ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, May 31, 2013

በአባይ ግድብ 'ጅኦ-ፖለቲካል' ጉዳይ ተቃዋሚዎች ያላቸው ሃሳብ እና መፍትሄ ሳይሰማ ህዝቡ በመላ ምት ላይ በተመሰረተ አስተሳሰብ ሀገሪቱ ወደ አልተፈለገ መንገድ እንዳትሄድ- የውጭ ፖሊሲያችንን የሚቀይሰው ማነው?((አጭር ማስታወሻ ከአልጀዚራ ቪድዮ ዘገባ ጋር)

ዛሬም የቅኝ ግዛት ውል መጥቀስ ምን ያህል ኃላ ቀርነት ነው? ግብፆች ዛሬም በ 1959 እአኤ  የተፈረመውን ግብፅን እና ሱዳንን የሚጠቅመውን ውል ይጠቅሳሉ።ኢትዮጵያ ግን ከቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ ዘመን እስካሁን ድረስ ውሉን ተቀብላ አታውቅም። የአባይ ጉዳይ አሁን ላለንበት በተለይ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ግብፅን ጨምሮ ከቅኝ ግዛት ተላቀው ነፃ ሀገር መሆን ከጀመሩበት ጊዜ እና የነዳጅ ዘይት ግኝት ማለትም ከ 1950 ዎቹ ወዲህ ለነበረን የሰሜንም ሆነ የሱማሌ ጦርነት ኢትዮጵያ በአቅም እንዳትደረጅ እና የአባይን ውሃ አጠቃቀም ጉዳይ እንዳታነሳ የተሸረቡ ተንኮሎች አካላት ነበሩ ማለት ይቻላል።
በኤርትራ ''ጀብሃን'' ለመርዳት ቀጥሎም ''ሻብያን'' ለማገዝ አንዳንድ የመካከለኛ ምስራቅ ሀገራትን፣ግብፅ እና ሱዳንን ያማለላቸው አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት የተዳከመች ኢትዮጵያን ለማየት ካላቸው ሕልም እና ከእዚሁም በአባይ ላይ እና በቀይባሕር ላይ ያላቸውን የበላይነት የማሳያ አንዱ እና ብቸኛ መንገድ አድርገው ስለሚያስቡ ነበር። በእዚህ ጉዳይ ብዙዎች ብዙ ብለዋል።እኔ የማክልበት የለም።

ሆኖም ግን የውጭው ተፅኖ መንስኤዎችን ብንዘረዝርም ትልቁ ጉዳይ ግን እኛ የውስጥ ጉዳይ አያያዛችን እና የመንግስታቶቻችን ብልህ የሆነ የህዝብ አስተዳደር ዘይቤ ማጣት ብሎም የውጭ ግንኙነቱን ባማከለ መንገድ አለመሆን አንዱ መጤን የሚገባው የነበረ እና አሁንም ያለ የችግሮቻችን ምንጭ ነው።በሌላ አንፃር  በየጊዜው የሚነሳውን ትውልድ ፍላጎት እየተመለክቱ መንግሥታቱ  እራሳቸውን ማስተካከል አለመቻል ከአባይ ጋርም ሆነ ካለንበት 'ጂኦ-ፖለቲካል' አቀማመጥ አንፃር የሚነሱትን ችግሮች በፍጥነት ከህዝብ ጋር ሆነው ለመፍታት ሲሳናቸው እንመለከታለን።

የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም በሃገርውስጥ ባሉ የመንግስት አሰራሮች ላይ ብቻ ሳይሆን በአለምአቀፍ ጉዳዮች በተለይ ኢትዮጵያን በቀጥታ የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሚይዙትን አቋም በየጊዜው ግልፅ ማድረግ ያለባቸው ይመስለኛል።ይህ ካልሆነ ሕዝብ በፅናት የሚቆምበትን መስመር ሳይመለከት እና ግልፅ የሆነ መንገድ አጥቶ የመዋለል አዝማምያ ለብሔራዊ አንድነትም ሆነ ለሉአላዊነታችን አድገኛ አዝማምያ ይፈጥራል። 

በአንድበኩል ህዝቡ መንግስት  የውጭ ኃይላትን በተመለከተ የሚሰጣቸውን  ማብራርያዎች አለማመን በሌላ በኩል ተቃዋሚዎች ስለጉዳዮች ያላቸው ሃሳብ እና መፍትሄ ሳይሰማ  ህዝቡ በመላ ምት ላይ በተመሰረተ አስተሳሰብ ሀገሪቱ ወደ አልተፈለገ መንገድ እንዳትሄድ ሁሉም ወገኖች ሊያስቡት የሚገባ አንኳር ጉዳይ ነው።

በመጨረሻም የአባይን ግድብ በተመለከተ ብዙ ጥያቄዎች ሊኖሩ ይቻላሉ። እኔም አለኝ።ጥያቄዬ ግን በግድቡ ጥቅምና ጉዳት አልያም መዋጮ ወዘተ በሚሉ ዙርያ አይደለም።ባለፈው በግንቦት 20 እለት መንግስት ውሃውን 'የማስቀየር ሥራ' ሰራሁ ብሎ በቀጥታ ለሕዝቡ ባስተላለፈው መልእክት ዙርያ ነው። አንድ ፕሮጀክት ያውም ከሀገር ውስጥ አልፎ የአካባቢ ሃገራትን ብሎም ስሩ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ የሚዘልቅ ጉዳይ የያዘን ጉዳይ- 'የአባይን ግድብ' ለምን በአደባባይ ውሃውን መንገድ የማስቀየስ ሥራ ሰራሁ ተብሎ ያውም በቀጥታ በኢቲቪ ማስተላለፍ  አስፈለገ? ለምን የበለጠ ለግብፅ እና ሱዳን አስጊ አለመሆኑ ላይ የማሳመን ሥራ አልተደከመም?

እርግጥ ነው የማሳመን ስራው ተሰርቷል የሚል ሃሳብ ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን የግብፃውያንን ስሜት ከሞራልም አንፃር ስሜታዊ እንዲሆኑ የታሰብ ካልሆነ በስተቀር የውሃውን መንገድ ማስቀየስ ሥራ በግንቦት 20 እለት ያንን ያክል መለፈፍ አስፈላጊ አይመስለኝም።የግድቡ መኖር በእራሱ ውሃውን መንገድ እንደሚያስቀይረው የታወቀ እስከሆነ ድረስ። ኢህአዲግ ለምን ግንቦት 20 ቀን ይህንን አደረገው?  የውጭ ፖሊሲያችንን እየቀረፀ ያለው ማነው? ኢህአዲግ የሚሰራውን እያወቀ ነው? ጥያቄዬ ነው።የግድቡ ሥራ የበለጠ የዲፕሎማሲ ሥራ በሚጠይቅበት ጊዜ የእዚህ አይነት ግብፅን ለማስደንበር እና ብሔራዊ 'ጀግንነትን' ለማስፈን የታሰበ እስኪመስል ድረስ በግንቦት 20 ቀን ''ውሃውን መንገድ አስቀየስኩት''  ማለት ለግብፅ ሕዝብ  የግብፅን መንግስት ''ጉሮሮህ ታነቀ ብለህ ንገረው'' ይመስላል። አሁንም እጠይቃለሁ የውጭ ፖሊሲያችንን የሚቀይሰው ማነው? 

አልጀዚራ ''inside story'' ፕሮግራም ግንቦት  22፣2005 ዓም (may 30,2013) በአባይ ግድብ ጉዳይ ላይ ከአዲስ አበባ አቶ በረከት ስምዖንን ፣ከለንደን ክሊር ፓስካ በአካባቢ ጥበቃ እና የምግብ ዋስትና  ኤክስፐርት እና ከካይሮ ላማ አልሃታል የአባይ ውሃ ኢንስቲቱት መስራች አባል ውይይት አዘጋጅቶ ነበር።Inside Story- Death on the Nile

No comments: