ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, June 10, 2013

ግልፅ በሆነው በአባይ ጂኦ-ፖለቲካዊ ጉዳይ መንግስትም ተቃዋሚዎችም ዝምታቸውን ያቁሙ!

 የአባይ ወንዝ  በግብፅ አፈር ላይ ሳተላይት ፎቶ(NASA)

ግብፆች  ከበሮ እየደለቁ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬም ሲዝቱ ተሰምተዋል።ዝርዝሩ ቢያንስ ለእዚህ ማስታወሻ አይጠቅምም።የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን መረጃው አይነገረውም።በአንድ ፓርቲ ስር ተሸብቦ በአባይ ሰበብ እበላሃለሁ እያለ የሚደነፋበትን ሀገር ጉዳይ እንዳይወያይ እድሉን አጥቷል።ሀገር የሚጠበቀው በአንድ ፓርቲ ብቻ አይደለም።ግልፅነት፣ነፃ የመረጃ ልውውጥ፣ወቅታዊ መረጃ ለሕዝቡ መስጠት ያስፈልጋል።መንግስት እና ተቃዋሚዎች ሊወያዩበት ሊነጋገሩበት የሚገባ አጀንዳ አባይ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል? ባለፉት ሶስቱም መንግሥታት ውስጥ በአፄ ሃይለስላሴ፣በደርግ እና በኢህአዲግ የሚያስማማ ጉዳይ የአባይ ጉዳይ ነው።አባይ መገደብ እንዳለበት ሁሉም መንግሥታት ያምኑ ነበር።ይህ ከፊት ለፊት የተቀመጠ ሀቅ ነው። ኢህአዲግ ደርግ የጀመረውን ''የጣና በለስ'' ፕሮጀክት ለእርድ ቢያቀርበውም ቅሉ።

በአንድ በኩል ኢህአዲግ ''ግብፅ ልትዋጋ አትችልም'' ሲል በሌላ በኩል  ተቃዋሚዎች ''ኢህአዲግም ሆነ ግብፆች የውስጥ ችግራቸውን ለማስቀየር የሚጠቀሙበት ስልት ነው ሲሉ'' ስናደምጥ ይሄው የግብፅ ፉከራ አንድ ሳምንት ዘለቀ።ይህ ጉዳይ የሚያሳየው አንገብጋቢ በሆነ በሀገራችን ጉዳይም ኢቲቪ  ህዝብን እንደማያወያይ አንድምሁር ለመጠየቅም የቻለ ወይም የተፈቀደለት ልበለው ሪፖርተር ጋዜጣ  ብቻ መሆኑን ነው። እኛ በሀገራችን ጉዳይ በሀገር ቤት ሚድያ ለምንድነው እንድንወያይ የማይደረገው? ግብፆች ኢቲቪም  ሆነ አራት ኪሎ  ውስጥ አሉ እንዴ? ነው ወይስ ጅብ እግሬን ሲቆረጥም ''አመመኝ'' ማለት ያለብኝ ኢቲቪ ወይንም መንግስት ሲፈቅድልኝ ብቻ ነው?

ተቃዋሚዎችስ የግብፅ እና የአባይ ጉዳይ ለዘመናት የታወቀ ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ።ብዙ ጥራዝ የሚወጣቸው ፅሁፎች ቢሮዎቻቸውን አጣበውት ''ችግር የለውም ጉዳዩ መንግሥታቱ  ከውስጥ ለሚነሳባቸው ተቃውሞ አቅጣጫ  ማስቀየርያ ነው'' እያሉ ከሚነግሩን ጉዳዩን እንዴት እንደሚያዩት፣ ለሀገር ያለውን አደጋ፣ሕዝብ ምን ማድረግ እንዳለበት ከእነመፍትሄው ማቅረብ ይገባቸዋል። ለግንቦት 20 በዓል አስመልክተው የተቃውሞ መግለጫ የሚያወጡ የተቃዋሚ ድርጅቶች እንዴት ይህን ትልቅ አካባቢያዊ ፣ሃገራዊ እና አለማቀፋዊ  ጉዳይ ላይ  ለሕዝቡ ያልተደናበረ አቅጣጫ አመላካች ሃሳብ መስጠት ያቅታቸዋል? እኔ በግሌ ይህ ጉዳይ  በጣም የሚያም  እንደሆነ ይሰማኛል።የብዙ ነገሮችም አመላካችም ነው።እንደምንኖርበት ጅኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ ከእዚህ በዘለለ ብዙ ችግሮች ወደፊት ሊገጥሙን ይችላሉ። የምኖርበት አለም ተለዋዋጭ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በእራሱ ፈጣን ግን ትክክለኛ ውሳኔ  ከፖለቲካ ድርጅት የሚጠበቅ ነው።የመፍትሄ ሀሳቦችም በእዚሁ ፍጥነት መሰጠት ይገባቸዋል።

የአባይ ጉዳይም ምንም አይነት ውስብስብ ገፅታ ቢሰጠውም ሕዝብ ግን የኢህአዲግ መንግስት ከህዝብ ጋር የተራራቀበትን ጉዳይ ሁሉ ከጥገናዊ ለውጥ በዘለለ መሰረታዊ ለውጥ አድርጎ ያለፈ ስህተትን የሚያርምበት የመጨረሻውን  መጨረሻ ዕድልን ሊጠቀምበት ይገባል እያለ ነው።ተቃዋሚዎችም 'ሰላሳ ትንንሽ ከመሆን አንድ ትልቅ መሆን' ከእዚህ ባለፈም የግብፅን ጉዳይ በተመለከተ ቢያንስ የመፍትሄ የሚሆን ሃሳብ  ማመንጨት እና ሕዝብ ሊይዘው የሚገባውንም አቅጣጫ ማመላከት ያላቸው ብቸኛ መንገድ ይመስለኛል።

እርግጥ ነው የግብፁ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሞሪስ ተቃዋሚዎችን ሰብስበው ሲነጋገሩ ኢህአዲግ ግን ገና አፉ ሲተሳሰር መታየቱ ከውስጡ ትክክለኛ ጊዜ ላይ አስፈላጊ መፍትሄ መስጠት በማይችሉ አመራር መሞላቱን ያሳያል።በግትርነት የተመራ ሀገር የለም። ህዝብንም ሀገርንም ይዞ ለመጥፋት ካልታሰበ በቀር። ችግሩ ገፍቶ ሲመጣ ሕዝብ እግር ስር ወድቆ መማፀን ላይቀር ዛሬ ከመረጃም ከመፍትሄም እርቆ መቀመጥ ለመንግሥትም ለሀገራችንም  አያዋጣም። 

ዝምታው ይሰበር።ብሔራዊ ሉአላዊነታችን  አደጋ ላይ የሚወድቅባቸው ብዙ እንቅፋቶች ተዘርግተው ይታያሉ። እነኝህ እንቅፋቶች ሊ ነቀሱ የሚችሉት ወሳኝ በሆነ ለውጥ ነው።የግድቡ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ በተለያዩ ሃገራት የገጠመው ተቃውሞ በግብፃውያን አይደለም። በኢትዮጵያውያን ነው። ኢትዮጵያውያን የሚጠይቁት ጥያቄዎች ደግም ይታወቃሉ።የሚገርመው ነገር ኢህአዲግ  ይህን ፅሁፍ በፃፍኩበት ቀን (ግብፅ ያዙኝ ልቀቁኝ በምትልበት ቀን) በካናዳዋ ከተማ ካልጋሪ  ላይ በተመሳሳይ መንገድ የገቢ ማሰባሰብያ መርሃግብር  ተሞክሮ መክሸፉ እየተነገረ ነው።መንግስት ''የኔ'' የሚላቸው ሰዎችን በእየ ሆቴሉ እየሰበሰበ የተቀረው የእንጀራ ልጅ ይመስል እየተገፋ በሚዋጣ ገንዘብ አይሰራም።ሁሉም ከልብ በመነጨ ስሜት ሊሳተፍበት ይገባል።ይህንን ለማድረግ ደግሞ መንግስት የተጠየቀውን ''ከድብብቆሽ ለውጥ'' በዘለለ መመለስ ሲችል ነው። ግድቡ በመንግስት ዘንድ  ከልብ ከታሰበበት ለምን ቢያንስ በሕዝብ የተነሱት ጥያቄዎች አይመለሱም? ለምን ነገ የጦርነት ድግሱ በር ላይ ሲደርስ  እግሩ ስር ወድቆ መንግስት አድነኝ ብሎ የሚማፀነውን ሕዝብ ጥያቄ ከወዲሁ መፍትሄ አይሰጠውም?
 
ጦርነት የለም የሚለው ጭፍን ድምዳሜ ለመድረስ ድፍረት የለኝም።ግብፅን ቢያንስ ኢትዮጵያን እንድታዳክም በሞራልም ሆነ በማተርያል የሚደግፉ ጠላቶች እንዳሉን ለማወቅ ብዙ መመራመር አይጠበቅም። አልጀዚራ ግብፅ ውስጥ የነበረውን የኢትዮጵያውያንን በተባበሩት መንግሥታት በር ላይ ያደረጉትን ሰልፍ እንዴት አድርጎ ሐረጋት መዞ ዜና እንደሰራበት ከተረዳን  ግብፅ አንዳንድ የአፍሪካ ቀንድን ለመቆጣጠር የዘመናት ሕልም የነበራቸውን  የመካከለኛ ምስራቅ ሃገራትን ማሰለፍ እንደምትችል ፍንጭ ይሰጠናል።

የአባይ ጉዳይ የዘመናት ቁስል ነው። ቀላል ነው ተብሎ እንደሚነገረው አይደለም።መንግሥታቱ የውስጥ ቅራኔዎችን ለማስታገስ ብለው ነው ብለን የምንዘብትበትም ጉዳይ አይደለም።ቢያንስ ጉዳዩ ዛሬ ባይሆን ነገም የማይለቀን ጉዳይ ነው።የዛሬው ትውልድ ውሳኔ የነገውም ዕድል ወይንም ፈተና መሆኑ አይቀርም።ዝምታ ግን ውርስ የለውም።ዝምታ መጨረሻው መፍትሄ ያልሆነ ግን መፍትሄ መሰል ነገር መወርወር ብቻ ይሆናል።ይህ ደግሞ በአሁኑ ትውልድ ላይ ብቻ ሳይሆን በመጭውም ትውልድ ላይ ለመፍረድ መደፋፈር ይሆናል።

አበቃሁ 
ጌታቸው 
ኦስሎ

1 comment:

Anonymous said...

grum eyta berta

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...