ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, January 11, 2022

ነገረ መስቀል አደባባይ


መስቀል አደባባይ

===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============

  • ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከስሜታዊ እና በአንድ ወገን ለመደነቅ ከመፈለግ የተነሳ የሚደረግ ስሜታዊ ንግግር ሊታቀቡ ይገባል።
  • የአደባባዩን ሂሳብ ካነሱትም ከንቲባዋ እንዳሉት አይደለም።
  • ከንቲባ አዳነች ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው።
መስቀል አደባባይ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ አካል

የመስቀል አደባባይ ከ1966 ዓም በፊት በመስቀል አደባባይነት የታወቀ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀል ደመራን ስታከብርበት ኖራለች።በንጉሱ ዘመንም ልዩ ልዩ ትርዒቶች እና የክብር ዘበኛ ሰልፍም ይታይበት ነበር። ከ1966 ዓም በኋላ ወታደራዊው መንግስት አሁን አደባብዩ ያለውን ቅርጽ ኢንዲይዝ የህዝብ መቀመጫውን ከመሬት ከፍ ለማድረግ ከቦሌ መንገድ የቀድሞው ወሎ ሰፈር አካባቢ ከድልድዩ ጎን ከነበረው ኮረብታ ላይ አፈር እያመጣ ደለደለው።ይህ ኮረብታ ያለበት ቦታ ላይ ደግሞ ባለ አራት ፎቅ አፓርታማ ሰርቶ ለኪራይ ቤቶች እንዲያከራይ ሰጠው። በመቀጠል አደባባዩን አብዮት አደባባይ በማለት ሰይሞ የማርክስ፣የኤንግልስ እና ሌኒን ፎቶ ሰቀለበት።በእዚህም ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ''በተቀደሰው ስፍራ እርኩሰት ቆሞ ስትመለከቱ አንባቢው ያስተውል '' የሚለውን የመጽሃፍ ቃል እየጠቀሱ ይነጋገሩበት ነበር። ሆኖም ግን ከ1983 ዓም በኋላ አደባባዩ የመስቀል አደባባይ ስሙ ተመለሰለጥ

መስቀል አደባባይ የኢትዮጵያ የግማሽ ክፍለዘመን ታሪክ በአደባባዩ አልፏል። በ1970 ዓም መጀመርያ ላይ በምስራቅ ኢትዮጵያ ዘልቆ የገባው የሱማሌ ወራሪ ሃይል ለመፋለም የዘመተው ሰራዊት የተሸኘው በእዚህ አደባባይ ነበር። የኢትዮጵያ ታላቁ የዓባይ ግድብ መሰረት ከተጣለ በኋላ የአዲስ አበባ ደስታውን የገለጠው በእዚሁ አደባባይ ነበር።በ2010 ዓም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ ሰልፍ ወጥቶ ለውጡን መደገፉን የገለጠበት እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የግድያ ሙከራ የተፈጸመውም በእዚሁ አደባባይ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ በመስቀል አደባባይ የሆነው 

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ መስቀል አደባባይን በተመለከተ አንድ ውዝግብ ተነስቶ ነበር። የውዝግቡ መነሻ ፓስተር ዘላለም የተሰኘ የፕሮቴስታንት ፓስተር ''መስቀል አደባባይን እንውረስ '' የሚል ጥሪ በማድረግ በአደባባዩ ላይ አንድ የፕሮቴስታንት ዝግጅት እንዳለ ጥሪ አደረገ። ይህንን ተከትሎ ሰባኪ ወንጌል ምህረተአብ እና የጅጅጋ እና የሱማሌ ክልል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ መቃርዮስ በአንድነት ሆነው የፕሮቴስታንት ፓስተር የተናገረውን ንግግር አወገዙ።በተለይ አቡነ መቃርዮስ የፓስተሩ ንግግር በህዝብ መሃል ጸብ የመዝራት ተግባር ስለሆነ ትክክል እንዳልሆነ ገለጡ። ይህ በእንዲህ እያለ እሁድ ይደረግ የነበረው የ''ኖ ሞር ' ሰልፍ ለሳምንት ተላልፎ የፕሮቴስታንት ዝግጅት ቀረበ።በዝግጅቱ ላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተገኙ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዝግጅቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ ስሜታዊነት የታየበት ነበር።ድምጻቸው ቁርጥ፣ቁርጥ እያለ አደባባዩ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀረጥ የተሰራ ስለሆነ የሁሉም ነው፣ የሚል ዐረፍተ ነገር ጨምሮ ሌሎች ዐረፍተ ነገሮችን አከታትለው ንግግር ሲያደርጉ በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የፕሮቴስታንት ተከታዮች በእየመሃሉ ላይ በጭብጨባ ያጅቧቸው ነበር።

ከንቲባ አዳነች በንግግራቸው ላይ ማንሳት የሞከሩት በቅርቡ መንግስት አደባባዩን ከማደሱ ጋር ተያይዞ የታደሰው በህዝብ ገንዘብ ነው እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ብቻ አይደለም የሚል ትርጉም ይዟል።ይህ በእንዲህ እያለ የአደባባዩ ዕድሳት ሲጀመር በወቅቱ የነበሩት ከንቲባ ታከለ ኡማ ከቤተ ክህነት ጳጳሳት እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ተጠሪዎች ተገኝተው በፕሮጀክቱ ሂደት ላይ ያላቸውን ምክረ ሃሳብ የጠየቁት የአደባባዩ ባለቤትነት ስላወቁ ነው። ዛሬ በጉዳዩ ላይ ልዩ ስብሰባ የጠራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንደሚሉት ከፕሮጀክቱ መጠናቀቅ በኋላ ርክክብ እንደሚደረግ ቃል ተገብቶ እንደነበር እየተናገሩ ነው።ቤተክርስቲያኒቱ የአደባባዩ የባለቤትነት ካርታ ጨምሮ ማስረጃዋ እንደማያወላዳ ብዙ ጊዘ ገልጣለች።

ከንቲባ አዳነች ያነሱት የዕድሳት ሂሳብ ጉዳይ  

መልሱን በጥያቄ ነው የምመልሰው።
  • የኢትዮጵያ ቱሪዝም የጀርባ አጥንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አይደለችም እንዴ?
  • ኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ ከምታገኘው የቱሪዝም ገቢ (በጥናት የተደገፈ ነው) በመስቀል ደመራ፣በገና እና በጥምቀት ወቅት የምታገኘው ገቢም ሆነ የቱሪስቱ ፍሰት ከ80% በላይ የሚሆነው በእነኝህ የቤተክርስቲያኒቱ በዓላት ወቅት መሆኑን ከንቲባ አዳነች ያውቃሉ?
  • የሚመጡት ቱሪስቶች ከ70% በላይ የሚሆኑት የሚጎበኙት የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅርሶች እና ገዳማት እንደሆነስ ያውቃሉ?
  • ላሊበላ ብቻ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት በአንድ ዓመት ብቻ ከ5 ሚልዮን ዶላር በላይ ከጎብኚዎች ለመንግስት ማስገባቱን ያውቃሉ? ላሊበላ ይህንን ያህል ገቢ እያስገባ የረባ የለስላሳ መጠጫ ቦታ እንደሌለውስ ያውቃሉ?
  • በገዳማት የሚደረጉ የቱሪስት ጉብኝቶች ገቢ ቤተ ክርስቲያኒቱ ምንም እየተጠቀመች አለመሆኑ እና የገቢ ደረሰኞቹን ቱሪዝም እንደሚካፈል ያውቃሉ?
  • ይህ ሁሉ ቱሪስት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሳቢያ መምጣት የስንት ሆቴሎች፣የትራንስፖርት ሰጪዎች፣የአገልግሎት ሰጪዎች እና ተያያዥ የሆኑ የስራ ዕድል በሚልዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች እንደከፈተስ ያውቃሉ?
ይህ ማለት የመስቀል አደባባይ የተገነባበት ገንዘብ ላይ መተሳሰብ የሚለውን ከንቲባ አዳነች ማንሳት ይሌለብዎት ሂሳቡ ሲታሰብ እርስዎ እንዳሉት ሳይሆን ሌላ ስለሆነ ነው። በመስቀል ደመራ ሳብያ የመጣው ቱሪስት ብቻ አስር የአሁኑ ዓይነት ዘመናዊ የመስቀል አደባባዮች አይሰራም እንዴ? ለምን የሂሳብ መተሳሰብ ጉዳይ ውስጥ ገቡ? ይህ ስሜታዊ የሆነ እና አብሮ የሚኖር ህዝብ መሃል ትክክል ያልሆነ አገላለጥ ስለሆነ ይቅርታ መጠየቅ አለብዎት።

አደባባዩ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ይበዛባታል እንዴ?  

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ችግር በሚገባ ነገሮችን ከስሩ ጠንቅቆ አለማወቅ ነው።ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቅርብ ዓመታት ባሳዩት የስራ ትጋት እና አፈጻጸም ህዝብ ጥሩ አመለካከት ይዟል።በገቢዎች ሚኒስቴር እና በመቀጠል በአዲስ አበባ አስተዳደር እየሰሩ ላሉት ስራዎች አክብሮት አለኝ።ነገር ግን ሁሉን ነገር ደግሞ ያውቃሉ ማለት አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚያውቁትን በራሳቸው የማያውቁትን አማካሪ መድበው ነው የሚንቀሳቀሱት። አሁን በአዲስ አበባ አስተዳደር አንጻር የሚታየው የአማካሪ ጉድለት ይመስለኛል። አዲስ አበባ የራሷ ፍልስፍና አላት። 

መስቀል አደባባይ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ይበዛባታል እንዴ?
  • ክርስትናን ጌታችን ባረገ በዓመቱ በ34 ዓም በጃንደረባው ክርስትናን ለተቀበለች ሃገር (ሃዋርያት ስራ 8) የራሷ የመስቀል አደባባይ ቢኖራት ይበዛባት ይሆን?
  • የክርስቶስን ግማደ መስቀል በክብር ተቀብላ በግሸን ደብረ ከርቤ ላስቀመጠች ቤተ ክርስቲያን ዓለም ይህንን ዜና እንዲያውቅ በስሙ የተሰየመውን መስቀል አደባባይ በባለቤትነት ይዛ ይህንኑ ለዓለም ለማሳየት መስቀል ሰቅላ አደባባዩ የመስቀል አደባባይ መሆኑን ለዓለም ቢታይላት የኢትዮጵያ መንግስት የሆነ ሁሉ የሚኮራበት ታሪካ አይሆንም ወይ?
  • በዓለም ላይ የእውነተኛ መስቀሉ በቆስጠንጢኖስ እናት ንግስት እሌኒ መገኘቱን የተገኘበትን የደመራ ስነ ስርዓት በዓለም ላይ በብቸኛነት የምታከብር ቤተ ክርስቲያን ይህንንም ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የመዘገበላት ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነው የመስቀል አደባባይ አድምቃ እና አክብራ መያዟ ለሃገር ኩራት፣ለትውልድ ቅርስ ነው እንጂ ክፋቱ ምኑ ላይ ነው?
  • ለመሆኑ ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ከመዘገበ በኋላ አሻራውን የሚያሳይ ምን ምልክት በአደባባዩ ላይ ተደረገ?
ሌሎች በርካታ ጥያቂዎችን ማንሳት ይቻላል። አዲስ አበባም ሆነች ሌሎች ከተሞች የቦታ ችግር የለባቸውም። ሁልም ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ላይ ባይተዋርነት ሊሰማው አይገባም። ለሙስሊም ወንድሞቻችንም ሆነ ለፕሮቴስታንት ተከታዮች ደረጃቸውን የጠበቁ አደባባዮች መኖሩ አስፈላጊ ነው።ይህ ግን ዜጎች በእምነታቸው እንዲጋፉ እየተደረገ መሆን የለበትም።በተለይ እንደመንግስት፣በተለይ እንደ ዋና ከተማ ከንቲባ አንድ አደባባይ የተሰራበት የገንዘብ ወጪ ስሌት ውስጥ ገብቶ ንግግር ማድረግ ስህተት ነው። ለወቅታዊ ችግር አፋጣኝ ውሳኔ መስጠት እና አሁን ያለውን የኢትዮጵያውያንን ህብረት ማጠናከር የመንግስት ሃላፊነት ነው።

=================////////============

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...