ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, December 12, 2022

ህወሓት ቀርጾ የሰጠውን የኦሮምያ ክልል ዓርማ እና ደርሶ የሰጠውን መዝሙር ከልሉ ውጭ በአዲስ አበባም ካልዘመርኩ ማለት የጽንፈኝነት የመጨረሻው ጥግ ነው።የአዲስ አበባ ህዝብ ኢትዮጵያውያን በፈቃዳቸው ኦሮምኛ አይማሩ አላለም።ይህንን በሃሰት የሚያራግቡ አመራሮች ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው። • አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጎን የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ ብትሰቅል ይመጥናታል።
 • አሁን በአዲስ አበባ የኦሮምያ ሰንደቅ ዓላማ እና የክልሉን መዝሙር በተመለከተ ያሉት አራት እውነታዎች 
 • የኦሮምያ ክልል ህዝብ በጊዜ መንቃት አለበት።
 • መንግስት ማድረግ የሚገባው 
==========
ጉዳያችን ምጥን
==========
ዛሬ ታህሳስ 3፣2015 ዓም በአዲስ አበባ ሽሮሜዳ አካባቢ በሚገኘው እንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት  እና የአየርጤና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የኦሮሚያ ክልል ዓርማ እና መዝሙር ተማሪዎች በግዳጅ እንዲዘምሩ በተደረገ ሙከራ ሳብያ ድጋሚ ተቃውሞ ተነስቷል::አዲስ አበባ የሁሉም ብሔሮች መኖርያ ሆና ሳለ የአንድ ክልል ዓርማ ይሰቀል የሚሉ በፌደራል አስተዳደር ስር የተሸሸጉ የፅንፈኛ ቡድኖች ዋና አቀንቃኞች ናቸው::በዛሬው ውሎ ከሽሮሜዳ ወደ አሜሪካ ኤምባሲና ወደ ጉስቋም ማርያም የሚወስደው መንገድ ለተወሰነ ጊዜ ዝግ ነበር::እዚህ ላይ ማወቅ የሚገባን ጉዳይ በኃይል ለመጫን የሚሞከር ማናቸውም ዓይነት ባሕል እና አመለካከት የበለጠ በህዝብ እየተጠላ ይመጣል::ይህ የታሪክ ሀቅ ነው::አሁን ይዘመር እየተባለ ያለው የኦሮምያ ክልል መዝሙር በህወሓት ተደርሶ ለኦሮምያ ክልል የተሰጠ ሲሆን መዝሙሩ በይዘቱ ከፋፋይና የቂም ቃላትን የያዘ ነው::የመዝሙሩ ይዘት ምንም ይሁን ምን፣አዲስ አበባ እንደ አንድ በህገ መንግስቱ እንደተመሰረተ ክልል የራሷ የሆነ የውስጥ መተዳደርያ ደንብ ሊኖራት ይገባል።ይህ መብት የክልል የመስፋፋት ፖሊሲ የያዙ የጽንፍ ኃይሎች እንደፈለጉ ከሕግ ውጭ እንዲፈነጩ አረንጓዴ መበራት እያሳዩ ያሉት አሁንም በስልጣልን ላይ ያሉት የቀድሞ ኦህዴድ እና ዘግይተው የተቀላቀሉት የኦነግ የጽንፍ አራማጆች ናቸው።

ዛሬ በአንዳንድ የአዲስ አበባ አንዳንድ ትምሕርትቤቶች የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማም ሆነ የኦሮምያ ዓርማ ሳይሰቀል ትምሕርቱ የተካሔደባቸው አካባቢዎች አሉ:: የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሳይሰቀል በትምህርትቤቶች ሳይሰቀል ትምሕርት ማስተማር በራሱ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሀገር የአንድነት ዓርማ ከተማሪዎች አዕምሮ በማራቅ የማድረግ ሙከራ ብቻ ሳይሆን የሕገመንግስት ጥሰት ነው።የመንግስት ህልውና መገለጫው የሰንደቅ ዓላማ በሚገባው የመንግስት ተቋማት ትምሕርትቤቶች ጨምሮ በሥነስርዓት መሰቀሉ አንዱ እና ዋነኛው ነው።

