ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, October 24, 2018

ወደ እንግሊዝኛ የተመለሰው የደራሲና ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው 'የጥፋት ዘመን' የተሰኘው መፅሐፍ ምረቃ በኦስሎ፣ኖርዌይ እና በዓማራ ብሔርተኝነት ዙርያ የሚነሱ ጥያቄዎች

ጉዳያችን/Gudayachn
ጥቅምት 14/2011 ዓም (ኦክቶበር 24/2018 ዓም)
መነሻ 

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአደገኛ መልኩ በብሔርተኝነት (በጎሳ) ፖለቲካ መናጥ የጀመረው ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ አዲስ አበባን በ1983 ዓም ከተቆጣጠረ ጀምሮ ነው።አንዳንዶች የብሔር አደረጃጀቶች ቀደም ብለው መኖራቸውን በማንሳት የኢትዮጵያን የብሔር ፖለቲከኞች ድምፅ መሰማት የጀመረው ቀደም ብሎ እንደነበር ያወሳሉ።ሆኖም ግን የ19ኛው ክ/ዘመን እና የ20ኛው ክ/ዘመን የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ አደረጃጀት እና የከተሞች መፈጠር የብሔር (የጎሳ) ፖለቲካን በእጅጉ ከማደብዘዝ አልፎ  ኢትዮጵያ ከብሄር ፖለቲካ በተለየ በሀሳቦች ዙርያ መደረጃት ወደ ርዕዮተ ዓለማዊ የአስተሳሰብ ልዕልና የደረሰች ሆና ነበር።

ጣልያን ሀገራችንን ለሁለተኛ ጊዜ በ1928 ዓም ከወረረ በኃላ እስከ 1935 ዓም በነበረው ቆይታ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የተጠቀመበት ብቸኛ እና ዋነኛ መንገድ ሀገሪቱን በጎሳ የመከፋፈል ሥራ ነበር።ጣልያን የመከፋፈል ሥራ ብቻ አይደለም የሰራው ከአድዋ ዘመቻ ጀምሮ እስከ ማይጨው ድረስ ለሽንፈቱ እንደ አንድ ምክንያት የሚያስበው በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ጎልተው ይታያሉ ያላቸውን የዓማራ አካባቢ ተወላጆች የሆኑት ላይ ሌላው ሕዝብ ጥላቻ እንዲያድርበት ቅስቀሳ የማድረግ ሙከራ ነበር። ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ይህንን የአምስት ዓመት የጣልያን መርዝ ለማምከን ከፍተኛ ሥራ ሰርተዋል።ከሥራዎቻቸው ውስጥ በሁሉም ክፍለ ሀገር ዋና ከተሞች በእኩል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መክፈት፣ካለ ምንም ማዳላት ከሱማሌ  እስከ አፋር፣ከምፅዋ እስከ ሞያሌ የገበሬውን ልጆች ለወላጆች ቀለብ እንዲሰጥ እያደረጉ አዲስ አበባ የአዳሪ ትምህርት ቤት አስገብቶ ማስተማር እና ዘር፣ጎሳ የማይለዩ የኢንዱስትሪ ከተሞች ለምሳሌ እንደ ወንጂ ያሉትን መመስረት የሚጠቀሱ ነበሩ።

በ1967 ዓም ዘውዳዊው ስርዓት በወታደራዊ መንግስት ሲቀየር ለውጡን ተከትሎ የተነሱት ሹክቻዎች መነሻቸው ርዕዮተ ዓለማዊ እና የነበረ እና ያልነበረ መደብ በመፍጠር ዙርያ እንጂ ብሔርን መሰረት ያደረጉ አልነበሩም።አንድ መቶ ሀያ አባላት የነበሩት የደርግ ምክር ቤት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የተውጣጡ ኢትዮጵያን ያስቀደመ  መፈክሩም ''ካለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም'' የሚል ነበር።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የብሔር ፖለቲካ በተደራጀ እና መንግስታዊ ቅርፅ ይዞ የወጣው ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት በ1983 ዓም በሽግግር መንግስት ሲመሰረት ነው።እስከ 1997 ዓም ድረስም የብሔር ፖለቲካ እንደፈለገ በሕዝቡ ውስጥ ለመስረፅ አልቻለም።ለእዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ ስር መሰረት ያለው ጠንካራ ማኅበራዊ እሴት በቀላሉ ሊሸረሸር ባለመቻሉ ነበር። ሆኖም ግን ይህ ሁኔታ ከ1990ዎቹ መጨረሻ እና 21ኛው ክ/ዘመን መጀመርያ ላይ የጎሳ ፖለቲካ  የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተን ጉዳይ እየሆነ መጣ።

በሀያ አንደኛው ክ/ዘመን መጀመርያ ላይ የተጠናከረ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴዎች ከታየባቸው ውስጥ የኦሮሞ እና የዓማራ  የብሔርተኝነት እንቅስቃሴዎች ናቸው።እንቅስቃሴዎቹ  የብሔር ፖለቲካ ጠበቃ ነች ያለውን ህወሓትን እራሱን ከማነቃነቅ በላይ በእራሱ በኢህአዴግ ተበልጦ ከስልጣኑ እንዲወርድ ሆኗል።ይህ ማለት ግን የለውጥ ኃይሉ ምንም ኢትዮጵያዊነት ቀዳሚ አጀንዳው ቢሆንም አደረጃጀቱ ግን አሁንም ብሄርን ያማከለ መሆኑ ይታወቃል።

የጥፋት ዘመን የተሰኘው መፅሐፍ በዓማራ ብሔርተኘንት ላይ አዲስ መነቃቃት ፈጥሯል።


ይህ በእንዲህ እያለ ነው የጋዜጠኛ እና ደራሲ ሙሉ ቀን 'የጥፋት ዘመን' የተሰኘው መፅሐፍ በሀገር ውስጥ እና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ መነበብ ጀመረ።መፅሐፉ ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ''ዓማራ'' ናችሁ በመባል የተፈናቀሉት ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የብሔርተኝነት ስሜት ተቀጣጠለ።በሌላ በኩል በኦሮምያ ከነበረው ሕዝባዊ አመፅ ጋር በተያያዘ በህወሓት የሚታዘዙ ወታደሮች ግድያ አንፃር በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ መቀጣጠሉ እንደ አንድ ስልት ብቻ ሳይሆን ከምር የእራሱ የሆነ አስፈሪ ቅርፅ ያዘ።ህወሓትም ትግራይ ላይ ለመቆየትም ሆነ ሕዝቡን በሰብዓዊ ጋሻነት ለመጠቀም  የብሔር ፖለቲካን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን የምዕራብ ትግራይ ነዋሪ አዛውንቶች እና አሮጊቶች በሽሬ ከተማ ክላሽ ጠብመንዣ እያስያዘ ያስፎክር ጀመር።

በዓማራ አንፃር የሚነሳው የብሔርተኝነት ጥያቄ አስመልክቶ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ሙሉቀን ጨምሮ የዓማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሚሉት አንድ ጉዳይ አለ።ይሄውም የሕልውና ጉዳይ ስለሆነ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴው አስፈላጊ ሆነ  የሚል ነው።እዚህ ላይ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ''የጥፋት ዘመን'' በተሰኘው መፅሐፍ ላይ ያቀረባቸው  ዓማራ በመሆናቸው ብቻ በግፍ የተገደሉ፣የተሰደዱ እና አካላቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን ታሪክ እጅግ ልብ የሚነካ እንደ ኢትዮጵያዊነትም የተፈፀመው ጉዳይ አሳፋሪ ነው።ይህ ማለት በመጠን ይለያይ እንጂ የእልቂት ድግስ በኦሮሞ፣ኮንሶ፣ራያ፣ጋምቤላ እና ሱማሌ ሁሉ ተፈፅሟል።የአንዱ ከአንዱ የሚከፋበትን መንገድ ለመግለጥ በርካታ ምክንያቶች መዘርዘር ይቻል ይሆናል።

የብሔር ፖለቲካ መለጎምያ ካልተበጀለት  መጨረሻውን የሚያውቀው የለም።

አሁን ጥያቄው አንድ ነው።ይሄውም መቼ ነው ኢትዮጵያ ያለፈ የቂም ቁስል እያመረቀዘ ከሚጎዳት አዙሪት የምትወጣው?  የሚለው ነው።ብዙዎች የዓማራ እንቅስቃሴ ከሌሎች የብሔር እንቅስቃሴዎች የተሻለ የሚያደርጉበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያዊነት ላይ ጥያቄ የማያነሳ ብቻ ሳይሆን  የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማን ብቻ የሚጠቀም መሆኑ ነው።ይህ ማለት ግን በብሄር ፖለቲካ ዙርያ አደገኛ ግብ ላይ ጥያቄ ዛሬም የለም ማለት አይደልም።ከጥያቀዎቹ ውስጥ አንዱ ዛሬ እንደዋዛ የተጀመረ የጎሳ ፖለቲካ ነገ ለልጆቻችን ብቻ አይደለም አሁን ላሉት አመራሮችም ለመመለስ ቢያስቡም እራሳቸውን በጠላትነት የሚያስፈርጃቸው መሆኑን ባሳብን ጊዜ ሁሉ ነገር በጊዜ መጠናቀቅ እንዳለበት አመላካች ነው።የብሔር ፖለቲካ ሲጀመር ብዙ ሰው ይከተለው እንጂ ወደ መደምደምያው ላይ በእኛ እና በእነርሱ  መካከል ያለ ልዩነት እንዳይፈጥር ያሳስባል።ይህንን ከህወሓት እና ከኦነግ መረዳት ይቻላል።ህወሓት በትግራይ ተማሪዎች ማኅበር አዲስ አበባ ላይ የተጠነሰሰው የብሔር ፖለቲካ ትግራይ ገበሬ ላይ ሲደፋ ሕዝቡን ህወሓት ከጠበቀው በላይ ብሄርተኛ አድርጎ ያወጣዋል ብሎ አልገመተ ይሆናል።አልያም ሲያስቡት በፈለጉት ደረጃ ሲደርሱ መልሰው የምያበርዱት መስሏቸው ይሆናል።ሆኖም ግን ይህ ሊሆን አልቻለም።የብሔር ፖለቲካ ክፋቱ በፈለጉ ጊዜ ልመልስህ ብለው ቢያስቡም የሚያመልጥበት ጊዜ አለ።የብሔር ፖለቲካ መለጎምያ ካልተበጀለት  መጨረሻውን የሚያውቀው የለም። ሀገር ይዞ ወዴት እንደሚያደርስ ለመገመትም ከባድ ነው።

በመጪው ቅዳሜ፣ጥቅምት 17፣2011 ዓም ( ጥቅምት 27፣2018 ዓም) በኦስሎ ከቀኑ 14.30 ጀምሮ በALNAFETGATA 2 (አንደኛ ፎቅ)   የሚመረቀው የጋዜጠኛ እና ደራሲ ሙሉቀን ''የጥፋት ዘመን '' የተሰኘው መፅሐፍ  የእንግሊዝኛ  ትርጉም ''The Amhara Holocaust'' አማርኛ ለማይናገረው የውጭው ዓለም እና በውጭ ለተወለዱ ኢትዮጵያውያን የጎሳ ፖለቲካ የደረሰበትን እጅግ አደገኛ ደረጃ አመላካች ነው።

በመጨረሻም ከእዚህ በፊት በአማርኛ የታተመውን  የመፅሐፉን ይዘት ተከትሎ ወንጀሉን የፈፀሙ ግለሰቦች ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጥ እና በውጭ የመኖራቸውን ያህል ተከታታይ የማጣራት ሥራ አከናውኖ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ የእስር ትእዛዝ እንዲወጣ በማድረግ ድርጊቱ ለትውልድ አስተማሪ እንዲሆን መደረግ አለበት የሚሉ የመኖራቸውን ያህል፣ ያለፈ ቂምን ትቶ የወደፊቱ ላይ ማተኮር  የሚሉ ኢትዮጵያውያንም አሉ።የሚናፈቀው አሁንም ግን ኢትዮጵያዊነት የነገሰባት፣እኩል ተጠቃሚነት በሕግ የተደነገባት ሀገር ማየት መሆኑን ሁሉንም ያስማማል።


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...