ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, December 6, 2022

ኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካን መርዝነት የተረዳ መሪ አላት ወይ? እንደርሱ ችግሩን የተረዱ የመንግስት ባለስልጣናትስ አሉ ወይ? መልሱ አዎን! ነው። መሪዎቿ ከሁሉ በፊት የሰው ህይወት ለመታደግ መንቀሳቀስ አልነበረባቸውም ወይ? አሁንም መልሱ አዎን! ነበረባቸው ነው።ኢትዮጵያውያን! ወቅታዊውን ችግር በቅንጥብጣቢ ጊዜያዊ መፍትሔ አንፈታውም።



ለውስጣዊ የጸጥታ ችግሮቻችን መፍትሔነት ሦስቱ መፈታት ያለባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች።


==========
ጉዳያችን ምጥን
==========
በማንነት ጥቃት ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ፣ሲታሰሩና ሲሰደዱ ዓመታት ተቆጠሩ።በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት እጅግ ጽንፈኛ እና ዘረኛ አደረጃጀት የነበራቸው እንደ ኦነግ ያሉ አደረጃጀቶች ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው በፌድራል እና በተለየ በኦሮምያ ክልል ከልዩ ኃይል አባልና አመራር እስከ የክልሉ ምክርቤት ድረስ ገብተዋል። ይሄው ኃይል የነበረውን የኢትዮጵያን የመጥላት እና በአማራ ላይ የተተረከለትን ትርክት እና እራሱ የፈጠራቸውን ፈጠራዎች ይዞ ትውልድ በክሏል። 

በወለጋ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ዘርን መሰረት አድርጎ እየተፈጸመ ያለው የሰሞኑን ጥቃት ከእዚህ በፊት ከነበረው በተለየ የክልሉ ልዩ ኃይል ከእዚህ በፊት በርካታ በደሎችን እና ግድያዎችን ቢፈጽምም እንደ የሰሞኑ ያለ ከሸኔ ጎን ተሰልፎ መንደሮችን እየለየ አብሮ የሚያጠቃ ሆኖ ዓይን ያወጣ ተግባር የለም።አሁን ክልሉ እራሱን መቆጣጠር ያቃተው ልዩ ኃይሉ በራሱ እንደፈለገው የሚሔድ ሆኗል።በሌላ በኩል እራሳቸውን ለመከላከል የተነሱ ሚሊሻዎችም ኢትዮጵያ ሃገራችን ነች መንግስት ካልተከላከለልን እራሳችንን እንከላከላለን ብለው ቢያንስ ቤተሰባቸውን ሊከላከሉ እየታገሉ ነው። በእዚህ ሁሉ መሃል እዚህም እዚያም ክፉ አካሄዶች ይኖራሉ።በምንም መለክያ ግን አማራ በሚል ዘርን በመለየት የተፈጸመውን ያህል ግፍ ግን በሌላው አልታየም።ከአርባጉጉ እስከ ጉርዳፈርዳ፣ከወለጋ እስከ ሻሸመኔ በጥላቻ ያልተፈጸመ የግፍ ዓይነት የለም።

የብዙዎች አፍ ማሟሻ በተለይ የወለጋው ዓይነት ችግር ሲፈጠር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የስድብ ውርጅብኝ ማውረድ ነው።አንዳንዶች ደግሞ መንግስት ቢቀየር መፍትሔ የሚመጣ፣አብዮት ቢካሄድ ኢትዮጵያ የምትቀየር ወይንም የእኛ ትውልድ ሰፈር ሰው አራት ኪሎ ቢገባ መፍትሄ የሚገኝ ሁሉ ነገር ጸጥ የሚል ይመስለናል። ይህ ሞኝነት ነው። በ1966 ዓም የኢትዮጵያ አብዮት ይዞት የተነሳው መሰረታዊ የህዝብ ተገቢ ጥያቂዎች ቢኖሩም የመንግስት ስሪቱን በሆይ! ሆይ! እና ድንጋይ በመወርወር ያፈረሱት ዛሬ ድረስ የማይለቀን የሃገር ውርደት አብሮ እንዳመጣ መካድ አይቻልም። ዛሬም የችግሩን ሥር መረዳት እና መፍትሄውም አንዱን ክር ለማሰር ሌላውን መፍታት ዓይነት እንዳይሆን ሁሉን ያማከለ መሆን አለብት። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ከማንም የዓለም ክፍል በተለየ የብዙ ችግሮችን የማለፍ እና በይቅርታ መጪውን መሻገር የሚችል ህዝብ ነው።ይህንን ሌላ እማኝ መጥራት አያስፈልግም የሰሜኑ ጦርነት ቆመ ሲባል ህዝብ የቂም በትሩን ሳይመዝ ወደ ቀሪ ህይወቱ ሄደ እንጂ እንዲህ ሆኜ እንዲያ ተደርጎ በሚል ክርክር ውስጥ አልገባም። ይህ ትልቁ ግን ያላደነቅነው ዕሴታችን ነው። ስለሆነም ዛሬም ይህንን ችግር የመፍታቱ ክህሎት እኛው ጋር አለ።

