Friday, May 17, 2013

የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሙዚቃ አቀራረብ ትውልዱን እንዳይተዋወቅ እያደረገ ነው።


በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ይመስለኛል።አዲስ አበባ የሚገኘው የፈረንሳይ የባህል ማዕከል በየአመቱ የአዝማሪ ቀን ብሎ የሚያዘጋጀው መርሃግብር እንደነበረው አስታውሳለሁ።በእዚህ ዝግጅት ላይ በኢትዮጵያ የሙዚቃ እድገት ላይም ሆነ ታሪክ ላይ ልዩ ልዩ ቅንብር ይቀርብበታል። አንድ ጊዜ ታድያ አንድ ፈረንሳዊ የኢትዮጵያን ሙዚቃ  ለረጅም ጊዜ ማጥናቱን ከተናገረ በኃላ  እንዲህ ማለቱን አስታውሳለሁ -
''የኢትዮጵያ አዝማሪ የህዝቡን ልዩነቱን እያኮሰሰ  አንድነቱን አጉልቶ የሚያሳይ የጅማት ክር ነው '' ማለቱን።እውነት ነው ኪነት በትንታውውም ሆነ በዘመናውቷ ኢትዮጵያ ላይ ያለው ቦታ የሚናቅ አይደለም።ዛሬ ምን እየተደረገ ነው? 

የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና '' የኅብረት ትርዒት '' የተሰኘ  ፕሮግራሙ 

ላለፉት ሰላሳ አመታት ገደማ   የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሙዚቃ ፕሮግራም የሚቀርብበት '' የኅብረት ትርዒት '' የተሰኛ ፕሮግራም አለው። ይህ ፕሮግራም ካልተሳሳትኩ አሁንም የቀጠለ ይመስለኛል። የኅብረት ትርዒት ዝግጅቶች ላይ ያሉት ልዩነቶች ምን ያህል ህዝብን አንድ የማድረግ እና የመለያየት ልዩነት እንዳላቸው ልብ ብላችሁ ካልሆነ  ልንገራችሁ። ነገሩ እንዲህ ነው።
በመጀመርያ ደረጃ ኢትዮጵያ ያላት አንድ ለናቱ ቲቪ ከሰላሳ አመታት በላይ መዝለቁን እና አሁን የጣብያ ቁጥር አንድ፣ ሁለት ቢባልም የተለየ ዝግጅት እንደማይቀርብ አንዘንጋ። 
ይህ ምን ማለት ነው? ስንል አሁን ያለነውን ትውልድም ሆነ የታዳጊ ሕፃናቱን ስነልቦና ወደድንም ጠላንም በየሳሎኑ ገብቶ እየተስተናገደ ነው ማለት ነው።የዜና ዘገባውን ህዝቡ በሚገባ አይከታተልም ብንልም  የኅብረት ትርዒትን ዝግጅት ግን በዘመናችን እንመንለከት ነበር።የዛሬው ታዳጊም እንዲሁ ያደርጋል። የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን  ''የኅብረት ትርዒት ፕሮግራም'' እንዴት ሕዝብ ያቀራርብ ነበር? ዛሬ ደግሞ እንዴት  ያራርቃል?
ቀድሞ  የኅብረት ትርዒት ፕሮግራሙቹ መሃከል በሚቀርበው በያንዳንዱ ዝግጅት ላይ በተቻለው መጠን የተለያዩ ብሔረሰብ ዘፈኖችን ያሳየን ነበር። የኪሮስ አለማየሁን እና የፀሃየ ዮሐንስን ትግርኛ፣ የእነ አሊቢራ ኦሮምኛ ወዘተ ትውልዱ ያወቀው የሀገሩን ብሔረሰቦች እያከበረ ያደገው አንዱ አስተማሪ የነበረው ለጆሮ የሚመቹ የኪነት ውጤቶች በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ብሔረሰቦች እንዴት እንደሚከይኑ እየተመለከተ እያደነቀ ስላደገም ጭምር ነው። 

በዘመነ ኢህአዲግ ቴሌቭዥን ጣብያው መርሃግብሮቹን ከአማርኛ ሌላ ተጨማሪ ቋንቋዎችን መክፈቱ ተገቢ ቢሆንም በሙዚቃ ፕሮግራሙ ግን ትውልዱን የማይተዋወቅ አድርጎታል። የአማርኛውን የኅብረት ትርዒትን ዝግጅት በሙሉ በአማርኛ ዘፈን የተሞላ እና ዘመናውም ሆነ ባህላዊ የሆኑ ለምሳሌ የኦሮምኛ፣የትግርኛ፣ወላይትኛ ዘፈኖች ዝር እንዳይሉ ታግደዋል። በትግርኛ  የኅብረት ትርዒትን ዝግጅ ላይም  አንድም  የአማርኛም ሆነ የኦሮምኛ ዘፈን ማቅረብ ብርቅ ብቻ ሳይሆን ፈፅሞ የማይሞከር ሆኗል።በኦሮምኛው መርሃግብር ላይም የትግርኛም ሆነ የአማርኛ ዘፈኖች የሉም።እዚህ ላይ ነው እንግዲህ  የአማርኛውን ፕሮግራም የሚመለከት ስለ ትግርኛ ወይም ኦሮምኛ ዘፈኖች እንዳያውቅ፣የትግርኛ ተመልካቹም እንዲሁ  የኦሮምኛም ሆነ የአማርኛ ዘፈን እንዳይመለከት ሲደረግ የኦሮምኛውም ሆነ የአፋር ፕሮግራሞች ሁሉ ተመሳሳይ ዕጣ ደርሶባቸዋል።
የእዚህ ሁሉ የተንኮል ሥራ ውጤት የሚታየው ደግሞ  በዘመነ ኢህአዲግ  የተወለደ ትውልድ ኢትዮጵያትን የመምራት ዕድል የገጠመው ጊዜ የሌላውን ባህል እንዴት ያከብራል? እንዴት የኦሮምኛ ወይንም የትግርኛ ተናጋሪ ወገኑን ያከብራል? 
የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት በፉከራ እና ከ ሌኒን መፅሀፎች በመጥቀስ አይከበረም። ጥቃቅን በሚመስሉ ግን ትልቅ ፋይዳ ባላቸው እንደ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ህብረት ትርዒት መርሃግብሮች በሚሰሩት የዕለት ተዕለት ሥራ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። በነገራችን ላይ ይህ ድርጊት በሀገሪቱ ብሔራዊ ራድዮም ላይ የሚታይ ነው። በዘመነ ደርግ የተለያዩ የሀገራችንን ቋንቋዎች ሙዚቃዎች መስማት የተለመደ ነበር።ለብሄር ብሔረሰቦች ቆምያለሁ እስከ ክልል ድረስ ከልያለሁ የለው መንግስት ግን የሌላውን ወገናችንን ዜማ አንዳንሰማ አግዶናል። እዚህ ላይ ይህ በትውልድ ላይ የሚሰራ ወንጀል የሚፈፀመው በአጋጣሚ ሳይሆን ታስቦበት እና ታቅዶ በመመርያ መሆኑ ነው ትልቁ አደጋ።


WACH HISTORY OF ETHIOPIAN MUSIC (The documentary film was recorded before22 years)




Wednesday, May 15, 2013

''ለምን ገደልከን?'' የሚለው የሰማዕታት ድምፅ ይጮሃል


ፎቶ አዲስ ፎርቹን ታህሳስ 4/2011 እኤአ 
 በባህርዳር አንድ የፌድራል ፖሊስ አባል በመንግስት ሚድያ 12 ሰዎች በሌሎች ዘገባዎች እስከ 18 ሰው  ግንቦት 4/2005ዓም መፍጀቱ ይታወቃል።የግድያው ምክንያት በደንብ አልተብራራም።''ከፍቅረኛው ጋር በነበረው ጥል ነው'' የተባለው ብቻ ምክንያት ነው እንዳይባል በመንገድ ላይ ሲሄድ  የነበረን ሰው፣መብራት በርቶበት ያገኘው ቤት ውስጥ ያሉ ነዋሪዎችን፣በአውቶቡስ ከጎንደር አቅጣጫ የመጡ የነበሩ መንገደኞችን አስወርዶ ወዘተ ነው  ድርጊቱን የፈፀመው። 
ይህ ጉዳይ መድበስበስ ያለበት ጉዳይ አይደለም።ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ።ለምሳሌ=
  • አብረውት የሰሩ የፖሊስ አባላት ስለ ግለሰቡ ምን ይላሉ? 
  • ባህሪው እንዴት ነበር? 
  • ከእነማን ጋር ያዘወትራል?
  • ፍቅረኛ የተባለችውስ ምን ትላለች?
  • ወላጆቹ እንዴት ነው ያሳደጉት?  ምን ይላሉ? 
እንደ ክልሉ የፖሊስ ኮሚሽነር አነጋገር (ለኢሳት በግንቦት 6/2005 በሰጡት ቃለ ምልልስ) ግለሰቡ በባህርዳር አካባቢ የሰራው ለ አራት አመታት ነው።አራት አመት ሲኖር ከሕዝቡ ጋር የደስታም ሆነ  ክፉ ጊዜ አሳልፏል።
  • በምን ምክንያት ያንን አይነት  አረመንያዊ ተግባር ፈፀመ?
  • የፌድራል ፖሊስ የስልጠና ማንዋል ችግር አለው?
  • አንድ የፌድራል ፖሊስ ሲሰለጥን የህዝብ ፍቅር እንዲኖረው ተደርጎ ነው ወይንስ የመንግስትን ትእዛዝ እንዲፈፅም ብቻ ነው የሚሰለጥነው? 
  •  ፖሊሶቹ ምን እየተባሉ ነው የሚሰለጥኑት? 
  • ኢትዮጵያን እንዴት ነው የሚረዷት? ኢትዮጵያ ማለት ለአንድ ፌድራል ፖሊስ የቷ ነች?
  • የህዝብ ፍቅር ማለት ለ ፌድራል  ፖሊስ ምን ማለት ነው? 
  • ጠላት የሚሉት ማንን ነው?
  • ወዳጅ የሚሉትስ? የሚሉትና ተመሳሳይ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው።አለበለዝያ ነገስ ቢሆን የህዝቡ ዋስትና ምንድንነው?  ግለሰቡ በሽተኛ እንደሆነ የተነገረ ነገር የለም።የኔ ሰው ገብሬ እራሱን ሲያጠፋ በሽተኛ ነው ተባለ።ጤነኛነቱን አረጋግጫለሁ ብሎ ክላሽ መንግስት ያስታጠቀው ገዳይ ፖሊስ ግን ሕዝብ ፈጀ። ለምን? አሰልጣኙም የስልጠና ማንዋሉም አስተማሪውም መፈተሽ አለበት።ጥልቅ ምርመራ  ያስፈልገዋል። አሁንም ''ለምን ገደልከን?''  የሚለው የሰማዕታት ድምፅ ይጮሃልና።
ጌታቸው 
ኦስሎ 

