በ ካርታ ጫወጣ ጎበዝ አደለሁም። ግን ጆከር የተባለች ካርታ መኖሯን አውቃለሁ።ጆከር ካርታ በ ሁሉም ቦታ ስለምትገባ በ ካርታ ጫወታ ጆከር የደረሰው ሰው የማሸነፍ እድል ስላለው ፊቱ በ ፈገግታ ይሞላል።
የ አትዮጵያ ና የ ኤርትራ ጉዳይን መሪዎቻችን የ ፖለቲካ መጫወቻ ''ጆከር'' ካርድ ካደረጉት ቆዩ። ፕሬዝዳንት ኢሳያስም ሆኑ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ይችን ''ጆከር'' የተባለችውን የ ካርታ ካርድ በየሀገራቸው ይጫወቱበታል። በስልጣን ላይ ለመቆየት ይችን የ ኢትዮጵያ ና ኤርትራ ካርድ ትመዘዛለች፣ትርገበግባለች፣ትውለበለባለች፣በ ንግግር ላይ ጣል ትደረጋለች፣አስፈላጊ ሲሆን ደሞ ወደ ፋይል ክፍል ትገባና ስትጠራ የ አራዳ ልጅ ''ከች በ ኮረኮንች'' አንደሚለው ''አንደገና ጆከር አንደገና'' ተብላ ትመዘዛለች።
የ ሃያአንደኛው ክፍለ ዘመን ልጆች አዲሱ አስተሳሰብ
በ ሃያኛው ክ/ዘመን አጋማሽ የተነሳ የ ኤርትራ ጉዳይ ይሄው እስከ ትናንትና ምሽት ድረስ ካርዱ እየተመዘዘ በሰው ሕይወት መቀለዱ ቀጥሏል። ይህን ችግር የፈጠረው ትውልድ ወደድንም ጠላንም እያለፈ ነው። በእናታቸው ከ እንደርታ (ትግራይ) የሚወለዱት ፕሬዝዳንት ኢሳያስም ሆኑ በ እናታቸው ከ ዓዲቇላ(ኤርትራ) የሚወለዱት ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ለምን የ ጆከሯን ካርታ በየጊዜው እየመዘዙ ሕዝቡን እንደምያሰቃዩት የሁሉም ሰው ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው ።
አንድ ነገር ግን መገንዘብ ይቻላል ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ህዝቡ የ ፖለቲከኞችን ልፈፋ ወደጎን ትቶ ነገሮችን የምያጠናበት ጊዜ ላይ መድረሱን ማንም ልብ ያለው ያለ አይመስልም። ኢሳያስም ሆኑ መለስ ካለ አንዳች ''ሃይ'' ባይ በ ፈለጉት መንገድ ላለፉት ሃያ አመታት የመሩት ሀገር ዛሬ ላይ ሲመለከቱት ብዙ ታሪካዊ ስህተቶች መኖራቸውን አፋቸው ባይናገረው ህሊናቸው ይፈርደዋል።ሁለቱም ባለፉት ሃያ አመታት በታሪክ ታይቶ ያልታወቀ ስደተኛ በመላው ዓለም ማፍራታቸው ቢያንስ ለ ህዝቡ ያልሰሩት አልያም ያጎደሉት ብዙ ሥራ መኖሩን ካልነገራቸው ጉድ ነው።
አዎን! በ አልፈው ታሪካችን በጎ ዘመን የመኖሩን ያህል የ ፈተና ዘመን አልነበርም ማለት አይቻልም። ግን ቀይ ሽብር አስመራ ላይ ሲሰማ አዲስ አበባም በተመሳሳይ መንገድ ትታመስ ነበር። በየዘመኑ የነበሩ ፈተናዎች በታሪክ አጋጣሚዎች የ ጦርነት አውድማ ያልሆኑ ቦታዎች ቢኖሩም መከራው ግን ያልጎበኘው ቤት አለ ማለት ይከብዳል። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን አንድ ደስ የሚል ሁሉንም የሚያስማማ ነጥብ አለ ። ይሄውም እንደ ሕዝብ ተነስቶ ሕዝብ በ ሕዝብ ላይ የሰራው በደል አለ ማለት ታሪካዊ ሂደቱን ና ክስተቱን አለማጠን ብቻ ነው ሳይሆን ተራ የ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ከመሆን የሚያልፍ አለመሆኑን ሁሉም መረዳቱ ነው። አሁን ቆም ብሎ የሚያስብ ትውልድ ይመጣ ዘንድ መስራት አስፈላጊ ነው። ብዙዎች የተዘጋ ታሪክ የሚመስላቸው ግን ፖለቲካ፣ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር፣ባህል፣ሃይማኖት፣ጆግራፍያዊ አቀማመጥ ወዘተ የ ሕዝቡን ችግር ከ ኢሳያሳዊ ና መለሳዊ የ መለያየት ፖሊሲ በዘለለ ማሰብን የግድ ይላል።


