ጉዳያችን /Gudayachn
ጥቅምት 11/2012 ዓም (ኦክቶበር 22/2019 ዓም)
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል በርካታ ለውጦች ታይተውበት፣ተስፋ ተሰንቆበት፣ስጋት ታጅቦበት እስከ ዛሬ ደርሷል።የኢትዮጵያ ሕዝብ አስደናቂ ትዕግስት፣መቻቻል፣መከባበር እና ከፍተኛውን የዋጋ ንረት ችሎ የኖረበት መንገድ ሁሉ አገሪቱ በርካታ መሰናክል የማለፍ አቅም እንዳላት አስመስክሯል።
በኢትዮጵያዊነት እና በፅንፍ የጎሳ ፖለቲካ ስንገላታ የነበረው አወዛጋቢ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መስመር አሁን መልክ እየያዘ የመጣ ይመስላል።በመጀመርያ የነበረው የጎሳ ፖለቲካ ፅንፈኞች ተፅኖ አሁንም ድረስ በፖሊስ፣በአስተዳደር እና በከተሞች የቀበሌ እና ክፍለ ከትሞች አስተዳደር ጭምር በመሰግሰግ ኢትዮጵያዊነት አገንግኖ እንዳይወጣ የተቻላቸውን እየፈፀሙ ይገኛሉ።ሌላው ቀርቶ በመስቀል ደመራ በዓል ሳይቀር የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የያዙ ኢትዮጵያውያን የደረሰባቸው እንግልት የእነኚህ የፅንፍ ፖለቲካ አራማጆች እጅ በፖሊስ እና የቢሮክራሲ መስመር ሁሉ ቦታ መያዝ ያመላከተ ጉዳይ ነበር።
መደመር የፖለቲካ መስመሩን እንዲቀይር ዕድል እንስጠው
የፅንፍ ፖለቲካ አራማጆች ቅጥ ያጣ ተግባር ባየለበት እና ሕዝብ ለመጨረሻው ፍልምያ መነሳት እንዳለበት ባመነበት ሰዓት ነበር ባለፈው ቅዳሜ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ መደመር የተሰኘው መፅሐፍ በይፋ በሚሊንየም አዳራሽ የተመረቀው። መፅሐፉ ኢትዮጵያዊነት የሚያገነግነው ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ በሚገባ ሊያጎላው እና ኢትዮያውነትን ከፍ አድርጎ ለማሳየት ሊጠቀምበት የሚገባ ብቻ ሳይሆን ከልብ መርምሮ መሰረተ ሃሳቡን ደግፎ መቆም ያለበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ከመደመር በተጨማሪ የኢህአዴግ ውሕደትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግፎት ሊቆም የሚገባው ሌላው መልካም አጋጣሚ ነው።ውሕደቱ የተከፋፈለ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ ኢትዮጵያን ወደተሻለ የፌድራል አስተዳደር የሚመራ መልካም ጎዳና ነው።ይህም ኢትዮጵያዊነትን የሚያገነግን ሌላው መልካም ፖለቲካ ነው።ነገር ግን ይህንን ደግፎ አለመቆም በራሱ ትልቅ የፖለቲካ ክሳራ ነው።ኢትዮጵያዊነትን የሚያገነግኑ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ጠቅላላ ህዝቡ በአዲስ መንፈስ እነኝህን ሃሳቦች ከፍ አድርጎ መነሳት እጅግ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።
የፅንፍ ኃይሎች የኢህአዴግ ውህደት እና የመደመር ፖለቲካ ለምን አስደነገጣቸው?