Monday, May 13, 2013

የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎችም ሆኑ መንግስት በጋራ ሲዘምሩለት የነበረው ጉዳይ እነሆ ደረሰ !


እድገት እና ለውጥ የተፈጥሮ ሂደት ናቸው። የሚመጣውን ለውጥ ተመልክቶ ከወዲሁ በቂ መሰናዶ ማድረግ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ጉዳይ ነው።በ 1983 ዓም የመንግስት ለውጥ ሲደረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ''በመሳርያ ትግል ብቻ ለውጥ መምጣት የሚቆምበት ጊዜ መሆን አለበት'' የሚሉ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ለሀገራችን በጎ የሚመኙ ብዙ ባእዳንም በቻሉት መንገድ ስለ ዲሞክራሲ በቅንነት ሰብከዋል። ኢትዮጵያ  ከሶሻሊስቱ ጎራ ተነጥላ የግል ሀብት እና የምዕራቡን አስተሳሰብ እንድታሰርፅ የሚጣጣሩ የመኖራቸውን ያህል 'ኢትዮጵያ ያለፈ ማንነቷን እና ያላትን የማደግ ዕድል ተጠቅማ ወደተሻለ ደረጃ መረስ ይገባታል' ያሉ ጥቂት አይደሉም።በለውጡ የመጀመርያ ሰባት አመታት ውስጥ ከለዘብተኛ  እስከ ፍፁም ተቃዋሚ የሆኑ የህትመት ውጤቶች ብቅ ብለዋል። ከለዘብተኛ የ ታዋቂው ጋዜጠኛ የሩህ መፅሄት ከፍፁም ተቃዋሚ እነ ጦብያ መፅሄት እና ጋዜጣን መጥቀስ ይቻላል።እዚህ ላይ ባለቤት የሌለበት ቤት ያጋኙ የመሰሉት የ ወሲብ መፅሄቶችን ሳንዘነጋ ነው።እርግጥ እነኝህ የወሲብ መፅሄቶች ከእድር እስከ መምህራን በተደረገ ርብርብ እና ጩሀት ''መብታቸው ነው'' እያለ ሲፈቅድላቸው የነበረው አካልም ጉዳዩን እንደገና እንዲመለከት አስገድዶታል። 

ከላይ በተጠቀሱት  የህትመት ውጤቶችም ሆነ በሌሎች  በተለይ እስከ 1997 ዓም ድረስ ጥቂቱን ከተሜ በሀገሩ ውስጥ ምን እየተደረገ እንዳለ እና የአለም አቀፍ ገፅታችንንም ጭምር ጥሩ መረጃ ሆነው ነበር። ይህ እንግዲህ እንዲህ እንዳሁኑ ኢንተርኔት ሳይኖር መረጃ ለማግኘት  ወረቀት ማገላበጥ የግድ የሚልበት ጊዜ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።በእነኚህ ዘመናት ሁሉ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎችም ሆነ መንግስትም በጋራ የዘመሩለት ጉዳይ አንድ እና አንድ ነበር።

የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎችም ሆነ መንግስትም በጋራ የዘመሩለት ጉዳይ እነሆ ደረሰ

