ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, May 11, 2013

''የትናንቱ እስር ከሙስናው ጉዳይ ይልቅ ፖለቲካው ድምፀቱ ነው የሚሰማኝ''



ሰሞኑን ኢትዮጵያ ከነበረው ዜና ውስጥ ሕዝቡን እያነጋገረ የነበረው የዋናው ኦዲተር ሪፖርት ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት፣የአሰራር ዝርክርክነት እና ለምን እንደተከፈሉ የማይታወቁ ክፍያዎች በመንግስት መስርያቤቶች ላይ መኖራቸውን የ 2004 ዓም የሂሳብ ምርመራ ሲያደርግ እንደረሰበት  ለምክርቤት ባቀረበው ሪፖርት መግለፁ ነበር።
መንግስት እና የመንግስት ደጋፊዎችም ጉዳዩን እንደዋዛ ለማለፍ ሲሞክሩ እና አለፍ ሲል ደግሞ ጉዳዩ ኢህአዲግን አይመለከትም የሚል ፅሁፍ በማህበራዊ ድህረ ገፆች ለማስነበብ ሲዳፈሩ አስገርመውኛል። በመሰረቱ በስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ማለት በእያንድንዱ የስልጣን መዋቅር ውስጥ አለ ማለት ነው።ይህ ማለት ከገንዘብ ጀምሮ ማናቸውንም የሀገሪቱን ሀብት በመሰለው መልክ ውሳኔ እየሰጠ ነው ማለት ነው። ይህ ''የመንግስት ሀ ሁ'' ነው። ይህንን ሃቅ ለመግፋት ያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም።በመሆኑም ለደረሰው የገንዘብ ብክነት የገዢው ፓርቲ አባላት እና ባለስልጣናት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ  ተጠያቂ የሚሆኑባቸው  ብዙ መንገዶች አሉ።
ባለፈው አመት ''ግሎባል ፋይናንሻል እንተክግርቲ'' የተሰኘ አለምአቀፍ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ከ 2000  እስከ 2009 ዓም እኤአ   ብቻ ከኢትዮጵያ ከ 11.7(አስራአንድ ነጥብ ሰባት ቢልዮን ዶላር) ቢልዮን ዶላር በላይ በህገወጥ መንገድ መውጣቱን ገልጧል። ይህ ማለት እንደ ኢትዮጵያ ላለች አንዲት ታዳጊ ሀገር የእድገቷ ብቻ ሳይሆን ሕልውናዋን የሚፈታተን ነው። ሚልዮኖች የሚበሉት አጥተው በሚንከላወሱባት ምድር  ይህንን ያህል ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ወጣ ሲባል እንዴት ዝም ይባላል? በሌሎች ሃገራት ቢሆን ከካብኔ እስከ ምክርቤት የመበተን እና መንግስት ስልጣን እስከመልቀቅ የሚደርስበት ጉዳይ ነበር። እኛ ሀገር ግን ስለ ጉዳዩ መንግስት ማብራርያ አልሰጠበትም። የሚጠይቀውም የለም። ለነገሩ አምባገነኖች ነፃ ሚድያውን ማፈን የሚጠቅማቸው ለእንደዚህ ያለ ጊዜ ነው።ፀጥ እረጭ ለማድረግ።
የ11.7 ቢልዮን ዶላር ጉዳይ ገርሞን (መቸም ሁሌ እንደገረመን ነው) ሳያበቃ የእራሱ የመንግስት መዋቅር የሆነው የዋናው ኦዲተር ሪፖርት ደግሞ አፍ የሚያስይዝ ሪፖርት ለምክርቤቱ አቅርቦ አፋችንን አስይዞናል።
በ ግንቦት 5/2013 እኤአ  ሪፖርተር ባወጣው ርዕስ አንቀፅ ላይ እንዲህ ዘግቦታል።የሪፖርቱን ዋና ዋና ነጥብ-

''- 1.4 ቢሊዮን ብር ያልተወራረደ ሒሳብ አለ፡፡
- 313.6 ሚሊዮን ብር ዕዳ ሳይመልሱ የተሸጡ ድርጅቶች አሉ፡፡
- 897.5 ሚሊዮን ብር ሕጋዊ ያልሆነ ክፍያና ወጪ ተደርጓል፡፡
- ያልተወራረደው 1.4 ቢሊዮን ብር በ57 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የታየ ነው፡፡
- 15 ድርጅቶች ወይም መሥሪያ ቤቶች ከልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ምንጮች ገቢ የሚሰበስቡ ቢሆኑም፣ የገቢ ሪፖርት የማያደርጉ በመሆኑ ኦዲት ማድረግ አለተቻለም፡፡
- በ13 ናሙና መሥሪያ ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ 132.364 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቧል፡፡
- 22 መሥሪያ ቤቶች 13.8 ሚሊዮን ብር ማስረጃ የሌለው ወጪ አድርገዋል፡፡
- 30 መሥሪያ ቤቶች ደንብና መመርያ በመጣስ 353.568 ብር የሚያወጣ ግዥ ፈጽመዋል፡፡
- በውሎ አበልና በትርፍ ሰዓት ተመን 11 መሥሪያ ቤቶች 1.4 ሚሊዮን ብር አባክነዋል፡፡
- በኤርፖርት ተርሚናል የተሰማራ አንድ የግል ድርጅት ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ ለመቀበል ፈቃድ ሳይኖረው ከአሥር ዓመታት በላይ እየሠራ እንደሚገኝና ተቆጣጣሪ አካላት ያደረጉት ምንም ነገር የለም፡፡
- 134.7 ሚሊዮን ብር ብድር ያልመለሱ የመንግሥት ድርጅቶች ሲኖሩ፣ የመንግሥት ትርፍ ድርሻ የሆነ 18.549 ሚሊዮን ብር ሳይከፍሉ የተሸጡ ድርጅቶች አሉ፡፡ 44.254 ሚሊዮን ብድር ያለባቸው ሲሸጡም የገዛው አካል ለመንግሥት መከፈል የነበረበትን ያልከፈለ መሆኑን፣ ወዘተ. ወዘተ. ወዘተ.''
በትናንትናው ግንቦት 2/2005 ዓ ም  የግምሩክ ባለስልጣን ምክትል እና ዋና ሥራ አስኪያጆች ከሙስና ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን ኢቲቪ በምሽቱ የዜና እወጃው ላይ ገልፆ ቀሪ የታሰሩትን ስም ዝርዝር ግን ሳይጠቅስ አልፎታል።

የነፃ ሚድያውን የሚተካ ፀረ-ሙስና አካል አይገኝም 


እነሆ አምባገነንነት የሰብአዊ መብት እረገጣን ይወልዳል፣የሰብአዊ መብት እረገጣ ሙስናን ይወልዳል፣ሙስና ብዙ ልጆች ይወልዳል እነርሱም ድህነት፣ሥራ አጥነት፣የተማረውን 'የኮብልስቶን' ሥራ  ነው ዕጣህ ማለትን፣በሺ የሚቆጠሩ ሕፃናትን የጎዳና ተዳዳሪነትን፣በሺህ የሚቆጠሩ እህቶችን ለአረብ ሀገራት የባርነት ግዞትን፣ሚልዮን ወጣቶች በሀገራቸው ተስፋ ቆርጠው መሰደድን ይወልዳል።ከ እዚህ ሁሉ ጋር ግን አንድ የማንረሳውን ልጅ ደግሞ ሙስና ይወልዳል አርሱም የጥቂቶችን ቅምጥል ሕይወት፣የሚላስ የሚቀመስ የሚፈልጉ ሚልዮኖች ባሉባት ሀገር በ ሚልዮን ብር የሚቆጠር ''ሐመር''መኪናን በአዲስ አበባ እያሽከረከሩ መታየትን ሌላም ሌላም ልጆች ይወልዳል።
አምባገነኖች እራሳቸው በምዘውሩት የፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዳኝ የሚሉት ጉዳቸውን ስለሚያውቁት ነው።አምባገነኖች የነፃ ሚድያን እንደ ጦር የሚፈሩት እውነተኛው የ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ነፃ ሚድያው ስለሆነ ነው።ነፃው ሚድያ እያንዳንዱ ባለስልጣን ከበላው እራት እስከ ቁርስ ድረስ ለሕዝቡ እንደሚዘግብ እና ማን የህዝብ አገልጋይ ማን ተገልጋይ መሆኑን ፍንትው አድርገው ስለሚያሳዩት አይፈልጉትም።ለእዚህ ነው እንደ እነ እስክንድር ያሉትን የነፃ ጋዜጠኛ ተምሳሌቶችን ''አሸባሪዎች'' እያሉ እስከ እድሜ ልክ እስራት የሚፈርዱባቸው ከአስተዳደራዊ በደል ባለፈ የሙስናውን ጎራ እንዳይነካኩ ከመፍርዓትም ነው።
 

ሙስና በኢትዮጵያ ከግለሰብ ደረጃ አልፎ  የመንግስት የአጠቅቀም ወይንም የአሰራር  ስርዓት (system) ሆኗል


በኢትዮጵያ መንግስት ዘንድ ሙስና አሳፋሪ ጉዳይ እንዳልሆነ ብዙ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል። አዎን የፀረ ሙስና ኮሚሽን አለ።ሚድያው የሙስና መጥፎነትን ይነግረናል።አሁን አሁን ለምን እንደቀረ አይታወቅም እንጂ ቀድሞ የሚቀርቡት ማስታወቂያዎች እና ድራማዎች በደንብ የተጠኑ አስተማሪ መስለው ነበር።በፀረ-ሙስና ኮሚሽን ውስጥ በመርማሪነት የሚቀጠር ሰው ደሞዙ በወር እስከ አስራሁለት ሺህ የሚደርስ፣ የሚሄድበት እና የሚዝናናበት ቦታ ሁሉ የታወቀ መሆን እንዳለበት የቅጥር መስፈርቱ ያዛል።አመታት ሲቆጠሩ ግን ቀደም ብሎ የተወሰነ ስልጣን የነበረውን የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥርስ አልባ የማድረጉ ሂደት ከአቶ መለስ ተከታታይ ቁጣ ጀምሮ ኮሚሽኑ ውስጥ የተቀጠሩት የመጀመርያ ደረጃ መርማሪዎች ድንጉጥ እንዲሆኑ ማድረግ የተለመዱ ሆኑ።ሰራተኞቹ በውጭ የሚያዩት እና የሚሰራው አልጣጣም አላቸው።እናም ግማሾቹ በሙስናው ተነካኩ የተቀሩት ሀገር ትተው ሄዱ ሌሎቹ ሥራ ቀየሩ።
ከአንድ ሁለት ወር በፊት ይመስለኛል ሸገር ኤፍ ኤም የፀረ ሙስና ኮሚሽኑን ኃላፊ '' ከእናንተ ሰራተኞች መካከል በሙስና የሚታሙ አሉ ይባላል።እና የእዚህ አይነት ችግር ሲገጥማችሁ እንዴት ነው የምትፈቱት?'' ተብለው ሲጠየቁ የመለሱት መልስ ''አዎን ይህ ያጋጥመናል በቅርቡም ተመሳሳይ ችግር አለ በቅርቡም ሁለት ሰራተኞች ላይ የተባለው ችግር ተገኝቷል።'' ብለዋል። ይህ አንግዲህ ለሚድያ የተባለው እንጂ ወደ ዝርዝሩ ሲመጣ የባሰ ጉዳይ እንደሚኖር ይታመናል።

በእዚህ ሁሉ ነው እንግዲህ ሙስና ከግለሰብ አልፎ አሰራር ስርዓት(system) የሆነው።የአሰራር ስርዓት(system) የሆነ ሙስናን ለመዋጋት ግለሰቦችን ሳይሆን አሰራሩን(system) ማስወገድ ይሻል። አቶ መለስም ሆኑ አቶ ሃይለማርያም ደጋግመው መንግስታቸው፣ባለስልጣኖቻቸው፣ነጋዴዎቻቸው ሁሉ  ሙሰኛ እንደሆኑ በምክርቤት የተለያዩ ስብሰባዎች ነግረውናል።ይህ ማለት ችግሩ የግለሰቦች ሳይሆን የአሰራሩ ሙሉ መዋቅር -የመንግስት ችግር ነው ማለት ነው።የአሰራር እና የጠቅላላ የመዋቅር ችግር ደግሞ በጥገናዊ ለውጥ አይስተካከልም።ሙሉ በሙሉ የፖሊስ ለውጥ በማድረግ እና ስርዓቱን በመቀየር ብቻ ይፈታል። ይህ በእርግጥ  ለመንግስት ከባድ ሊሆን ይችላል።ለሕዝቡ ግን ከባድ አይደለም። ምክንያቱም የሙስና ውጤት ልጆች በሀብት ከመምነሽነሽ በቀር ሌሎቹ አብረውት ስለሚኖሩ ያውቃቸዋል።እናም የሙስና ዋናውን ግንድ የመንግስትን መላውን መዋቅር ትተን ግለሰቦችን አንንቀስ።ግንዱን ትተን ቅርንጫፎችን አንቀነጣጥብ።በአደባባይ ሙስና እንደፈፀሙ የተናገሩ ግን በፈረንጁ አፍ ''ሶሪ'' መሰል ንግግር አድርገው የሚኖሩባት ሀገር ውስጥ መኖራችንን አንዘንጋው።
በዘመነ ኢህአዲግ ፓርቲው ሙስና መኖሩ ትዝ የሚለው ሊያስወግዳቸው የሚፈልጋቸው ባለስልጣናት ሲኖሩ ወይንም እንደ ሰሞኑ አይኑን ያፈጠጠ ሪፖርት በተለያዩ ሚድያዎች ሲገለፅ ነው።የውስጥ ሹክቻ በሙስና ማንኪይ ትገላበጣለች። ትናንት የታሰሩት ባለስልጣናት ጉዳይ ላይ ''ለምን አሁን?'' የሚል ጥያቄ የቀረበለት የቀድሞው አዲስ ነገር አምደኛ ዘሪሁን ትናንት ከኢሳት ጋዜጠኛ መሳይ ለቀረበለት ጥያቄ የመለሰው መልስ ግን አንጀት ጠብ የሚል ሆኖ አግኝቼዋለሁ እናም  በእርሱ ሃሳብ ልደምድም። ''የትናንቱ እስር ከሙስናው ጉዳይ  ይልቅ ፖለቲካው ድምፀቱ ነው የሚሰማኝ'' ነበር ያለው።

አበቃሁ 
ጌታቸው 
ኦስሎ 

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...