ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, December 16, 2022

ብልጽግና የኢትዮጵያ የነገ ተስፋ የሆኑ ልጆቿን የሚከፋፍል አጀንዳ በአዲስ አበባ እያራመደ ነው።አስገራሚው ነገር የፓርቲው የሌሎች ክልል አባላት ይህንን ሃገር በታኝ አጀንዳውን ለማስቆም ምንም ጥረት ሲያደርጉ አለመታየታቸው ነው።  • ድርጊቱ ምንም ዓይነት የጎሳ ፖለቲካ ቅብ ለመቀባት ቢሞከር የድርጊቱ ዋና ግብ የኢትዮጵያን መጪ ትውልድ መከፋፈል እና ኢትዮጵያን ማዳከምን መድረሻው ያደረገ የመርዝ ብልቃጥ ነው።
  •  በምድር ላይ ያለ ማንም መንግስት የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማውን የሚገዳደር  የአንድ ክልል ሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ተማሪዎቹ እየዘመሩ እርስበርሳቸው እንዲከፋፈሉ ሲያደርግ ተሰምቶ አያውቅም።

=========
ጉዳያችን ምጥን
=========

አንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ብልጽግን በጎሳ ፖለቲካ የማያምን እንደሆነ ሲናገሩ '' እኛን ብልጽግናዎችን አትከፋፍሉን።እኛ ብልጽግናዎች ከዘር የተከፋፈለ አስተሳሰብ የጸዳን ነን። እኛ የምንሰራው ለአንዲት ኢትዮጵያ ነው።'' ማለታቸውን አስታውሳለሁ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ይበሉ እንጂ በብልጽግና ውስጥ የተሰገሰጉ ህዝብ የሚያውቃቸው ዋልታ ረገጥ የለየላቸው አክራሪ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ግን መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር።ይህም በመሆኑ ዛሬ ላይ ኦሮምያን እንደ አንድ ሃገር የምትመስላቸው ለሕግም ለሕዝብም የማይገዙ ጡቷን አጥብታ ያሳደገቻቸው ኢትዮጵያ ነገ ልጆቿ በአንድነት እና በፍቅር ተምረው አድገው እኩል ብሔራዊ ስሜት እንዳይኖራቸው ለማድረግ እንቅልፍ ያጡ ፖለቲከኞች የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ''እኛን አትከፋፍሉን በጎሳ አናስብም '' ካሉት ከብልጽግና ውስጥ ነው።

ሰሞኑን የብልጽግና ኦሮምያ ክልል ተወካዮች በየትኛውም የሕግ አግባብ የሌለ እና የኢትዮጵያ የነገ ተስፋ ልጆች ነገ አድገው እንዳይግባቡ ለማድረግ ከፋፋይ ዘመቻ በይፋ ተከፍቶባቸዋል። በየትኛውም የዓለም ክፍል የሌለ በአንድ ትምሕርት ቤት ውስጥ ሁለት መዝሙር እና ሁለት ሰንደቅ ዓላማ ለመስቀል ከራሱ ከብልጽግና የተወከሉ የአዲስ አበባ ባለስልጣናት ካለምንም እፍረት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና ፋና ብሮድካስት እየቀረቡ ይህንን የመከፋፈል አጀንዳ ሲመጻደቁበት መታየታቸው ነው።

በአዲስ አበባ ትምሕርት ቤቶች የኦሮምያ ክልል ዓርማ  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በሚገዳደር መልኩ እንዲሰቅል፣የክልሉ መዝሙርም የሃገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር በሚጋፋ መልኩ እንዲዘመር የአዲስ አበባ ክልል አስተዳደር ባለስልጣናት የጀመሩት ተግባር የኢትዮጵያን መጪ ትውልድ ለመበተን ያለመ እና የባዕዳን ተልዕኮ ያለበት ነው።ምንም ዓይነት የጎሳ ፖለቲካ ቅብ ለመቀባት ቢሞከር የድርጊቱ ዋና ግብ የኢትዮጵያን መጪ ትውልድ መከፋፈል እና ኢትዮጵያን ማዳከም ነው።ይህ ምንም ዓይነት ምርምር የማይጠይቅ ግልጽ እና ጥርት ያለ ጉዳይ ነው። በምድር ላይ ያለ ማንም መንግስት የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማውን የሚገዳደር  የአንድ ክልል ሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ተማሪዎቹ እየዘመሩ እርስበርሳቸው እንዲከፋፈሉ ሲያደርግ ተሰምቶ አያውቅም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የቱ ጉዳይ ምን ያህል እርቀት ሃገር እንደሚበትን፣የትኛው በትዕግስት ቢታለፍ ለጊዜው ችግር እንደሌለው ጠንቅቆ እና ልቅም አድርጎ ያውቃል።የቱ ጋር መሞት እንዳለበት የቱን በትዕግስት ማለፍ እንዳለበት ይረዳል። ችግሩ መሪዎቹ ያወቁት ሲመስላቸው አያውቁትም።የተረዱት ሲመስላቸው ሁል ጊዜ እንደ እንግዳ ደራሽ ሲደናገሩ ህዝቡ ቀድሞ ከፊታቸው ይደርሳል። በሰሞኑ የአዲስ አበባ ተማሪዎች የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን እና መዝሙር በሚጋፋ መልኩ የኦሮምያ ክልል መዝሙር እና ዓርማ እንዲዘመር እና እንዲሰቀል የሚወተውቱት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና በፋና እየቀረቡ የሚናገሩት አሳፋሪ፣አንድ ፊደል ቆጥርያለሁ ኢትዮጵያ ጡቷን አጥብታ አሳድጋኛለች ብሎ የሚያስብ ዜጋ የማይናገረው ኃላፊነት የማይሰማው ንግግር ነው።

በመጀመርያ ከከንቲባ አዳነች ጀምሮ ምክትል ከንቲባው አቶ ዣንጥራር እና የአዲስ አበባ ክልል አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ ከንቲባዋ ሕዝብ ሲያወያዩ የተናገሩት አቶ ዣንጥራር በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ታኅሳስ 6/2015 ዓም የተናገሩት እና ታኅሳስ 7/2015 ዓም አቶ ሳምሶን መለሰ ደግሞ በፋና ቴሌቭዥን ቀርበው ሲናገሩ ጉዳዩን የአዲስ አበባ ህዝብ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ኦሮምኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በቋንቋቸው እንዳይማሩ ከመፈለጉ አስመስሎ ለማቅረብ ብዙ ሲጋጋጡ ማየት እራሱን የቻለ ድራማ ነው። ይህ በራሱ የተቀመጡበትን የሕዝብ ወንበር ክብር አለመስጠት ነው። አቶ ሳምሶን ፋና ቴሌቭዥን ላይ ጋዜጠኛ ዳዊት መስፍን ደጋግሞ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ላይ አይደለም ጥያቄው እያለው መልሶ ወ/ሮ አዳነች እና አቶ ዣንጥራር ሲሉት የነበረውን ስለአፍ መፍቻ ቋንቋ ለማስረዳት በመሞከር ዋናውን ጥያቄ ለማለፍ የሞከረው ሙከራ አስቂኝ ነበር።ጋዜጠኛ ዳዊት ግን አልለቀቀውም ደጋግሞ ወደ ዋናዋ ጥያቄ ''በአዲስ አበባ የኦሮምያ ዓርማ እና የክልል መዝሙር ከብሔራዊ መዝሙር ጋር እንዲዘመር የሚያዝ የሕግ አግባብ አለ ወይ?'' በማለት ጠየቀ።

የእዚህን የጉዳያችን ምጥን የማጠቃልለው ድርጊቱ ምን ያህል የኢትዮጵያን መጪ ትውልድ ለመከፋፈል የታለመ የባዕዳን እጅ እንዳለበት የሚያመለክተውን መልዕክት ከላይ በፋና ቴሌቭዥን ዓርብ ታኅሳስ 7/2015 ዓም አቶ ሳምሶን መለሰ በግልጽ አስቀምጠውታል። በእዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ ጋዜጠኛ ዳዊት ጠየቀ -
''የኦሮምያ ዓርማ እንዲሰቀል ያደረግነው እና የክልሉ መዝሙር እንዲዘመር የተደረገው ኦሮምኛ የሚማሩ ልጆች ስላሉ ነው ብለዋል።አዲስ አበባ ደግሞ ብዙ ብሔሮች አሉ እና ነገ ሌሎቹ ኢዲስ አበባ በቋንቋቸው ሲማሩ እነርሱም የክልላቸውን ሰንደቅ ዓላማ እንዲሰቀል፣የክልላቸውም መዝሙር እንዲዘመር ታደርጋላችሁ?''

አቶ ሳምሶን የአዲስ አበባ ትምሕርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሲመልሱ ''አዎን እናደርጋለን '' ነበር ያሉት።

ይህ ምላሽ በራሱ የሚገልጸው የኦሮምያ ክልል መዝሙር፣ዓርማ የተባለው ሁሉ ግቡ የኢትዮጵያን መጪ ትውልድ ዋና እምብርት የሆኑትን ትምሕርትቤቶች ማዕከል አድርጎ ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ስሜትን ማጥፋት እና መከፋፈል ነው።ይህ ደግሞ እየተሰራ ያለው በብልጽግና ውስጥ ከፍተኛ ባለስልጣናት በብሔር ከተደራጁ የጽንፍ ኃይሎች ጋር እጅና ጓንት ፈጥረው እያራገቡት ያለው አጀንዳነው።ብልጽግና የኢትዮጵያ የነገ ተስፋ የሆኑ ልጆቿን የሚከፋፍል አጀንዳ በአዲስ አበባ እያራመደ ነው።አስገራሚው ነገር የፓርቲው የሌሎች ክልል አባላት ይህንን ሃገር በታኝ አጀንዳውን ለማስቆም ምንም ጥረት ሲያደርጉ አለመታየታቸው ነው።

==========////==========

ይሄንን በልጅነቱ በኢትዮጵያ ፍቅር የተቃጠለ ትውልድ ለመበተን ነው ዓላማው።
የዜግነት ክብር!No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...