ጉዳያችን / Gudayachn
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድቧን መስራት ከጀመረች አስር ዓመታት የሆነው ቢሆንም ግብፅም ሆነች ኃያላኑን ከፍተኛ መወራጨት ያሳዩት ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ነው።ለእዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ግድቡ በነበረበት አያያዝ በፕሮጀክት አፈፃፀሙ ለዓመታትም የማያልቅ መሆኑን ባላቸው መረጃ ባዕዳኑ ያውቁት ስለነበረ ነው።የግንባታው ኮንትራት የወሰደው እና በከፍተኛ የሙስና እንዲሁም የአቅም ማነስ ሲንገዳገድ የነበረው የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በምን ያህል ደረጃ ግድቡን የመፈፀም አቅም የሌለው ነገር ግን የሕዝብ ገንዘብ አለአግባብ እየዘረፈ እንደነበር በዝርዝር ባእዳኑ ያውቁ ነበር።ሜቴክ እስከ 37 ቢልዮን ዶላር የሚያወጣ የውጭ ግዢ ሲፈፅም ካለጨረታ በዘመድ አዝማድ የድለላ ሥራ እንደነበር ከሁለት ዓመት በፊት የአቃቢ ሕግ ሪፖርት ያስረዳል።ከእዚህ ባለፈ በዓባይ ግድብ ግንባታ ላይ ያልሰራውን የፕሮጀክት ሥራ ክፍያ ቀድሞ በመውሰድ የሚወነጀለው ይሄው ድርጅት ኢትዮጵያን ቀብሮ እንደሚሄድ ባዕዳኑ ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር በግድቡ ላይ የጠነከረ ስሞታ ማሰማት አላስፈለጋቸውም።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ግን በፕሮጀክቱ ላይ የተወሰደው መሰረታዊ የለውጥ ማስተካከያ ፕሮጀክቱ በሁለት እግሩ መቆም መቻሉ እና እውን እየሆነ መምጣቱን ሲታወቅ ነው ግብፅም ሆነች ኃያላኑ መንግሥታት ድምፃቸው መሰማት የጀመረው እና በኢትዮጵያ ላይ በቀጥታ ተፅኖ ለመፍጠር እየሞከሩ ያሉት።ላለፉት አንድ ዓመታት ከግድቡ ጋር በተያያዘ ብዙ ሰበቦች ሲደረድሩ የነበሩት የውጭ ኃይሎች አሁን በቀጥታ ስለ ግድቡ ከማውራት ይልቅ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚገቡበት ሰበብ ፍለጋ ለማግኘት ሲባዝኑ ይታያሉ።ስለሆነም የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ እስከ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ድረስ ለማድረስ ላይ ታች ሲሉ የከረሙበትም ሆነ አሁን ደግሞ ወደ ቡድን 7 እና በሰሜን የጦር ቃልኪዳን ሀገሮች ስብሰባ ምክክር ላይ ሳይቀር የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ መነጋገርያ ያደረጉበት ዋናውን ሚስጥር ማወቁ ጠቃሚ ነው።ይህንን ምስጢር ለማወቅ ግን ግብፅ እና ኃያላኑ ምን እንዲሆን ነው የሚፈልጉት? በጋራ ጥቅም በተለይ የዓባይን ግድብ በተመለከተ የምያስማማቸው ነጥብ ምን ሊሆን ይችላል? ወደ እዚህ ነጥብ ለመምጣት ስልታዊ መንገድ አድርገው ያሰቡት መንገድ ምንድነው ብሎ መጠየቅ ያስፈላግል።
በአባይ ግድብ አንፃር ግብፅም ሆነች ሱዳን የመጀመርያ ዕቅዳቸው የነበረው ኢትዮጵያን በውስጥ የማተራመስ አጀንዳ ከሞላ ጎደል እንዳልሰራ እና ኢትዮጵያን ለመበተን አጀንዳ የተሰጣቸው ኃይሎች አንድ በአንድ እንደተመቱ የቀረው አስተሳሰባቸውም ከምርጫው በኃላ በርዕዮተ ዓለም ደረጃም እንደሚመታ ግልጥ ሆኖላቸዋል።ስለሆነም አሁን ሃያላኑንም ሆነ ግብፅ እና ሱዳንን በጋራ በአባይ ግድብ ላይ እንዲሆን የሚፈልጉት ምንድነው? ግብፅም ሆነች ሱዳን በቀጥታ ኢትዮጵያን መውረር እንደማይችሉ ያውቁታል።ግብፅም ግድቡ ላይ አንዳች አደጋ ልፍጠር ብትል እስከ 6ሺህ ኪሎሜትር የሚወነጨፍ ሚሳኤል የታጠቀቸው ኢትዮጵያ የአስዋንን ግድብ በደቂቃ እንደምታደባየው ግብፆች ያውቃሉ።አንድ ሺህ ኪሎሜትር ማለት ከአዲስ አበባ አስመራ ነው ከአዲስ አበባ ካይሮ 3ሺህ አምስት መቶ ኪሎሜትር ነው።ኢትዮጵያ በእዚህ በኩል አልፋ ሄዳለች።በሌላ በኩል የአባይ ግድብ ማለት ግብፅን መቆጣጠር ማለት ብቻ ሳይሆን መካከለኛው ምሥራቅን መቆጣጠር እንደሆነ ኃያላኑ መንግሥታት ገብቷቸዋል።መካከለኛው ምስራቅ የታሸገ ውሃም ሆነ የሩዝ፣የፍራፍሬ እና የስጋ ምርት ሳይቀር ከግብፅ የሚቀርብለት የአባይ ወንዝ ትሩፋት ነው።
ስለሆነም ኃያላኑም ሆኑ ግብፅ የአባይ ግድብን በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በቀጥታ መቆጣጠርን እንደአንድ መፍትሄ ሊያስቡት አይችሉም ማለት አይቻልም።አሁን እየሄዱበት ያለው ሂደት የሚያሳየው ይህንኑ ነው።በመጀመርያ ግብፅ ጉዳዩን የዓለም አቀፍ ፀጥታ ችግር አድርጋ እንድታቀርብ ተነገራት ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምስራቅ፣ከሩቅ ምስራቅ እስከ ደቡብ አፍሪካ የግብፁ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሮጡ።ሆኖም አልተሳካም።ግብፅ የአባይ ግድብ በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር ከሚሆን የፀጥታ ችግር ነው ተብሎ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ሀገሮች (ናቶ) ወይንም በተባበሩት መንግሥታት ስር ቢሆን የተሻለ የፀጥታ ዋስትና እንደሚሆናት ታስባለች።ኃያላኑ ደግሞ ይህ ለእነርሱ ግብፅን መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን መካከለኛው ምሥራቅን መቆጣጠር እና ኢትዮጵያ እንዲሁም አፍሪካ እንዳይነሱ መድፈቂያ አንዱ መንገድ እንደሚሆን ያስባሉ።ጥያቄው ይህንን ግብ ለማሳካት ኃያላኑ ምን ሲያደርጉ ሰነበቱ? የሚለው ነው።
ይህንን ግብ ለማሳካት ኃያላኑ በመጀመርያ ያደረጉት ሱዳንን ማማለል ነው።የባዕዳን ጦር ካለ ሱዳን መሸጋገርያነት ሊሆን እንደማይችል ያውቃሉ።ስለሆነም ሱዳንን ከአሸባሪነት መዝገብ ከመሰረዝ ጀምሮ እስከ ድጎማ ድረስ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ የተሰራ ሥራ ነው።ከአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት እስከ የእስራኤል የደህንነት ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ወደ ካርቱም በረራ ያደረጉትም ላለፈው አንድ ዓመት ብቻ ነው።የግብፅ እና ሱዳን ጦር የጦር ልምምድ ሁለት ጊዜ ያደረጉት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ነው።የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እና የአባይ ግድብ ጉዳይ ከሦስት ጊዜ በላይ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ውይይት እንዲደረግበት የተሞከረው ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ነው።በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ በመግባት አሜሪካ ግልፅ የሆነ የተፅኖ እጇን ለማሳረፍ በምክርቤት ደረጃ ውሳኔ ያሳለፈችው ባለፉት ጥቂት ቀናት ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ የሕግ ማስከበር ተግባር መውሰዱን እና እርሱን ተከትሎ በከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ሥራ የሚራገበው የሰብዓዊ መብት ጉዳይን እንደ አንድ መግቢያ ጉዳይ ወስዶ 'ወደፊት ርሃብ ትራባላችሁ' ዘመቻ በኃያላኑ ሚድያም ሆነ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከአሁኑ እየተራገበ ያለው ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ነው።ይህ ሁሉ ውክብያ እንደ መንገድ ጠራጊ እያመቻቸ ያለው ኢትዮጵያን ማተራመስ እና የፀጥታ ችግር አለ፣ሕግ ለማስከበር ዓለም አቀፍ ኃላፊነት አለብን በሚል ሰበብ ወደ ኢትዮጵያ ጦራቸውን ለማትመም ነው።ባጭሩ እነኝህ ሁሉ ግባቸው አንድ ነው።ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን አዋክቦ ኢትዮጵያን በተባበሩት መንግሥታት ጭምር ለማስወገዝ እና በሰብዓዊ መብት ሰበብ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሉዓላዊነት መግፈፍ እና የዓባይ ግድብን ለአካባቢው ፀጥታ ሲባል በሚል ግድቡን በ'ናቶ' ቁጥጥር ስር ማዋል ነው።የ'ናቶ' ያለፉት የቅርብ ታሪኮች ደግሞ ለእዚህ ምስክር ናቸው።በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ መፍረስ ሂደት ኃላፊነት አለብኝ ብሎ ድርጅቱ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ላይ ያዘነበው የቦንብ ውርጅብኝ ማስታወስ ነው።በሊብያ የውስጥ ጉዳይ ገብቶ በትርፖሊ ላይ የወረደው የአየር ኃይል ድብደባ ማሰብ ነው።
ስለሆነም ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ላይ እየታሰበ ነገር ግን የማይሳካው የባዕዳን የሃሳብ ጥግ የት ድረስ እንደሚሄድ ከአሁኑ ማወቅ እና በአስፈላጊ ንቃት እና ትጋት ላይ መገኘት አስፈላጊ ነው።''ኢትዮጵያ የዓለሙ መፋረጃ'' ነች የሚባለው አባባል ቀላል አባባል አይደለም።ግፈኛ ኃያላን ብዙ ግፍ ሊውሉባት ሞክረዋል።ዛሬ ግን የሉም።ከማለፋቸው በፊት ግን ጥፋት አላደረሱባትም ማለት ግን አይደለም።ለጥፋቷ ሌላው እና ዋና ጠላቶቿ ደግሞ ከውስጧ ሆነው ለባእዳን አሳልፈው የሚሰጧት ናቸው።ጠላቶቿም የሚነሱት በእዚሁ የውስጥ ከሃዲዎች በተነሱባት ጊዜ ነው።ዛሬ ለኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ ጥብቅና የምንቆምበት፣ከሀዲዎችን ካለምንም ይሉኝታ የምንዋጋበት እና ኢትዮጵያ ወደፊት ቀጥላ እንድትነሳ የራሳችንን ድርሻ ጥለን ለወደፊቱ ትውልድ የምናሸጋግርበት ጊዜ ነው።ኢትዮጵያ ታሸንፋለች።በእዚህ ማንም ጥርጥር ሊገባው አይገባም።ከስነልቦና ጥቃት እራስንም ሆነ ህዝብን መጠበቅ እና የባዕዳን የድፍረት ሃሳብን ጥግ አውቆ መዘጋጀት ግን ይጠበቃል።በኢትዮጵያ ላይ ከኃያላኑ እስከ የተባበሩት መንግሥታት፣ከ'ኔቶ' እስከ ቡድን 7 የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በየጊዜው ከሚሰጡን ከፋፋይ አጀንዳዎች እራሳችንን ጠብቀን ለኢትዮጵያ ዘብ መቆም ግዴታ ነው።
==========================
ማስታወቂያ /Advertisement
===============================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ?
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ -
No comments:
Post a Comment