ወደ አንዱ መገለጫ እና የብዙ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን በተለይ የአማራ ተወላጅ በሚል የተገደሉበት፣የተዘረፉበት እና የተሰደዱበት የወለጋው ጉዳይ ስንመጣ ኦነግ ሸኔ የብሔር ጥያቄውን ወደ የመሬት ጥያቄ በማውረድ የኦሮሞ ህዝብ እና የአማራ ህዝብን ለማጋጨት የሞከረበት ሙከራ ሰሞኑን ወደ አደገኛ ደረጃ እየተቀየረ ነው።ወለጋ የኦሮሞ መሬት ብቻ ጎጃም የአማራ መሬት ብቻ ወይንም ጅጅጋ የሱማሌ ብቻ የሚለው አስተሳሰብ መሰረታዊ የአስተሳሰብ ችግር ብቻ ሳይሆን የህወሃት/ኢህአዴግ የተከለው መርዝ ነው። መርዙ አለ።ልንክደው አንችልም።የሰዎች አስተሳሰብ ቀይሯል።ይህንንም መሬት ላይ ያለ ሃቅ ነው አንክደውም። መፍትሔዎቹ በአጭር ጊዜ ቆራጥ አቋም የሚፈልጉ እና በረጅም ጊዜ የሚሰሩ ሥራዎች ይፈልጋል።

ኢትዮጵያውያን! ወቅታዊውን ችግር በቅንጥብጣቢ ጊዜያዊ መፍትሔ አንፈታውም። 

ቅንጥብጣቢ ጊዜያዊ መፍትሔዎች ችግሩን አይፈቱትም።የፖለቲካ አደረጃጀቶች እና ክልሎች በህዝቡ ስም በሚያደርጉት ጊዜያዊ ስምምነት እና ጎን ለጎን በመቀመጥ በሚደረግ ዲስኩር አይፈታም።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን በወለጋ ጉዳይ ላይ ቸልተኝነት አሳይተዋል የሚሉ የብዙዎች ድምጽ ነው።ይህ ቸልተኝነት የሚገለጸው ችግሮች በተፈጠሩ ጊዜ የሚያሳዩት የምላሽ እና የቁጣ መጠን በሚድያ አልታየም ብቻ ሳይሆን ወዲያው የጦር ኃይል አዝምተው ንጹሃንን ለመታደግ አልቻሉም የሚለው ነው። ይህ ተገቢ ጥያቄ ነው።ማናቸውም ችግር ከመታየቱ በፊት የማይተካው የሰው ህይወት መታደግ ይቀድማል።የጸጥታ ችግር አተናተን እና ቅድምያ ዝግጅት እና ህዝብን የመከላከል ደረጃ መንግስት በኦሮምያ ክልል ያሳየው መዝረክረክ የትም አልታየም።የሻሸመኔን ጥቃት እና የወለጋ የሰሞኑ ሁኔታዎች በቂ ማሳያዎች ናቸው።

ከእዚህ በተለየ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኦነግ ጋር አንድ አድርገው የሚያዩ ሰዎች ሁሌ የሚረሱት ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢህአዴግ ስር ሆነው ከኦነግ ጋር የነበረውን የአይጥና ድመት መሳደድ፣በኋላም ይሄው ቡድን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ከናይሮቢ ድረስ ሰው ልኮ ግድያ መሞከሩን እና ወለጋ ላይም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ህይወት ለመቅጠፍ ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጉን ይረሱታል።ምክንያታዊ ዕሳቤዎች መልካም ናቸው።አሁን በወለጋ ባለው በሰሞኑ ጉዳይ በኦነግ ሸኔ በኩል በዋናነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፋኖን እንዳዘመቱ ነው ቅስቀሳ የተያዘው።ሌላው ቀርቶ የጨፌ ኦሮምያ ምክርቤት አባላት ሳይቀሩ በትናንትናው ዕለት በመንግስት ላይ እየዘመቱ የሸኔን ቀጥተኛ አቋም ያንጸባረቁ ለእዚህ ሁሉ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የኦሮሞ ጠላት አድርገው ነው ያቀርቧቸው። 

በመሆኑም ይህንን ችግር በስሜት እና በግርግር የሚፈታ አይደለም።የጉዳዩ ቁልፍ ያለው እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣የኢትዮጵያ ህዝብ እና የመከላከያ ኃይል በቅደም ተከተል መመለስ ያሉባቸው  እና ለመልሱም ሁሉም ሊያግዛቸውም የሚገባው የችግሩ ማጠንጠኛ ቁልፍ የሚሆነው አሁንም በሦስቱ ጥያቄዎች አመላለስ ላይ ነው።ኢነርሱም ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢህአዴግ/ህወሃት እና ኦነጋዊ የጎሳ ፖለቲካን እንዴት መንቀል ይችላሉ? ህዝቡስ ይህንን በምን ያህል ደረጃ ለማገዝ ቆርጦ ይነሳል? የሕግ የበላይነት እንዴት ይከበራል? የሚሉት ናቸው።መልሶቹን መስጠት ያለብንም ሁላችንም የሚመለከቱን ጥያቄዎች እንደየደረጃችን እነኝህ ይመስሉኛል።
=================

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...