የመንግስት የመዝሙር ስንኞች 

የመንግስት ስንኞች በገዢው ፓርቲ ህወሓት ሆነ ይመሩት በነበሩት በ አቶ መለስ ብዙ ጊዜ ተዜሟል ። ስንኞቹን በምክርቤት ስብስባ፣በጋዜጣዊ መግለጫዎች፣በመንግስት ልሳን በሆኑት ራድዮ እና ቲቪ፣የመንግስት ደጋፊ እና አድናቂዎች፣መንግስትን በሚደጉሙ ምዕራባውያን አፈቀላጤዎች፣ ማክያቶ እየጠጡ ''ይች ሀገር የሚሻላት '' ብለው ንግግር በሚጀምሩ ከዩንቨርስቲ በወጡ ምሁራን፣ ውዘተ ተዘምሯል። የመዝሙሩ ስንኞች 
  • ሰላማዊ ትግል አስፈላጊ ነው፣
  • የትጥቅ ትግል የነፍጠኛ አስተሳሰብ ነው፣
  • ሰላማዊ ትግል የሚቃወም ሃሳቡን በሌሎች ላይ ለመጫን የሚሻ ውስጡ አማባገነን አምባገነን የሚሸት ነው፣
  • ታሪካችን የጦርነት ታሪክ ነው መንግስት ለመቀየር ሁል ጊዜ ጫካ መግባት አለብን እንዴ?
  • ለምን በሰላማዊ መንገድ በምርጫ መንግስት ለመቀየር፣የተበደለውን ሕዝብ ድምፅ ለመሆን አንጥርም?
  • ጦርነት ናፋቂዎች ለኑሯቸው ማደላደያ ነው እንጂ ሰላማዊ ትግል ነው የሀገራችን እጣ ፋንታ፣
  • ''ኢህአዲግ በሰላማዊ ትግል ያምናል ማንም ሃሳቡን በተቃውሞ ሰልፍም ሆነ በፈለገው መንገድ ይችላል''  (የጎዳ ላይ ነውጥ ናፋቂዎች፣የብርቱካናማው አብዮት ናፋቂዎች የሚሉትን አባባሎች አሁን እርሱልኝ)፣ውዘተ ተዘምረዋል።

የተቃዋሚ አካላት የመዝሙር ስንኞች

  • ህገመንግስቱን አክብረን በሰላማዊ መንገድ ትግላችንን እናፋፍማለን፣
  • ብቸኛ መንገድ የምንለው የሰላማዊ የትግል መስመር ነው፣
  • የሰላማዊ ትግል ስንል ሕዝብ ይወስናል ማለታችን ነው።መንግስት ካልሰማው ግን ይህ የተራበ ሕዝብ መንግስትን ሊበላ ይችላል፣
  • እኛ በትጥቅ ትግል ዘላቂ ሰላም፣ዲሞክራሲ እና እውነተኛ የህዝቡን ችግር የሚፈታ መንግስት ይመጣል ብለን አናስብም፣
  • ለሰላማዊ ትግል ሁሉም ሕዝብ እኩል ድምፁን ማሰማት አለበት፣ ወዘተ 

ሜዳውም ይሄው ፈረሱም ይሄው -የሰማያዊ ፓርቲ የሰላማዊ የትግል መድረክ ያማይደገፍበት ምን ምክንያት አለ?

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በመርህ ደረጃም ቢሆን መንግስት እና ተቃዋሚዎች(በሀገር ውስጥ ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱት) በጋራ የዘመሩለት ጉዳይ ቢኖር የሰላማዊ ትግልን ወርቃማ መንገድነት ነው።መንግስትም ጥይት አታጩሁብኝ እንጂ ችግር የለም ብሏል( ስለተግባራዊነቱ እንዳትጠይቁኝ)።ሰላማዊ ትግል ሲባል በሰላማዊ መንገድ ካለምንም ሁከት ተቃውሞን በተለያየ መንገድ መግለፅ ነው።ይሄውም በሰላማዊ ሰልፍ፣በረሃብ አድማ፣ተቃውሞን በሚያሳዩ ልዩ ልዩ መንገዶች ለምሳሌ ጥቁር በመልበስ፣መሬት በመቀመጥ፣ከቤት ባለመውጣት፣ወዘተ ይገለፃል።

