Monday, January 13, 2020

ጉዳያችንን በቀላሉ በቴሌግራም ይቀላቀሉ።

በርካታ አጫጭር ዜናዎች፣ማስታወቂያዎች በኖርዌይ፣ስቃንዲንቭያ፣በአገር ቤት እና በሌላው ዓለም የተከናወኑ ጉዳዮች ያገኛሉ።
Add Gudayachn on Telegram.

ይህንን ይጫኑ = t.me/gudayachn 

ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Saturday, January 11, 2020

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በኤኤንሲ 108ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ በደቡብ አፍሪካ ያደረጉት ንግግር Ethiopian Prime Minister Abiy Ahmed's speech on 108th anniversary of African National Congress (ANC)

 January 11/2020  
Video = South African Broadcasting Corporation (SABC) News


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

በኢትዮጵያ በደንቢ ዶሎና ጋምቤላ መሃል የታገቱት 13 ሴት እና 4 ወንድ የደንቢ ዶሎ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ጉዳይ ብሔራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትኩረት ተነፍጎታል።


ጉዳያችን /Gudayachn
ጥር 2/2012 ዓም (ጃንዋሪ 11/2020 ዓም) 

  • በምዕራብ ወለጋ፣ መንግስት ከሸማቂዎች  ጋር ግልጥ ጦርነት ላይ ነው። መንግስት በእዚሁ አካባቢ በሚያደርገው ሽፍቶችን የማጥራት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።በቅርቡ ሁሉም ነገር ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ይመለሳል። ለእዚህም በሽፍቶቹ የተጎዳው ሕዝብ ከፍተኛ ትብብር እያደረገልን ነው - አቶ ታዬ ደንዳበኦሮምያ የብልፅግና ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ

ከሳምንታት በፊት በምዕራብ ኢትዮጵያ በኦሮምያ ክልል የምትገኘው የደንቢ ዶሎ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች በዩንቨርስቲው በተነሳ ግጭት ሳቢያ ተማሪው በራሱ ወደ ትውልድ ቀዬው ለመሄድ ሲነሳ የተወሰኑ የዓማራ ክልል ተማሪዎች ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ በጋምቤላ በኩል አድርገው ለመምጣት በትራንስፖርት ተሳፍረው ጉዞ ይጀምራሉ።ሆኖም ያሰቡት ሳይደርሱ ደምቢ ዶሎ እና ጋምቤላ መካከል 'ሱድ' የምትባል ቦታ ሲደርሱ ጎረምሶች መኪናውን አስቁመው 18 ተማሪዎችን ማለትም 14 ሴቶች እና 4 ወንዶችን አግተው ወደ ጫካ ይገባሉ።ከእነኝህ ውስጥ ተማሪ አስምራ ሹሜ የተባለችው ወጣት በድንገት አምልጣ በብዙ ፈተና እና መከራ በአሁኑ ጊዜ አዲስ ዘመን ከተማ ከቤተሰቦቿ ጋር ተቀላቅላለች።