የኢህአዴግ የውህደት ጉዳይ ድርጅቱ በሙሉ ድምፅ በሐዋሳ በወሰነው መሰረት መቀጠሉ የሱማሌ ክልልን ጨምሮ አፋር፣ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ክልሎች በከፍተኛ ጉጉት እየጠበቁት ነው።ህወሓት የተቃውሞ መግለጫ ብታወጣም፣የትግራይ ኤሊቶች እና የንግዱ ማኅበረሰብ ይህንን ውህደት እንደሚደግፈው መገመት ይቻላል።ምክንያቱም የትግራ ኤሊቶች እና ነጋዴዎች በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውረው ለመስራትም ሆነ በአዲስ አበባ እና ሌሎች ቦታዎች ያላቸውን የንግድ ሥራ ለመስራት የኢሕአዴግ ውህደት ሰላማዊ ሁኔታ ከሕዝቡ ጋር እንደሚፈጥሩ ስለሚያውቁ ሰላማዊ ሽግግሩን በውህደት ቢያልቅ እና ትግራይም ህዝቡ እንደፈለገ የመዘዋወር መብቱ እንዲጠበቅ ይፈልጋሉ። ይህ ማለት ህወሓት ያወጣችው መግለጫ በራሱ ሕዝቡን የተቃረነ መሆኑን ለማወቅ ይቻላል።ስለሆነም በትግራይ ያለው አማራጭ አንዱ ህወሓት በራሷ ላይ ለውጥ አድርጋ ወደ ለውጡ ጎራ መግባት ወይንም በተቃዋሚዎች መቀየር አልያም የመጨረሻው አማራጭ የውሕደቱ ሂደት ደግፎ መቆም ነው።
ይህ በእንዲህ እያለ የፅንፍ ኃይሎች የኢህአዴግን ውህደት የፈሩበት ዋና መንገድ ኦደፓ ውስጥ ላለፉት ዓመታት የተሰገሰጉ የፅንፍ ፖለቲካ አራማጆች በሙሉ ዋና መንጠላጠያቸውን የጎሳ ፖለቲካ በሁለት መንገድ እንደሚያጡ እና ከስራ ውጪ እንደሚሆኑ ስለተረዱት ነው።አንዱ መንገድ ኦዴፓ ወደ ውህደቱ ሲመጣ በሁሉም ክልል የመንቀሳቀስ ዕድል ሲኖረው ሌሎች የቀድሞ የኢህአዴግ አጋሮችም በኦሮምያ በሁሉም ክልል የመንቀሳቀስ መብታቸው ይከበራል። ይህ ማለት ፅንፈኞቹ የግድ ከጉረኖ እየወጡ በአደባባይ የፖለቲካ አቅማቸው ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰባቸው ጥግ የሚጋለጥበት ስለሆነ ነው።
የፅንፍ ፖለቲካ አራማጆች ትልቁ ድንጋጤ የዶ/ር ዓቢይ የመደመር ፅንሰ ሃሳብ ነው ።መደመር ሕብረ ብሔራዊ ጉዳይ ስለሆነ የጎሳ ፖለቲካን አፈርድሜ የምያበላው ብቻ ሳይሆን የሃሳብ ድውይ አድርጎ በሕዝብ ፊት የሚያንተባትበው አደገኛ ጉዳይ እንደሆነ አውቀውታል። ስለሆነም አጥብቀው ይፈሩታል።
''በመደመር እና በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መሃል ብዙም ልዩነት አይታየኝም'' አለ ሃጅ ጃዋር ለኤልቲቪ ቴሌቭዥን የመደመር መፅሐፍ በሚመረቅበት ቀን በሰጠው ቃለ መጠይቅ።በመቀጠልም መፅሐፉን ለማራከስ አሉኝ ያላቸውን ቃላት ሁሉ ለመጠቀም ሞከረ። ይህ በራሱ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አስቂኝም ጉዳይ ነው።ጃዋር ሊነግረን የፈለገው በቀኝ ኃይሎች እና በግራ ኃይሎች መሃል ልዩነት የለም የማለት ያህል ነው። ቀጠለናም አብዮታዊ ዲሞክራሲ አሳሳችው መሰል ''አብዮታዊ ዲሞክራሲን በሙሉ ማጥላላትም ትክክል አይደለም'' አለ።እውነተኛ ወዳጅ የችግር ጊዜ አይደል የሚገኘው።አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሊቀበር አንድ ሐሙስ ሲቀረው ጃዋር ሊደርስላት ስንገዳገድ ይታያል።