የሰማያዊ ፓርቲ የሰላማዊ የትግል መስመር ተከትሎ የተቃውሞ ጥሪ አስተላልፏል።በጥሪው መሰረት የአፍሪካ ህብረት ምስረታን 50ኛ አመት በአል ምክንያት በማደረግ ለሚመጡት አለምአቀፍ ማህበረሰብም ሆነ የሰላማዊ ትግልን አስፈላጊነት ከ 20 አመት በላይ ለሰበከን መንግስት የህዝቡን ድምፅ ለማሰማት 
1ኛ/ ከግንቦት 15 እስከ 17/ 2005 ዓም ህዝቡ ጥቁር በመልበስ እና 
2ኛ/ ግንቦት 17/2005 ዓም  ህዝቡ ሰላማዊ የተቃውሞ ድምፁን በአፍሪካ ህብረት ፊት ለፊት እንዲያሰማ ጥሪ አቅርቧል።
የሰላማዊ ትግል አንዱ ተመራጭነት ንብረት ሳይወድም፣የሰው ሕይወት ሳይቀጠፍ በሰላም እና በሰለጠነ መንገድ ተደማምጦ ሃሳብን መግለፅ ሃሳብን ያዳመጠው መንግስት ደግሞ ችግሩን ከስሩ አይቶ እራሱን እንዲያርም እና ሃገሩን የእውነት ሀገር ማድረግ ይጠበቅበታል።ሃያ አንድ አመት የተዘመረለት የሰላማዊ ትግል አፍጥጦ መጣ። የዘመሩቱ የዘመሩትን ያህል ናቸው? የሚባልበት ጊዜ ነው። ሰማያዊ ፓርቲ እርግጥ ነው ከተመሰረተ ገና 17 ወራትን ነው ያስቆጠረው።ላለፉት 21 አመታት አልዘመረም። ነገር ግን የሰላማዊ ትግልን አስፈላጊነት የነገሩን ከረም ያሉት ተቃዋሚዎችም ሆኑ ''የሰላማዊ ትግል ነው የኢትዮጵያ ዕጣ'' ያለን መንግስት ''ሜዳውም ይሄው ፈረሱም ይሄው'' ማለት የሚቻልበት ጊዜ ይመስላል። ይህ ማለት ሌሎች ተቃዋሚዎችም ከዝምታ ይልቅ  አብረው ለዘመሩለት ሰላማዊ ትግል  ለመቆም፣መንግስትም በአንዳቸው ላይ ላይተኩስ፣ላያስር እና ላያንገላታ ማለት ነው።
በውጭ የሚገኘው ማህበረሰብም ከማህበራዊ ድህረ ገፆች ጀምሮ እርቀት ሳይገድበው የጥያቄው አካልነቱን ልዩ ልዩ ስልቶች እየቀየሰ መደገፍ አለበት።ምናልባት መንግስት ላለፉት 21 አመታት የዘመረውን መዝሙር ከረሳው ''ሰላማዊ ትግል '' ወደ ፋይል ክፍል የሚገባበት አጋጣሚ እንዳይሆን መስጋት ካለበት አሁንም በመጀመርያ መንግስት መሆን አለበት።''የሰላማዊ ትግል ለኢትዮጵያ አይበጅም ወያኔ የሚገባው በለመደው ንግግር ብቻ ነው'' የሚሉቱን ለጊዜው አቆይተን የሰላማዊ ትግል የዘመርንሎቱ ሁሉ አሁን የሰማያዊ ፓርቲን ጥሪ  የምንገፋበት ምን አይነት ሞራል ይኖረን ይሆን? 

አበቃሁ 
ጌታቸው 
ኦስሎ 

Saturday, May 11, 2013

''የትናንቱ እስር ከሙስናው ጉዳይ ይልቅ ፖለቲካው ድምፀቱ ነው የሚሰማኝ''



ሰሞኑን ኢትዮጵያ ከነበረው ዜና ውስጥ ሕዝቡን እያነጋገረ የነበረው የዋናው ኦዲተር ሪፖርት ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት፣የአሰራር ዝርክርክነት እና ለምን እንደተከፈሉ የማይታወቁ ክፍያዎች በመንግስት መስርያቤቶች ላይ መኖራቸውን የ 2004 ዓም የሂሳብ ምርመራ ሲያደርግ እንደረሰበት  ለምክርቤት ባቀረበው ሪፖርት መግለፁ ነበር።
መንግስት እና የመንግስት ደጋፊዎችም ጉዳዩን እንደዋዛ ለማለፍ ሲሞክሩ እና አለፍ ሲል ደግሞ ጉዳዩ ኢህአዲግን አይመለከትም የሚል ፅሁፍ በማህበራዊ ድህረ ገፆች ለማስነበብ ሲዳፈሩ አስገርመውኛል። በመሰረቱ በስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ማለት በእያንድንዱ የስልጣን መዋቅር ውስጥ አለ ማለት ነው።ይህ ማለት ከገንዘብ ጀምሮ ማናቸውንም የሀገሪቱን ሀብት በመሰለው መልክ ውሳኔ እየሰጠ ነው ማለት ነው። ይህ ''የመንግስት ሀ ሁ'' ነው። ይህንን ሃቅ ለመግፋት ያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም።በመሆኑም ለደረሰው የገንዘብ ብክነት የገዢው ፓርቲ አባላት እና ባለስልጣናት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ  ተጠያቂ የሚሆኑባቸው  ብዙ መንገዶች አሉ።
ባለፈው አመት ''ግሎባል ፋይናንሻል እንተክግርቲ'' የተሰኘ አለምአቀፍ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ከ 2000  እስከ 2009 ዓም እኤአ   ብቻ ከኢትዮጵያ ከ 11.7(አስራአንድ ነጥብ ሰባት ቢልዮን ዶላር) ቢልዮን ዶላር በላይ በህገወጥ መንገድ መውጣቱን ገልጧል። ይህ ማለት እንደ ኢትዮጵያ ላለች አንዲት ታዳጊ ሀገር የእድገቷ ብቻ ሳይሆን ሕልውናዋን የሚፈታተን ነው። ሚልዮኖች የሚበሉት አጥተው በሚንከላወሱባት ምድር  ይህንን ያህል ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ወጣ ሲባል እንዴት ዝም ይባላል? በሌሎች ሃገራት ቢሆን ከካብኔ እስከ ምክርቤት የመበተን እና መንግስት ስልጣን እስከመልቀቅ የሚደርስበት ጉዳይ ነበር። እኛ ሀገር ግን ስለ ጉዳዩ መንግስት ማብራርያ አልሰጠበትም። የሚጠይቀውም የለም። ለነገሩ አምባገነኖች ነፃ ሚድያውን ማፈን የሚጠቅማቸው ለእንደዚህ ያለ ጊዜ ነው።ፀጥ እረጭ ለማድረግ።
የ11.7 ቢልዮን ዶላር ጉዳይ ገርሞን (መቸም ሁሌ እንደገረመን ነው) ሳያበቃ የእራሱ የመንግስት መዋቅር የሆነው የዋናው ኦዲተር ሪፖርት ደግሞ አፍ የሚያስይዝ ሪፖርት ለምክርቤቱ አቅርቦ አፋችንን አስይዞናል።
በ ግንቦት 5/2013 እኤአ  ሪፖርተር ባወጣው ርዕስ አንቀፅ ላይ እንዲህ ዘግቦታል።የሪፖርቱን ዋና ዋና ነጥብ-

''- 1.4 ቢሊዮን ብር ያልተወራረደ ሒሳብ አለ፡፡
- 313.6 ሚሊዮን ብር ዕዳ ሳይመልሱ የተሸጡ ድርጅቶች አሉ፡፡
- 897.5 ሚሊዮን ብር ሕጋዊ ያልሆነ ክፍያና ወጪ ተደርጓል፡፡
- ያልተወራረደው 1.4 ቢሊዮን ብር በ57 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የታየ ነው፡፡
- 15 ድርጅቶች ወይም መሥሪያ ቤቶች ከልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ምንጮች ገቢ የሚሰበስቡ ቢሆኑም፣ የገቢ ሪፖርት የማያደርጉ በመሆኑ ኦዲት ማድረግ አለተቻለም፡፡
- በ13 ናሙና መሥሪያ ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ 132.364 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቧል፡፡
- 22 መሥሪያ ቤቶች 13.8 ሚሊዮን ብር ማስረጃ የሌለው ወጪ አድርገዋል፡፡
- 30 መሥሪያ ቤቶች ደንብና መመርያ በመጣስ 353.568 ብር የሚያወጣ ግዥ ፈጽመዋል፡፡
- በውሎ አበልና በትርፍ ሰዓት ተመን 11 መሥሪያ ቤቶች 1.4 ሚሊዮን ብር አባክነዋል፡፡
- በኤርፖርት ተርሚናል የተሰማራ አንድ የግል ድርጅት ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ ለመቀበል ፈቃድ ሳይኖረው ከአሥር ዓመታት በላይ እየሠራ እንደሚገኝና ተቆጣጣሪ አካላት ያደረጉት ምንም ነገር የለም፡፡
- 134.7 ሚሊዮን ብር ብድር ያልመለሱ የመንግሥት ድርጅቶች ሲኖሩ፣ የመንግሥት ትርፍ ድርሻ የሆነ 18.549 ሚሊዮን ብር ሳይከፍሉ የተሸጡ ድርጅቶች አሉ፡፡ 44.254 ሚሊዮን ብድር ያለባቸው ሲሸጡም የገዛው አካል ለመንግሥት መከፈል የነበረበትን ያልከፈለ መሆኑን፣ ወዘተ. ወዘተ. ወዘተ.''
በትናንትናው ግንቦት 2/2005 ዓ ም  የግምሩክ ባለስልጣን ምክትል እና ዋና ሥራ አስኪያጆች ከሙስና ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን ኢቲቪ በምሽቱ የዜና እወጃው ላይ ገልፆ ቀሪ የታሰሩትን ስም ዝርዝር ግን ሳይጠቅስ አልፎታል።

የነፃ ሚድያውን የሚተካ ፀረ-ሙስና አካል አይገኝም 


እነሆ አምባገነንነት የሰብአዊ መብት እረገጣን ይወልዳል፣የሰብአዊ መብት እረገጣ ሙስናን ይወልዳል፣ሙስና ብዙ ልጆች ይወልዳል እነርሱም ድህነት፣ሥራ አጥነት፣የተማረውን 'የኮብልስቶን' ሥራ  ነው ዕጣህ ማለትን፣በሺ የሚቆጠሩ ሕፃናትን የጎዳና ተዳዳሪነትን፣በሺህ የሚቆጠሩ እህቶችን ለአረብ ሀገራት የባርነት ግዞትን፣ሚልዮን ወጣቶች በሀገራቸው ተስፋ ቆርጠው መሰደድን ይወልዳል።ከ እዚህ ሁሉ ጋር ግን አንድ የማንረሳውን ልጅ ደግሞ ሙስና ይወልዳል አርሱም የጥቂቶችን ቅምጥል ሕይወት፣የሚላስ የሚቀመስ የሚፈልጉ ሚልዮኖች ባሉባት ሀገር በ ሚልዮን ብር የሚቆጠር ''ሐመር''መኪናን በአዲስ አበባ እያሽከረከሩ መታየትን ሌላም ሌላም ልጆች ይወልዳል።
አምባገነኖች እራሳቸው በምዘውሩት የፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዳኝ የሚሉት ጉዳቸውን ስለሚያውቁት ነው።አምባገነኖች የነፃ ሚድያን እንደ ጦር የሚፈሩት እውነተኛው የ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ነፃ ሚድያው ስለሆነ ነው።ነፃው ሚድያ እያንዳንዱ ባለስልጣን ከበላው እራት እስከ ቁርስ ድረስ ለሕዝቡ እንደሚዘግብ እና ማን የህዝብ አገልጋይ ማን ተገልጋይ መሆኑን ፍንትው አድርገው ስለሚያሳዩት አይፈልጉትም።ለእዚህ ነው እንደ እነ እስክንድር ያሉትን የነፃ ጋዜጠኛ ተምሳሌቶችን ''አሸባሪዎች'' እያሉ እስከ እድሜ ልክ እስራት የሚፈርዱባቸው ከአስተዳደራዊ በደል ባለፈ የሙስናውን ጎራ እንዳይነካኩ ከመፍርዓትም ነው።
 

ሙስና በኢትዮጵያ ከግለሰብ ደረጃ አልፎ  የመንግስት የአጠቅቀም ወይንም የአሰራር  ስርዓት (system) ሆኗል


በኢትዮጵያ መንግስት ዘንድ ሙስና አሳፋሪ ጉዳይ እንዳልሆነ ብዙ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል። አዎን የፀረ ሙስና ኮሚሽን አለ።ሚድያው የሙስና መጥፎነትን ይነግረናል።አሁን አሁን ለምን እንደቀረ አይታወቅም እንጂ ቀድሞ የሚቀርቡት ማስታወቂያዎች እና ድራማዎች በደንብ የተጠኑ አስተማሪ መስለው ነበር።በፀረ-ሙስና ኮሚሽን ውስጥ በመርማሪነት የሚቀጠር ሰው ደሞዙ በወር እስከ አስራሁለት ሺህ የሚደርስ፣ የሚሄድበት እና የሚዝናናበት ቦታ ሁሉ የታወቀ መሆን እንዳለበት የቅጥር መስፈርቱ ያዛል።አመታት ሲቆጠሩ ግን ቀደም ብሎ የተወሰነ ስልጣን የነበረውን የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥርስ አልባ የማድረጉ ሂደት ከአቶ መለስ ተከታታይ ቁጣ ጀምሮ ኮሚሽኑ ውስጥ የተቀጠሩት የመጀመርያ ደረጃ መርማሪዎች ድንጉጥ እንዲሆኑ ማድረግ የተለመዱ ሆኑ።ሰራተኞቹ በውጭ የሚያዩት እና የሚሰራው አልጣጣም አላቸው።እናም ግማሾቹ በሙስናው ተነካኩ የተቀሩት ሀገር ትተው ሄዱ ሌሎቹ ሥራ ቀየሩ።
ከአንድ ሁለት ወር በፊት ይመስለኛል ሸገር ኤፍ ኤም የፀረ ሙስና ኮሚሽኑን ኃላፊ '' ከእናንተ ሰራተኞች መካከል በሙስና የሚታሙ አሉ ይባላል።እና የእዚህ አይነት ችግር ሲገጥማችሁ እንዴት ነው የምትፈቱት?'' ተብለው ሲጠየቁ የመለሱት መልስ ''አዎን ይህ ያጋጥመናል በቅርቡም ተመሳሳይ ችግር አለ በቅርቡም ሁለት ሰራተኞች ላይ የተባለው ችግር ተገኝቷል።'' ብለዋል። ይህ አንግዲህ ለሚድያ የተባለው እንጂ ወደ ዝርዝሩ ሲመጣ የባሰ ጉዳይ እንደሚኖር ይታመናል።

በእዚህ ሁሉ ነው እንግዲህ ሙስና ከግለሰብ አልፎ አሰራር ስርዓት(system) የሆነው።የአሰራር ስርዓት(system) የሆነ ሙስናን ለመዋጋት ግለሰቦችን ሳይሆን አሰራሩን(system) ማስወገድ ይሻል። አቶ መለስም ሆኑ አቶ ሃይለማርያም ደጋግመው መንግስታቸው፣ባለስልጣኖቻቸው፣ነጋዴዎቻቸው ሁሉ  ሙሰኛ እንደሆኑ በምክርቤት የተለያዩ ስብሰባዎች ነግረውናል።ይህ ማለት ችግሩ የግለሰቦች ሳይሆን የአሰራሩ ሙሉ መዋቅር -የመንግስት ችግር ነው ማለት ነው።የአሰራር እና የጠቅላላ የመዋቅር ችግር ደግሞ በጥገናዊ ለውጥ አይስተካከልም።ሙሉ በሙሉ የፖሊስ ለውጥ በማድረግ እና ስርዓቱን በመቀየር ብቻ ይፈታል። ይህ በእርግጥ  ለመንግስት ከባድ ሊሆን ይችላል።ለሕዝቡ ግን ከባድ አይደለም። ምክንያቱም የሙስና ውጤት ልጆች በሀብት ከመምነሽነሽ በቀር ሌሎቹ አብረውት ስለሚኖሩ ያውቃቸዋል።እናም የሙስና ዋናውን ግንድ የመንግስትን መላውን መዋቅር ትተን ግለሰቦችን አንንቀስ።ግንዱን ትተን ቅርንጫፎችን አንቀነጣጥብ።በአደባባይ ሙስና እንደፈፀሙ የተናገሩ ግን በፈረንጁ አፍ ''ሶሪ'' መሰል ንግግር አድርገው የሚኖሩባት ሀገር ውስጥ መኖራችንን አንዘንጋው።
በዘመነ ኢህአዲግ ፓርቲው ሙስና መኖሩ ትዝ የሚለው ሊያስወግዳቸው የሚፈልጋቸው ባለስልጣናት ሲኖሩ ወይንም እንደ ሰሞኑ አይኑን ያፈጠጠ ሪፖርት በተለያዩ ሚድያዎች ሲገለፅ ነው።የውስጥ ሹክቻ በሙስና ማንኪይ ትገላበጣለች። ትናንት የታሰሩት ባለስልጣናት ጉዳይ ላይ ''ለምን አሁን?'' የሚል ጥያቄ የቀረበለት የቀድሞው አዲስ ነገር አምደኛ ዘሪሁን ትናንት ከኢሳት ጋዜጠኛ መሳይ ለቀረበለት ጥያቄ የመለሰው መልስ ግን አንጀት ጠብ የሚል ሆኖ አግኝቼዋለሁ እናም  በእርሱ ሃሳብ ልደምድም። ''የትናንቱ እስር ከሙስናው ጉዳይ  ይልቅ ፖለቲካው ድምፀቱ ነው የሚሰማኝ'' ነበር ያለው።

አበቃሁ 
ጌታቸው 
ኦስሎ 

Thursday, May 9, 2013

የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 30 ይከበር! የዲሞክራሲ መብታችን ወደፊት እንጂ ወደኃላ መንሸራተት አይገባውም-ሚያዝያ 30፣1997 ዓም የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ (ቪድዮ)

ሚያዚያ 30፣1997ዓም ዕሁድ አዲስ አበባ ምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የ ዲሞክራስያዊ ለውጥ የሚጠይቅ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጎ ነበር። በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም የገባበት- ሁሉም ነገር ካለ አንዳች እረብሻ የተጠናቀቀበት ታሪካዊ ሰልፍ ነበር።ይህ ሰልፍ ከተደረገ እነሆ ስምንት አመታትን አሳለፈ።
  • የዲሞክራሲ መብታችን ወደፊት እንጂ ወደኃላ መንሸራተት አይገባውም።
  • አዲሱ ትውልድም ለመጪው ትውልድ ፍርሃትን እና አምባገነንነትን ማውረስ የለበትም። 
  • የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 30 ማንኛውም ሰው በሰላማዊ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍም የማድረግ መብት እንዳለው ይገልፃል።
  • ይህ ግን በተለያየ መንገድ ተሸራርፎ ሕጉ ስለመፃፉም ለመርሳት የሚዳዳቸው አለቆች በዝተውብናል።
  • ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃ የመግለፅ መብታቸው ይከበር!
  • የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 30 ይከበር!


ሚያዝያ 30፣1997 ዓም የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ (ቪድዮ)