የዛሬ የቶክዮ ኦሎምፒክ መክፈቻ ስነስርዓት
Photo= © Getty Images 2021
በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ -
- ኢትዮጵያ እና ኦሎምፒክ
- በዘንድሮው ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው በመክፈቻው ስነስርዓት ላይ ለምን ሁለት ሰው ብቻ ታየ?
- የዶ/ር አሸብር እና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሁኔታዎችን አለመከታተል እና አለማመቻቸት የፈጠረው ክፍተት ምንድነው?
- አሁን ውድድሩ ላይ ይተኮር!
ኢትዮጵያ እና ኦሎምፒክ
ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መሳተፍ የጀመረችው ሜልቦርን፣አውስትራልያ እኤአ 1956 ዓም ጀምሮ ሲሆን እስከ እኤአ 2016 ዓም በሪዮ እስከተደረገው የኦሎምፒክ ውድድር ድረስ በተከታታይ ተሳትፋለች።በእነኝህ ውድድሮች ውስጥ ከሜልቦርን ውጪ በሁሉም ውድድሮች ቢያንስ አንድ ሜዳልያ አግኝተናል።ከፍተኛ የሜዳልያ ቁጥር ያስመዘገብንባቸው ውድድሮች ሞስኮ ኦሎምፒክ 4 መዳልያዎች፣ባርሴሎና እና አትላንታ በያንዳንዳቸው 3 ሜዳልያዎች አግኝተናል።በመቀጠል በሲድኔ ኦሎምፒክ 8 ሜዳልያዎች ያገኘን ሲሆን በቀጣይ የተደረጉት በአቴንስ እና በቤጂንግ በእያንዳንዳቸው 7 ሜዳልያዎችን አግኝተናል።በለንደን 2016 ዓም እኤአ እና በ2016 ዓም በሪዮ በድምር 16 ሜዳልያዎች አግኝተናል።
በ2020 ዓም እኤአ በቶክዮ፣ጃፓን መደረግ የነበረበት የኦሎምፒክ ውድድር በኮቪድ 19 ምክንያት ውድድሩ ዘግይቶ ዛሬ ሐምሌ 16/2013 ዓም ተጀምሯል።በዛሬው ደማቅ የመክፈቻ ስነሥርዓት ላይ አንድ ሺህ እንግዶች ቢገኙም ስታድዮሙ ግን በሰው ሳይሞላ ስነ ስርዓቱ በቀጥታ ለመላው ዓለም እንዲታይ ሆኗል።በእዚህ የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ልዑክ በስታድዮሙ መሃል ሲያልፍ በሁለት ሰው ብቻ መታየቱ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አበሳጭቷል።
በዘንድሮው ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው በመክፈቻው ስነስርዓት ላይ ለምን ሁለት ሰው ብቻ ታየ?
ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለኦሎምፒክ ውድድር ዝግጅት ቀደም ብላ ነበር ዝግጅቷን የጀመረችው።በተለይ ለልምምዱ ተብሎ ከእዚህ በፊት አትሌቶች ወደ ሆቴል የሚገቡበት ጊዜ አጭር መሆኑ ኢንዲቀርና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ልዩ ክትትል ጭምር የአትሌቶች የሆቴል ቆይታ ከስምንት ወራት ቀድሞ እንዲሆን ተደርጎ ቆይቷል።በበጀትም በኩል 150 ሚልዮን ብር ተበጅቶለታል።በልምምዱ መሃከል ክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ተገኝተው አበረታተዋል።በኃላም አትሌቶቹ እና የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባላት በቤተመንግሥት ተጠርተው ሽኝት ተደርጎላቸዋል።ባጭሩ በመንግስት በኩል የነበረው ክትትልም ሆነ ማበረታቻ በኢትዮጵያ ልክ አቅም ብቻ ሳይሆን ከእዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ መልኩ ድጋፍ ነበር።
ይህ በእንዲህ እያለ በዛሬው የኦሎምፒክ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ በርካታ አትሌቶች በስታድዮሙ ይታያሉ ተብሎ ሲጠበቅ ሁለት ብቻ ታይተዋል።ምክንያቱን አስመልክተው አንዳንዶች በማኅበራዊ ሚድያ የተለያዩ ምክንያቶችን ቢሰጡም፣ሰይፉ ፋንታሁን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሸብርን እና ኮማንደር ደራርቱን ወደ ጃፓን ደውሎ አነጋግሯል።በቃለ መጠይቆቹ ላይ በርካታ ነጥቦች ተነስተዋል።ለምሳሌ ለምን ሁለት ብቻ ገቡ ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር አሸብር ጧት የስድስት ሰው መግብያ ካርድ ለደራርቱ አስረክብያለሁ በሰዓቱ ስላልደረሱ ነው፣እኔም ዘግይቼ ስሰማ ደነገጥኩ ሲሉ ደራርቱ በበኩሏ በቦታው ለመድረስ ሞክረው ነገር ግን በመረጃ ክፍተት በመጡበት በኩል መግባት እንደማይቻል እንደተነገራቸው ገልጣለች። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ላይ ቀርቦ የተጠየቀው አትሌት ገዛሐኝ አበራ ጉዳዩ እንዳሳዘነው ገልጦ ምክንያቱን በተመለከተ ብዙም መረጃ እንደሌለው በሚገልጥ መልኩ ምላሽ ሰጥቷል።አለባበስን በተመለከተ የተጠየቁት ዶ/ር አሸብር ከአዲዳስ ኩባንያ ጋር በገባነው የማስተዋወቅ ውል መሰረት ነው ካሉ በኃላ መልሰው የሱፍ ልብሶች ተሰፍተው እንደነበር ይገልጣሉ።ኮማንደር ደራርቱ በሌላ በኩል የሀገር ልብስ ተዘጋጅቶ እንደነበር ገልጣለች።
በቃለ መጠይቁ ላይ የአትሌቶች መንደር የመግባት ፍቃድ በተመለከተ ኮማንደር ደራርቱ መረጃ እንደሌላት በሚገልጥ መልኩ መግባት አለመቻሉን ስትጠቅስ ዶ/ር አሸብር ደግሞ ለሁሉም የመግባት መብት አለው ካሉ በኃላ ለማደር ግን አትሌቶች ብቻ ናቸው የሚችሉት ብለዋል።ሌላው ለዶ/ር አሸብር የተጠየቁት የሚወዳደሩ አትሌቶች 31 ሆነው እያለ ለምን 101 ልዑክ ሄደ? የሚል ነበር።እርሳቸውም ሲመልሱ ሌላው አሰልጣኝ የቦርድ አባል እያለ ቁጥሩ እንደጨመረ ገልጠዋል።ኮማንደር ደራርቱ በሌላ በኩል የቡድን መሪ ዶ/ር በዛብህ በቂ መረጃ ባላገኘበት ሁኔታ ለእዚህም በትውልድ እንግሊዛዊ የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያዊት ለመረጃ ክፍተት አስተዋፅኦ እንዳደረጉ እና በእሳቸው ተሳትፎ ከእዚህ በፊት ቅሬታ እንዳቀረበች አስታውቃለች።ዶ/ር አሸብር ግን ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ በርካታ ሥራ የሰራች እና ልትመሰገን የሚገባት ነች ብለዋል።
የዶ/ር አሸብር እና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሁኔታዎችን አለመከታተል እና አለማመቻቸት የፈጠረው ክፍተት ምንድነው?
ከላይ በቃለ መጠይቆቹ ላይ በግልጥ እንደሚታየው በዶ/ር አሸብር እና በኮማንደር ደራርቱ መሃል በሀገር ቤትም ቀደም ብሎ እንደተሰማው የተናበበ አሰራር እንዳልነበረ በግልጥ ይታያል። ደራርቱ እያለቀሰች እንደተናገረችው የአትሌቲክ መንደር መግባት የማይቻል እንደሆነ ነው የምታውቀው ዶ/ር አሸብር ደግሞ የመግቢያ ካርድ ሰጥቻቸዋለሁ የታክሲ ቫውቸር ነው የሰጧቸው በርሱ ተጠቅመው መድረስ ነበረባቸው። እኔም ዘግይቼ ነው አለመድረሳቸውን ያወኩት ብለዋል።ይህ በራሱ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው ካርድ መስጠታቸውን ብቻ እንደ ኃላፊነት መወጣት መውሰዳቸው በራሱ አስገራሚ ነው።ካርዱን ሲሰጡ ያሉትን መረጃዎች በትክክል ለእነደራርቱ ነግረዋቸዋል? አዳዲስ መረጃዎችስ ተከታትለው በሞባይል የትደረሳችሁ እያሉ ጠይቀዋል?
በሌላ በኩል አለባበስን በተመለከተ በመክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ የአዲዳስን ልብስ ለብሳችሁ ግቡ የሚል ሕግ አለ ወይ? ሁሉም ሀገር ባህላዊ ልብሱን ለብሶ ሲገባ (ከእዚህ በፊትም ኢትዮጵያ እንደምታደርገው) ኢትዮጵያ ያውም 150 ሚልዮን ብር የተመደበለት ኦሎምፒክ ምን ያህል ገንዘብ አስፈልጎት ነው የመክፈቻው ላይ የአዲዳስን ልብስ ማስተዋወቅ አስፈላጊ ስለነበር ነው ብለው ዶ/ር አሸብር የሞገቱት? ከእዚህ በተለየ ሱፍም ተሰፍቶ ነበር ያሉት በአዲዳስ ልብስ እንደሚገባ እየታወቀ ለሱፍ ማሰፍያ ወጪ ወጥቷል ማለት ነው? በደራርቱ በኩል የሀገር ልብስ መዘጋጀቱን ገልጣለች።
ኢነኝህ ሁኔታዎች የሚያሳዩት የኢትዮጵያ ስፖርትን ለዘመናት ያቀጨጨው የተዝረከረከ አሰራር፣ቅንነት የሌላቸው ሰዎች አመራር እና ሙስናም ነው። በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ያለው ዝርዝር ችግር ይህ ነው ብሎ ለመደምደም ቀረብ ብሎ መመርመር ቢያስፈልግም በዛሬው የቶክዮ ኦሎምፒክ ጉዳይ ግን ዋናው ምክንያት የተናበበ አሰራር አለመኖሩ እና አንዱ አንዱን ለማሳጣት የሚደረግ ሩጫ ውጤት ይመስላል። እዚህ ላይ በዋናነት የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጃፓን ምን የማመቻቸት ሥራ ሰርቷል።እነደራርቱ በተለያዩ ሀገሮች ለውድድር ቢሄዱም ቶክዮን ያህል ውስብስብ ከተማ ውስጥ በቡድን ታክሲ ተሳፍረው እንዲመጡ በሚል ያለምንም ድጋፍ መጠበቅ ይከብዳል። ያውም በኮቪድ ምክንያት ከታክሲ ውጪ ወደ ስታድዮሙ ለሎች መኪናዎች ባልተፈቀዱበት ሁኔታ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ኢትዮጵያ ኤምባሲ በየሀገሩ የምትከፍተው እንዲህ ላለ ጊዜ ካልሆነ ለመቼ ሊሆን ነው? እዚህ ላይ የኢምባሲው ድጋፍ ምን እንደነበር የታወቀ ነገር የለም።ሆኖም ግን ይህንን የመረጃ ክፍተት የመሙላት እና የኢትዮጵያውያንን ልዑክ በቦታው መግባቱን የመከታተል እና ድጋፍ የመስጠት ስራ ከኤምባሲው በተጨማሪ የኮሚቴው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሸብር ግን የማይተካ ሚና እንዳላቸው ጥያቄ ውስጥ አይገባም።
አሁን ውድድሩ ላይ ይተኮር!
አሁን ባለው መረጃ ተወዳዳሪዎቹ አትሌቶች፣ተኩአንዶ ተወዳዳሪዎች እና ሌሎችም ገና ሀገር ቤት ነው ያሉት።ወደ ጃፓን የሚገቡት ከነገ ቅዳሜ ጀምሮ ነው። ለእዚህም ምክንያቱ አሁን በጃፓን ባለው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በጉልበታቸው ላይ የመዛል ስሜት ስለሚያመጣ በቀዝቃዛዋ በኢትዮጵያ መቆየታቸው አስፈላጊ ስለሆነ ነው ሲሉ ዶ/ር አሸብር ተናግረዋል።አሁን ጊዜው የመነታረክያ አይደለም።ኢትዮጵያ ታላላቅ ውድድሮች ከፊቷ ይጠብቃታል።የዛሬውን የመክፈቻ ስነ ስርዓት በተመለከተ የመገምገምያ እና የማረምያ ጊዜው ከውድድሩ በኃላ ይደርሳል።አሁን ሙሉ ትኩረት መሆን ያለበት ወደ ውድድሩ ነው። ተወዳዳሪዎቹንም የመወዳደር ስነ ልቦናቸውን ከፍ እንዲያደርጉ በኮማንደር ደራርቱም ሆነ በዶ/ር አሸብር በኩል መስራት ስራዎች ከመኖራቸውም በላይ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናትም ሆኑ የንግድ ማኅበረሰቡ ተወዳዳሪዎቹ የተለያዩ ሽልማቶች እንደሚጠብቃቸው ተስፋ መስጠት ይገባል።
ተወዳዳሪዎች በእርግጠኝነት የማሸነፍ ስነ ልቦናቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ካደረጉት ዝግጅት መረዳት ይቻላል።
ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጨምሮ ለኢትዮጵያ ስፖርት መጫጨት ምክንያቶቹ ውስጥ አንዱ አስተዳደራዊ ችግር መሆኑን መንግስት ተመልክቶ ወደፊት ለውጥ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ መሰራት እንዳለበት የኦሎምፒክ ኮሚቴው ሁኔታ አመላካች ነው።የኢትዮጵያ ስፖርት በፌድረሽን ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የመንግስት እና የግል ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ የስፖርት ኮሚቴዎች ለረጅም ጊዜ ሳይቀየሩ የቆዩ፣የገንዘብ አጠቃቀማቸው ግልጥነት የሌለው እና ተጫዋቾች የኮሚቴ አመራሮችን የሚፈሩበት ሁኔታ በራሱ የግንኙነቱ ችግርም ወደፊት መታየት እንዳለበት የሚያመላክት ነው።
ኢትዮጵያን ወክለው በቶክዮ የሚወዳደሩ አትሌቶቻችን ሁሉ በድል እንዲመለሱ እንመኛለን።
ድል ለኢትዮጵያ!
==========================
ማስታወቂያ /Advertisement
===============================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ?
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ -
No comments:
Post a Comment