ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, December 28, 2022

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በታላቅ ግርማ ሞገስ በሰዓታት ውስጥ ከመቀሌ አሉላ አባነጋ አየር ማረፍያ ጀምሮ መቀሌን መቆጣጠር ይጀምራል!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ


በእዚህ ምጥን ጽሑፍ ስር ፡ 
  • ምስጋና ለኢትዮጵያ ህዝብ ይገባዋል፣
  • አድናቆት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራር ያስፈልጋል።
  • የትግራይ፣አፋር እና አማራ ክልሎች በጋራ በየትኛውም ወገን ለሞቱ ወገኖች ለሦስት ቀናት የሃዘን ቀናት ቢያውጁ፣ 
  • የኢትዮጵያ ሕዝብ ዐይኑን በጨው ሳይሆን በአጃክስ አጥቦ ለታየው የህወሃት አመራር እንዴት ዓይነት ንስሃ እንደሚገባ እየጠበቀ ነው።
=========
ጉዳያችን ምጥን
=========

የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ የደም እና የአጥንት መስዋዕትነት የከፈለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በታላቅ ግርማ ሞገስ ከሰዓታት በኋላ የመቀሌን አሉላ አባነጋ አየርማረፍያን ጨምሮ መቀሌን ይቆጣጠራል።መከላከያ ላለፉት ተከታታይ ወራት የህወሓትን ታጣቂ ኃይል በተቀናጀ እና ልዩ በሆነ ኦፕሬሽን በሦስት አቅጣጫዎች በመግባት የትግራይ ሁሉንም ከተሞች ነጻ ካወጣ በኋላ መቀሌን በቅርብ እርቀት ከቦ መቆየቱ ይታወቃል።በእዚህም መሰረት ወደ መቀሌ የመግባቱ ሂደት እንደተጀመረ ህወሓት ትጥቅ ለመፍታት እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር በመስማማቱ መከላከያ መቀሌን ከቦ እንዲጠብቅ ታዞ ነበር።በመቀጠል በፕሪቶርያ፣ደቡብ አፍሪካና ናይሮቢ፣ኬንያ ድርድር ከተደረገ እና ህወሃት ትጥቅ ለመፍታት በፊርማ ካረጋገጠ በኋላ መከላከያ ወደ መቀሌ ከሰዓታት በኋላ በታላቅ ግርማ ሞገስ ወደ መቀሌ እንደሚገባ ታውቋል።

ምስጋና ለኢትዮጵያ ህዝብ ይገባዋል!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ህወሃት በከፈተው ኢትዮጵያን የመበተን ዘመቻ ወቅት ኢትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃ እንድትኖር ከህይወት መስዋዕትነት እስከ ንብረቱ ከፍሏል። እዚህ ላይ ግን ለማንሳት የምሞክረው ህዝብ ውስጣዊ አንድነቱን ከመጠበቅ ባለፈ ህወሃት ህዝቡን ለማጫረስ በትግራይ ህዝብ እና በቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ መሃል ግጭት ለመፍጠር የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ቢከፍትም በመሃል ሃገር በሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ አንዳች የግጭት ኮሽታ ሳይሰማ እርስ በርሱ ተደጋግፎ የህወሓትን የመሃል ሃገር የግጭት ድግስ አክሽፏል።ለእዚህም ምስጋና ይገባዋል።

አድናቆት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራር ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ እጅግ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ አልፋለች።ይህም ሆኖ ደግሞ እጅግ ጥበብ የተሞላበት እና ትዕግስት የሚፈልግ አመራር የሚያስፈልግበት ጊዜ ነበር።የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራር ከህወሃት ጋር የሰላም መንገድ ለመከተል የቻለውን ሁሉ አድርጓል።የሰላም ጥረቶቹን በተመለከተ ይህንን ሊንክ ተጭነው ማዳመጥ ይችላሉ።

በእነኝህ ሁሉ ጥረቶች ሳይሳኩ ሲቀሩ እና የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ ሲወድቅ ደግሞ በቀጥታ ወደ ጦር ግንባር በመዝመት ለኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን መሪ መሆናቸውን አሳይተዋል።ይህ ብቻ አይደለም በአሁኑ የሰላም ሂደት ላይም በርካታ ውጣ ውረዶችን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያን ብቻ በመመልከት ብዙ ጉዳዮችን በትዕግስት እንዳለፉ እና አሁን ለተደረሰበት የሰላም ሂደት ደረጃ እንዲደርስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ አመራሩ ጥረት እና ቅንነት የተሞላበት ሂደት ያደረገውን አስተዋጾ ለመረዳት ይቻላል።ለእዚህ የሰላም ሂደት የመንግስት አመራር ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።ይህንን ለመረዳት አንድ ሰው ቤተመንግስት ውስጥ መሆን የለበትም። የህወሃትን እኩይ አካሄድ በመመልከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አመራራቸው ለሃገር ሲባል ብዙ ትዕግስት ለማድረጉ በቀላሉ ማወቅ ይቻላል።

የትግራይ፣አፋር እና አማራ ክልሎች በጋራ በየትኛውም ወገን ለሞቱ ወገኖች ለሦስት ቀናት የሃዘን ቀናት ቢያውጁ፣

በአማራ እና በአፋር ክልል በህወሃት ዘመቻ በብዙ ሺህ ሰላማዊ ዜጎች ላይ እልቂት ተፈጽሟል፣ሴቶች ተደፍረዋል፣ንብረት ተዘርፏል።በተመሳሳይ መንገድ በትግራይ በህወሃት አስገድዶ ዘመቻ እንደ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አደራዳሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የናይጀርያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ገልጻ ከሆነ ከግማሽ ሚልዮን በላይ ህይወቱ አልፏል።

ይህ በእንዲህ እያለ በትግራይ ቤተሰባቸውን ያጡ ሰዎች ለቅሶ እንዳይቀመጡ የህወሃት ካድሬዎች እያስፈራሩ እንደሆነ ተሰምቷል።ከእዚህ ሁሉ በላይ ግን በሦስቱ ክልሎች በጦርነቱ የብዙ ሰው ቤት በሃዘን ተውጧል።ሃዘን ደግሞ ጊዜ ተወስኖለት ስሜቱን መግለጹ በራሱ የሰላም ሂደት ነው።አብሮ መብላት ብቻ ሳይሆን አብሮ ማልቀስም ያስማማል።እዚህ ላይ በቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ወለጋን ጨምሮ የነበረው የሞት ቁጥር ሳይገባ በሦስቱ ቦታዎች ብቻ ሃዘን ለምን? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል።ሆኖም ግን ይህ የሶስት ክልሎች በአንድነት በሚጋሩበት ቦታ የነበረው የንጹሃን እልቂት ቁጥር እና ውድመት እጅግ ከባድ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በቀጣይም ተመሳሳይ ችግር የፖለቲካ አካሎች ቢያስቡም ህዝብ ግን ባለው ጊዜ ህመሙን በጋራ ሃዘን አስታሞ በመጪው ጊዜም ህወሃት መልሶ ወደ ግጭት እንዳይመራው ውስጣዊ አንድነቱን ማጠናከሩ ጥቅም አለው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዐይኑን በጨው ሳይሆን በአጃክስ አጥቦ ለታየው የህወሃት አመራር እንዴት ዓይነት ንስሃ እንደሚገባ እየጠበቀ ነው።

ለእዚህ ምንም ዓይነት ማብራርያ አያስፈልገውም።የህወሃት አመራሮች ከግማሽ ሚልዮን በላይ ህዝብ አጫርሰው በከረቫት ብቅ ብለው መታየታቸው እና አለማፈራቸው የኢትዮጵያ ህዝብ የእየቤቱ መነጋገርያ ነው።አሁን ለራሳቸው ንስሃ ገብተው ዳግም ኢትዮጵያን ከልብ ይቅርታ ይጠይቃሉ ወይንስ በለመዱት አፋቸው ደልለው መልሰው ሃገር ያምሳሉ? የሁሉም ጥያቄ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን እየጠበቀ ነው።

በመጨረሻም አሁን ኢትዮጵያ እየሄደችው ያለው መንገድ ወደ ጽኑ ሰላም እና አንድነት እንዲመራልን ለእዚህም አምላኳ እንዳይለያት የሁላችንም ጸሎት ሊሆን ይገባል።
=================////=========

No comments: