ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, January 12, 2022

ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ



👉ብቸኛው የጦርነቱ ማሳረጊያ ምንድን ነው?

👉መንግስት ለትግራይ ህዝብ ከህወሃት የመውጫ ስልት (Exist Strategy) ያዘጋጅ።

👉መንግስት እና ህዝብ በጋራ በጥንቃቄ ሊይዙት የሚገባው ጉዳይ።

=====================

ጉዳያችን ልዩ /Gudayachn Special

=====================

''አልገባችሁም!'' ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ

ሻምበል ፍቅረስላሴ ''እኛና አብዮቱ'' በተሰኘው መፅሐፋቸው ውስጥ የደርግ አባላት ወደ ቤተ መንግስት ሄደው ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ዘንድ ቀርበው ከንጉሱ የገጠማቸውን አስገራሚ ምላሽ በመጽሃፋቸው እንዲህ ሲሉ አስፍረዋል።

''የፖለቲካ እሥረኞች በሙሉ እንዲፊቱ የሚለው ጥያቄ እንደተነበበ ንጉሡ ጣልቃ ገብተው “ለመሆኑ የፖለቲካ እሥረኞቹ እነማን ናቸው?” የሚል ጥያቄ አቀረቡ። “በእርግጥ የምናውቃቸው የፖለቲካ እሥረኞች ባይኖሩም ማንኛውም የፖለቲካ እሥረኛ እንዲፈታ ነው የምንጠይቀው” አሉ ሻለቃ ተስፋዬ ገብረኪዳን። ንጉሡ ራሳቸውን ነቅነቅ አድርገው ጽሑፉን የሚያነበውን የደርግ አባል እየተመለከቱ “አልገባችሁም!” ብለው ዝም አሉ። በእርግጥም አልገባንም። ተማሪዎችና የተለየ ዓላማ የነበራቸው የተማሩ ሰዎች የሰነዘሩትን መፈክር ብቻ ነበር ይዘን ንጉሡ ፊት የቀረብነው። በፖለቲካ እሥረኝነት ስም በከፍተኛ ደረጃ ለጣሊያን ወራሪ መንግሥት በባንዳነት አድረው አገራችንን የወጉ፣ ለቅኝ ተገዥነትም የዳረጉትን እንደ ኃይለሥላሴ ጉግሳ ያሉ ወንጀለኞች የፖለቲካ እሥረኞች ተብለው ከግዞትና ከእሥር ቤት አስወጥተን እንደ ጀግና ራሳቸውን እንዲቆጥሩ አደረግናቸው።''

ከላይ የተጠቀሰው የሻምበል ፍቅረ ስላሴ መጽሐፍ አስተማሪ መልዕክት አለው።ሆኖም ግን የእዚያን ጊዜ ሁኔታ ከዛሬው ጋር እንዳለ መግጠም ላይሰራ ይችላል።በአንድ ወቅት እስረኛ መፍታት ስህተት ከነበረ ሌላ ጊዜ አንዴት ይታያል? የራሱ ጥናት ይፈልጋል።አንዳንድ ታሪካዊ ክስተቶች ትክክለኛነታቸውን ለመረዳት በራሱ ጊዜ እና የጠራ መረጃ ይፈልጋሉ።ዛሬ ትክክል አይደለም የምንለው ነገ በታሪክ መነፀር ሲታይ ትክክል ሊሆን ይችላል።ዛሬ ስህተት የምንለውም ነገ በታሪክ ሲቃኝ ትክክል ሊባል ይችላል።የዛሬው ጽሑፍ መነሻ ስለ እስረኛ መፈታት ጉዳይ አይደለም።መነሻ አና መድረሻው ስለ 3 ጉዳዮች ነው። እነርሱም -

ብቸኛው የጦርነቱ ማሳረጊያ ምንድን ነው?

መንግስት ለትግራይ ህዝብ ከህወሃት የመውጫ ስልት (Exist Strategy) ያዘጋጅ።

መንግስት እና ህዝብ በጋራ በጥንቃቄ ሊይዙት የሚገባው ጉዳይ የሚሉት ናቸው።

============

ብቸኛው የጦርነቱ ማሳረጊያ ምንድን ነው?

ሽብርተኛው ህወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ ጦርነት ከፍቶ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያልፈነቀለው ድንጋይ ባይኖርም በመጨረሻ የሞት ጣር ላይ መውደቁ ዕውን ሆኗል።ከእዚህ ሁሉ ጥፋት በኋላ ህወሃት ለትግራይ ያተረፈው ሞት እና እልቂት ነው።አሁን ጥያቄው የጦርነቱ ማሳረጊያ ምንድን ነው? የሚለው ነው። አንዳንዶች ድርድር የሚደረግ እና በእዚያ የሚቋጭ አድርገው የሚያስቡ አሉ።አንዳንዶች በተራዘመ ሁኔታ ህወሃትን ማዳከም እና በመጨረሻ እጁን ማሰጠት የሚሉ አሉ።ሌሎች ሌላ ሃሳብ ሊሰጡ ይችላሉ።ይህ ሁሉ ግን የመጨረሻው መፍትሄ በተለይ ለህወሃት ዓይነት ሽብርተኛ ቡድን የሚያዋጡ መንገዶች አይደሉም።

ስለሆነም ለየትኛው የጦርነት ማሳረጊያ እንዘጋጅ? የመጨረሻው የጦርነቱ ማሳረጊያ ምንም ዓይነት ምክንያት በመስጠት ቢዘገይም ለሃገር መፍትሄው እና የጦርነቱ ማሳረጊያ መከላከያ መቀሌን እና ትግራይን ከህወሃት አላቆ ህዝቡን ነጻ ማውጣት ነው።ይህንን መቼም የማይቀረው የመድረሻ ግቡን መወሰን እና አጥርቶ ማስቀመጥ አስፈላጊ የሚሆነው ለዘማቹም ሆነ ነጻ ለሚወጣው ህዝብም የስነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ ጠቃሚ ስለሚሆንም ጭምር ነው።በእርግጥ ሁሉም መንገድ ተሞክሯል።ከመቀሌ መልስ የሆነ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይኖር እና ከእዚህ መለስ የሚኖር መፍትሄ የአማራ እና የአፋር ህዝብን ሲያደማ የሚያኖር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የጸጥታ ዋስትና ስጋት ላይ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ያላት ተደማጭነት ያኮስሳል። ስለሆነም የጦርነቱ ማሳረጊያ መከላከያ ወደ ትግራይ ገብቶ ህወሃትን ማንበርከክ እና ቢያንስ ከእዚያ በኋላ ህወሃትን ተቃውሞ የሚወጣ አንጃ ከራሱ ከህወሃት ውስጥ ከወጣ ንግግር ሊታሰብ የሚችለው መከላከያ መቀሌን ሲቆጣጠር ነው።

አንዳንዶች ህወሃት መከላከያ ወደ መቀሌ ገብቶ የበለጠ እልቂት እንዲፈጠር እና ለዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብ ለማሳጣት ይፈልጋል።ስለሆነም አለመግባቱ ጥሩ ስልት እንደሆነ ያብራራሉ።ይህ በአንድ ወቅት የሚያስማማ ሃሳብ ሊሆን ይችላል።በቅርቡም ይህንኑ ተንኮል መንግስት በማወቁ ከመግባቱ መቆጠቡ ለወቅቱ ትክክለኛ መፍትሄ ሊሆን ይችላል።ሆኖም ግን መከላከያ ለረጅም ጊዜ ሳይገባ ቀርቶ ህወሃት ከአሁኑ ፈተና በውጭ ድጋፍም ተነስቶ የህዝቡን ማህበራዊ እና የምጣኔ ሃብት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ትንሽ የመውተርተርያ ጊዜ ካገኘ ሃማስ በሊባኖስ መሬት ቆንጥጦ እንዴት ነቀርሳ እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል። ስለሆነም መቀሌ የመግቢያ ጊዜው መዘግየት እና የመዘግየቱ የጊዜ እርዝመት መመጠን እና ትክክለኛውን ጊዜ መምረጥ ደግሞ አስፈላጊ ነው።በምንም ዓይነት መንገድ ብናስበው የጦርነቱ ማሳረጊያ መከላከያ መቀሌ መግባቱ መሆኑን ሁሉም ሊረዳው ይገባል።

መንግስት ለትግራይ ህዝብ ከህወሃት የመውጫ ስልት (Exist Strategy) ያዘጋጅ።

የመንግስት ለትግራይ ህዝብ የጽሞና ጊዜ መስጠቱ ትክክለኛ ነው። መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አገናዝቦ የወሰደው እርምጃ ነው።በተለይ የጽሞና ጊዜው ቀድሞ ያልተረዳ የህወሃት አድናቂ ከአሁኑ የኢትዮጵያ ድል በኋላ በደንብ እንደሚገባው ግልጥ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት የህወሃት ወራሪ ጀሌ በአማራ እና አፋር ላይ የሰሩት የፋሺሽት ስራ ለታሪክ ተቀምጦ አሁንም በትግራይ ላይ ጥፋት እንዳይደርስ አሁንም የትግራይ ህዝብ ህወሃትን በማስወገድ ተግባር ላይ ግንባር ቀደም እንዲሆን ዕድል ተሰጥቶታል።

ይህ በእንዲህ እያለ ግን ህዝብ ድንገት ተነስቶ ያውም እንደ ህወሃት ላለ ወደ ግማሽ ክፍለዘመን ለሚሆን ጊዜ በጠባብነት እና በጥላቻ ፖለቲካ ያደነዘዘው የትግራይ ህዝብ በዘገምተኛ የአብዮት ለውጥ ህወሃትን ያስወግዳል ማለት አይቻልም።ስለሆነም ሁለት ጉዳዮች መሟላት ይፈልጋሉ። እነርሱም ህዝቡን ሸብበው የያዙትን በሃይል ማስወገድ ኢና ለህዝቡ ከህወሃት የሚላቀቅበት የመውጫ ስልት ማቅረብ ናቸው።ሸብበው የያዙትን በሃይል ማስወገድ አሁንም መንግስት እየሰራው ያለው ጉዳይ ነው። ቀሪው መንግስት አዘጋጅቶ ማቅረብ ያለበት ''የማርያም መንገድ '' መኖር አለበት። ይህ መንገድ ደግሞ ለህወሃት አመራሮች ሳይሆን ለትግራይ ህዝብ ህወሃትን የሚያስወግድበት የመውጫ ስልት ነው።ይህ ስልት በራሱ ተጠንቶ እና ተዘርዝሮ መቅረብ ያለበት ቢሆንም እንደመንደርደርያ ግን መንግስት የሚከተሉትን የመውጫ ስልቶች እና አፈጻጸሞች መመልከት ይቻላል። እነርሱም

  • ተከታታይ መልዕክቶች ለትግራይ ህዝብ በሚል መተላለፍ አለበት 
  • ህወሃትን ሊተካ የሚችለው እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ በተሻለ አቀራረብ እና የሰው ሃይል ቢያንስ ሳምንታዊ መግለጫ መስጠት። በእዚህ መግለጫ የትግራይ ህዝብ እራሱ የማያውቃቸው አጠገቡ የተፈጸሙ ጉዳዮች ጨምሮ ተያያዥ ጉዳዮች መውጣት አለባቸው።ለምሳሌ በአንዱ የትግራይ ክፍል የተነሳ ጸረ ህወሃት እንቅስቃሴ በልዩ መግለጫ መውጣት አለበት ።
  • ከህወሃት መሃከል ያሉ የሃሳብ ልዩነቶችን ለትግራይ ህዝብ በእየዕለቱ ማቅረብ እና በሂደት የነገሮች አካሄድ እያየ የህወሃት ሞትን ማለማመድ።
  • ከራሱ ከትግራይ ህዝብ የተውጣጡ ሽምቅ ተዋጊዎች ትግራይን ከህወሃት ነጻ ለማድረግ እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ ማድረግ እና መከላከያ ከጎናቸው ሆኖ እንዲገፉ ማድረግ እና 
  • ከእዚህ በፊት በጉዳያችን እንደተገለጠው ወደ ትግራይ የሚተላለፍ ትልቅ ጉልበት ያለው የራድዮ እና የቴሌቭዥን ስርጭት በየቀኑ በልዩ ፕሮግራም እንዲደርስ ማድረግ። እዚህ ላይ ኢቢሲም ሆነ ሌሎች በትግርኛ የሚተላለፉ ስርጭቶች አሏቸው።በጦርነት ጊዜ የሚደረግ ልዩ የፕሮፓጋንዳ ስርጭት ከመደበኛ አሰራሮች የተለየ ስለሆነ ልዩ ስርጭቱ በከፍተኛ ወጪም ቢሆን በጀት ተመድቦ መሰራት ያለበት ነው። አሁንም ቢሆን በከፍተኛ ባለሙያዎች የታገዘ ስራ ይፈልጋል። ይህ ስራ ለህዝቡ በተለያየ መንገድ በአይሮፕላን ወረቀት ከመበተን ጀምሮ በድንገት የስልክ መስመር ከፍቶ በትግራይ ላሉ ስልኮች ሁሉ መረጃ መላክን ይጨምራል። እዚህ ላይ የመብራት አገልግሎት በክልሉ የለም ቢባልም ከተከዜ ግድብ እና በነዳጅ አንዳንድ ከተሞች አሁንም ብቅ ጥልቅ የሚል መብራት መኖሩ እየተሰማ ስለሆነ የመረጃ ስርጭቱን መንግስት ቢቀጥልበት ይችላል።
ከላይ የተጠቀሱት መንደርደርያ የመውጫ ስልቶች ዋና ግባቸው የጦርነቱ ማሳረግያ የሆነው የመከላከያ ወደ ትግራይ መግባት በማያስደነበር መንገድ ብቻ ሳይሆን ከህወሃት ለመገላገል የቸኮለ ህዝብ ስነ ልቦና የማዘጋጀት ሂደት አካል ነው።

መንግስት እና ህዝብ በጋራ በጥንቃቄ ሊይዙት የሚገባው ጉዳይ።

አሁን ባለበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብ የህወሃት ሽብርተኛ ቡድንን ከጦር ሜዳ ውግያ እስከ ተቋማት ሰርጎ መግባት ሙከራ ለመመከት ጭሏል። ሆኖም የጁንታው የመጨረሻ ምሽግ ያለው በፕሮቴስታንት፣የኦርቶዶክስ እና የእስልምና የእምነት ተቋማት ውስጥ ነው። እነኝህ ተቋማት እጅግ የበሰሉ፣ሃገራቸውን የሚወዱ እና በመንፈሳዊ ህይወታቸው ምሳሌ የሆኑ አባቶች የመኖራቸውን ያህል ተቋማዊ መዋቅሩ ላይ ህጋዊ በሆነም ሆነ ባልሆነ መንገድ የተቀመጡ መኖራቸው ይታወቃል። በእነኝህ መዋቅሮች ላይ ደግሞ ሙስና እና ጥቅመኝነት ውስጥ የተዘፈቁ ስላሉ ከእዚህ ላለመውጣት ሲነኩ ሌላ ህዝብ እና መንግስት የሚያጋጩ ጉዳዮች እየመዘዙ ሃገር እንዳያምሱ መንግስት እና ህዝብ በጥንቃቄ በመመልከት መጓዝ አስፈላጊ ነው።

የሁሉም ገዢ ሃሳብ የጋራ የሆነች ኢትዮጵያ ነች። በዕምነት ተቋማት ውስጥ ያለው ብልሹ አሰራሮች የማስተካከል ስራ መቼም ቢሆን ቀጠሮ ሊሰጠው አይገባም። አሰራሩን ለማስተካከል ግን የመንግስት ጥበቃ እንዳለ ሆኖ በራሳቸው ከውስጣቸው በሚወጡ እውነተኛ የእምነቱ ልጆች እንዲከወን አማኙም ሆነ መንግስት የመስራት ሃላፊነት አለባቸው። መንግስት የተባለ ተቋም በራሱ ከእምነት ተቋማቱ ውጭ ስላልሆነ የሚና አለያየት እንጂ አንዱ አንዱን አይመለከትህም ተባብሎ ተቋማቱን ከሙስና የማጽዳት ስራ በራሱ ከባድ ያደርገዋል።ሆኖም ግን በራሱ ይስተካከል ተብሎ መተዉ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር የሚጎዳት ብቻ ሳይሆን፣ድህረ ጦርነት የእምነት ተቋማት ያላቸውን እጅግ ጠቃሚ ሚና እንዳይጫወቱ ያደርጋል።

ስለሆነም ተቋማቱን ማጠናከር የእምነታቸውን አፈጻጸም ሳይሆን የቢሮ አሰራራቸውን እና የአገልግሎታቸውን ተደራሽነት የተከታዮቻቸውን መንፈሳዊ እርካታ በሚሰጥ መልኩ እንዲሁ ከአሁኑ ካልተደረገ በሁሉም የጦርነት ሰለባ በሆኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች ህዝቡን በቀላሉ ስነ ልቦናውን ለማከም ያስቸግራል።ስለሆነም ልዩ ትኩረት ይፈልጋል።የዕምነት ተቋማት በኢትዮጵያ የግጭት ምክንያት ሊሆኑ አይገባም።ህዝቡ አኗኗሩን እያወቀበት ተቋማቱ እንዲፋጠጡ ለማድረግ የሚሞክሩት እነኝሁ ያልጸዱት አደናባሪዎች መሆናቸውን መረዳት ቀላል ነው።ስለሆነም የእምነት ተቋማት፣ህዝብ እና መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል።

ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ትልቁን የፈተና ጊዜ ያለፈችው ይመስላል። አሁን ከስሜታዊነት በራቀ መልኩ አፈጻጸሙን ማሳመር ነው።ለእዚህ ደግሞ የጦርነቱ ማሳረግያ ምንም ጊዜ ቢወስድ መድረሻው መቀሌን እና ትግራይን ከጁንታው ማስለቀቅ ነው።ይህንን ለማድረግ ደግሞ የጽሞና ጊዜውን መልክ ለማስያዝ ለትግራይ ህዝብ የመውጫ ስልት ነድፎ ማቅረብ እና መምራት ይፈልጋል። ለድህረ ጦርነት የህዝብ ስነ ልቦና መታከም ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት ያለባቸውን የአሰራር እና የሙስና ችግር ህዝብ እና መንግስት ተባብረው ማስተካከል እና ኢትዮጵያን ሊያግዙ የሚችሉ በጋራ አጀንዳዎች ላይ ሁሉ ምዕመናኖቻቸውን የሚያንቀሳቅሱ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ እንዳይሆን ግን በእምነት ተቋማቱ ውስጥ በጁንታው የተሰማሩ የቀድሞ ካድሬዎች የአሁን ደግሞ ሙሰኞች መጽዳት አለባቸው።

=========////=============

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...