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መንገዳገድ ያሳስበው፣የመደመር ሕብረ ብሔራዊ ፈድራሊዝም ያሰጋው እና የኢህአዴግ ውህደት ያስደነገጠው የፅንፍ ፖለቲካ አራማጅ ኃይል ተደናግጧል ። መደናገጡ ደግሞ ያለ የሌለ ኃይሉን አንቀሳቅሶ የኢትዮያን ሕዝብ ለመረበሽ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዙርያ የቄሮ ነን ያሉ ሕዝቡን እዚህ እና እዚያ እንዲረብሹ በማድረግ የለውጡን ሂደት ለመረበሽ ሞክረዋል።ይህንን እኩይ ስራቸውን ሊገፉበት ይችላሉ። ህዝቡ ግን ከመደመር እና የኢህአዴግ ውህደት ከመደገፍ ጎን በመቆም የጥፋት ኃይሎች በማያሻማ መንገድ የማስጠንቀቂያ ደወል ማሰማት እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም ሀሳቦች እና ኢትዮጵያዊነት አገንግኖ እንዲወጣ የማገዝ ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።በእዚህ ሰልፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሶስት መልዕክት ማስተላለፍ ይችላል። እነርሱም -
1ኛ) የብሔር ፖለቲካ እንደሚያጫርሰው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ወደ መጨረሻ የውድቀት ገደል የሚገፋ ስለሆነ ፈፅሞ እንደማይቀበለው ለጥፋት ኃይሎችም ሆነ ለዓለም ዓቀፉ ማኅበርሰብ ግልጥ መልዕክት ያስተላልፋል።
2ኛ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በሙሉ መተማመን የመደመር ሃሳባቸውን እንዲያራምዱ እና አብሯቸው እንደሚቆም በግልጥ ያሳያል።እርሳቸውን ተፃረው የጎሳ ፖለቲካ ለማስፈን የሚፈልጉ ኃይሎችን ያስጠነቅቃል፣
3ኛ) የህዝቡን አንድነት መልሶ የሚያረጋግጥበት መልካም አጋጣሚ ይሆናል።
ስለሆነም አክትቪስቶች፣ቅን ዜጎች እና በውጭ የምትኖሩ ሁሉ ከሰሞኑ የደመቀ የድጋፍ ሰልፍ የኢህአዴግን ውሕደት በመደገፍ እና የመደመር ፅንሰ ሃሳብን በመደገፍ ምድር አንቀጥቅጥ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ትርጉሙ ትልቅ መሆኑን ልትረዱት ይገባል።ለማስታወስ ያህል፣የሰኔ 15ቱ ሰልፍ በፊት ቀደም ብሎ አንድ ሳምንት በአዲሱ የለውጥ ኃይል ላይ የዛቻ እና የማደናቀፍ ሙከራ አዘል መግለጫ ሲወጣ ጉዳያችን ምሽቱን መፍትሄው በአዲስ አበባ ታላቅ ሰልፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁማ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ብዙዎች አሳድገውት በአንድ ሳምንት ውስጥ ሰልፉ መቀናበሩ ይታወሳል። እዚህ ላይ ጉዳያችን ይህንን አደረገች ለማለት ሳይሆን ሃሳብ ሲሰጥ ብዙዎች ካመኑበት ወዲያው የሃሳቡ አራማጆች የመሆናቸው መልካም ሂደት ለመጠቆም ነው። ይህ ሰልፍ አሁንም ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ እና የለውጡን ምህዋር በኢትዮጵያዊነት ፍቅር እንዲፀና የራሱ ታሪካዊ ሚና ያለው መሆኑን መዘንገት አያስፈልግም።
መደመር በዜማ
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment