Picture Source: - Harvard Business Review Staff/Roc Canals/ azatvaleev/Getty Images
ጉዳያችን /Gudayachn
የማኅበራዊ ሚድያዎች በመላው ዓለም ሕዝብ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የፈጠሩት መልካም ከባቢያዊ ሁኔታ ቢኖርም፣በሌላ በኩል ያበላሹት ደግሞ እጅግ ብዙ ጉዳዮች አሉ።የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ለማበላሸት ተንኮለኞች ተጠቅመውበታል።በሀገሮች መሃል ግጭት እንዲባባስ ከማድረግ አልፎ በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮች እንዲወሳሰቡ ምክንያት ሆኗል።በሌላ በኩል ሀገሮች የውስጥ የፖለቲካ ጉዳያቸው ባልተፈለገ መንገድ እንዲሄድ ከማድረግ አልፎ የምርጫ ሂደቶች ወደ አልተፈለገ መንገድ እንዲሄዱ ማድረጉ ተነግሯል።ለምሳሌ በዩክሬን እና ሩስያ መሃል ያለው የማኅበራዊ ሚድያ ንትርክ፣በአዘርባጃን እና አርመንያ መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው አለመግባባት እንዲቀጣጠል የማኅበራዊ ሚድያው ንትርክ መንግሥታቱ ተረጋግተው እና በሰከነ መንገድ ለመፈለግ ፋታ የሚሰጣቸው አልሆነም። በሌላ በኩል በአፍሪካም ሆነ በአሜሪካ ማኅበራዊ ሚድያው በቀጥታ ተፅዕኖ ሲፈጥር ታይቷል።
በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሚድያው መረጃ ከመስጠት ባለፈ ህዝብን በዕውቀት ለማነፅ ያደረገው አስተዋፅኦ ምንድነው? ብለን ብንጠይቅ ራሱን የቻለ ምርምር ቢጠይቅም በደምሳሳው የሚታየው ግን እዚህ ግባ የሚባል ጥቅም እየሰጠ አይደለም።ከእዚህ ይልቅ ለፖለቲካ ሹክቻ እና አንዱን ጎሳ ከሌላው ለማጋጨት የማኅበራዊ ሚድያው ሚና ቀላል አይደለም።በእርግጥ መረሳት የሌለበት ጉዳይ የማኅበራዊ ሚድያ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ሰፍኖ የነበረውን ጎሳን መሰረት ያደርገው የህወሓት መር ኢህአዴግ ስርዓትን ለማጋለጥ የተጫወተው ሚና ቀላል እንዳልነበር መካድ አይቻልም።
በሌላ በኩል አሁን ያለው ዓለም አቀፍ መሰረት ያደርገው የማኅበራዊ ሚድያ ለምሳሌ እንደ ፌስቡክ እና ትውተር ያሉት ሚድያዎች እንደ ኢትዮጵያ የራሷ ታሪክ፣ባሕል እና የሕዝብ ግንኙነት ላለው ሀገር የተደበላለቀ ውቅያኖስ ውስጥ የመዘፈቅ ዕጣ ያተረፈ ከመሆኑም በላይ ወጣቶቻችን በማይኖሩበት አኗኗር ዘይቤ የተቀረፀው እና በማያውቁት የውጭው ዓለም ባሕል እና አስተሳሰብ የታሸው እሳቤ በራሱ ሌላ ውጥንቅጥ የሆነ ሁኔታ እየፈጠረ ለመሆኑ በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል።ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ ውጤቱ ትውልዱ የሚኖርበት ማኅበረሰብ ሌላ ነገር ግን የገባበት የማኅበራዊ ሚድያ በአዕምሮው ውስጥ እየፈጠረበት ያለው ደግሞ ሌላ መሆኑ በራሱ በአካል ሀገር ውስጥ በአስተሳሰብ ግን የባዕዳን ተገዢ የሆነ የሀገሩን ችግር የማይፈታ ትውልድ እያፈራን እንዳንሄድ ያሰጋል።ስለሆነም ኢትዮጵያ በማኅበራዊ ሚድያ አንፃር የገጠማት እና ወደፊት ሊገጥማት የሚችለውን ችግር ያገናዘበ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለባት።
ከላይ የተጠቀሰው የማኅበራዊ ሚድያ የራሳቸው ባሕል እና ታሪክ ያላቸው ሀገሮች ገብተው እንደፈለጉ እንዋኝበት ቢሉ ፈፅሞ ሊሆን የሚችል አይደለም።ለእዚህ ደግሞ አስተማሪዋ ቻይና ነች። ቢቢሲ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በመስከረም 1፣2012 ዓም የቻይናን ማኅበራዊ ሚድያ አጠቃቀም አስመልክቶ ''Social media in China: What you need to know" በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ ላይ ቻይና በዓለም ላይ ካሉ ሁሉ የማኅበራዊ ሚድያን ለገበያ ከሚጠቀሙት ውስጥ ቀዳሚ ሀገር መሆኗን ጠቅሶ ሆኖም ግን ፌስቡክ፣ትውተር እና ዩቱብ ዝግ መሆናቸውን ጠቅሶ ቻይናውያን እነኝህን ማኅበራዊ ሚድያዎች በዜና ምንጭነት እንደማይጠቀሙባቸው ያብራራል።በአንፃሩ ግን ቻይና የራሷ የሆነ ብሔራዊ ማኅበራዊ ሚድያዎች አሏት።
እነኝህም ወይቦ፣ተንረን እና ዮኩ (Weibo, Renren & YouKu) የተሰኙ ማኅበራዊ ሚድያዎች ሥራ ላይ እንደሆኑ ያብራራል።
ወደ ኢትዮጵያም ስንመጣ መፍትሄው ይሄው ነው።ኢትዮጵያ የሕዝቧን ባሕል፣ስነልቦና፣ታሪክ እና የእርስ በርስ ግንኙነት የሚያጠነክር የሀገሪቱን የኤሌክትሮኒክስ ገበያ ልውውጥ በሚያፋጥን መልኩ የራሷ የማኅበራዊ ሚድያ በኢትዮጵያ ቴሌ ተቆጣጣሪነት እና አጋዥነት መክፈት አለባት።በእዚህ ማኅበራዊ ሚድያ ታዋቂ አርቲስቶች፣ምሑራን እና ታዋቂ ሰዎች ሁሉ ወጣቱን የሚያስተምሩበት፣ክልል ከክልል የሚተዋወቁበት እና የሚቀራረቡበት፣ወጣቶች በተሻለ መልክ ተቀራርበው ጠቃሚ መረጃዎች የሚያገኙበት ይሆናል።ኢትዮጵያ የራሷ ማኅበራዊ ሚድያ በብሔራዊ ደረጃ ትውልዷን በሚያንፅ እና አሁን ሀገሪቱን እየጎዳ ያለው የጎሳ ፖለቲካን ለማርገብ የራሷን ማኅበራዊ ሚድያ መፍጠር እና ይህ ሀገርኛ ቃና ያለው ማድረጉ በእጅጉ ጠቀሜታ አለው።በእዚህ ትውልድ ይታነፃል፣ማኅበራዊ ሚድያውም ከማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አገናኝነት በዘለለ ለምጣኔ ሃብቱም የሚያደርገው አስተዋፅኦ ቀላል አይሆንም።ስለሆነም መንግስት ይህንን ጉዳይ በጥብቅ ሊያስብበት ይገባል።ኢትዮጵያ የራሷ ማኅበራዊ ሚድያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስታዘጋጅ ከውጭ የሚመጡትን እንደ ቻይና መዝጋት አይኖርባትም።በሀገር ውስጥ የተፈጠረው በራሱ ተመራጭ ሆኖ ህዝቡ እንዲወደው በማድረግ ብቻ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።በሀገር ውስጥ የሚፈጠረው ማኅበራዊ ሚድያ ትስስር መረብ የውጭውን ቀድሞ ወይንም እኩል እንደሚሄድ ለማወቅ ሕዝብ በቀላሉ ባህላዊ መሰረቱን የተበቀለትን ማኅበራዊ ሚድያ እንደሚመርጥ መረዳት በራሱ በቂ ነው።
********************************
ማስታወቂያ /Advertisement
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ?
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ -
No comments:
Post a Comment