ተማሪ አስምራ ሹሜ ለቢቢሲ በሰጠችው ቃል እንዲህ ብላለች -

''አካባቢው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ በመሆኑ በእርሱ ውስጥ ይዘውን ገቡ። ይዘውን ሲሄዱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ከማየት ውጭ ለማስጣል የሞከረ አልነበረም።እየጮህን ነው ይዘውን የሄዱት። የጫካውን ግማሽ እንደተራመድን የተወሰኑት ሴቶች መራመድ አቃታቸውና ወደቁ። ታዲያ እነርሱን 'ተነሱ፤ አትነሱ' እያሉ ለማንሳት ሲሞክሩ ነበር እኔ ከአይናቸው የተሰወርኩት።በጫካው ውስጥ ለሁለት ቀናት ያህል ካደርኩ በኋላ፤ በሦስተኛው ቀን ወደ ዋናው የመኪና መስመር መውጣት ቻልኩ። ግራ ተጋባሁ፤ ስልኬን ስለወሰዱት ስልክ መደወል አልቻልኩም፤ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር።እንደምንም ብዬ ወደ መስመር ስወጣ አንድ አማርኛ በትንሹም ቢሆን መናገር የሚችሉ አባት አገኘሁ። እርሳቸው እንዳዩኝ 'የእኔስ ልጆች እንዲህ አይደል የሚሆኑት' ብለው በማዘን ኮታቸውን አለበሱኝ።
'ከታየሁ እኔም እገደላለሁ' ብለው ደብቀው አስቀመጡኝ። 'የት ነው መሄድ የምትፈልጊው' አሉኝ። 'ደምቢ ዶሎ ለፌደራል ፖሊሶች ስጡኝ' አልኳቸው። ከዚያም መኪና ለምነው አሳፍረው ላኩኝ። መረጃውንም ለፌደራል ፖሊሶቹ ተናግሬያለሁ። ፌደራል ፖሊሶቹ 'ቦታው እንኳን ለተማሪ ለወታደርም አስጊ ነው፤ እንከታታላለን' አሉኝ።
ከታገቱት መካከል አንዷ ጓደኛዬ መጀመሪያ አካባቢ ስልክ እየሰጧት ትደውልልኝ ነበር። ለማውራት ብዙም ነፃነት ባይኖራትም 'በጣም እያሰቃዩን ነው፤ ምግብም ሲያሻቸው ይሰጡናል፤ ሲፈልጉ ደግሞ ይከልክሉናል' ስትል ነግራኛለች። የምትደውልበትን ስልክ 'የእነርሱ ነው ያዥው' ብላኝ ነበር። ከዛን ቀን በኋላ ግን አይሰራም፤ እነርሱም ደውለው አያውቁም፤ እኛም አግኝተናቸው አናውቅም።ይመለከታቸዋል ለተባሉ አካላት፤ ለአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት፣ ለፀጥታ እና ደህንነት መረጃውን ሰጥቻለሁ፤ ጠይቄያለሁ። 'እንከታተላለን' ነው ያሉኝ።ከዚያ መምጣቴን የሚያውቁ የተማሪዎቹ ወላጆችም ያለሁበት ድረስ እየመጡ ያለቅሳሉ፤ እኔ ግን 'መንግሥት ይዟቸዋል፤ አሁን ይመጣሉ' እያልኩ ከማረጋጋት ውጭ የማደርገው ጠፍቶኛል።"
ቢቢሲ የታገቱት ተማሪዎች ወላጆችን አነጋግሮ እንደገለጠው የአንዷ ወላጅ ልጃቸው ከታገተች ከሰሙ ከአራት ሳምንታት በላይ መሆኑን እንደገልጡ ዘግቧል።ይህ በእንዲህ እያለ ጉዳዩን አስመልክቶ የኦሮምያ የፀጥታ ባለስልጣናት በቂ ምላሽ እንዳልሰጡ ነው የተሰማው። ከአንዲት ተማሪ የስልክ ንግግር በመነሳት የአጋቾቹ ዋና ፍላጎት አስመልክቶ ቢቢሲ እንደዘገበው አጋቾቹ  ሕዝብ ልጆቻችንን ብሎ መንግስትን ሲያስጨንቅ መንግስት ከእኛ ጋር እንዲደራደር ያስገድደዋል የሚል ስሌት እንዳላቸው ይጠቅሳል።ጉዳዩ ግን ብሄራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት ይሻል።የእገታ ጉዳይ የሽብር ተግባር ነው።ሽብር ደግሞ የአገር ውስጥ  ሳይሆን አካባቢያዊም፣ዓለም አቀፋዊም የጋራ ችግር ነው። 
በሌላ በኩል በምዕራብ ወለጋ፣ መንግስት ሕዝቡን ሲዘርፉ እና ሲያሰቃዩ ከነበሩ  ሸማቂዎች ጋር ጋር ግልጥ ጦርነት ላይ እንዳለ በኦሮምያ የብልፅግና ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ አቶ ታዬ ደንዳ ለቪኦኤ ትናንት ጥር 1/2012 ዓም  ገልጠዋል።እንደ እርሳቸው ገለጣ በምዕራብ ወለጋ መንግስት በሸማቂዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ ያለው ሁሉም የሰላማዊ መንገድ ከተሞከረ በኃላ መሆኑን ካብራሩ በኃላ እስከዛሬ ሰላማዊውን ሕዝብ ሲጎዱ ምንም ያላለ ዛሬ በሽፍታ ላይ እርምጃ ሲወሰድ የሚናገር አንዳንድ ማኅበራዊ ሚድያ ዘገባዎች  ትክክል አይደሉም ብለዋል።አቶ ታዬ ደንዳ በእዚሁ ማብራርያ መንግስት በእዚሁ አካባቢ በሚያደርገው ሽፍቶችን የማጥራት ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለና በቅርቡ ሁሉም ነገር  ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ይመለሳል ለእዚህም በሽፍቶቹ የተጎዳው ሕዝብ ከፍተኛ ትብብር እያደረገልን ነው ብለዋል። 
ዘግይቶ የደረሰን ዜና 
ታግተው የነበሩ 21 የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መለቀቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት አስታወቀ
********************
በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ጫካ ውስጥ ታግተው መቆየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለኢቲቪ ተናግረዋል።
ታግተው ከነበሩ ተማሪዎች ውስጥ 13 ሴትና 8 ወንድ በድምሩ 21 ተማሪዎች በሰላማዊ ሁኔታ መለቀቃቸውን አቶ ንጉሱ አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም ቀሪ 6 ተማሪዎች በእገታ ላይ መሆናቸውን በአካባቢው የተሰማራው የፀጥታ ኃይል መረጃ መስጠቱን ተናግረዋል ።
ምንጭ = የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን 


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Friday, January 3, 2020

ኢቢሲ ከብርሃን ባንክ ጋር ፈጠረ የተባለው ስምምነት መንግስትን የሚያሳማ እና በባንኮች መካከል ያለውን ጤናማ ውድድር የሚያበላሽ እንግዳ ስምምነት ነው።

የኢትዮጵያ ራድዮ እና ቴሌቭዥን ዋና መስርያ ቤት 

ጉዳያችን / Gudayachn
ታህሳስ 24/2012 ዓም (ጃንዋሪ 3/2020 ዓም)
===============
ዛሬ ዓርብ ታሕሳስ 24/2012 ዓም የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዜና ላይ ኢቢሲ (የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን) ከብርሃን  ባንክ ጋር  ስምምነት ፈጠሩ የሚለው ዜና ሲጀምር እንዲህ በማለት ይጀምራል -
'' የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና ብርሃን ባንክ የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር አብረው ሲሰሩ ቆይተዋል'' ካለ በኃላ ዜናው በመቀጠል ''የጠበቀ ግንኙነቱን ለማጠናከር የመግባብያ ስምምነት ተፈራርመዋል'' ይላል ዜናው። ዜናው ላይ የብርሃን ባንክ ባለስልጣናት እና የኢቢሲ ኃላፊዎች ሳቅ በሳቅ ሆነው ስለምን እንደተዋዋሉ ሳይነግሩን ተስማሙ የሚለው ደጋግሞ ሲነገር በዜናው ላይ ይታያል።

የኢቢሲ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር  ንጉሴ  ምትኩ በእዚሁ በስምምነቱ  ዜና  ላይ ብርሃን ባንክን ሲገልጡ ''ባጭር ጊዜ ተመስርቶ ስኬታማ እንደሆነ እኔም በነበረኝ ምልከታ ምስክር ለመሆን ችያለሁ ብዬ አስባለሁ'' ብለው ሲናገሩ  ዜናው ያሳያል።በሌላ በኩል የብርሃን ባንክ ማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም መስፍን ''ከኢቢሲ ጋር ያደረግነው ስምምነት የብርሃን ባንክን ቪዝብሊቲ ከፍ የሚያደርግ ነው'' ብለዋል።

ስህተት 1 
ነፃ የውድድር ሜዳ ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያሳያል 

የባንክ ኢንዱስትሪው በኢትዮያ ከአስራ አምስት ያላነሱ ባንኮች የያዘ እና ውድድር ላይ የሚገኝ ነው።የግሎቹ ባንኮች እርስ በርስ ከፍተኛ ውድድር ላይ ናቸው።ለመንግስትም ተገቢውን ግብር ያስገባሉ።መንግስት ደግሞ በተቀበለው ግብር መልሶ የማኅበራዊ እና የመሰረተ ልማት አገልግሎት ይሰጣቸዋል።መንግስት ለሁሉም ባንኮች እኩል አገልግሎት ሊሰጥ ነው የሚገባው። መንግስት ማለት አንዱ እጁ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ነው። ኢቢሲ በተናጥል ከአንድ የግል ባንክ ጋር የዕድሜ ልክ የመስለ ስምምነት አደረገ ተብሎ መቅርቡ መንግስት በባንኮች ውድድር ውስጥ አንዱን ደግፎ የመቆም ያህል ያስቆጥረዋል።በዛሬው የስምምነት ዜና መግቢያ ላይ ኢቲቪ የብርሃን ባንክ እና ኢቲቪ አብረው ሲሰሩ ቆይተዋል የሚል ዓረፍተ ነገር ተጠቅሟል።ምንድነው አብረው ሲሰሩ የቆዩት? በምን መስፈርት? ድንገት ተዋደዱ? የህዝብ ሀብት የሆነ ድርጅት እንደፈለገ ከፈለገው የግል ድርጅት ያውም ከፍተኛ ውድድር በሚታይበት ቁልፉ የምጣኔ ሀብት አንቀሳቃሽ ከሆነ ከአንዱ ተወዳዳሪ ባንክ ጋር  በተናጥል አብሬ እየሰራሁ ነበር ሲል ምን ማለቱ ነው?ይህን እኔ አይደለሁም የምጠይቀው የውድድር ሕጉ እራሱ የሚጠይቀው ሞራላዊ ጥያቄ ነው።


ስህተት 2 
የመንግስት ሚድያ ሥራ አስኪያጅ ከተወዳዳሪ ባንኮች ውስጥ የሚያደንቀውና የማያደንቀውን ባንክ ሚድያውን ወክሎ መናገር የለበትም 

መንግስታዊ ድርጅቶች  ያውም ቁልፍ የሆነው ሁሉንም እኩል እንዲያገለግል የሚጠበቅበት የመንግስት ልሳን ኢቢሲ ሥራ አስኪያጅ ስለ አንዱ የግል ባንክ በምልከታ በሚል ከግል ባንኮች ውስጥ አንዱን ነጥለው ከላይ እንደተጠቀሰው ''ስኬታማ'' ነው የሚል ቃል መናገር የለባቸውም።እዚህ ላይ የብርሃን ባንክ ስኬታማ ነው አይደለም የሚል ክርክር እየገባሁ አይደለም።ኢቢሲ ማለት ያለበት በዘገባው ሚዛናዊ ዘገባ አቅርቦ ወይንም የባንኩ ባለስልጣን ያሉትን ጠቅሶ ማለት ይችላል።በምልከታ ግን ስኬታማ ነው ስለዚህ ስምምነት አደረግን ማለት ተገቢ አይደለም።በሁሉም ባንኮች ግብር የሚተዳዳር   ኢቢሲ አንዱን ነጥሎ በምልከታ ስኬታማ እንዴት ሊለው ይችላል? ይህ በራሱ የመንግስት ሚድያን ተጠቅሞ  ያልተከፈለ ማስታወቂያ ነው።የግል ስሜት እና ግንኙነት ሌላ ነገር ነው።የህዝብ ንብረትን እኩል ለሁሉም ተወዳዳሪ ባንኮች  ክፍት ማድረግ ሌላ ነገር ነው።


ስህተት 3
የመንግስት ሚድያ የአንዱ ባንክ የመታየት አቅም ከሌላው ጎልቶ እንዲወጣ የመስራት መብት የለውም 

ከዜናው ለመረዳት እንደሚቻለው ብርሃን ባንክ በእዚህ ስምምነት ተጠቅሞ እንደ የማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጁ ገለጣ ባንኩ የበለጠ ''ቪዚብልቲውን'' (ጎልቶ የመታየት አቅሙን) ከፍ እንደሚያደርግ ተገልጧል።በመጀመርያ ደረጃ  ኢቢሲ በምን መስፈርት ተጠቅሞ ነው  ከሌሎች ባንኮች በተለየ ከብርሃን ጋር የተዋዋለው? በሥራ አስኪያጁ ምልከታ? ወይንስ በቦርድ አባላቱ ውሳኔ? ግልጥ አይደለም።መንግስታዊ የመገናኛ አውታር ያውም በመንግስታዊነቱም ሆነ በግዙፍነቱ ትልቁ ኢቢሲ ስምምነት ከማድረጉ በፊት ሌሎች ባንኮችን አወዳድሯል? ወይንስ ጨረታ አውጥቷል? ደግሞስ የሕዝብ ንብረት የሆነው  ኢቢሲ የህዝብ ሀብት የሆኑት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እንዴት ይህንን ውል አላደረገም።ምናልባት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር  ይህንን ስምምነት ቢያደርግ መንግስታዊ ወይንም የህዝብ ሀብት ከመሆኑ አንፃር ይህ ጥያቄ አይነሳም ነበር። ብርሃን ባንክም ከግል ሚድያ ጋር ይህንን ስምምነት ቢያደርግ ጥያቄው አይነሳም።ምናልባት የግል ሚድያው ሥራ አስኪያጅ  ብርሃን ባንክን በምልከታዬ (ኦዲት ሪፖርቱን ሳይጠቅሱ) ስኬታማ ነው እያሉ ቢናገሩ ኖሮ ቅሬታ አያስነሳም ነበር። የህዝብ ሀብት ኢቢሲ የግል ስምምነት በሚመስል መልኩ ከተወዳዳሪ ባንኮች አንዱን ''ቪዚብልቲው'' ከፍ እንዲል ሊሰራ ነው የሚል ቀልድ መሰል  ንግግር  ባልሰማን ነበር።

ለማጠቃለል 

ከላይ ለማስረዳት እንደተሞክረው የባንኮች የውድድር ሜዳ ላይ መንግስታዊ ሚድያ ያውም ግዙፉ ሚድያ በምንም መስፈርት አንዱን ባንክ ነጥሎ አብሬው እሮጣለሁ ተወዳዳሪዎቹን እንዲቀድም እረዳዋለሁ መሰል ሥራ ውስጥ እንዲገባ የንግድ ሕጉም፣የመንግስት አሰራርም ሆነ ሞራላዊ ሁኔታዎች አይፈቅዱለትም።ቢያንስ ይህ ስምምነት ሲደረግ ኢቢሲ የሄደበት ለሁሉም ባንኮችም ሆነ ሚድያ ግልጥ የሆነ ሂደት ካለ ያሳይ።ከእዚህ ውጪ ግን ምንም አይነት አሰራር ያለ አይመስለኝም። በውድድር ዓለም ውስጥ የመንግስት ድርጅቶች በተለይ ቁልፍ የሆኑት ለምሳሌ መንግስታዊ ሚድያ (ሁሉንም ኢትዮጵያ የመሸፈን አቅም ስላላቸው)፣ የውሃ እና ፍሳሽ፣መብራት፣ቴሌ የመሳሰሉት በውድድር ዓለም ባሉ የግል ድርጅቶች ውስጥ ገብተው ካለምንም  ሕጋዊ ሂደት አንዱን እጅ ይዘው ከፍ ሊያደርጉ፣ሌላውን ደግሞ ችላ ሊሉ አይችሉም። እነኝህ መንግስታዊ አካላት ለሁሉም እኩል የማገልገል ግዴታ አለባቸው።ምክንያት - ከሁሉም በሚሰበሰብ ቀረጥ የሚተዳደሩ ናቸው እና መንግስትን ያሳሙታል።ይህንን ሁኔታ ከንግድ ሕጉ አንፃር እና ከመንግስታዊ ድርጅቶች መመርያ አንፃር ሌሎች አጣቅሰው ብዙ ሊሉበት እንደሚችል እገምታለሁ።


የመጨረሻው መጨረሻ ግን ለብዙ ዓመት በማኅበራዊ ሚድያ የጠየኩት EBC በእንግሊዝኛ ብቻ ሳይሆን በቴሌቭዥን ላይ ስፅፍ በአገሪቱ ፊደል ''ኢቢሲ'' ብሎ ይፃፍ የሚለውን ጥያቄ ለአንድ ሺኛ ጊዜ እጠይቃለሁ።ይህ ለመላው ዓለም የኢትዮጵያን መልክ የሚያሳይ ከልጆች ሳይቀር አዕምሮ የማይጠፋ ያደርገዋል።ፊደል እንደሌለን የእንግሊዝኛ ፊደል ብቻ ማድረግ ያለማወቅ ደረጃ ነው።በአማርኛ እያወሩ ኢቢሲ ብሎ አለመፃፍ ጤነኛ አስተሳሰብ አይደለም።አንድ ቀንም ይህ ጉዳይ የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻ የሚከፈትበት ጉዳይ መሆን አለበት።




ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Wednesday, January 1, 2020

መንግስት በግልፅ ተነጋግሮ ካላረመው ኢትዮጵያ ከባድ የፀጥታ አደጋ ያሰጋታል

ጉዳያችን GUDAYACHN   
ታሕሳስ 22/2012 ዓም (ጃንዋሪ 1/2019 ዓም)

'ሳይቃጠል በቅጠል' የምትለው የኢትዮጵያውያን አባባል ትልቅ ትምህርት አላት።ቅጠል እራሱ ተቀጣጣይ ነው።እሳት ሲቀጣጠል በቅጠል ላጥፋው ብትል አትችልም።ምክንያቱም እሳቱ እራሱ ሊያጠፋው የመጣውን ቅጠል ይበላዋል።ሳይቃጠል ገና በትንሽ ጭስ ላይ እያለ ግን በቅጠል ብትመታው ያለው ፍንጥርጣሪ እሳት ተበታትኖ ይጠፋና ትልቅ የእሳት አደጋ ሳያስከትል እና ነፋስ እያግለበለበ ሳያቀጣጥለው የመጥፋት ዕድል አለው። 

የኢትዮጵያ ወቅታዊው ፖለቲካ በቅንነት ኢትዮጵያን ወደተሻለ መንገድ ለማሻገር የሚተጉ የመኖራቸውን ያህል የተለመደውን የሴራ ፖለቲካ እያውጠነጠኑ ያደፈጡ ኃይሎችም አሉ።የሴራ ፖለቲካው ደግሞ በራሱ በመንግስት የቢሮክራሲ መዋቅር ውስጥ የተተበተበ እና በጎሳ መር ድርጅቶች ላይ ሁሉ ማድራቱ ነው አደጋው።ስለሆነም በኢትዮጵያ ወሳኝ በሆኑ መንግስታዊ ድርጅቶች ላይ ሁሉ የቅርፅ እና የዓይነት መልክ እያመጣ ኢትዮጵያዊ ቃናውን እያሳጣው እንዳይሄድ እያንዳንዱን መዋቅር መልሶ መላልሶ መፈተሽ እና አላስኬድ ያለውን አሰራር እና ፖሊሲ ሁሉ መከለስ ያስፈልጋል።

አሁን ላለው የኢትዮጵያ በር ላይ የፀጥታ አደጋ ውስጥ የሚጠቀሰው አንዱ የክልሎች ልዩ ኃይል ጉዳይ ነው።አንዲት አገር አገር የሚያሰኛት እንደ አገር የጋራ ተቋማት ሲኖሯት ነው።በተለይ ቁልፍ የሆኑት መንግስታዊ  ተቋማት ለምሳሌ የጦር ኃይል እና የፀጥታ ኃይሉ በአገሪቱ ካሉት ክፍሎች ለአንዱ ባላዳላ መልክ ሁሉንም ባማከለ እና የገንዘብ ምንጩም በአገሪቱ የጋራ ሀብት የሚተዳደር ካልሆነ እጅግ አደገኛ ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሆነ አመላካች ነው።

በኢትዮጵያ ከ1967 ዓም ወዲህ ባሳለፍናቸው ሁለት የአምባገነን መንግሥታት ታሪክ ለአምባገነንነት ዋና ምሰሶ ሆነው ያገለገሉት በተለይ ለፖለቲካ ስልጣኑ ሶስቱ ምሰሶዎች ናቸው።እነርሱም የወታደራዊ፣ደህንነት እና የኢኮኖሚ አውታር ናቸው። ከእነኝህ ውስጥ የወታደራዊውን ጉዳይ ብንመለከት በደርግ ዘመን ከጎሳ የፀዳ ወታደራዊ ኃይል ቢኖረውም በውስጡ ግን የስልጣን ወንበሩን የሚያስጠብቁ ''ቅልብ ጦር'' የሚባል በኮ/ል መንግስቱ የሚታዘዙ አስፈሪ የሰራዊት ኃይል ነበሩ።ይህ ጦር ከሌላው የኢትዮጵያ ጦር የተለየ ሆኖ እንዲወጣ ሲደረግ ዋና ዓላማው የሚቃወሙትን ሁሉ በኃይል ለመስበር ነው። በዘመነ ህወሓት-ኢህአዴግም ''አግአዚ'' የሚባል ጦር ነበር።ይህ የጦር ኃይል ከቅልብ ጦር የሚለየው በአንድ ጎሳ የተፈረጀ እና እንደተባለውም ለይስሙላ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ አባላት ቢኖሩትም ከስያሜው ጀምሮ  እስከ ማዕከላዊ ማዘዣው ድረስ ከአንድ ጎሳ ጋር የተመደበ ይልቁንም ይህ ሰራዊት የሚሰራው የጭካኔ ሥራ ሁሉ ከጎሳው ተግባር ጋር እየተገናኘ የሄደበት ታሪክ የተስተናገደበት ሁኔታ ነበር።

የአሁኑ አስፈሪ ሁኔታ ምንድነው?

ያለፈ የታሪክ ስህተት ለአሁኑ አስተማሪ ነው።ደርግን የቅልብ ጦር ጭካኔ ስልጣኑን አልጠበቀለትም።ህወሓትም የአጋዚ ጦር አላዳናትም።የሁለቱም ጦር አባላት የት እንዳሉ አይታወቅም።ምናልባት የአጋዚ ጦር አሁንም አለ ይሆናል።ነገር ግን እያረጀ ከመሄድ እና ወደ የግል ህይወቱ ከመግባት በቀር የሚያመጣው ነገር የለም።ከእነኝህ ሁሉ ተምሮ ዛሬን ማስተካከል ተገቢ ነው። 

በኢትዮጵያ በክልሎች ያለው የልዩ ኃይል ብዛት፣የስልጠናው ዓይነት እና እየታጠቀ ያለው የጦር መሳርያ አይነት ሁሉ ስንመለከት እና በፍጥነት መታረም ካልቻለ ከደርግም ሆነ ከህወሓት የባሰ አደጋ ለኢትዮጵያ አያስከትልም ማለት ሞኝነት ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ሃሳብ የሚሰጡ ሰዎች አንዳንዴ የሚገርሙኝ ትልቁን አደጋ ላይ ሲጮሁ እና መንግስት እንዲታረም ሲጮሁ አለመታየታቸው ነው። በትንሹ ጉዳይ ደግሞ ከሚገባው በላይ አጋኖ በማቅረብ ለመጠላለፍያነት ሲደክሙበት ይታያሉ። ከእዚህ የክልሎች ኃይል እያፈረጠሙ መሄድ በላይ ለኢትዮጵያ ውስጣዊ የፀጥታ ችግር የከፋ ጉዳይ ምን አለ? 

በተለየ ሁኔታ በአሁኑ ሰዓት የክልል ልዩ ኃይል ጡንቻ ማፈርጠም በእየክልሉ እንደቀጠለ ነው።በቅርቡ  ካልተሳሳትኩ በሰላም ሚኒስቴር አቅራቢነት የተወካዮች ምክር ቤት የክልል ልዩ ኃይል ትጥቅ የሚፈቱበትን ሁኔታ ላይ መነጋገሩ ተነግሮ ነበር።ሆኖም ጉዳዩ መልሶ የት እንደደረሰ አልተሰማም። በትግራይ ቁጥሩ የማይታወቅ የክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አለ።በዓማራም በተመሳሳይ መልክ እንዲሁ ክልሉ በመንግስት ጦር ሳይሆን በልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ነው ፀጥታውን የሚያስከብረው።በኦሮምያም እንዲሁ የክልሉ ልዩ ኃይል አሁን በከፍተኛ በጀት እየተደጎመ የ28ኛ እና 29ኛ ዙር ሰልጣኞችን አሰልጥኖ ማስመረቁ ሰሞኑን ተነግሯል።

የክልል የጦር ኃይል በተመለከተ ሁሉም ክልል ወደራሱ የአገር መልክ እየሄደ ያለ ይመስል እንደ ቀዝቃዛው ጦርነት የስልጠና እሽቅድምድም ላይ ያለም ይመስላል። በመጀመርያ ደረጃ የክልል ልዩ ኃይል ስልጠና ከዋናው የኢትዮጵያ ጦር ኃይል የስልጠና እና የትጥቅ ደረጃ ጋር እንዲገዳደር ተደርጎ መሰልጠኑ ምን ዓይነት አገራዊ ርዕይ ነው? የክልል ልዩ ኃይል የስልጠና ዓይነቱ ጣርያ የት ላይ ይቆማል? ለምሳሌ ወደፊት ታንከኛ፣አየር ኃይል እያሉ ላለማሰልጠናቸው ምን ዋስትና አለ? ሰሞኑን በኦሮምያ የታየው የክልሉ ልዩ ኃይል ከኢትዮጵያ የምድር ጦር ኃይል እኩል የሰለጠነ እንደሆነ ከእንቅስቃሴው መመልከት ይቻላል።በተለያዩ አስተሳሰቦች በምትናጠው የኦሮምያ ክልል ውስጥ የብሔራዊ ጦሩ ሚና ምን ሊሆን ነው? ብሎ አለመጠየቅ ምን ዓይነት የፖለቲካ እብደት ነው? ቀድሞ ክልሎች ትንንሽ የፀጥታ ጉዳዮችን እንዲፈቱ ከበድ ያለ ሲያጋጥማቸው በቶሎ ማዕከላዊ መንግስት የፌድራል ጦር ኃይል እንዲልክ እንዲጠይቁ ተደርገው ነበር የተሰሩት።አሁን ግን የስልጠናው ገደብም ሆነ የሚይዙት የጦር መሳርያ አይነት መጠን የሚታወቅ አይመስልም። 

ሰሞኑን በተመረቁት የኦሮምያ ልዩ ኃይል ስልጠና ምረቃት ላይ በአዋሽ ቢሾለ በመገኘት የመረቁት የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሲናገሩ  "የልዩ ኃይሉ ተልዕኮዎች መካከል አንዱ የተገኘውን ድል ማስቀጠል ነው" ብለዋል።ምክትል ፕሬዝደንቱ በተጨማሪም የልዩ ኃይሉ ተልዕኮ የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ ከማስጠበቅ በተጨማሪ የኦሮሞ ህዝብ ጥቅም እና መብት ማረጋገጥ የተጣለበት ሃላፊነት ነው ብለዋል። ልዩ ኃይሉ የአንድ ብሔርን ጥቅም እና መብት ማስጠበቅ የተጣለበት ኃላፊነት የሚለው አባባል እንደአገር የማሰብ የጋራ ርዕይ አይደለም።ይሄው ሰራዊት ግን ነገ በአዲስ አበባ ውስጥ ግባ ሲባል ለአዲስ አበቤ መብት ሳይሆን ለጎሳው መብት ለማስከበር እንደሆነ አቶ ሽመልስ ዛሬ ላይ ቆመው በግልጥ እየነገሩን ነው። ይህ ሁኔታ ነው የጎሳ ግጭት የሚያመጣው።የእኔ የሚለው ሰራዊት ያጣ ሕዝብ ወደ ጎሳው ልዩ ኃይል እንዲያማትር ሊያደርገው ነው።መንግስት ማለት ሁሉን በእኩል የሚዳኝ እንጂ የአንዱ አባት የሌላው እንጀራ አባት ሊሆን አይገባም።

ባጠቃላይ ከእዚህ በፊት የኦሮምያ ልዩ ኃይል በሱማሌ ክልል ላይ፣የሱማሌ ልዩ ኃይል በኦሮምያ ክልል ላይ እንዲሁም የኦሮምያ ልዩ ኃይል በሰሜን ሸዋ የዓማራ አዋሳኝ ክልሎች ላይ ያደረሱት ግጭት እና የሰው ሕይወት መጥፋት ይታወቃል። ይህ የክልል ልዩ ኃይል የኢትዮጵያ መጪ ዘመን አደጋ ነው።መንግስት ቁልፍ ከሆኑ አካላት ውስጥ አንዱ የሆነውን የወታደራዊ እና የደህንነት  አካሉን በአግባቡ በማዕከላዊነት መያዝ ይገባዋል። ፌዴራሊዝም አሰራር አለው።ክልሎች የፀጥታ ኃይል ይኖራቸዋል ቢባል የምድር ጦር ያህል ሰራዊት ያሰለጥናሉ ማለት ፈፅሞ ሊሆን አይችልም። መጪው ምርጫ ስርዓት ሊይዝ የሚችለው ክልሎች ያላቸው የልዩ ኃይል በሙሉ ፈርሶ ወደ አንድ ብሔራዊ ዕዝ ሲገባ እና በክልሎች የሚኖረው የፀጥታ ኃይል በፖሊስ አደረጃጀች ደረጃ ከተቀመጠ ብቻ ነው።ይህ ካልሆነ እያንዳንዱ ክልል የልዩ ኃይሉን በምድር ጦር ደረጃ የማሰልጠን እሽቅድምድም ውስጥ የማይገባበት ምንም ሁኔታ የለም። ከሰሞኑ የኦሮምያ ልዩ ኃይል ስልጠና የተመለከቱ የሱማሌ፣የዓማራ፣የአዲሷ ሲዳማ፣ቤንሻንጉል ወዘተ ክልሎች ሁሉ የልዩ ኃይል ስልጠና በጀት መጨመር ላይ ይሮጣሉ።ይህ ደግሞ ልማቱን ያቀጭጫል።ነገሩ ሲገፋ ነገ የውጭ ኃይሎች በጎን በልማት ስም እየገቡ የአንዳንድ ክልሎች ልዩ ኃይል ስልጠና በጀት ማዕከላዊ መንግስት ባላወቀው መንገድ አይደጉምም ማለት አይቻልም።ክልሎች የወታደራዊ ኃይላቸው ጉልበት ሲፈረጥም ደግሞ የሌሎች ክልሎች ወሰን ጋር ግፍያ ውስጥ ይገባሉ። መዘዙ ብዙ ነው።እየተሄደ ያለው ሁሉ የማዕከላዊ መንግስትን አቅም እያደከሙ በግርግር የክልሎች ጉልበት እንዲጠነክር የሚያደርግ ሂደት ነው። ይህ ማለት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የማዕከላዊ ስልጣን እየተሸረሸረ በጎጥ ድርጅቶች የኢትዮጵያ መጪ ዕድል የመወሰን አደጋ አለው ማለት ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩም መንግስት ከልቡ ከምርጫው በፊት አንድ አይነት ወሳኝ እርምጃ መውሰድ አለበት።   

                                        በቅርቡ የተመረቀው የኦሮምያ ልዩ ኃይል በከፊል (ፎቶ =ፋና)
ጉዳያችን / Gudayachn
 www.gudayachn.com

The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church is in turmoil in Athens, Greece.

His Holiness Abune Mathias I, Patriarch of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church, met with Greece's Ambassador to Ethiopia, Antonios Sg...