አሁን በአዲስ አበባ የኦሮምያ ሰንደቅ ዓላማ እና የክልሉን መዝሙር በተመለከተ ያሉት አራት እውነታዎች 
 • በእዚህ ጊዜ አጀንዳው የተነሳበት ምክንያት በኦሮምያት ክልል ውስጥ በጽንፈኛው የኦነግ ሸኔ የቀረውን የክልሉን የኦሮምኛ ተናጋሪ አንዱን የኦህዴድ ሌላውን የሸዋ ኦሮሞ እያለ እየከፋፈለ ስለሆነ በእዚህ ሳብያ በተነሳው የክልሉ የውስጥ ውጥረት እንደ ማብረጃ ተደርጎ ተወስዷል።
 • በእዚሁ የመከፋፈል አጀንዳ ላይ የጋራ የክልሉ አጀንዳ በመፍጠር የውስጥ አንድነት ያመጣል በሚል ይህ የባንዲራ ጉዳይ ተፈልጓል።
 • በኦሮምያ ክልል እና በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ እና በአዲስ አበባ ዙርያ ጋር በተቀናጀ የተፈጸሙ ዘግናኝ የሙስና ዘራፊዎች በሰሞኑ የመንግስት እንቅስቃሴ ሊመቱ እንደሆነ ስላወቁ ይህንን የባንዲራ አጀንዳ ማንሳት እና ክልሉ እንዳይረጋጋ እና ቀጥሎም መንግስትን ማዋከብ ተፈልጓል።
 • በእዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ ላይ ከውስጥ ሆነው በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ በክፍተኛ አመራር ላይ ያሉ ከጽንፈኞቹ ጋር የሚሰሩ አሉ።እነኝህ ከሁሉም ገለልተኛ መስለው ሁሉንም እየወቀሱ ግን የጽንፍ ኃይሉን የሚደግፉት አጀንዳውን በይበልጥ ከመንግስት ወገን ሆነው በማራገብ ነው።
የኦሮምያ ክልል ህዝብ በጊዜ መንቃት አለበት።
 • አሁን በትምሕርትቤቶች ውስጥ ህጻናቱን ኦሮሞ የሆነ እና ያልሆነ የሚል ክፍፍል ለመፍጣር በንጹሃን አዕምሮ ላይ ወንጀል መስራት ተጀምሯል።ይህንን የኦሮሞ ህዝብ በስሙ የሚደረገውን ንግድ ሊቃወመው ይገባል።
 • የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የጸናችው በእነ ጀነራል ጃጋማ ኬሎ፣ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ እና በሌሎች ሚልዮኖች የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ነው።ዛሬ ከህወሃት የተሰጣቸውን ዓርማ እና መዝሙር ይዘው አዲስ አበባ ላይ ህዝብ ለመከፋፈል የሚነሱ የጽንፍ ኃይሎችን መቃወም ከኦሮምኛ ተናጋሪው ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል።
መንግስት ማድረግ የሚገባው 
 • ፌድራል መንግስት ላይ ተቀምጠው እንደኦሮምያ ክልል አስተዳደር ኢትዮጵያን ለማስተዳደር የሚሞክሩትን በጊዜ አደብ ማስገዛት አለበት።እነኝህ ናቸው የአዲስ አበባ ህዝብ ጥላቻ ስላለበት ነው የሚል የተሳሳቱ ቃላትን በመግለጫዎቻቸው ላይ እየሰነቀሩ ጉዳዩን ሌላ ቅርጽ እንዲይዝ የሚያደርጉት። የአዲስ አበባ ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያዊ የሆነ የማንም ክልል ቋንቋ ማንም በፍላጎቱ አይማር የሚል ቅሬታ የለውም። 
 • አዲስ አበባ በተለየ መልኩ የሁሉም ክልል መኖርያ መሆኗን የኦሮምያ ክልል የጽንፍ ኃይሎች እንዲያውቁ ለመጨረሻ ጊዜ ማሳወቅ ብቻ ሳይሆን ህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት አዲስ አበባን መብቷን ሊያከብርላት ይገባል።አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጎን የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ ብትሰቅል ይመጥናታል።
 • በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች በአዲስ አበባም የሰንደቅ ዓላማ አሰቃቀል ሥነ ስርዓት በተለይ በትምህርት ቤቶች በሚገባ እንዲተገበር ልዩ የቁጥጥር ሥርዓት ማውጣት አለበት። ዛሬ በአዲስ አበባ ከእዚህ በፊት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይሰቅሉ የነበሩ ሁሉ ከጭቅጭቅ በሚል ያልሰቀሉ መኖራቸው ተሰምቷል። ይህ የመንግስት የመኖር እና አለመኖር መገለጫ አንዱ ማሳያ ነው። በሃገሪቱ ዋና ከተማ የሃገሩ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን በአግባቡ ማሰቀል ያልቻለ መንግስት ማለት ትርጉሙ ብዙ ነው።
ለማጠቃለል የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ከኦሮምያ ክልል አርማ እና ህወሓት ቀርጾ የሰጠውን የኦሮምያ ክልል ዓርማ እና ደርሶ የሰጠውን  መዝሙር ከልሉ ውጭ በአዲስ አበባም ካልዘመርኩ ማለት የጽንፈኝነት የመጨረሻው ጥግ ነው።የአዲስ አበባ ህዝብ ኢትዮጵያውያን በፈቃዳቸው ኦሮምኛ አይማሩ አላለም።ይህንን በሃሰት የሚያራግቡ አመራሮች ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው።እደግመዋለሁ፣በፍላጎቱ ማንም በቋንቋው አይማር በሚል የአዲስ አበባ ሕዝብ አልተቃወመም።አዲስ አበባ የሁሉም ክልሎች መኖርያ ስለሆነች አንድ ክልል ለብቻው ተነጥሎ ዓርማውን በትምሕርትቤቶች መስቀሉ ግን አደጋ አለው ሕገመንግስታዊም አይደለም እያለ ነው።ከጭቅጭቅ በሚል አጓጉል አካሄድ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያልተሰቀለባቸው ትምሕርት ቤቶችም በፍጥነት ሰንደቅ ዓላማውን መስቀል ሕገመንግስታዊ ግዴታቸው ነው!

No comments: