ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, December 31, 2022

የእነደብረጽዮን ወደ አዲስ አበባ መምጣት ለፖለቲካዊ እርቅ ወይንስ ለአገራዊ እርቅ?



=============
ጉዳያችን ምጥን
=============

በኢትዮጵያ ፌድራን መንግስት እና በህወሃት መሃከል በደቡብ አፍሪካ ከተደረገው የሰላም ስምምነት ወዲህ የሰላም ሂደቱ በፍጥነት እየሄደ ነው። በሂደቱ ላይ ግን ከኢትዮጵያ ወገንም ሆነ ከህወሃት ወገን ያለው ትችት እንደቀጠለ ነው።ሁሉንም ወገን ያስማማው እና ያስደሰተው አንዱ እና ብቸኛው ጉዳይ የትግራይ ህዝብ በተለይ በከተሞች ያለው ህይወት ወደነበረበት ቦታ የመመለስ ሂደቱ መፋጠኑ ነው።የመብራት እና የስልክ አገልግሎት የጀመረ ሲሆን የባንክ አገልግሎትም በሁሉም ቅርንጫፎች ባይሆንም አገልግሎት ጀምረዋል። በቅርብ ቀናት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እያለ በመንግስት ወገን የተሄደበትን ሂደት የሚተቹት በተለይ የመርህ ጥሰት የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈጉባዔ በድንገት የአሸባሪነት ፍረጃ ያልተነሳለት ህወሃት ጋር መገናኘታቸው ከፍተኛ ትችት ከማስነሳቱ በላይ መንግስት ለራሱ ሕግ ያለውን የማክበር ደረጃው ጥያቄ ላይ ጥሎታል።ፓርላማው በትናንትናው ዕለትም ባደረገው ዝግ ስብሰባ የራሱ የብልጽግና አባል የፓርላማ አባላትም በከፍተኛ ደረጃ የአካሄድ ስህተቱን አስመልክተው አስተያየት ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል የህወሃት ደጋፊዎች በሃሰት የውጭውን ዓለም ''ጀኖሳይድ ተፈጸመ ሺዎች ተደፈሩ'' እያሉ ሲዋሹ ስለነበር የአሁኑ የህወሃት እርቅ የሚይዙት የሚጨብጡትን አሳጥቷቸዋል።በተለይ እነደብረጽዮን ወደ አዲስ አበባ መምጣት እና ''ፋሽሽት '' እያሉ ሲሰድቡት ከነበረው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ይገናኛሉ የሚለው ዜና እንደሰሙ ድበረጽዮን እና ጌታቸው ድሮም ለዶ/ር ዐቢይ በስውር ሲሰሩ የነበሩ ናቸው የሚል ርቀት ያህል ሄደዋል።

በእዚህ ሁሉ መሃል ግን በትግራይም ሆነ በቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ህዝብ ሰላም መምጣቱን ከከፍተኛ ስጋት ጋር ተቀብሎታል።
ዛሬ ሰላም ሆነ ማለት ግን ቀጣይ ነው አይደለም የሚለውን ምላሽ በጥራት ይሰጣል ማለት አይደለም።ይህ ሰላም የመጣው የኢትዮጵያ መከላከያ ከጥምርጦሩ ጋር ሆኖ የትግራይን 90% በላይ ከተማና ገጠር ነጻ ካወጣ በኋላ መሆኑ ይህ ድል ባይመጣ ኖሮ ህወሃት መቼም ወደ ድርድር ጠረንጴዛ እንደማይመጣ የታወቀ ነው።ይህንን መሰረታዊ ጉዳይ ስናስብ ነው ይህ እርቅ ፖለቲካዊ ነው ወይንስ ሃገራዊ እርቅ ነው? የሚል ጥያቄ እንድንጠይቅ የሚያስገድደን።

