ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, January 23, 2022

በኢትዮጵያ በሚፈጠሩ አንዳንድ ቅሬታዎች ማኩረፍ አይገባም።በጋራ የባለቤትነት እና በበጎ ህሊና አብሮ ማቅናት ያስፈልጋል።



በእዚህ ጽሑፍ ስር -

- ኢትዮጵያ አሁን የት ላይ ነች?
- በወይብላ ማርያም የደረሰው ጥቃት ጉዳይ እና የአዲስ አበባ አስተዳደር መግለጫ፣
- በኢትዮጵያ ፈጽሞ ተስፋ አይቆረጥም!
=============
ጉዳያችን / Gudayachn
=============

ኢትዮጵያ አሁን የት ላይ ነች?

አሁን ኢትዮጵያ ያለችው የት ነው? ብለን ብንጠይቅ እና ያለችበትን ለመቃኘት ብንሞክር ማነፃፀርያ ያስፈልገናል።ይህንን ጥያቄ በጥቂት ዓረፍተ ነገሮች መግለጡ አስቸጋሪ ነው።አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን አንደየአመለካከቱ ሁሉም የተለያየ ሃሳቦችን ሊሰጥ ይችላል።ለእዚህ አጭር ጽሁፍ የሚሆነው ማነፃፀርያ ግን ከሕወሓት ወደ መቀሌ ሲሸሽ የነበረችው ኢትዮጵያን ማሰብ አና ዛሬ ያለችበትን መመልከት በቂ ነው።ህወሓት ወደ መቀሌ በሸሸበት ጊዜ በኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካው ጦዞ እጅግ አደገኛ የመጠፋፋት ፖለቲካ ጫፍ የደረሰበት፣በኦሮምያ ክልል የነበረው የፅንፍ ጫፍ ከማበጡ የተነሳ ፋብሪካዎች በየቀኑ የምነዱበት፣የሱማሌ ክልል ለራሱ ለክልሉ ተወላጅም ሆነ ከሌላ ክልል ለመጡ ሁሉ ሲኦል የሆነበት፣የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ተሟጦ ብድር መክፈት የማትችል ብቻ ሳይሆን ህወሓት ከግል የአውሮፓ አና አሜሪካ ባንኮች ሳይቀር በከፍተኛ ወለድ ተበድሮ ገንዘቡ የት አንደደረሰ ያልታወቀበት፣ በዲፕሎማሲው ረገድ ደቡብ ሱዳን ሳትቀር የህወሓት አትዮጵያ አንድታደራድረኝ አልፈልግም በሴራ ፖለቲካ እየተበተቡኝ ነው ብላ የወቅቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩምን ገላምጣ ያባረረችበት፣የኢትዮጵያ ጉዳይ አደገኛ ደረጃ ላይ ከመድረሱ የተነሳ ባልተለመደ መልክ የሩስያ አና የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአንድ ቀን አዲስ አበባ ገብተው ነገሩን ያነፈነፉበት ጊዜ ነበር።ባጭሩ ኢትዮጵያን አጅግ የተወሳሰበ አና በጎሳ ፖለቲካ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ትቷት ህወሓት ወደ መቀሌ በሸሸበት ጊዜ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ኢትዮጵያን የተረከቧት።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ መጀመርያ ባዶ የሆነውን የሀገሪቱን ካዝና ከተባበሩት የአረብ ኢምሬት ድጎማ ከመጠየቅ ጀምሮ ሳይውሉ ሳያድሩ አንገብጋቢውን የትምህርት ፖሊሲ ጉባዔ ከፈቱ፣በመቀጠል ወደ ጅጅጋ የመጀመርያ ጉዞ አድርገው በእዚያ ያለውን ችግር የመገምገም ስራ ሰሩ።

ይህ በእንዲህ እያለ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ የት ላይ ነች? ብለን ስንጠይቅ በብዙ ችግር ውስጥ አልፋ፣ችግሮቿ ሁሉ ባይቀረፉም፣ዛሬም ጽንፈኞች እና ሽብርተኞች እረፍት ባይሰጧትም፣ከትልቅ አደጋ ግን ተርፋለች ማለት ይቻላል።ይህ ማለት ወደፊት ሌላ መልኩን የተቀየረ ፈተና አይገጥማትም ማለት አይቻልም። ሆኖም ግን መጪው ተስፋ ደግሞ እጅግ ትልቅ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በእዚህ ሁሉ የጦርነት ሂደት ውስጥ የሃገሪቱ ፕሮጀክቶች ግን አልቆሙም።የአባይ ግድብ፣መከላከያን ጨምሮ የሚሰሩ የመዋቅር ስራዎች መቀጠል፣ከፍተኛ የውጭ ዲፕሎማሲ በመቋቋም ህልውናዋን ማስጠበቅ መቻል እና ለሎች ሊጠቀሱ የሚችሉ ተግባራት አሉ።ሁሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ ተደርጎ ማቅረብ ራስን በስነ ልቦና ቀድሞ የመግደል ያህል ነው።ከእዚህ ይልቅ ተስፋ ሰንቆ፣በጎውን አጎልብቶ በጋራ መስራት አና ኢትዮጵያ ትውልድ አንድወጣላት መስራት ነው አስፈላጊው ጉዳይ።

በወይብላ ማርያም የደረሰው ጥቃት ጉዳይ እና የአዲስ አበባ አስተዳደር መግለጫ

ኢትዮጵያ በህወሃት ተተክሎባት ያሰቃያት የጎጠኘነት ነቀርሳ የተለየ ትርክት ይዞ በኦሮምያ ክልል የመንግስት መዋቅር ውስጥ በስውር እንዳለ ምንም የሚያጠራጥር ጉዳይ የለም።የጎሰኝነት በሽታው በኦሮምያ ክልል ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክልል በተለያየ መጠን ቢኖርም በገንዘብ፣በመዋቅር እና በአሰራር በኦሮምያ ክልል ያለው ግን ለራሱ ለክልሉ ነዋሪም አለፍ ሲልም ለመንግስትም አደጋ አለው። ባለፈው ሃሙስ በወይብላ ማርያም ታቦተ ህጉ ለጥምቀት በዓል ወጥቶ በሚመለስበት ጊዜ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይዛችሁ አታልፉም በሚል የኦሮምያ ክልል ፖሊስ ወጣቶችን አስተባብሮ ምዕመኑን ከመበተን በላይ ሶስት ወጣቶች በተተኮሰባቸው ጥይት ተገድለዋል።

ይህንን አጉራ ዘለል ጥቃት ከመንግስት ባለስልጣናት ለምሳሌ አቶ አገኘሁ ተሻገር በትውተር ገፃቸው ላይ
''ሰሞኑን በ አአ ከተማችን የጥምቀት በአልን ተከትሎ ታቦት ይለፍ አይለፍ በሚል በተነሳ ግጭት ህይወታቸው በተቀጠፉ ወጣቶች እጅግ በጣም አዝኛለሁ። የህን ችግር በፈጠሩ የፀጥታ አካላት ላይ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ለህግ መቅረብ አለባቸው።'' በማለት ገልጠዋል።በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ፣ኢዜማ፣ባልደራስ እና የእናት ፓርቲ መግለጫ አውጥተዋል። በእዚህ መሰረት ኢዜማ የግጭቱ መነሻ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከመንጠቅ ባለፈ የሃገር ልብስ ላይ ያለ ጥለት፣ቲሸርት ሳይቀር በኦሮምያ ፖሊሶች ሲከለከል እንደነበር በመግለጫው ላይ አካቷል።ባልደራስ ባወጣው መግለጫ ላይ በምዕመኑ ላይ ጥቃት የፈጸሙ ለፍርድ እንዲቀርቡ ሲጠይቅ፣እናት ፓርቲ ደግሞ የኦሮምያ ክልል ማብራርያ እንዲሰጥ በመግለጫው ላይ ጠይቋል።

ይህ በእንዲህ እያለ የአዲስ አበባ መስተዳድር ያወጣው መግለጫ ላይ ''በዓላት በመጡ ቁጥር ድብቅ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ ሃይሎች በኢትዮጵያ ሰላም የለም ለማስባልና የአሸባሪውን ቡድን ተቀጥላ ፍላጎቶች ለማስፈፀም፤ በህዝብ የተመረጠን መንግስት በአመፅና ግርግር ለማውረድ ፤ በህዝቦች መሃከል ጥርጣሬና ግጭት ለመፍጠር፤ ብሎም ህዝባዊ በአሉን ወደለየለት ትርምስ ለመክተት፤ ህዝብን የሚሸብሩ ድርጊቶችን ለመፈፀም አቅደው ቢንቀሳቀሱም ሀገሩን እምነቱንና ባህሉን አክባሪ የሆነው ህዝባችን ባደረገው ርብርብ በዓሉ ጠላት በተመኘው ልክ ሳይሆን በሰላም ተጀምሮ በሰላም ተጠናቋል::'' ካለ በኋላ ወጣቶች ኢትዮጵያ በእግዚአብሄር እጅ ነች ለማለት እና ''ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች'' የሚለውን የመጽሃፍ ቅዱስ ቃል ለማሳየት የሰሩት እና በአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ይዘው የወጡትን ቅርጽ እንደ ጸብ ጫሪ የቆጠረበት መንገድ አስገራሚ ሆኗል።

የመስተዳድሩ መግለጫ ይህንን ክስተት የገለጠበት ዓረፍተ ነገር እንዲህ ይላል ''ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአራዳ ክ/ከተማ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አጠገብ ፀብ አጫሪና አሳፋሪ ድርጊት እንዲሁም ከባህረ ጥምቀቱ ወደ ደብሯ በመመለስ ላይ በነበረችው በወይ ብላ ማርያም ታቦት በቡራዩ ከተማ አዋስኝ አካባቢ የገጠማት መስተጓጎል እና ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው አለመግባባት ህይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን የከተማ አስተዳደሩ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶታል፡፡'' ይላል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር መግለጫ ''በአራዳ ክ/ከተማ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አጠገብ ፀብ አጫሪና አሳፋሪ ድርጊት'' ያለው ይህንኑ ወጣቶች የሰሩት የኢትዮጵያ ካርታ በእጅ ላይ ሆኖ የሚያሳየውን ቅርፅ ነው።በእዚህ ደረጃ ይህንን ቅርጽ የተቃወመበት መረጃ የማህበራዊ ሚድያ ላይ ጽንፍ የጠል ቡድኖች ያሉትን መነሻ አድርጎ ይመስላል። ምክንያቱም የከተራ ዕለት ቅርጹ እንደተለቀቀ የጽንፍ የጠል ቡድኖች ጸያፍ የሆነ ስድብ ጨምሮ እየነቀፉ ቪድዮ ሲለቁ ነበር።ወዲያው ይህንን ተከትሎ ቅርጹ እንዲፈርስ በፖሊስ ታዘዘ። እዚህ ላይ ምንም ነገር ቢሆን የሆነ ግጭት የሚያነሳ ከመሰለው ፖሊስ ለመረዳትም ሆነ ለማጤን ጊዜ ሳይኖረው በውክብያ እንዲፈርስ ወሰነ ብንል፣ሁኔታው ካለፈ በኋላ መግለጫ ያወጣው የአዲስ አበባ አስተዳደር በጽንፈኛ እና ጠል ፌስ ቡክ ቀስቃሾች ጋር በተመሳሳይ ካለምንም ማስረጃ ''በአራዳ ክ/ከተማ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አጠገብ ፀብ አጫሪና አሳፋሪ ድርጊት'' በሚል መግለጡ መታረም ያለበት ነው። ይህ ጭስ በሌለበት እሳት ፍለጋ የመሰለ አካሄድ አንድ ትልቅ የመንግስት ተቋም የመረጃ ምንጩ በትክክለኛ መስመር እና በማስረጃ መደገፍ አለበት። ይህ ነገሮችን ወደ አላስፈላጊ መንገድ የመውሰድ አደገኛ አካሄድ ነው።

በኢትዮጵያ ፈጽሞ ተስፋ አይቆረጥም!

