ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, November 14, 2020

ህወሓት በጎንደር እና ባሕርዳር ላይ የፈፀመው የሮኬት ጥቃት ለኢትዮጵያ መንግስት አምስት ጥቅሞችን ይዞ ይመጣል።

ጉዳያችን / Gudayachn
ኅዳር 5/2013 ዓም (ኖቬምበር 14/2020 ዓም)



ትናንት ምሽት በባሕርዳር  እና ጎንደር አየር ማረፍያ አካባቢ ላይ  ከህወሓት የተወረወረው ሮኬት መሆኑን መንግስት ተናግሯል::ውርወራው ግን በባህርዳር በተለምዶ መኮድ አካባቢ፣በጎንደር ደግሞ አዘዞ አካባቢ የተፈፀመው ውርወራ ይህ ነው የተባለ ጉዳት አለማድረሱ እና በቀጣይ ዝርዝር መረጃ መንግስት እንደሚሰጥ ገልጧል።

አሁን በጉግል ምልከታዬ መሰረት ከመቀሌ እስከ ጎንደር ያለው እርቀት  በመኪና መንገድ 559 ኪሜ ሲሆን በአየር ላይ ወደ 240 ኪሜ ነው::ከመቀሌ ባሕርዳር ደግሞ በመኪና 615 ኪሜ ሲሆን በአየር ላይ 310 ኪሜ ነው:: የሕወሃት ሮኬት ቀድሞም መንግስት እንደተናገረው እስከ 300 ኪሜ ገደማ ነው::

የሮኬት ጥቃቱ ህወሓት ከመደበኛ ተዋጊነት ወርዳ ወደ ሐማስ መሰል ሽብርተኝነት መውረዷ በግልጥ የታየበት ነው።በትግራይ ውስጥ መሬት ላይ ያለውን ውጊያ መቆጣጠር ስላልቻሉ የመጨረሻ ያላቸውን ኃይል አሟጠው የመጠቀማቸው ማሳያ ነው።የሮኬቶቹን አጠቃቀም በተመለከተ ከግብፅ ወይንም ከሌላ የጠላት ሀገር በስልክ እና ቪድዮ የተደገፈ ድጋፍ ተደርጎላቸው ይሆናል።ይህ ግን አሁንም መሬት ላይ ያለውን የጦርነቱን እውነታ አይቀይረውም።ምክንያቱም መሬት ላይ ያለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ሰራዊት የህወሓትን ጁንታ ቡድን ወደ ጠበበ ኮርነር እያስገባው ከመሆኑ በላይ የነዳጅ እስከ ስንቅ አቅርቦቱ እየተመናመነ ነው።ይህም በመሆኑ በትናንትናው ዕለት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን መጋዘንን ሰብሮ ለስደተኞች የመጣውን እህል መዝረፉን እና ወደ 90 የሚጠጉ የድርጅቱን ሰራተኞች ማገቱን ኢሳት ከተባበሩት መንግሥታት ባገኘው አስተማማኝ ምንጭ ገልጧል።የእዚህ የሮኬት ጥቃት ዓላማዎች ሊሆኑ የሚችሉት ሁለት ናቸው።እነርሱም -የመጀመርያው ህወሓት የሞት አፋፍ ላይ አይደለሁም፣አለሁ ለማለት ሲሆን።ሁለተኛው ዋናው ዓላማው ግን በዓማራ ክልል እና በሌሎች የኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ ሕዝብ ጥቃት እንዲፈፅም ግጭት ለመፍጠር ነው።በእዚህም የትግራይ ሕዝብ ውስጥ ለመወሸቅ ዋስትናውን ለማረጋገጥ ነው።ስለሆነም ህዝቡ አሁንም በጥንቃቄ መሄድ አለበት።

የሮኬት ጥቃቱ ለኢትዮጵያ መንግስት ጥቅምም አለው - ጥቅሞቹ -

1) መንግስት ለሚወስደው የሕግ ማስከበር ስራ መቀጠል አስፈላጊነትን ለዓለምአቀፍፉ ማኅበረሰብ የሚያሳምንበት ተጨማሪ በቂ ምክንያት አሰጥቶታል::ሕወሃት ከተሞች ላይ የሚተኩስ በመሆኑ ትጥቁን ማስፈታት እንዳለበት ያሳምንበታል::አንዳንድ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና አህጉራዊ አካላት ጦርነቱን ማቆም እና ሁለቱ ወገኖች ቢደራደሩ የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል።ሱዳን በኢጋድ ኃላፊነቷ ጠይቃለች።የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ ስደተኞች እንዳይመጡብኝ በሚል ሰግቻለሁ የሚሉ ድምፆች በድፕሎማቱ አስተያየት ተገልጧል።ጦርነቱን ብታቆሙ የሚለው ሃሳብ አንዱ መነሻ ይህንን ያህል የሚያሰጋ ኃይል አይደለም፣በቀላሉ ድርድር በቂ ነው በሚል ምክንያት ነው።አሁን ግን የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርገው የሕግ ማስከበር ሥራ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እና ማንም ሊናገረው እንደማይችል፣የፀጥታ ስጋት እና የህዝብ ደህንነት ጉዳይ እንደሆነ በሚገባ ያሳምንበታል።በሌላ በኩል መንግስት ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሟል ለሚሉ አሁን አፋቸውን የሚዘጉበት ጊዜም ነው።የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጥቃት በትግራይ የተመረጡ ቦታዎች ላይ መፈፀሙ ምን ያህል አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ ያልሆነ ለመሆኑ ማሳያም ነው።ስለሆነም ሮኬቱ ጥቅምም ይዞ መጥቷል።

2) የዓለም መንግስታትም የእዚህ ዓይነት ሮኬት ኃላፊነት በማይሰማቸው ኃይሎች እጅ መግባቱ በራሱ ሃሳብ ውስጥ ይጥላቸዋል::ምስራቅ አፍሪካም እንዳይታወክ በሊብያ፣ሶርያ እና የመን የተሰራው ዓይነት ስሕተት ተሰርቶ አካባቢው እንዳይታወክ ከመንግስት ጎን በመቆም መንግስት ሁኔታዎችን እንዲቆጣጠር ለመደገፍ በውስጥ እንዲሰሩ ያስገድዳቸወዋል::ርግጥ ነው ይህ ዓይነቱ ዕሳቤ እነግብፅን አይመለከትም::ሆኖም የምስራቅ አፍሪካ መታወክ የዓለም አቀፍም ሆነ የአፍሪካ ቀንድ አሸባሪዎችን እንደሚያነቃቃ የሚያውቁ ሃያላኑ መንግሥታት አሁን ጉዳዩን ትኩረት ይሰጡታል።የአውሮፓ ሕብረትም ቀድሞ ትግራይ ላይ በሚደረገው ውግያ ስደተኛ ፈራሁ እንዳላለ አሁን ወደ ከተሞች የሚወረወሩ ሮኬቶች መኖራቸው የበለጠ ስደተኛ ያመጣል የሚል ስሌት ውስጥ ይገባል።ስለሆነም መንግስት የትግራይ ጦርነትን መጨረሱ ጥቅም እንዳለው በሚገባ ያምናል። 

3) ኢትዮጵያውያን በተለይ በዓማራ ክልል ያሉ የገፈቱ ቀድሚ ቀማሾች ከቀድሞ የበለጠ እንዲነቁ ያደርጋል።ይሄውም አካባቢያቸውን በኃላፊነት ከመጠበቅ ጀምሮ እስከ ጦር ሜዳ መፋለም ድረስ የበለጠ ያነሳሳቸዋል። 

4) የትግራይ ሕዝብ ይህንን የሮኬት ውርወራ ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ለማስፈጀት ሌላ የእብደት ሥራ እንደሰራ እንዲያስብ ያደርገዋል።መዘዙም የበለጠ ከማስፈራቱ በላይ የአየር ክልሉን እንደፈለገ የሚቀዝፍን መንግስት በሮኬት ውርወራ ለማስፈራራት መሞከር አንበሳን ከስር በእንጨት ወግቶ የመፎከር ያህል አደገኛ መዘዝ እንዳለው ያውቃል።ስለሆነም ህዝቡ ጦርነቱ ቶሎ አብቅቶ ወደ ሰላማዊ ሕይወት እገባለሁ እያለ ሲጠብቅ የሮኬት ጥቃቱን ሲሰማ ጦርነቱ እንደሚራዘም ስለሚያስብ የህዝቡ ከዳር መመልከት እንደማያዋጣ እና የህወሓት ወንጀለኞች በቶሎ አሳልፎ መስጠት አስፈላጊነት ላይ እንዲወስን ያደርገዋል።

5) ኤርትራ ከመቼውም ጊዜ በላይ በህወሓት ላይ ዘመቻዋን በሁሉም መስክ እንድታደርግ ያደርጋታል።ኤርትራ የህወሓት ዋነኛ ኢላማ እንደሆነች ታውቃለች።ህወሓት ይህ ሮኬት አላት ማለት ለኤርትራ ቀዳሚ የፀጥታ አደጋ አለው።ስለሆነም ከእዚህ በፊት ከነበራት ውሳኔ በበለጠ አሁን የበለጠ በህወሓት ላይ የተቀነባበረ ዘመቻ አስፈላጊነቱ ላይ ትወስናለች።ሌላው ኤርትራ እና ኢትዮጵያ በጣምራ ጥቃት ከአሁን በኃላ በህወሓት ላይ ቢጀምሩም  ለማንም የውጭ ኃይል የሚያሳምኑበት በቂ መረጃ አላቸው።ይሄውም ህወሓት የሁለታችንም የፀጥታ እና የደህንነት ስጋት ነው።ሮኬት ሁሉ እየወረወረ ነው።ይህ ደግሞ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሱዳንም፣ለጅቡቲም (በተለይ ኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት የምትጠቀምበት ስለሆነ) ስጋት ነው ማለት ይችላሉ።በእዚህም የሚቃወም አንዳች ሀገር ሊኖር አይችልም።

በመሆኑም እንደ ጉዳያችን ዕይታ የሮኬት ውርወራው እነኝህ ጥቅሞችን ለኢትዮጵያ ይዞ ይመጣል።አሁን ህወሓት ሁሉ ነገር ከእጇ ወጥቷል።በማይካድራ የፈፀመችው የዘር ማጥፋት ወንጀልን በተመለከተ የተባበሩት መንግስት ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል መሆኑን ትናንት ማስታወቁ ይታወቃል።

ጉዳያችን ዩቱብ ሰብስክራይብ ያድርጉ 

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።