የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ብርቱካን ሜደቅሳ
ጉዳያችን/ Gudayachn
==============
አዋቂው የኢትዮጵያ ሕዝብ
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል፣የዲሞክራሲ አጠቃቀም እና የሰላም አመሰራረት ሂደት ሁሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ምንም ዓይነት መደናገር የለም።ሕዝቡ ቀድሞ ለዘመናት አብሮት የኖረው ባሕል፣እምነት እና ታሪክ በፖለቲካ ባሕሉ፣የመብት እና ዲሞክራሲ አጠቃቀሙ፣ የሰላም አመሰራረቱ እንዲሁም የመንግስት ስሪቱ ምንነት ላይ ሁሉ አሻራውን ጥሎ እና ቀርፆት ሄዷል።
ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር መነሻው ከሕዝቡ ሳይሆን ከሕዝቡ ውስጥ እየወጡ እንምራህ የሚሉት ቀድሞ የጦር አበጋዞች፣ላለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን ደግሞ የውጪውን በማድነቅ ናላቸው የዞረ ልሂቃን እና የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች ናቸው ችግር የፈጠሩበት።ትናንት ሰኔ 14/2013 ዓም የተደረገው ምርጫም ሆነ በ1997 ዓም የተደረገው ምርጫ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳየው ጨዋነት፣ስነ ስርዓት እና ቁርጠኝነት ሁሉ የሚያሳየው ይህንኑ አዋቂነቱን ነው።ይህ በራሱ ትልቅ ሀብታችን ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎቻችንም መሻሻል አሳይተዋል
በዘንድሮው ምርጫ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የቅስቀሳ ሂደትም ሆነ በምርጫው ጊዜ እና ምርጫው ከተጠናቀቀ በኃላ ያሳዩት ጨዋነት፣በሚሰጧቸው መግለጫዎች ያሳዩት ለሕግ መገዛት እና ለጋራ ሃገራዊ ርዕይ ያሳዩት ታማኝነት ሁሉ የሚያሳየው የፖለቲካ ፓርቲዎቻችንም ሆኑ መሪዎቻችን የሕዝቡን ስሜት ተከትሎ ትልቅ መሻሻል ማሳየታቸውን ያመለክታል።በተለይ የእዚህ ለውጥ ሂደት በራሱ ለውጡን ተከትሎ ወዲያውኑ ወደምርጫ አለመገባቱ፣ከሁለት ዓመታት በኃላም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መነሳቱ እና እንደገና የሀገሪቱ ያልሰከኑ የፖለቲካ ሂደቶች የመስከኛ ጊዜ ማግኘታቸው፣የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት እና ታማኝነት በሁሉም ዘንድ አመኔታ በማትረፉ እና የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ''የጥሞና ጊዜ'' የሚል የአራት ቀን ልዩ የማስከኛ እና የማሰብያ ጊዜ ለሕዝቡም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲዎች መስጠቱ ሁሉ የምርጫውን ሂደት ጥሩ ገፅታ ሰጥተውታል።እዚህ ላይ ግን የኢትዮጵያ ጦር ኃይል እና የፀጥታ አካሉ ሁሉ ሌት ከቀን ለፀጥታው መስፈን ያደረጉት አስተዋፅኦ ሁሉ አለመዘንጋት ተገቢ ነው።
የአሁኑ ምርጫ ሀገር የቅንጦት ነገሮች የምትፈልግበት አይደለም።ምርጫው ሀገር የማዳንም ምርጫ ነው
አንድ ሰው በራበው ጊዜ የተገኘውን ምግብ ተመግቦ ህይወቱን ያቆያል እንጂ ቆይ ዶሮ አርጄ፣ዶሮው ተገንጥሎ፣ሽንኩርት ተቁላልቶ ዶሮ ወጥ ይሰራልኝ አይልም።ኢትዮጵያ የዘንድሮውን ምርጫ ስታደርግ ጥቃቅን ችግሮችን ሁሉ ነቅሳ የተዋጣለት ምርጫ አትጠብቅም። ከእዚህ ይልቅ ኢትዮጵያን ለመበታተን ያሰፈሰፉ የፅንፍ ኃይሎችን የሚያስታግስ፣ለ27 ዓመታት የተዘራውን የጎሳ ፖለቲካ የሚነቀንቅ እና የሚነቅል፣የኢትዮጵያን አንድነት ለማፅናት የሚተጋ እና ከሙሰኝነት ለፀዳ አስተዳደር የሚተጋ መሆኑን እና ከውጭ የመጣባትን ሕልውናዋን የሚዳፈር ሙከራ እና በዓባይ ግድብ ሁለተኛ ሙሌት ምክንያት የሚመጣባት ተግዳሮትን የሚያስወግድ የሚሉትን መሰረታዊ ጉዳዮች እንደዋና መስፈርት ከማስቀመጥ ውጪ በአላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ በመግባት የሀገሪቱን አንድነት የሚጎዳ እንዳይሆን ብቻ የሚለው መስፈርት ተቀምጦ የተካሄደ ምርጫ ነው።ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ሀገር በአንድነት ቆሞ የጎሳ ፖለቲካው የዘራው እሾህ ተነቅሎ የሚታሰብ ሌላ ጉዳይ ነው።ምክንያቱም ኢትዮጵያ አሁን በእዚህ ምርጫ በሁለት እግሯ የማቆም አስፈላጊነት ላይ ብቻ የተተኮረበት ነው። ይህንን ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ሕዝቡም ሆነ መንግስት የተረዱት ይመስላል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለ ረጅም ርዕይ እንዲሆኑ የፌስቡክ ተሳዳቢዎችን ዕውቀት-አልባ ንትርኮች ሊያደምጡ አይገባም
በዘመናዊ ታሪክ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንፃራዊ በሆነ መልኩ በተሻለ አደረጃጀት፣የሰው ኃይል እና ሀገራዊ የጋራ ርዕይ የቆሙበት ጊዜ አሁን ይመስላል።ይህ ግን የመጨረሻው የጥራት ደረጃ ደርሰዋል ማለት አይደለም።አንፃራዊ መልኩ የሚለው ሊሰመርበት ይገባል።የፖለቲካ ፓርቲዎች በሌሎች ሀገሮች የመቶ እና መቶ ሃምሳ ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠሩ፣የራሳቸው ታሪካዊ አነሳስ እና ዳራ ያላቸው፣በርካታ የሚያስታውሷቸው ጀግኖች እና መስዋዕትነት የከፈሉ ምሑራን፣ገበሬዎች፣የሃይማኖት ሰዎች ወዘተ ያሏቸው ናቸው።ፓርቲዎቹ በታሪክ፣በፍልስፍና እና በልህቀት ደረጃም እየጎለመሱ የሄዱ እና በሂደት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሀገሮች የፖለቲካ ፍልስፍና ምንጭ እስከመሆን ደርሰዋል።
በኢትዮጵያም ኢትዮጵያ ካሳለፈቻቸው የፖለቲካ ውጣ ውረዶች፣ እና የመንግስት አምባገነናዊ አገዛዞች አንፃር በሂደት የተወለዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተከስተዋል።ለምሳሌ ኢዜማ በትግል ሂደቱ ተወልዶ ሀገር ውስጥ ከነበሩ ፓርቲዎች በመዋሃድ የተመሰረተ፣ብልጥግና በሀገር ውስጥ ትግል ሂደት ከገዢው ፓርቲ ፈልቅቆ የወጣ እና የእናት ፓርቲ በአጭር ጊዜ ተመስርቶ ዕጩዎች በማቅረብ ግን የሶስተኛነት ደረጃ የያዘ ነው። የሁሉም አመጣጥ የተለያየ ቢሆንም ሁሉም በሀገራዊ አንድነት ላይ የማይፃረሩ መሆናቸው አንዱ ዓይነተኛ ጉዳይ ነው።
አሁን በምርጫው ያሸነፉም ሆኑ ያላሸነፉ ፓርቲዎች እራሳቸውን ማዘጋጀት ያለባቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገሩ ሆነው መሰራት እና መዘጋጀት አለባቸው።ፓርቲዎቹ የአጭር ጊዜ ሳይሆን የረጅም ጊዜ ርዕይ ይዘው ለመነሳታቸው ምልክቶች ይታያሉ።ለምሳሌ የኢዜማን እና የብልጥግና ፓርቲዎች የረጅም ጊዜ ርዕይ እንዳላቸው የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ።ለምሳሌ ኢዜማ የራሱን ዘመናዊ ቢሮ፣መፃህፍት ቤት እና አዳራሽ ሁሉ ማደራጀቱ፣ብልጥግናም የረጅም ጊዜ መመርያ ፍልስፍናውን ''መደመር'' ማንፀባረቁ ሁሉ የኢትዮጵያ ፓርቲዎች የረጅም ጊዜ ርዕይ እየያዙ ለመምጣታቸው አንዱ ማሳያ ነው።ይህ በሌሎች ፓርቲዎችም ሊበረታታ የሚገባ ነው።ይህንን የረጅም ጊዜ ርዕይ አጠናክሮ የመሄድ ሂደት የማይረዱ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕቅድ 'ከአፍ እስከ አፍንጫ' ድረስ ያጠረ አድርገው የሚያስቡ ዕውቀት አልባ የፈስቡክ ተሳዳቢዎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና አመራሮቻቸውን እያነሱ በተራ ስድብ መጠመዳቸው መመልከት የሚያሳዝን ቢሆንም ፓርቲዎቹ እና አመራሮቹ ግን ስድስተኛው ምርጫ ብቻ ግባቸው አለመሆኑን ነገር ግን ገና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገሩ፣በየዘመኑ የሚነሱ የፖለቲካ ፍልስፍናዎችን ቅርፅ እየሰጡ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል የቆረጡ መሆናቸውን ለወዳጆቻቸውም ሆነ ለነቃፊዎቻቸው በማሳየት የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ የበለጠ የጠነከረ መሆኑን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
==========================
ማስታወቂያ /Advertisement
===============================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ?
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ -
No comments:
Post a Comment