በስብሰባው ላይ ከተሳተፉ የኦስሎ ኖርዌይ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን በከፊል
ጥቅምት 8/2012 ዓም (ኦክቶበር 19/2019 ዓም)
የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ
የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ያደረጉትን ንግግር በሙሉ የያዘ መፅሐፍ በተለያዩ ጥራዞች ''ፍሬ ከናፍር'' በሚል ስም ይታወቃል።መፅሐፉ ንጉሡ በእያንዳንዱ በዓል፣የውጭ እንግዳ ሲቀበሉ እና በእራት ግብዣ ላይ ሁሉ ያደርጉት ንግግር በሚገባ በቀን፣በወር እና በዓመት ተለይቶ የተፃፈ መፅሐፍ ነው።መፅሐፉን በገበያ ላይ ባያገኙት በእርግጠኝነት አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዋና መስርያ ቤት ጀርባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቤተ መዘክር (ወመዘክር) መፅሐፍት ቤት ጎራ ብሉ አያጡትም።በእዚህ መፅሐፍ ላይ በእያንዳንዱ ዓመት ኢጣልያ ከኢትዮጵያ ከተባረረች ጊዜ ጀምሮ እስከ 1960ዎቹ ድረስ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ወደ ውጪ አገር ለትምህርት ሲሄዱ በቅድምያ ንጉሰ ነገሥቱን ቤተ መንግስት ሄደው አግኝተው መሰናበት እና ምክር ለመቀበል ሲሄዱ ለተማሪዎቹ ያደረጉት ንግግር የመፅሐፉ አንዱ አካል ነው።በእዚህ ጊዜ ንጉሡ የሚያደርጉት ንግግር ላይ ለትምህርት የሚሄዱ ተማሪዎችን የሚሉት አንድ የተለመደ ዓረፍተ ነገር አለ። ይሄውም የወጣቶቹ ወደ ውጪ መሄድ የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ መሆኑን ንጉሡ ደጋግመው የሚጠቀሙበት አነጋገር ነው። ወጣቶቹ በውጭ አገር በሚቆዩበት ጊዜ ሁሉ እና በኃላ መስራት ያለባቸው ሁሉ የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ መሆኑን አበክረው የተናገሩበት ንግግር በተደጋጋሚ ይገኛል።የንጉሡ ምክርም ይሄው የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ በሚል ዓረፍተ ነገር የተሞላ ነው።ዛሬ በኦስሎ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያደርጉት ስብሰባም የሚያስታውሰው የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ በሚል ሃሳብ ዙርያ ነው።
የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ - በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዛሬው የኦስሎ ስብሰባ
ዛሬ ጥቅምት 8/2012 ዓም የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ በጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያውያን ታሕሳስ 10/2019 ዓም እኤአ ኦስሎ፣ኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ በተገኙበት የሚሰጠው የኖቤል ሽልማት መርሐግብር ላይ የኢትዮጵያውያን ሚና ምን መሆን አለበት በሚል ሃሳብ ዙርያ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በኖርዌይ (ኢትዮጵያ ኮሚኒቲ) ሰብሳቢ አቶ ፍቅሩ፣ከኤርትራ ማኅበረሰብ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን የተገኙ ሲሆን በመርሐግብሩ መጀመርያ ላይ አቶ ጌታቸው በቀለ የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ ሰብሳቢ የኖቤል ሽልማቱ ከኢትዮጵያን አልፎ አፍሪካውያን የፈጠረው ልዩ ስሜት ከደቡብ አፍሪካ እስከ ምዕራብ አፍሪካ ያሉ የመገናኛ ብዙኃን በርካታ ዘገባዎች እያቀረቡ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከኖቤል ሽልማቱ በፊት በጉግል ፍለጋ የነበረው ቁጥር በአማካይ ወደ ሰላሳ አራት ሚልዮን የነበረ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ባለፈው ሳምንት የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ከተገለጠ በኃላ ቁጥሩ በአስር እጥፍ አድጎ ወደ ሶስት መቶ አርባ ሚልዮን ማሻቀቡ ኢትዮጵያን በምን ያህል ደረጃ በመላው ዓለም በበጎ ጎኑ እንዳስጠራት ለማወቅ እንደሚቻል ገልጧል።
በመቀጠል የኖቤል ሽልማት ምንነት እና በኖርዌይ የምንኖር ኢትዮጵያውያን የሚጠበቁብን ስራዎች በተመለከተ ማብራርያ የሰጡት አቶ ለማ ናቸው። አቶ ለማ በንግግራቸው መግቢያ ላይ ሽልማቱ የፈጠረው ደስታ ታላቅ መሆኑን አውስተው፣ይህንን ታላቅ ዕድል በሚገባ በመጠቀም የኢትዮጵያን ስም ከፍ ማድረግ እንደሚቻል አብራርተዋል።በተጨማሪም የሽልማቱ ምክንያት ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው ሰላም ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በአገር ውስጥ በሰሩት መልካም ተግባር መሆኑን ካብራሩ በኃላ የኖቤል ሽልማት የሚሰጠው ድርጅት ኖቤል ኢንስቲትዩት እንደሚባል እና የተሸላሚዎችን ታሪክ በመላው ዓለም የማስተዋወቅ ሥራ በመስራት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ የሚሰራው ''ኖቤል ሴንተር'' የሚሰኝ መሆኑን አብራርተዋል።
ከስብሰባው ተሳታፊዎች በከፊል
በመቀጠል የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሰብሳቢ አቶ ፍቅሩ ይህንን ስብሰባ ያዘጋጀው የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክን አመስግነው፣የኖቤል ሽልማቱ የተሰጠበት ቀን ኮሚኒቲው ምሽቱን ጥሪ አድርጎ ደስታውን በአንድነት መግለጡን እና በዕለቱ ከኖርዌይ ቴሌቭዥን ዘጋቢዎች መገኘታቸውን ገልጠዋል።ከእዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኮምኒቲ የኖቤል ሽልማት ዝግጅት በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ለማግኘት ጥረት ማድረጉን እና ኤምባሲውም በራሱ መረጃ እየጠበቀ መሆኑን እንደገለጠ አስታውቀዋል።ከእዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ የምንም እና ማንም የፖለቲካ ድርጅት አቀንቃኝ አለመሆኑን አፅንኦ ሰጥተው አሁንም ከሁሉም ስብስቦች ጋር ለመገናኘት እየሞከረ መሆኑን ገልጠዋል።
ስብሰባው በተከታይ በኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው በቀለ አወያይነት ተሰብሳቢዎቹ በኖቤል ሽልማቱ ስነ ስርዓት ሰሞን በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሚና እና የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በማገዝ ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎች ዙርያ ተሰብሳቢዎቹ ሃሳብ ሰጥተዋል። ከተሳታፊዎች ከተሰጡት ሃሳቦች ውስጥ -
'' እኔ በሕይወቴ ያላየሁት ጉዳይ ነው ያየሁት'' አሉ አንድ እናት ስለ ኖቤል ሽልማቱ ሲናገሩ በመቀጠል '' ዜናው ሲነገር ነጮቹ ድንገት መጥተው ከበቡኝ እየሳሙ 'ግራቱለረ' የምስራች! አሉኝ።ቀኑን ሙሉ ስሳም የዋልኩት፣ልጄ ድንገት ደውሎ 'ግራቱለሬ' ማሚ ብሎ ደስታው ሲቃ እየተናነቀው አናገረኝ።ትምህርት ቤቱ ተማሪው ሁሉ ከቦት ደስታውን እየገለጡለት እንደሆነ ነገረኝ።ይህ ብቻ አይደለም።የትምህርት ቤቱ የክፍል ልጆች ጋር ተሰብስበው በዓል አደረጉ።ይህ ጉዳይ በልጆቻችን ላይ የፈጠረው የሞራል ልዕልና በቃላት የምገልጠው አይደለም።እባካችሁ ልጆቻችን የኢትዮጵያን መከራ ስናወራ ሲሰሙ ነው ያደጉት። ቢያንስ ደስታ እስኪ የሚሰሙበት ጊዜ እንዲሆን ይህንን የኖቤል ሽልማት አስመልክቶ አንድ አይነት ትልቅ ዝግጅት ማዘጋጀት አለብን።ይህንን ዝግጅት ላይ ለመገኘት የኖርዌይ ተወላጆች ሁሉ እየጠየቁ ነው እና ይህ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል'' ብለዋል።
ሌላ እናት ቀጠሉ '' የሽልማቱ ቀን በርካታ ቴክስት ከኖርዌይ ተወላጆች ደረሰኝ።ብዙዎቹ የጉዲፈቻ ኢትዮጵያውያንን ያሳደጉ ናቸው። ሁሉም የሚያሳድጉዋቸው ልጆች ይህንን ደስታ የሚያሳዩበት አንድ አይነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚገናኙበት የጋራ ደስታ መግለጫ በዓል እንዲዘጋጅ እና በእዚህ ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ቃል ገብተዋል። ስለሆነም እባካችሁ ከእኛ ይልቅ ልጆቻችን የሚኮሩበት እና በአገራቸው የሚኮሩበት መልካም ዕድል እንፍጠር'' ብለዋል።
ስብሰባው በመቀጠል ከኤርትራ ማኅበረሰብ የመጡ አቶ ንጉሡ አስተያየት የሰጡ ሲሆን በአስተያየታቸው ''እኔ አሁን ኤርትራ ቀድሞ የኢትዮጵያ ክፍለ አገር የመጣሁ የዓቢይ ወጤት ደጋፊ ነኝ።አብረናችሁ ነን።ኢትዮጵያ እና ኤርትራ አንድ ሕዝብ ነን በእዚህ ዝግጅት ላይም አብረናችሁ ነን'' ብለዋል።
በመጨረሻም ስብሰባው ከመጠናቃቁ በፊትበሚከተሉት ነጥቦች ላይ የጋራ መግባባት ተደርሶበት ስብሰባው ተፈፅሟል። እነኝህ በጋራ መግባባት የተደረሰባቸው ነጥቦች -
- የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ቀድም ብሎም እንደገለጠው ከኖቤል ሽልማቱ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ወደ ኦስሎ ሲመጡ ለሚኖረው የክብር አቀባበል፣እስከ የሚመለሱበት ጊዜ ያለው ዝግጅት ዙርያ የሚያስተባብር አንድ ግብረ ኃይል በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ እንዲመሰረት እና ወደ ሥራ እንዲገባ፣ይህ ኮሚቴ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን፣
- የኢትዮጵያ ኤምባሲ (ስዊድን ፣ስቶኮልም የሚገኘው) ከኢትዮጵያ ኮሚንቲ ጋር አብሮ እንዲሰራ እና ዝግጅቱ ውበት ያለው እንዲሆን መስራት እንዲጀመር፣
- ኢትዮጵያን ባላቸው የግልም ሆነ የቡድን ግንኙነት (ኔትዎርክ) የኖቤል ሽልማቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስም የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይህንን ታሪካዊ እና አገራዊ ፋይዳ ያለው ዝግጅት በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና በባለቤትነት እንዲያስተናግዱ እና አስፈላጊውን ጥሪ ከኮምንቲ እንዲጠብቁ፣
- አንድ ልዩ የደስታ መግለጫ መርሃግብር ሁሉንም ኢትዮጵያውያን፣አፍሪቃውያን እና የኖርዌይ ተወላጆች የሚያሳትፍ ዝግጅት እንዲኖር በእዚህ ዝግጅት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የሚገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይም ኢትዮጵያውያንን የሚያገኙበት መልካም አጋጣሚ እንዲፈጠር የሚሉት ዋና ዋና ነጥቦች ነበሩ።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በተሰጡት ሃሳቦች ዙርያ አስተያየት ከሰጠ በኃላ በስብሰባው መደሰቱን እና በርካታ ጠቃሚ ግብዓቶች መገኘታቸው እና አሁንም በዝግጅቱ ማማር ዙርያ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አብረው እንዲሰሩ እና በተቀናጀ መልክ ለመስራት እና የኢትዮጵያን ስም ከፍ ለማድረግ ለመስራት ጥሪ አቅርቦ የዕለቱ ስብሰባ ተፈፅሟል።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment