ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, February 7, 2022

በትግራይ የኢትዮጵያ ኦ/ ተ/ ቤ/ክርስቲያንን ከቅዱስ ሲኖዶስ ለመለየት ህወሓት የሚሰራውን እኩይ ተግባር ለማምከን መንግስት፣ምዕመናን፣መንፈሳዊ ማኅበራት፣ማኅበራዊ ሚድያዎች፣ እና ከቤተክርስቲያኒቱ ዕምነት ውጪ ያሉ ሊያውቋቸው እና ሊከተሏቸው የሚገቡ ሦስት መሪ ሃሳቦች


ከውቅሮ 20 ኪሜ እርቀት የሚገኘው የአብርሃወአጽብሓ ገዳም
===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============

በትግራይ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ከቅዱስ ሲኖዶስ እንዲለዩ ህወሓት በእብሪት መወሰኗን ለብጹአን አባቶች በዶ/ር ደብረጽዮን መነገሩን ትናንት ጉዳያችን ጽፋ ነበር።የህወሓት ልሳኖችም እንደ መልካም ሥራ ሲዘግቡት ታይተዋል። የህወሓት ልሳኖችም ሆኑ የምዕራብ ሚድያዎች ለምሳሌ ቢቢሲ አማርኛ ''ትግራይ ያሉ ካህናት ወሰኑ'' በሚል ዜናውን ለቀውታል።ይህ መታረም ያለበት እና በህዝቡ ስም እየነገደ ያለው ህወሓት እና አሰርጎ ያስገባቸው መዋቅሩ መሆኑ መታወቅ አለበት።

አሁን የትግራይ ገዳማት ሊቃውንት ጉዳዩን አስመልክተው በቀጣይ ህዝቡን የሚነግሩትም ሆነ የሚጸልዩበት ጉዳይ ስለሚሆን እርሱን በሂደት የሚታይ ነው። በእዚህ ጽሁፍ ግን ለማቅረብ የምሞክረው የችግሩ መሰረታዊ ጭብጥ ፖለቲካ እና ፖለቲካ ስለሆነ ከውጭ ያለው ምዕመን፣መንግስት፣መንፈሳዊ ማኅበራት፣ማኅበራዊ ሚድያዎች እና ከቤተክርስቲያኒቱ ዕምነት ውጭ ያሉት ሊያውቁት እና ሊከተሉት የሚገባቸው ሦስት መሪ ሃሳቦችን ነው። እነኝህ ሃሳቦች ሁሉም ከተግባባቸው ችግሮቹ ተለይተው የፈጠረው ህወሓት ላይ እና እርሱን ተከትለው በእየዕምነቱ ውስጥ ተሰግስገው የህወሓትን ዓላማ ለማስፈጸም የሚጥሩትን ለመነጠል እና ምዕመኑን እና ቤተክርስቲያኒቱን ለማዳን ይረዳል።ሦስቱ መሪ ሃሳቦች -

1) በትግራይ ያሉ አባቶች በጊዜያዊ ሁኔታዎች እና በተጽዕኖ ውስጥ መሆናቸውን መረዳት እና ከበዛ ነቀፋ እና ክብርን የሚነኩ መልዕክቶች እንዳይተላለፉ ሁሉም ጥንቃቄ ማድረግ 

ይህ ማለት 
  • ጉዳዩ ፖለቲካ እንጂ ሃይማኖታዊ አለመሆኑን በሚገባ መረዳት፣
  • በትግራይ ያሉ ብጹዓን አባቶች አባቶቻችን መሆናቸውን ጉዳዩ ፖለቲካዊ መሆኑን ሁሉም እንዲያውቅ ማድረግ፣
  • ፖለቲካዊ ጉዳይ ከሃይማኖታዊው ጉዳይ እንዲለዩ አባቶችን በትህትና ደጋግሞ ማስረዳት
  • ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና እና ዶግማ አንጻር የሚኬዱ አካሄዶች አግባብ ባለው በቤተክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጡ መግለጫዎች መጠበቅ።
2) ምዕመናን ሃይማኖት እና ፖለቲካ እንዳይቀላቀልባቸው ህወሓት በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ በስውር መዋቅሮቹ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚፈጥራቸውን ቀጣይ የልዩነት አጀንዳዎች ነቅቶ መጠበቅ እና በመንፈሳዊ አግባብ መከላከል።

ይህ ማለት 

  • ህወሓት አብያተ ክርስቲያናትን በቀጥታ በመዋቅሩ ስር አድርጎ የጦርነት ማካሄጅያ እና የሃብት ማጋበሻ ለማድረግ እንደሚፈልጋቸው ማወቅ እና ምዕመኑን ከእዚህ አደጋ መጠበቅ
  • ሁሉም ትግራይ የተወለደ ወይንም ትግርኛ ተናጋሪ ሁሉ ከህወሓት የቤተክርስቲያን መክፈል ጉዳይ ጋር አብሮ ይቆማል የሚል የተሳሳተ ሃሳብ መውጣት። በተለይ ይህ አለመሆኑን የሚያውቁት መንፈሳውያኑ እና ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ያደጉት ብቻ እንጂ ከውጭ ያለው አይረዳውም።
  • ስለሆነም ከውጭ የተሳሳተ ሃሳብ ይዘው ትግራይ በመወለዳቸው ወይንም ትግርኛ በመናገራቸው ብቻ ለመግፋት ከሚሞክሩት መከላከል።
  • በማናቸው የማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉ ከአንደበት የሚወጡ ዘርን መሰረት ያደረጉ ንግግሮች ወዘተ መጠንቀቅ 

3) ከእዚህ በፊት በዘመነ ህወሓት ቅዱስ ሲኖዶስ ተከፍሎ በነበረበት ጊዜ የነበሩ ችግሮችን አሁን በልምድ መውሰድ 

ይህ ማለት 

  • አባቶች ጉዳዮችን ወደ መሃል የጋራ ነጥብ እስኪያመጡ ጊዜ መፈለጉን እና በትዕግስት፣ በጸሎት እና በጊዜው የሚፈታ መሆኑን ከባለፈው መማር፣
  • ሁል ጊዜ ጉዳዮችን ከማክረር ይልቅ ማለዘብ እና ችግሩ ህወሓት የጠነሰሰው ነገር ግን የህዝብ ጉዳይ ለማድረግ እንደሚሞክር አውቆ ይህንን በተግባር ማክሸፍ፣
  • በእዚህ ችግር ሂደት ጋር የባዕዳን እጅ እንዳለበት ማወቅ የእነርሱን አጀንዳ የሚያስፈጽሙትን መለየት እና ዓላማቸውን ማክሸፍ
  • ለምዕመናን መዳረስ ያለባቸው አገልግሎቶች ባለው መንገድ ሁሉ የበለጠ ተግቶ በመስራት ማድረስ መቻል።በእዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን መንፈሳዊ አገልግሎት ከመቀሌ እስከ ሞያሌ ለማድረስ ቀላል ስለሆነ ይህንን ዕድል ተጠቅሞ ትክክለኛ የመንፈሳዊውን እና የነፍስ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ትምሕርቶች መስጠት፣
  • በትግርኛ የሚያስተምሩ መምሕራን ከመቼውም ጊዜ በላይ የህወሓት የመለያየት ፖለቲካ ቢያንስ መንፈሳዊነት አለመሆኑን ሕዝቡን ማስተማር እና
  • ክፉ የሚያደርግ እና ዛሬ ለመለያየት ከህወሓት ጎን ቆሞ ቤተክርስቲያንን ለማድማት የሚሞክር ነገ በሥጋውም ሆነ በነፍሱ የሚጎዳበት በመሆኑ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ችግሩ ከእዚህ በፊት እንደነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ መለያየት በአንድ ቀን ሲፈታ አባቶች ሁሉን በይቅርታ አልፈው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ስለሚፈታ ከአሁኑ በጥበብ መራመድን ማወቅ ጠቃሚ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው።
በመጨረሻም ህወሓት ይህንን የትግራይ ቤተክርስቲያንን ከቅዱስ ሲኖዶስ የመለየት ምክር ባዕዳን እንደምክረ ሃሳብ ያቀረቡለት እና ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል ሊጠቀሙበት ያሰቡት መሆኑን ሁሉም ወገን ሊረዳው ይገባል።ስለሆነም ከህወሓት የዘር ፖለቲካ ጋር አብሮ የሚሄዱ አስተሳሰቦችን ከራሱ ከትግራይ ህዝብ መንፈሳዊ ህይወት ጋር የተለየ መሆኑን አንጥሮ ማሳየት እና ማጉላት የህወሓትን ተንኮል ሜዳ ላይ ያሰጣዋል።ስለሆነም መንግስት፣ምዕመናን፣መንፈሳዊ ማኅበራት፣ማኅበራዊ ሚድያዎች፣ እና ከቤተክርስቲያኒቱ ዕምነት ውጪ ያሉ ሁሉ ጉዳዩን በስሜታዊነት ከማቀጣጠል ከላይ ከተነሱት ሦስት ነጥቦች አንጻር መቃኘት ጠቃሚ መሆኑን ሊረዱት ይገባል።

======================////==================


No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...