>> የኢትዮጵያን መጪ ምርጫ የዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብ እንዳያውቀው አንዳንድ የውጭ ሚድያዎች እያፈኑት እንደሆነ እንንቃ!
ጉዳያችን / Gudayachn
ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ሰኔ 14/2013 ዓም (ጁን 21/2021 ዓም) ልታካሂድ የቀራት ስድስት ቀናት ብቻ ናቸው።ይህ ምርጫ ኢትዮጵያ ከእዚህ በፊት ካደረገቻቸው ምርጫዎች የተሻለ የሚባልባቸው ብዙ ነጥቦች አሉት።በአንፃሩ ደግሞ ለመጪው የምርጫ ጊዜ መሻሻል የሚችሉ ልምዶችም የሚቀሰሙበት ነው።የምርጫ ቦርድ በተሻለ መልኩ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ሲሰራ መታየቱ፣የተወዳዳሪ ፓርቲዎችን ለመወዳደር የሚያበቁ መስፈርቶች ግልፅነት እና ደረጃ መጠበቅ፣የምርጫ ካርዶች አሰረጫጨት እና ችግር ያለባቸው ጣብያዎችን ለመሰረዝ ያሳየው ቁርጠኝነት እና የመረጃ ፍሰቱ ጥሩ የሚያስብሉት ናቸው።በአንፃሩ በአንዳንዳንድ የምርጫ ጣብያዎች በተለይ በኦሮምያ እጩዎችም ሆኑ ፓርቲዎች እንደፈለጉ ለማስተዋወቅ አለመቻላቸው እንደ ጉድለት የሚታይ ነው።
ይህ ምርጫ መታየት ያለበት ኢትዮጵያ ካለችበት ከጊዜው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ነው።ኢትዮጵያውያን የተለያየ አስተሳሰብ እንዲይዙ ከሶስት አስር ዓመታት በላይ ተሰርቶብናል፣በጎሳ ፖለቲካ ተሰቃይተው ብዙ ጉዳት ደርሶብናል፣ፅንፍ የያዙ ሃሳቦች ሀገሪቱን ወጥረው ይዘው ትውልዱን ለማደናበር ሞክረዋል፣በሌላ በኩል የውጪ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ለመረባረብ ያሰፈሰፉበት ጊዜ ነው።ስለሆነም ምርጫው ሃገረ መንግስት ከማቆም ባለፈ የኢትዮጵያን ህልውና የማስጠበቅ አደራም ይዟል።
ይህንን ምርጫ በተመለከተ የዓለም ዓቀፍ ማኅበረሰብ እንዳያውቀው አንዳንድ የውጭ ሚድያዎች እያፈኑት እንደሆነ ማስተዋል ይገባል።ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን መልካም ስም ለማጠልሸት ከያዙት ፕሮጀክት አንፃር መሆኑ ግልጥ ነው።ስለሆነም በአዲስ አበባ ወኪሎች ያሏቸው ዓለም አቀፍ ሚድያዎች በአዲስ አበባ ስላለው የምርጫ ዜና እና ስለሂደቱ ይህ ነው የተባለ ዘገባ አልሰሩም።አሁንም ምናልባት የምርጫው ቀን ኢትዮጵያን ለማጠለሸት ይጠቅማል ያሉትን ክፍል ብቻ መርጠው እንደሚያቀርቡ ግልጥ ነው።ስለሆነም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስተዋወቁ ሥራ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ላይ መውደቁን መረዳት ይገባል።
ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባለው የማኅበራዊ ሚድያ በተለይ በትውተር ከምርጫው በፊት ኢትዮጵያ ምርጫ ልታደርግ መሆኑን የሚገልጡ ፅሁፎች በውጭ ቋንቋዎች ማስተዋወቅ እና ከምርጫው በኃላ ባሉት ጥቂት ቀናትም ምርጫው መካሄዱን እና ውጤቶቹን ማስተዋወቅ ለሀገር ገፅታ የሚሰጠው ጥቅም ትልቅ ነው።እነኝህን ስራዎች ማድረጉ የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት። እነርሱም -
- ኢትዮጵያን በጦርነት፣በረሃብ ለመሳል የሚታትሩትን የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ላይ መሆኗን እንዲነገር ስለማይፈልጉ ይህንኑ ለዓለም ሕዝብ ለመንገር ይጠቅማል፣
- ኢትዮጵያን በአምባገነን መንግስት ለመፈረጅ እና በአፍሪካውያን ወንድሞቻችን መሃል ለማስጠላት የሚደረገውን ጥረት ያከሽፋል፣
- በውጭ የተወለዱ ኢትዮጵያውያንም መረጃ የሚያገኙት ከተሳሳተ የውጭ ሚድያ ስለሆነ በእዚህ የምርጫ ማስተዋወቅ ሥራ በሀገራቸው ምን እየተደረገ እንዳለ እንዲረዱ ያደርጋል፣
- ከምርጫው በኃላ የኢትዮጵያን መንግስት ሕጋዊ እንዳልሆነ ለማስመሰል ጥረት የሚያደርጉት ዛሬ ምርጫው እንዲነገር ስለማይፈልጉ ከወዲሁ የምርጫውን ሂደት ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በመንገር የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲያደርግ ለማዘጋጀት ይጠቅማል።
==========================
ማስታወቂያ /Advertisement
===============================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ?
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ -
No comments:
Post a Comment