ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, June 18, 2021

በሳውዲ አረብያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስቃይ ላይ ናቸው።በጉዳዩ ላይ በሳውዲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከሳውዲ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መነጋገራቸው ተሰምቷል።

አምባሳደር ሌንጮ ከሳውዲ ምክትል ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እና በሳውዲ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ዳይሬክተር  አምባሳደር  ጋር ሲወያዩ 

ጉዳያችን ዜና  / Gudayachn News

በሳውዲ አረብያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ ፖሊሶች ቤታቸው እየተሰበረ ጭምር እየታሰሩ ነው።ኢትዮጵያውያኑን የሳውዲ ፖሊሶች እና ተባባሪ ታጣቂዎች የሚያሳድዷቸው የመኖርያ ፈቃድ የላችሁም እያሉ ሲሆን።ከተያዙት ውስጥ ግን ፍቃድ ያላቸውም እንደሚገኙበት የሚናገሩ አሉ።ኢትዮጵያውያኑን ፖሊሶቹ ከያዙ በኃላ እጅግ አስከፊ ወደ ሆነ እስር ቤት የሚወረውሯቸው ሲሆን በእስር ቤት ውስጥ የገቡ ኢትዮጵያውያን እንደሚናገሩት እስር ቤቱ ከፍተኛ ሙቀት ያለው፣የሚተኙበት ቦታም  በተባይ የተሞላ መሆኑን በሳውዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይናገራሉ።

በአሁኑ ጊዜ በርካታ ኢትዮጵያውያን በከተማ የሚደረገው የቤት ለቤት ፍተሻ እና በመንገድ ላይ መያዝን በመፍራት ወደበረሃማው የሳውዲ ገጠራማ ቦታ ለመደበቅ እየሞከሩ ሲሆን በእነኝህ የገጠር ቦታዎች ደግሞ ከ40 ዲግሪ በላይ የሚወጣው  ሙቀት ያሰቃያቸዋል። ወደገጠር የሚወጡት ሳይታሰብ ስለሆነ የሚበሉትም ሆነ የሚጠጡትን ሳይዙ ስለሚሄዱ አንዳንድ ጊዜ በአጋጣሚ ከሚያገኙት መንደር ተጠግተው ለመለመን ይገደዳሉ።በአሁኑ ጊዜ በሳውዲ እስር ቤት ከሚገኙት ኢትዮያውያን ውስጥ ሕፃን ልጆቻቸውን እንደያዙ ቤታቸው እየተሰበረ እንዲወጡ ተደርገው እስር ቤት የገቡ ሁሉ የሚገኙ ሲሆን በእስር ቤት ውስጥ በህመም ላይ ያሉ ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ ከሳውዲ የሚሰማው ዜና ያመለክታል።

ይህ በእንዲህ እያለ በሳውዲ አረብያ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ አምባሳደር ሌንጮ ከሳውዲ ምክትል ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እና በሳውዲ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ አምባሳደር  ጋር ትናንት መነጋገራቸው ለማወቅ ተችሏል።አምባሳደር ሌንጮ ከምክትል ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያውያኑ የመኖርያ ፍቃዳቸው (''ኢቃማ'') እንደተቃጠለባቸው እና በእጃቸው ላይም ገንዘብ አለመኖሩ ለችግር እንደዳረጋቸው አምባሳደሩ ለሳውዲው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አስረድተዋል።ከእዚህ በተጨማሪ በእስር ቤት ያሉት ኢትዮያውያን ጉዳይ እና ፖሊሶቹ በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሱ ስለሚገኘው በደል እና ኢትዮጵያም የዜጎቿ መብት እንዲከበር በዝርዝር መነጋገራቸው ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል በሳውዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ይህንኑ ንግግር አረጋግጦ ንግግሩ እንደቀጠለ እና አንድ ዓይነት መፍትሄ ላይ እስኪደርሱ ድረስ እንደሚቀጥል ከጠቀሰ በኃላ ኢትዮጵያውያን እስከዛው ድረስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ መልዕክት በማኅበራዊ ሚድያ አሰራጭቷል።አሁን ዘግይቶ በወጣ ዘገባ ደግሞ የፖሊሶች የቤት መስበር ተግባር ትንሽ ጋብ ያለ ሲሆን ይህ ግን እስከመቼ እንደሚዘልቅ አልታወቀም።በትናንትናው ዕለት በሳውዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢትዮጵያንን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀምር የሚገልጥ ከእዚህ በታች የምታዩትን ማስታወቂያ አውጥቷል።
ሆኖም ግን ብዙዎች በእዚህ ማስታወቂያ ብዙም ተስፋቸው አልለመለመም።ምክንያቱም ያለው ቁጥር እና ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ የሚባሉት ቁጥር አይመጣጠንም።አልፎ አልፎ እንደሚታየውም ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ በኃላ ተመልሰው ወደ ሳውዲ የሚገቡ መኖራቸው ሌላው አስቸጋሪ ጉዳይ ነው። በሳውዲ አረብያ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በባህር እየተሻገሩ የገቡ እና የመንን እንደመሸጋገርያ አድርገው ወደ ሳውዲ አረብያ የገቡ እንደሆነ ይነገራል።በሳውዲ የሚኖሩ ኢትዮያውያን ትኩረት ይሻሉ።ኢትዮጵያ በብዙ ጉዳዮች ተወጥራ ብትገኝም የዜጎች ጉዳይን ግን በሳውዲ ለረጅም ጊዜ ከኖሩ እና ስለ ሀገሩም የጠለቀ ዕውቀቱም ሆነ አቅም ያላቸው ኢትዮጵያንን ያጣመረ ሥራ መስራት እና የኢትዮጵያንን ስቃይ ጋብ የሚልበትን መላ መፈየድ ያስፈልጋል።

==========================
ማስታወቂያ /Advertisement 
===============================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...