የራስን ጤንነት መጠበቅ አስፈላጊ ነው። 

ባጠቃላይ ጠልነት አደገኛ ወቅታዊ የሃገራችን ችግር ነው።ልጆች ቤት ውስጥ ከወላጆቻቸው በሚሰሙት እና በመልክ በማያውቁት ዕምነት፣የመንግስት ባለስልጣን ወይንም ታዋቂ ሰው ላይ በሚሰነዘር የጠልነት ወሬ የተነሳ የማያውቁትን ሰው ጠልተው ይኖራሉ።ይህም እንደ ባህል ሆኖ ጠልነትን ከልጅነታቸው ይለማመዳሉ።ጠልነት ሃገር ያፈርሳል። ጠልነት ጦርነት ያስነሳል።ጠልነት በሽታ መሆኑን በግልጥ የመገናኛ ብዙሃን አስፍተው ሊናገሩበት፣የስነ ልቦና ጠበብት ህዝቡን ሊያስተምሩበት ይገባል።ይህ ካልሆነ የሰዎችን መልካም ሃሳብ ከመቀበል በፊት በጭፍን የመጥላት ውጤት መልካሙንም ሃሳብ የማንቀበል ብኩን እንዳንሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።ሁሉም ከእራሱ ጋር መወያየት አለበት። 

==============////==============

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...