ፕሮፌስር ብርሃኑ ነጋ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር
ነሐሴ 6/2010 ዓም (ኦገስት 12/2018 ዓም)
በኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ውስጥ ላለፉት አስር ዓመታት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገሮች እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ከፍተኛ አመራር እና በውጭ ያለው የአባላት ልዑክ በጥቂት ቀናት ውስጥ አዲስ አበባ እንደሚገባ ለማወቅ ተችሏል።ንቅናቄው ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ሁለት አይነት ስልቶችን በጥምረት በትግል ስልትነት የተጠቀመባቸው መንገዶች ሕዝባዊ እንቢተኝነት እና የትጥቅ ትግል የሚሉ ሲሆኑ በግብነት የተቀመጡት ደግሞ ስርዓቱን ለዲሞክራሲያዊ ለውጥ ማስገደድ ወይንም ማስወገድ የሚሉ ነበሩ። በሐምሌ ወር መጨረሻ 2010 ዓም የድርጅቱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ፣ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እና አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በተገኙበት ዋሽንግተን ላይ በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ድርጅቱ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ አሁን የተፈጠረውን የዲሞክራሲያዊ ሂደት ማገዝ የዜግነት ግዴታ መሆኑን አስምረውበታል። የድርጅቱ ሊቀመንበር በእዚሁ በዋሽንግተኑ መግለጫ ላይ የድርጅቱ ወደ ሀገር ቤት የመግባት ፋይዳ አስመልክተው ሲናገሩ : -
'' አርበኞች ግንቦት 7 አሸነፈ አላሸነፈ የሚለው ፈፅሞ እኛ ኮንሰርን የምናገርገው ጉዳይ አይደለም።ግንቦት 7 ስንመሰርት ጀምሮ እስካሁን የምንሄድበት መንገድ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት ማንም አሸነፈ ማን አስፈላጊ ነው የሚል ነበር።አሁን ያ ስርዓት ተመሰረተ እያልን አይደለም።ነገር ግን ሂደቱን ማገዝ ይገባናል።አሁን ኢትዮጵያ የተፈጠረው የለውጥ ኃይል መልካም ጅምር መቀልበስ የለበትም።ይህንን ማገዝ ደግሞ ሀገር የማዳን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሀገር የማዘመን ሂደት ነው'' ብለዋል።
በእዚሁ መግለጫ ላይ አርበኞች ግንቦት ሰባት በማንነት እና በብሔር ጉዳይ አስመልክቶም ፕሮፌሰር ብርሐኑ ሲናገሩ : -
'' ማንነትን በተመለከተ እኛ ግልፅ አቋም አለን። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካ በራሱ የሚመለከተው አጠቃላይ ማኅበረሰብን የሚመለከት ነው።የሀገር ጉዳይ እና የፖለቲካ ጉዳይ ለእዚህኛው የሚፈቀድ ለእዛኛው የማይፈቀድ የሚባል ነገር የለም።የፖለቲካ ውሳኔ በወል የሚሰጥ እንጂ አንዱን የሚመለከት ሌላውን የማይመለከት ሊሆን አይችልም። በእኛ አመለካከት በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ነው የምንከተለው።ይህ ማለት ግን በቋንቋ ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶች ጋር በጠላትነት እንተያያለን ማለት አይደለም።ይህንን ሀገር ልትገባበት ካለችበት 'ሲኦል' እናውጣ ካልን የሰከነ ውይይት ማድረግ እንደሚፈልግ እናምናለን።'' ብለዋል።
አርበኞች ግንቦት ሰባት ባለፈው ወር መጨረሻ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር በሁለት ክፍል የተከፈሉ ለሁለት ተከታታይ ቀናት መወያየቱ ይታወሳል።በኢትዮጵያ ውስጥ ሀገራዊ አጀንዳ እና በዜግነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት ለማምጣት ከሚታገሉ ድርጅቶች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚገኘው የአርበኞች ግንቦት ሰባት በሀገር ውስጥ በከፍተኛ ስሜት እየተጠበቀ ለመሆኑን ከሀገር ቤት የሚመጡ ዘገባዎች ያሳያሉ። ለእዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድንገት ደራሽ አለመሆናቸው እና በ1997 ዓም በነበረው ምርጫ እና በምርጫው ሂደት በነበረው ቅስቀሳ ሁሉ የፖለቲካ አቋማቸውን እና እሳቤያቸውን ሕዝብ የማወቁ ፋይዳ አንዱ ምክንያት ነው።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራሮች እና የአባላት ልዑክ አዲስ አበባ ሲገባ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከመላ ሀገሪቱ መጥቶ እንደሚቀበላቸው እና በአዲስ አበባ ስታድዮም፣ በሚሊንየም አዳራሽ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ልዩ የአቀባበል መርሃ ግብር እንደሚኖር ይጠበቃል።በመጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ ሰሞኑን ከገቡት የተቃዋሚ ድርጅቶች በተለየ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር እና ልዑክ ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ መንግስት ማናቸውንም ወጪ ለመሸፈን በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ቢቀርብም ድርጅቱ በእራሱ ማናቸውንም ወጪ እንደሚሸፍን ማስታወቁን የዋዜማ ራድዮ በዛሬው ዕለት ገልጧል።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment