ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, June 6, 2013

ከፍልጥ ፈሊጥ ይቅደም! የግብፅ እና የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ (የጉዳያችን ጡመራ ማስታወሻ)

(የግብፅ ፕሬዝዳንት ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር ያደረጉት ሚስጥራዊ የተባለ ግን  በቀጥታ በቴሌቭዥን  ይተላለፍ የነበረ ቪድዮ ከፅሁፉ መጨረሻ ይመልከቱ) 

የግብፁ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሞርሲ ''የሳላፍስት ኑር'' ፓርቲ መሪ ዮንስ ማክሆን፣የሊበራል ፖሊቲካ ኮመንታተር አምር ሃምዛዊ  ያሳተፈ  ስብሰባ በኢትዮጵያ አባይ ግድብ ዙርያ ባለፈው ሰኞ(26/05/2005 ዓም) ስብሰባ አድርገው ነበር።በስብሰባው ላይ የብሔራዊ ሳልቨሽን ግንባር በፕሬዝዳንቱን ስብሰባ እንደማይገኝ የገለፀው ስብሰባው ግልፅነት እና ብዙም ውጤት የማይጠብቅበት መሆኑን በመግለፅ ነበር።


በሌላ በኩል የግብፅ ''የሙስሊም ወንድማማማቾች ነፃነት እና ፍትህ ፓርቲ'' መሪ ሞሐመድ  ኤልካታንቴ  ግንቦት 28፣2005ዓም ለአረብኛው ''አልሃራም'' ጋዜጣ እንደተናገሩት ''የግብፅን ሕዝብ ሳናማክር ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ከኢትዮጵያ ጋር አንገባም'' ካሉ በኃላ ቀጥላ ግብፅ ስለምታደርገው ጉዳይ ሲናገሩ '' በመጀመርያ  የዲፕሎማሲ ጥረት እናደርጋለን ይህ ካልተሳካ አለምአቀፍ ገልጋዮች ጉዳዩን እንድያዩት እናደርጋለን በመቀጠል ብዙ አማራጮች አሉን ይህም አካባብያዊ ድርጅቶች እንደ አረብ ሊግ አለም አቀፍ ድርጅቶች እንደ የተባበሩት መንግሥታት ያሉት በጉዳዩ እንዲገቡ እንጋብዛለን'' በማለት ገልፀዋል።

ግብፅ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ኢትዮጵያን ያገለለ ሱዳን እና ግብፅን ብቻ የሚጠቅመውን (በግብፅ እና ሱዳን ብቻ የተፈፀመውን) የ 1959 እ.አ.ቆጣጠር  ውል   እንዲከበርላት ለዘመናት ስትታትር ተስተውላለች።ሆኖም ግን ውሉን ኢትዮጵያ በሶስቱም መንግሥታት በቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ፣በደርግ እና በአሁኑ መንግስት ተቀባይነት አላገኘም። የአባይ ወንዝ ፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ  በተለይ የታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ተብለው በሚጠሩት ኢትዮጵያ፣ሩዋንዳ፣ቡሩንዲ፣ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፣ታንዛንያ፣ኬንያ፣ዑጋንዳ፣ደቡብ ሱዳን፣ሰሜን ሱዳን፣ግብፅን ያካተተ ውይይት ሲደረግ ቆይቶ በ 2010 እኤአ ቆጣጠር  ከግብፅ እና ከሱዳን በቀር ሌሎች ሃገራት በፊርማም ሆነ በአዎንታዊ መልኩ የተቀበሉት ውል ተረጋገጠ። ውሉም  ''የኢንተቤ ውል'' በመባል ይታወቃል።

የእዚህ አይነቱ የታችኛው ተፋሰስ ሃገራት መስማማት ግብፅ ከጉዳዩ ጋር ብዙ ለመጮህ ሳይመት ቀረ።ይህ በእንዲህ እያለ ኢትዮጵያ የአባይን ግድብ ስትጀምር ግብፅ ''የህዝብ ዲፕሎማስን'' ማጠናከር ላይ አተኮረች። ለእዚህም አይነተኛ ማስረጃ የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷን ማጠናከር፣ከግብፅ አብዮት በኃላ ከወጣቶች የተውጣጡ ልዑካን ኢትዮጵያን መጎብኘት ወዘተ ተጠቃሽ ነበሩ። ይህ እንግዲህ የግብፅ አብዮት ወዴት እንደሚሄድ ሳይታወቅ በነበረበት ደረጃ መሆኑ ነው።


የግብፅ አብዮት በውድም ይሁን በግድ በመደራጀቱ ብቻ ቀድሞ የተገኘው ''የእስላማዊ ወንድማማቾች ህብረት'' እጅ ሲወድቅ አለምአቀፉ ህብረተሰብም ሆነ የግብፅ ሊበራል አሰሳሰብ ያላቸው ወገኖች በግብፅ ጉዳይ ስጋት ላይ ወደቁ።በተለይ ''የእስላማዊ ወንድማማቾች ህብረት'' በፅንፈኛ አመለካከቱ ብቻ ሳይሆን የግብፁን ፕሬዝዳንት ሁስነ ሙባረክን አዲስ አበባ ላይ ለአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ከቦሌ አየርማረፍያ ወደ ቤተመንግስት ሲሄዱ ለመግደል ሙከራ ያደረገ መሆኑ ስለሚታወቅ የሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ያሰጋቸው ቢኖሩ አይፈረድባችውም። በ አሜሪካ ዩንቨርሲቲ የምህንድስና ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት የእስላማዊ ወንድማማቾች ህብረት እጩ እና የአሁኑ የግብፅ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሞሪስ ለአሜሪካም ሆነ ለእስራኤል እንደ ሙባረክ የማይመቹ መሆናቸውን ለመተንበይ ብዙ ሊቅ መሆን የማይይቅ ሆነ።

በእዚህ ሁሉ ሁኔታ ነው እንግዲህ የአባይ ግድብ በኢትዮጵያ የተጀመረው እና አሁን  21% የተሰራ መሆኑ የተነገረው። እዚህ ላይ የሰሞኑ የግብፆች ግርግር ለምን አዲስ ሆነ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። መልሱ የግብፆችን ልማድ እንዳለ ትተን  እኛም ዲፕሎማስያዊ ጥበብ ያነሰን መሆኑን ማንሳት አንዱ ምላሽ ሊሆን ይችላል ። የማይለቀን ''የካድሬ ምክር መስማት'' ኢትዮጵያን መጉዳቱን ቀጥሏል።ግድቡ ስራውን እየቀጠለ ሳለ ግንቦት 20ን ጠብቆ ውሃውን መንገድ አስቀየርኩት ማለት ይህንንም በቴሌቭዥን በቀጥታ ማስተላለፍ የነበረው ጥቅም አይታየኝም።ለግብፁ ፕሬዝዳንት ግን ህዝባቸውን ለማስደንበር ተጠቅመውበታል። ''የኢንተቤን ውል'' ዙርያ ከመከራከር ይልቅ አዲስ ድንጋፄ ፈጥረው ግብፅ በቶሎ ግድቡን እንድታስቆም ይሻሉ። ኢትዮጵያ ይህንን የግንቦት 20 ስነ-ስዓት  የተወሰኑ ካድሬዎች ከኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች ጋር ሳይወያዩ የሰሩት ድርጅታዊ ሥራ ይመስላል።በሙያዊ ጉዳዮች መግባት የካድሬዎች ሥራ ባይሆን እና ዲፕሎማውን ለባለሙያው ተውልን ባማረ ነበር።በእውቀት ላይ ያልተመሰረተ ''ብሔራዊ ጀግና'' ለመባል ብቻ የሚሰሩ የካድሬ ፕሮፓጋንዳ መሰል ችግሮች አንዳንዴ የሚያስከፍሉት ዋጋ የትየለሌ ስለሚሆን ከፍልጥ ፈልጥ የሚያስቀድሙት ባለሙያዎች ቢደመጡ ለሀገራችን የሚበጅ ብቸኛ መንገድ ነው።

ግብፅ ለዘመናት የኖረ ጭፍን ሃሳቧን ታቆማለች ማለት አይቻልም።የእኛ የቤታችን ሥራ ግን አለ። በግድቡ ሂደት ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በበለጠ የሚሳተፍበትን  መልክ ማስያዝ እና ግልፅነትን የተላበሰ ስራውን ከካድርያዊ አሰራር መለየት እና ሁሉንም በሚያባብል መልክ ማቅረብ አስፈላጊ ነው።ስለአባይ ግድብ ገንዘብ መሰብሰብ የሚገባው አምባሳደር ሳይሆን ሕዝብ ያውም ተራው ሕዝብ ነው።የእዚህን ጊዜ ነው የእኔነት ስሜት የሚዳብረው። ፖለቲካን ከልማት ሥራ መለየት (ምንም ተያያዥነት ቢኖራቸውም) እና ሕዝብ ካለአንዳች ተፅኖ እንዲሰራው ማድረግ ተገቢ ነው። ከፍልጥ ፈልጥ ቀደመ ማለትም ይህ ነው። የሆነው ቢሆን ግን ግብፅ እስከ አራት ኪሎ ድረስ ገብታ እንድትፈተፍት የሚፈቅድላት ኢትዮጵያዊ አይኖርም።የቤታችንን ጉዳይ ለእኛ ተዉት -ግብፆች እና አጋሮቻችሁ ማለት  ኢትዮጵያዊነት ነው።

አበቃሁ 
ጌታቸው 
ኦስሎ 






ጉዳያችን GUDAYACHNgetachewb221@gmail.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...