በ1956 ዓም የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ማኅበረሰብ
Photo credit to Peace core
በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚከተሉትን ነጥቦች ያገኛሉ።
- የህወሓት ትምህርት ሚኒስትር ገነት ዘውዴ እና የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ
- ኮሌጁ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስር መውጣት አለበት። ለምን?
- የንግድ ሥራ ኮሌጅ ምሩቃን ማኅበር የት ገባህ? ኮሌጁ ለምን ቦታውን እንዲለቅ ይደረጋል?
የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ በኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስምንት ዓመታት ቀድሞ በ1935 ዓም የተመሰረተ በወቅቱ የንግድ ትምሕርት ቤት በሚል ነበር።የንግድ ትምሕርት ቤቱ ወደ ኮሌጅ ካደገ በኃላም ሆነ በፊት በኢትዮጵያ የመንግስትም ሆነ የግል ዘርፍ የሚያገለግሉ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን አፍርቷል።የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅን ያህል ዕድሜ ጠገብ የሆነ የንግድ ሥራ ላይ አትኩሮ የሚሰራ ኮሌጅ በአፍሪካ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።ከሳሃራ በታች ያሉ ሀገሮች ለምሳሌ እንደ ዩጋንዳው ማካረሬ የመሰሉ በቅኝ ግዛት ዘመን የተመሰረቱ ኮሌጆችም ቢሆኑ በንግድ ሥራ ላይ ብቻ አትኩረው የሚሰሩ አይደሉም።በመሆኑም ከእጅ ያለ ወርቅ ሆኖ እንጂ የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ በዓለማችንም ረዘም ያለ ጊዜ ካስቆጠሩ የንግድ ሥራ ኮሌጆች ውስጥም የሚመደብ ነው።
የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከአውሮፓ ስመ ጥር የንግድ ኮሌጆች ጋር እኩል የተመሰረተ ነው።ችግሩ እኛ እራሳችንን አናውቅም። ለምሳሌ በኖርዌይ የሚገኘው እና ዝነኛው የንግድ ሥራ ዩቨርስቲ 'ቢአይ' BI የተመሰረተበት ዓመት እና የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ የተከፈተበት ዓመት እኩል 1935 ዓም (እኤአ 1943 ዓም) ነው።የኖርዌይ የንግድ ዩንቨርስቲ 'ቢአይ' በአሁኑ ጊዜ ከመላው ዓለም የሚመጡ ተማሪዎች የሚመርጡት እና በጥራቱም በዓለም ካሉት ምርጥ የንግድ ሥራ ዩንቨርስቲዎች በእርሱ ደረጃ ያሉት 1% ብቻ ናቸው። ኢትዮጵያ የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅን ቢያንስ በአፍሪካ ደረጃ ያለ ምርጥ የንግድ ሥራ ኮሌጅ ማድረግ ነበረባት።ነገር ግን ላለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ዛሬም ሰላም ከሚነሷት በታኝ ኃይሎች ጋር ስትዋጋ፣በኃላም እነኝሁ ሲያደሟት የኖሩት ህወሓት ሆነው ቤተ መንግስት ሲገቡ ኮሌጁን ለማቆርቆዝ ሲደክሙ ነው የኖሩት።
የህወሓት ትምህርት ሚኒስትር ገነት ዘውዴ እና የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ
ህወሓት የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ ሲቆጣጠር የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ቀደም ብሎ በወታደራዊው መንግስት መውደቂያ ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ከታወጀው ቅይጥ ኢኮኖሚ አንፃር እየተነቃቃ ነበር።ቀደም ብሎም ኮሌጁ በአሜሪካ እና አውሮፓ ከሚገኙ መሰል ኮሌጆች ጋር ባለው የረጅም ጊዜ መልካም ግንኙነት አንፃር ኮሌጁ በወታደራዊው መንግስት ዘመንም ዕድገቱን አላቆመም። በተለይ ከካናዳ መንግስት ጋር ባለው መልካም ግንኙነት ኮሌጁ ተጨማሪ ክፍሎችን ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ መፅሐፍት ቤቱን የሰራው በወታደራዊ መንግስት ዘመን ነበር።በእዚሁ ዘመንም ብዙ መምህራኑ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ወደየተለያዩ ሀገሮች እየሄዱ የመማር አድል ገጥሟቸዋል። በእዚህ ደረጃ የተደራጀው ኮሌጅ በህወሓት የትምህርት ሚኒስትር ገነት ዘውዴ (እውቁ የቀዶ ጥገና ሐኪም ፕሮፌሰር አስራት ዮዲት ጉዲት ነው የሚሏት) ዘንድ በበጎ አልታየም። ወ/ሮ ገነት ዘውዴ የትምህርት ሚኒስትር በሆኑበት ጊዜ በኢትዮጵያ አዳዲስ የግል ኮሌጆች ብቅ እያሉ ከመምጣታቸውም በላይ የመጀመርያ ዲግሪ መጀመርም ሆነ በዩንቨርስቲ ደረጃ መጠራት ከትምህርት ሚኒስትር ማግኘት ቀላል ነበር።
የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ አስተዳደር የጠየቀው ደግሞ በጣም ቀላል ሁለት ጥያቄዎችን ነበር።እነርሱም የዲግሪ መርሃግብር ለመጀመር እና ወደ ዩንቨርስቲ ደረጃ ለማደግ ነበር።ለእዚህ ደግሞ በወቅቱ ዩንቨርስቲ ከተባሉት እና በዲግሪ ደረጃ እንዲያስተምሩ ከተፈቀደላቸው የግል ኮሌጆች አንፃር የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ በአያሌው ልቆ የሄደ ነበር። ሆኖም ግን ወ/ሮ ገነት ከለከሉ።በወቅቱ የግል ጋዜጦች ሳይቀሩ ይህንን ጉዳይ ፅፈውበት ነበር።ለመከልከሉ አንዱ ምክንያት የነበረው የመቀሌ ዩንቨርስቲ እየተመሠረተ ስለነበር የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲን ጨምሮ ሌሎች ዩንቨርስትዎችን የማቆርቆዝ ፕሮጀክት አካል እንደነበር በግልጥ ህዝቡ ያወራ ነበር። ቆይቶ የሆነውም ይሄው ነበር።የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ በግፊት የዲግሪ መርሃግብር ቆይቶ ቢጀምርም ኮሌጁ ሕልውናውን ይዞ እንዲያድግ ከማድረግ ይልቅ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስር እንዲገባ ተደረገ።በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ፋክልቲ ያለው ቢሆንም የንግድ ሥራ ኮሌጅ እዚያው እንዲገባ ተደረገ።
ኮሌጁ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስር መውጣት አለበት። ለምን?
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ የኢትዮያን ንግድ በዘመናዊ መልክ ለማሳለጥ ትልቅ እና ቁልፍ የሚባል ሚና የተጫወተ ነው።ይህ ኮሌጅ ለኢትዮጵያ ንግድ እድገት ቀያሽ ከመሆን አልፎ የአፍሪካን ዘመናዊ ንግድ ላይ አሻራ ለማስቀመጥ የሚችል ነው። ብዙ ሀገሮች በንግድ ሥራ ላይ ይልቀት ደረጃ ያላቸውን ኮሌጆች ሆነ ዩንቨርስቲዎች ከሌሎች ጋር በመቀላቀል አያዳክሙም። ኢትዮጵያ የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅን አስፍታ እና የበለጠ አልምታ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ እድገት ቁልፍ ሚና እንዲኖረው ማድረግ አለባት።ስለሆነም ኮሌጁ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስር ከመታሰር ወጥቶ በራሱ በመላው ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ኮሌጆች በስሩ እንዲከፍት ሊደረግ ይገባል።ለእዚህም ለኮሌጁ ጥራት እና ብቃት እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቢሮክራሲያዊ አካሄድ ወጥቶ በራሱ የንግድ ከባቢ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ዩንቨርስቲ መሆን ይገባዋል።እዚህ ላይ መሰመር ያለበት በተለይ በአሁኑ ጊዜ የንግድ ሥራ ሙያ በራሱ እጅግ ሰፊ እና ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ እና እንደቀድሞው የአካውንቲንግ፣ባንክ እና አስተዳደር ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን በኢንፎርሜሽን ዘመን ስልታዊ ስልጠናዎች ከተለያዩ የሙያ ክህሎቶች ጋር መሰጠት ስላለበት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስር ሆኖ የቢሮክራሲ ሰለባ መሆን ለንግድ ሥራ ዩንቨርስቲዎች እጅግ አስቸጋሪ ከባቢያዊ ሁኔታ ከመፍጠሩም በላይ እድገታቸውን ያቀጭጨዋል ተወዳዳሪ ዓለምንም አልፏቸው እንዲሄድ ያደርጋል።
የንግድ ሥራ ኮሌጅ ምሩቃን ማኅበር የት ገባህ? ኮሌጁ ለምን ቦታውን እንዲለቅ ይደረጋል?
የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ አንዱ ዝነኛ የውጪ አካሉ ወይንም አጋሩ ውስጥ የሚቆጠረው የንግድ ሥራ ምሩቃን ማኅበር ነው። የንግድ ሥራ ምሩቃን ማኅበር የተመሰረተው በ1941 ዓም ሲሆን የማኅበሩ አባላት ከሚንስትርነት ማዕረግ እስከ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከፍተኛ ባለሙያዎች ድረስ አባላት ናቸው።በኢትዮጵያ የግልም ሆነ የመንግስት መስርያ ቤቶች የማኅበሩ አባላትን ማግኘት ከባድ አይደለም። አሁን የማኅበሩ አባላት የንግድ ሥራ ኮሌጅን ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስር ወጥቶ በራሱ የሚተዳደር የንግድ ዩንቨርስቲ እንዲሆን ማድረግ እና አሁን በተለይ የተጋረጠበትን በሰንጋ ተራ ራስ አበበ አረጋይ መንገድ የሚገኘው እና ላለፉት 80 ዓመታት የነበረበትን ህንፃ እንዲለቅ መጠየቁን ሪፖርተር እንግሊዝኛ ዛሬ ሐምሌ 24/2013 ዓም ዘግቧል።ጉዳዩን በመቃወም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የንግድ ሥራ ኮሌጅ በቅርስነት መመዝገቡን የሚገልጥ ደብዳቤ ፅፏል።
የአዲስ አበባ አስተዳደር ለኮሌጁ መነሳት የሰጠው ምክንያት ደግሞ በዙርያው የፋይናንስ ድርጅቶች እየተስፋፉ ስለሆነ ለእነርሱ ማስፋፍያ በሚል ነው። ይህ አስቂኝም አስገራሚም ነው። አንድ ልጅ ያሳደገውን ወላጁን የመግፋት ሥራ ማለት ነው።የንግድ ሥራ ኮሌጅ ከምንም አንስቶ ኢትዮጵያ ዛሬ የበርካታ ባንኮች ባለቤት አደረጋት።ይሄውም ለ80 ዓመታት ብቁ የሰው ኃይል በማሰልጠን ሲሆን ዛሬ ያደጉት ልጆቹ ኮሌጁን ወደ ተሻለ ቦታ ማድረስ ሲገባቸው ግቢውን ይጋፉት ጀመር።ኮሌጁ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ምላሽ የገንዘብ ድርጅቶች ዙርያውን መኖራቸው የበለጠ ኮሌጁ እና ድርጅቶቹ ተመጋግበው እንዲኖሩ የሚያደርግ እንጂ ተቃርኖ እንደሌለው ገልጦ ጉዳዩ ትክክል አለመሆኑን ማስታወቁ ተገልጧል።እዚህ ላይ የገንዘብ ድርጅቶች እና ባንኮች የንግድ ሥራ ኮሌጅ ቦታን ከመፈለጋቸው የተነሳ ባላቸው የገንዘብ አቅም የአዲስ አበባ አስተዳደር ቢሮን ተጋፍተው እንዳይሄዱ የሕዝብ ከኮሌጁ ጎን መቆም አስፈላጊ ነው።ምክንያቱም ይህ የኢትዮጵያ የንግድ ታሪክ በዘመናዊው ዘመን የነበረውን አሻራ የማጥፋት አደገኛ አካሄድ ነው።
ባጠቃላይ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ማለት የነበራትን መስራች ኮሌጆችም ሆነ ድርጅቶች ማንነት አሻራቸው እና ማንነታቸው ሳይነቀል ማሳደግ፣ማበልፀግ እና ለትውልድ ማስተላለፍ ነው።የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅም ከቦታው የማንሳቱን ሙከራ በብርቱ መቃወም ያስፈልጋል። ይህ ብቻ አይደለም።የንግዱ ማኅበረሰብ፣የገንዘብ ድርጅቶች፣ባንኮች፣የንግድ ምክር ቤት እና የንግድ ሥራ ኮሌጅ ምሩቃን ማኅበር ድርጊቱን ከመቃወም አልፈው ኮሌጁ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስር ወጥቶ በራሱ የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ቅርንጫፍ ኮሌጆች እንዲከፍት በማድረግ የኢትዮጵያን የንግድ ሥራ እንዲሁም የአፍሪካ የንግድ ሥራ የልቀት ማዕከል ለማድረግ መነሳት ያስፈልጋል።ለእዚህም የመንግስት አካላትን ቀርቦ ማስረዳት እና አፈፃፀሙን መከታተል ይፈልጋል።
==========================
ማስታወቂያ /Advertisement
===============================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ?
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ -
No comments:
Post a Comment