ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, January 21, 2022

በወይብላ ማርያም ላይ የተፈፀመው ወንጀል ከባድ የሚያደርገው በራሱ በመንግስት መዋቅር ስር ባለ አካል መፈፀሙ ነው።ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም መንግስት መውሰድ ያለበት የመፍትሄ እርምጃ።




በአዲስ አበባ ቀራንዮ መድሃኔዓለም አካባቢ የወይብላ ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ታቦታት፣ ጥር 12፣2014 ዓም ወደማደርያቸው እየተሸኙ ሳለ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከከበሮው ላይና እጃችሁ ላይ ማየት የለብንም ያሉ ፖሊሶች በሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ ከአስለቃሽ ጭስ እስከ ጥይት ተኩሰውባቸዋል::ታቦታቱም ወደ መንበራቸው መመለስ ስላልቻሉ ወደቀራንዮ መድሐኔዓለም ሔደው በእዚያ አድረዋል::ፖሊስ በተኮሰው ጥይት አራት ወጣቶች ተመተው ሆስፒታል ገብተዋል::ትናንት ከመሸ ህይወቱ ያለፈ እንዳለ ተሰምቷል::ዛሬም የሌላው ወጣት ህይወት ማለፉ እየተነገረ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው የአደባባይ በዓላት ውስጥ የጥምቀት በዓል አንዱ እና ዋነኛው ነው።በዓሉ መከበር የጀመረው በአጼ ገብረመስቀል ዘመን ከዛሬ 1500 ዓመት በፊት ማለትም በ5ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ ነው።የበዓሉ አከባበር ላይ ስርዓት በመስራት በ12ኛው ክ/ዘመን ቅዱስ ላልይበላ፣በአጼ ይኩኑ አምላክ ዘመን የነበሩት ኢትዮጵያዊው ታላቅ ቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት በኋላም በ15ኛው ክ/ዘመን አጼ ዘርያዓቆብ ክብረ በዓሉ ደምቆ እንዲከበር ስርዓቱን አጽንተው ለትውልድ አስተላልፈዋል።የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ በዓል ነው።በክርስትና ታላቅ ቦታ የሚሰጠው የእግዚአብሄር ልጅ የመሆን ታላቅ ሃብት የሚገኝበት የጥምቀት መታሰቢያ በዓል በመሆኑ እና ይህንንም እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ መስርቶት የሄደው ስርዓት ነው።ጥምቀት አንዴ ወንድ በ40 ሴት በ80 ቀን የሚፈጸም የማይደገም ስርዓት ሲሆን ይህ በየዓመቱ የሚደረገው የጥምቀት በዓል ለመታሰቢያ የሚደረግ የእግዚአብሄር ታላቅ ውለታ የሚዘከርበትም ጭምር ነው።

የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ችግሮች መፈጠር የጀመሩት በዘመነ ህወሃት ነው።ከአዲስ አበባ ወጣ ባሉ ቦታዎች ለምሳሌ እንደ ሃረር፣ድሬዳዋ፣ባሌ ገጠራማ ቦታዎች እና በወልዲያም ጭምር ለጥምቀት በዓል የወጡ ምዕመናን ተንገላተዋል።በወልዲያ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳይቀር በህወሃት አጋዚ ወታደሮች ተገድሏል።በዘመነ ህወሃት የጥምቀት በዓል እንደ ህዝብ ከህዝብ ማጋጫ ሆኖም ቀርቧል። በተለይ በሙስሊሙ እና በክርስቲያኑ መሃል ጸብ ለመጫር ህወሃት ሆን ብሎ በዋዜማው አጋጪ የሆኑ መግለጫዎች በማውጣት ውጥረቶች እንዲከሩ ያደርግ ነበር። በእዚህም ሙስሊሙና ክርስቲያኑ እርስ በርሱ እንዲጠላላ እና እንዲፈራራ ለማድረግ ያልተደረገ ጥረት የለም።የድምጻችን ይሰማ የሙስሊሙ እንቅስቃሴ እንደ አክራሪ እንቅስቃሴ በክርስቲያኑ ዘንድ እንዲታይ ህወሃት ብዙ ጥረት አድርጓል። ይህ ሁሉ ግን አልተሳካም።

ከህወሃት ወደ መቀሌ መባረር በኋላ ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ አዲሱ ጥቃት የታየው ከኦሮሞ ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው አካላት በህወሃት የተተረከላቸውን ቤተክርስቲያኒቱ የነፍጠኛ ነች የሚለው ትርክት ሰለባዎች ነበሩ።እነኝህ ቤተክርስቲያንን እና ኢትዮጵያ ሲባል የሚያማቸው ከሁሉም ደግሞ በሰንደቅ ዓላማዋ ላይ ጥርስ የነከሱ የአናሳ አስተሳሰብ አራማጆች ናቸው።

የዘንድሮም የጥምቀት በዓል ቀድሞ ችግር የነበረባቸው የድሬዳዋ፣ሃረር እና ጅጅጋ ሳይቀር በጣም ባማረ እና ከሁሉም በላይ የሙስሊም ወንድሞች፣እህቶች እና እናቶች በኮሚቴ ሆነው የጸጥታ ስራውን አብረው የሰሩበት ለክርስቲያን ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ውሃ እና ሌላ የሚያስፈልገውን ሁሉ እያቀረቡ ያስተናገዱበት ጊዜ ሆኖ አልፏል።ለቪኦኤ አማርኛው ከድሬዳዋ ሃሳባቸውን የገለጡ የሙስሊም እናት ሲናገሩ የድሬዳዋ የድሮ ፍቅሯ ዘንድሮ ተመልሷል። እናቶች ከየመንደሩ ተውጣጥተን በጋራ ጥበቃ እያደረግን በጥሩ ሁኔታ አልፏል በማለት ገልጠውታል።የጅጅጋ እና የሃረር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ መቃርዮስም በዓሉ በጥሩ ሁኔታ መከበሩን እና ይህንን ላደረጉ የጸጥታ አካላት ሁሉ የከበረ ምስጋና አቅርበዋል።

ይህ ሁሉ ጥሩ ነገር እያለ ግን ከአራት ኪሎ በጥቂት እርቀት የምትገኘው የወይበላ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከላይ እንደተገለጠው አሳዛኝ ሁኔታ ደርሷል።የችግሩ ግዝፈት ደግሞ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ጥቃት የሚፈጽሙት አካላት አደገኛነት በራሱ በመንግስት መዋቅር ውስጥ መሆናቸው ነው።ምዕመናኑ በፖሊስ የመጠቃታቸው ምክንያት ደግሞ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን ለምን ያዛችሁ የሚል ነው።ይህ ትልቅ ህመም ነው።ይህ ካለምንም ማጋነን ጦርነት ያስነሳል። መንግስት የተባለ አካል በራሱ መዋቅር ውስጥ ያለ የኦሮምያ ፖሊስ በእዚህ ያህል ደረጃ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጠል መሆኑን እያወቀ ውሎ ማደሩ በራሱ አነጋጋሪ ነው። ችግሩ ከራሱ የመንግስት መዋቅር ስር ለመሆኑ የጥምቀት በዓል ዋዜማ ላይ የወጣው የፖሊስ መግለጫ በራሱ ገላጭ ነው።መንግስት ሁለት እና ሶስት የተለያዩ መግለጫዎች ሊኖሩት አይገባም።በመጀመርያ የወጣው መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ኮክቡን ካላየን መሰል መግለጫ ከተደመጠ በኋላ መልሶ የአዲስ አበባ መስተዳደር አርሞ አቅርቦታል።ይህ ሁሉ መደናበር ምንድን ነው? ይህ በራሱ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና የሰንደቅ ዓላማዋ ጠል ቡድን የመንግስትን ስልጣን በመጠቀም ህዝብ ለማስፈራራት እየሞከረ እንደሆነ አመላካች ነው። ህዝብ ማስፈራራት ብቻ ሳይሆን የኦሮምያ ፖሊስ ምዕመናኑን በትኖ በወጣቶች ላይ ተኩሶ ህይወት አልፎ ታቦታቱ ወደ ቦታቸው ሳይገቡ አድረዋል።

አሁን ያለፈውን ሳይሆን ወደፊት ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጸም ምን ይደረግ? የሚለው ነው ዋናው ቁም ነገር። ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም የሚለያት ህዝቧ ከ95% በላይ የሚሆነው በዕምነት ውስጥ የሚኖር ህዝብ ነው።ይህ ማለት ሃገሪቱ የልማት ዕቅዷም ሆነ የመንግስት ባህሪ ለአማኙ ህዝብ ትልቅ ዋጋ መስጠት እና እሴቱን ሊጠብቅ እና ሊጠነቀቅ ይገባዋል ማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህግ ደግሞ በሃይማኖት እሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በከፍተኛ ወንጀል ፈርጆ እጅግ ከባድ ቅጣት እንዲፈረድ አያደርግም። ሃይማኖት የህዝብ ስስ ብልት ነው።ሃይማኖቱ ሲነካ በቀላሉ ሃገር ይታመሳል።ከሞት በኋላ ያለውን ህይወት ዋጋ የሚሰጥ ህዝብ ያለበት ሃገር ዛሬ ስለ ሃይማኖቱ መሞት ክጽድቅ በላይ የሆነ ጽድቅ ነው።

ህዝባቸው ከ75% በላይ አማኝ ባልሆነባቸው እንደ አውሮፓ ያሉ ሃገሮች ብቻ ሳይሆኑ በብዙ የአፍሪካ ሃገሮች ህግ ላይ ማንም ሆነ ማንም በአንድ መስጊድ ወይንም ቤተክርስቲያን ላይ ትንሽ የተባለ የማናናቅ ወይንም ምዕመኑን የሚያስቆጣ ጥፋት ከፈጸመ እጅግ ከባድ የሆነ ቅጣት ይጠብቀዋል።ስለሆነም የሃይማኖት ተቋማት እጅግ ይከበራሉ።መንግስትም የሚሰጠው የህግ ከለላ ከፍ ያለ ነው።ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ አይታይም።ምናልባት በህጉ ላይ ይቀመጥ እንጂ ዝርዝር የጠበቁ ህጎች በአዲስ መልክ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መውጣት አለበት። ለህጉም ተፈጻሚነት ጥብቅ ክትትል ያስፈልገዋል።ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሙስሊምም ሆነ ክርስቲያን በዕምነት ተቋሙ ላይ አንዳች ማንም እንደማያደርግ ዋስትና ያስፈልገዋል። ይህ ህግ ደግሞ ከታች ያሉ ተማሪዎች ሁሉ እንዲማሩት ማድረግ ያስፈልጋል።አሁን በኢትዮጵያ የሚጎድለው ይህ ነው።የዕምነት ተቋማት ላይ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሳይቀሩ ያላቸው መብት ምን ያህል ውሱን እንደሆነ አያውቁም ወይንም እያወቁ የፖለቲካ ማጋጫ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው።ስለሆነም የዕምነት ተቋማትን በማናቸውም መንገድ ያጠቃ ማንኛውም ግለሰብ የሚደርስበት ቅጣት ከፍተኛ እና አስተማሪ እንዲሆን የሚያሳይ የነበረውን ህግ የሚያጠናክር ህግ የተወካዮች ምክር ቤት ማውጣት እና መንግስት የማስፈጸም ተግባሩን ሊወጣ ይገባል። ህጉ የሚወጣው ለጨዋው የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም።ህዝቡ ለሺህ ዓመታት ተከባብሮ ኖሯል።ለባለጌ ግን የህጉ ተጠናክሮ መውጣት ስርዓት ያስይዛል።ችግሩ ህግ በማውጣት ብቻ አያበቃም።ያጠፉት መቀጣት አለባቸው።በወይብላ ማርያም ምዕመናን ላይ የተፈጸመው የኦሮምያ ፖሊስ ጥቃት በተመለከተ ይህንን ያደረጉት የፖሊስ አባላትም ሆነ ትዕዛዙን ያስተላለፉ በህግ ሲቀጡ ማየት ህዝብ ይፈልጋል። ስለሆነም መፍትሄዎቹ ግልጥ ናቸው። የተወካዮች ምክር ቤት በእምነት ተቋማት ላይ የሚደረግ ማናቸውም ጥቃት እና የጥቃት ሙከራ በተመለከተ ህጉን ማጥበቅ አለበት።ከእዚህ ጋር በተያያዘ እንደከእዚህ ቀደሙ ተድበስብሶ መታለፍ የሌለበት የወይብላ ማርያም ጉዳይ ተጣርቶ ወንጀለኞች ለህግ መቅረብ አለባቸው።

==========////==========





No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...