አሁን ባለበት ደረጃ በመንግስት እና በህወሃት መሃከል የተደረገው ስምምነት ፖለቲካዊ ነው።ፖለቲካዊ እርቅን ወደ ሃገራዊ እርቅ ለመውሰድ እና በፖለቲካዊ እርቅ የታረቁት ሁሉ ከመስመሩ እንዳይወጡ የሚያደርግ የህዝብ አስገዳጅነት የሚኖረው እርቁ ሃገራዊ እርቅ መሆን ከቻለ ብቻ ነው።የኢትዮጵያ ህዝብ ድሮም ከህወሃት ጋር የነበረው ጦርነት በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ህወሃት በመዝመቱ እና ከአሁን በኋላ የህወሃትን የበደል ቀንበር መሸከም የሚችል ትከሻ ስለሌው ነው።

ፖለቲካዊ እርቅን ሃገራዊ እርቅ ለማድረግ የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች አሉ።ሃገራዊ እርቅ ርትዕ የሆነች ፍትሕ ይፈልጋል።የተበደለው እና የተዘመተበት ሃገር እና መከላከያ ነውና ይህ ወንጀል ለወደፊቱ ትውልድም እንዳይቀጥል አንድ ዓይነት ያጠፋው የሚቀጣበት የተበደለም የሚካስበት ዓይነተኛ መንገድ ይፈልጋል።በአፋር እና በአማራ ህዝብ ላይ የተፈጸመው በደል እና የግፍ ዓይነት ለፈጻሚዎቹ የሚያስተምር የፍርድ ሂደት ያስፈልጋል። በተመሳሳይ በትግራይ ህዝብ ላይ የተፈጸመ የህግ ጥሰት በመከላከያ አባላት በኩል የተፈጸመ ካለ መንግስት ከእዚህ በፊት በጀመረው የማጣራት ሂደት መሰረት አጣርቶ ለፍርድ ማቅረብ አስፈላጊ ነው።

ሰላም የሚጠላ የለም።በትግራይ የሚኖረው ሰላማዊ ህዝብ የመሰረተ አገልግሎት ማግኘቱ እና ከሁሉም በላይ ለሁለት ዓመታት በህወሃት ከታገተበት እገታ በመከላከያ እና ጥምር ጦር ብርቱ መስዋዕትነት ከእገታው ተላቆ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መገናኘቱ ሁሉ ያስደስታል።ከእዚህ ሁሉ ጋር ግን እርቁ የቀድሞ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እርቅ እንዳይመስል ህወሃት የተጣላው ከአገር ጋር ነው እና አገራዊ እርቅ የሚሆንበት መንገድ ቢፈለግ መልካም ነው።ይህ ሲባል ደግሞ ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር የሚደረገውን ምክክር ይጠብቅ ማለት አይቻልም።ሌላም ጥያቄ አለ።በኢትዮጵያ መከላከያ ላይ ህወሃት ጥቃት ሲፈጽም ከኢትዮጵያ ጎን ቆማ የተራዳችው የኤርትራ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ እነደብረጽዮን መጥተው የእርሳቸው አለመገኘት ፍትሃዊ አያደርገውም የሚሉ አሉ።የአዲስ አበባ ህዝብ ደግሞ ''ኢሱ! ኢሱ!'' ማለት እንጂ ደብረጽዮን! ማለት አልለመድም።አሁን ባለው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታም አይልም።አቶ ኢሳያስስ እሺ ብለው ይመጣሉ ወይ? 

ይህ በእንዲህ እያለ በህወሃት እና በመንግስት መሃል የተደረገው የሰላም ስምምነት በሚፈልጉት መጠን እጃቸውን መጥለቅ ያልቻሉት አንዳንድ የምዕራብ መንግስታት ብሽቀት እንደፈጠረባቸው ተሰምቷል።የብሽቀቱ መነሻ ደግሞ ሁለት ናቸው። አንዱ የአፍሪካ ሕብረት በእዚህ ያህል አቅም አደራድሮ በመቶሺዎች የተሰለፉበትን ጦርነት ወደሰላም ማምጣቱ አንድ የተሞክሮ ልምድ ሆኖ አፍሪካ ያለማንም የምዕራባውያን ጣልቃገብነት ወደፊት እንድትራመድ ያደርጋትና ጥቅማችንን ማሳካት አንችልም የሚል ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ስምምነቱ በቶሎ አይጠናቀቅም የተራዘመ ክርክር ውስጥ ይገባሉ የሚለው የሃገራቱ ግምት አለመሳካቱ ነው።ድርድሩ በጣም ቢራዘም ኖሮ እነኝሁ የውጭ መንግስታት በተለያየ አጀንዳዎች እየበለቱ ጉዳዩን አክርረው ጥቅማቸውን ለማስከበር ያመቻቸው እንደነበር ያምናሉ።ባለፈው ዓርብ ወደ መቀሌ የበረሩት ዲፕሎማቶች ስብሰባው ላይ ነበር ለማለት እንጂ በቀጥታ የሚገቡበት እና ከእነ ኦባሳንጆ ጋር የሚስተካከል ቀጥታ ሚናቸው ታይቶ ለአፍሪካውያን ይህንን ሰራን የሚያስብል አንዳች ለሚድያ የሚበቃ ጉዳይ ይዘው አልመጡም።ይህ ማለት አሜሪካ የመሳሰሉ ሃገሮች እጅ በተዘዋዋሪ አይታይም ማለት አይደለም።ነገሮች በቶሎ ባይቋጩ ኖሮ ከእዚህ በበለጠ መልኩ የስቴት ዲፓርትመንት በየቀኑ መግለጫ ሲሰጥ እና በኋላም ሂደቱን በእጃቸው ሙሉ በሙሉ ለማስገባት አይሞከርም ማለት አይቻልም።

ለማጠቃለል፣የሰላም መምጣት የማስደሰቱን ያህል ህወሃት የሸር ፖለቲካውን መልሶ እንዳይረጭ ህዝብ ዋስትና ይፈልጋል።ማንም ደግሞ ህወሃት የሰራው ወንጀል ተለባብሶ  ታልፎ፣እርቁም ፖለቲካዊ እርቅ ብቻ ሆኖ ፍትህ ሳይጨምር ከሄደ ስጋታችን ያይላል።ስጋቱ ደግሞ ይህንን ለማስተካከል የሚነሳ ሌላ የህዝብ ንቅናቄ ተነስቶ ከምርጫ ፖለቲካ የራቅን ሌላ ፍትጊያ ውስጥ የምንገአብ ሃገር እንዳንሆን ከመስጋት የሚመነጭ ነው።የጀርመን ህዝብ የናዚ ፓሪትን ከሽንፈቱ በኃላ በዕርቅ ልፍታው ቢል ኖሮ ዛሬ ለደረሰበት የልማት ደረጃ አይደርስም ነበር።የጣሊያን ህዝብ የሞሶሎኒ ፋሺሽት ፓርቲ በጥምር መንግስት ውስጥ ይቆይ ብሎ ቢተውው ኖሮ ዛሬ ምናልባት የምናውቃት ጣልያን ላትኖርትችላለች።ህወሃትም ከእርቁ በኋላም ታደሰ ወረደ በግልጽ እንዳሉት የእርቁ ዓላማ እርሳቸው ጠላት የሚሏቸውን የኢትዮጵያ መንግስት እና የኤርትራ መንግስትን መከፋፈል መሆኑን ተናግረዋል።በመሆኑም ፖለቲካዊ እርቅ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሲጠፉ አብሮ ይጠፋል።አገራዊ እርቅ ኝ ያሻግራል።በመሆኑም እነደብረጽዮን አዲስ አበባ መጥተው እርቁን ይፈጽማሉ የሚለው የሰሞኑ ወሬ ጥያቄ ይዞ መጥቷል። ይሄውም እርቁ ፖለቲካዊ ነው ወይንስ አገራዊ? የሚል ነው።
==========////=======

No comments:

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)