በኢትዮጵያ መልካም ስራዎች የመሰራታቸውን ያህል ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፣የጠል ቡድኖች የማህበራዊ ሚድያ ዘመቻዎች እና በኦሮምያ ክልል ያለው የሰንደቅ ዓላም ጠል ቡድኖች እና ይህንንም የክልሉ ፖሊስ ከወጣቶች ጋር ተባብሮ የፈጸመው ጥቃት እና በውጤቱ የሶስት ወጣቶች ህይወት መጥፋቱ እጅግ ልብ የሚሰብር ተግባር ነው። ሌላው ልብ ሰባሪ ተግባር ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ለተፈጸመው ጥቃት ይቅርት አለመጠየቁ እና የተጎዱ ቤተሰቦችን ካሳ ለመስጠት የተሰራ ስራ አለመኖሩ የጠብ መጫሩ እና የጠል አስተሳሰቡ ልክ ማጣቱን ያሳያል።

ይህ ሁሉ ቢሆንም በኢትዮጵያ ተስፋ መቁረጥ ግን ፈጽሞ አይገባም።የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይም በማኩረፍ የባዕድ ስሜት ማንም ሊሰማው አይገባም።ኢትዮጵያ በበጎ ፈቃድ የተወሰኑ ሰዎች የሚሰጡን እና ሲፈልጉ የሚነጥቁን አይደለም።የኢትዮጵያ አባቶች እና እናቶች በመስዋዕትነት ያስረከቡን ሃገር ነች።የችግሮችን መፍትሄ ማንም ዜጋ ሲያቀርብ በባለቤትነት ስሜት መሆን አለበት።ከእዚህ ጋር ደግሞ አብሮ መሄድ ያለበት በበጎ ህሊና በመልካም የተሰሩ ስራዎችን ደግሞ ማበረታታት ያስፈልጋል።አሁን ባለው መንግስት ስራ ውስጥ አንዳንዶች በጭፍን እና ባልተረጋገጠ ጉዳይ በመሰለኝ የሌለ የሴራ ፖለቲካ እንዳለ ከማሰብ ይልቅ በትክክል የቱ ጋር ችግር እንዳለ ለይቶ ያንን የታመመውን ክፍል እንዲታከም መስራት እና መድከም ያስፈልጋል።እዚህ ላይ የሚጠቀሰው አንዱ በኦሮምያ ክልል ያለው የጽንፍ ሃይል ጥፋት ነው። ይህንን መዋጋት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ እና ዕዳም ጭምር ነው።ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እራሱን ለሞት አሳልፎ የሰጠ ኮ/ል አብዲሳ አጋም መሆኑን፣ ለኢትዮጵያ ለመሞት የዘመቱት ጀነራል ጃጋማ ኬሎ እና ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የኦሮምኛ ተናጋሪዎች ከካራማራ እስከ ናቅፋ ህይወታቸውን የሰዉት በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ስር መሆኑን የኦሮሞ ማህበረሰብም በሚገባ ይረዳል።ሆኖም ግን አሁን ላለው ትውልድ በሰፊው ይህንን ታሪክ የማስተማር፣ደጋግሞ የማስረዳት ስራ በተለይ የኦሮምኛ ቋንቋ የሚችሉ በማህበራዊ ሚድያ ጭምር ከአሁኑ ጊዜ ሳይሰጡ መስራት አለባቸው።በኢትዮጵያ በሚፈጠሩ አንዳንድ ቅሬታዎች ማኩረፍ አይገባም።በጋራ የባለቤትነት ስሜት፣በብሩህ ተስፋ እና በበጎ ህሊና አብሮ ማቅናት ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ፈጽሞ ተስፋ አይቆረጥም!
========///=========



No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...