ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, November 18, 2017

የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በኖርዌይ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ ኦስሎ ከተማ ውስጥ አደረገ።

ፎቶ ከኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በኖርዌይ ድረ-ገፅ የተወሰደ 

ጉዳያችን ዜና  / Gudayachn News 
==========================

የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በኖርዌይ ዛሬ ህዳር 9፣2010 ዓም በኦስሎ ከተማ "አንቲ ራሲስት ሴንተር" በሚገኘው ህንፃ ስድስተኛ ፎቅ በሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ ባደረገው የአባላት ስብሰባ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱን መርጧል። የማኅበረሰቡ አማካሪ ቦርድ አባላት በአቶ የሱፍ፣ ዶ/ር ሙሉዓለም እና ዶ/ር ሰይፉ አስመራጭነት አምስት የስራ አስፈፃሚ አባላት ተመርጠዋል።በእዚህም መሰረት 1/ አቶ ፍቅሩ 2/ ወጣት ስርጉት፣ 3/ወጣት ማርታ 4/ አቶ አያሌው እና 5/ አቶ ለገሰ  ሲሆኑ በሰብሳቢነት አቶ ፍቅሩ ተመርጧል።በእዚህ የስራ አስፈፃሚ ምርጫ ለበርካታ ዓመታት በኖርዌይ የኖሩ ኢትዮጵያውያን በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በረጅም ጊዜ የስራ ዘመኑ ሙሉ በሙሉ በወጣት የሰው ኃይል መተካቱ  መደሰታቸውን በሰጡት አስተያየት ገልጠዋል።

አዲስ የተመረጡት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ አምስቱ የስራ አስፈፃሚ አባላት 

የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ እንቅስቃሴ የጀመረው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1987 ዓም እንደሆነ የማኅበረሰቡ ድረ ገፅ ያስረዳል።የአዲሱ ትውልድ ወደ አመራር መምጣት በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በጋራ ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያንፀባርቁበት የጋራ መድረካቸው እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል። የዛሬው ምርጫ ከመደረጉ በፊት የአማካሪ ቦርዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት የኢ-ሜል መረብ አማካይነት ከሁለት ወራት በፊት ቅስቀሳ ሲያደርግ ነበር። በዛሬው የምርጫ ሂደት የተደሰቱት በኖርዌይ ለረጅም ዓመታት እንደኖሩ የሚነገረው አቶ ካሳ በኢትዮጵያውያን የኢ-ሜል መረብ ዛሬ ማምሻውን በላኩት የደስታ መልዕክት እንዲህ ብለዋል: -

"በጣም የሚመሰገን ስራ ነው የተሰራው በቦርድ ኮሚቲዎች የተደረገው ዝግጅት ለመልካም ውጤት በቃን ዛሬ። እስካሁን አይቸው የማላወቀው ለውጥ ነው ያየሁት አጠር መጠን ያለ ስብሰባ ነበር። እንደዚህ አይነት ደስ የሚል ስብሰባ የመጀሬያ ነው "  ብለዋል።

በሌላ በኩል አቶ መምህሩ በእዚሁ የኢ-ሜል መረብ ላይ በእንግሊዝኛ ማምሻውን ምርጫውን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት:- 

" ይህ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ጥረት ላደረጋችሁ  የቦርድ አባላት እና በምርጫው ላይ ለተሳተፋችሁ ሁሉ ምስጋናዬ የላቀ ነው።ለአዲሱ የስራ አስፈፃሚ ሰብሳቢ አቶ ፍቅሩ እና ሌሎች ተመራጭ አባላት መልካም የስራ ዘመን እመኛለሁ" ብለዋል።

የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በኖርዌይ የስራ አስፈፃሚ ምርጫ የሚያደርገው በእየሶስት ዓመቱ እንደሆነ ህገ ደንቡ ያዛል። በዛሬው ምርጫ ከስራ አስፈፃሚ አባላት በተጨማሪ ሶስት የቁጥጥር ኮሚቴ አባላትን መርጧል። በመጨረሻም ተመራጭ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የቱንም አይነት የፖለቲካ አመለካከት ይኑረው፣ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ይምጣ ወይንም ምንም አይነት የሃይማኖት እምነት ይከተል ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያዊነትን ብቻ መሰረት አድርገው ሁሉንም በእኩል ደረጃ እንደሚያገለግሉ በመረጣቸው ሕዝብ ፊት ወጥተው ቃላቸውን ሰጥተዋል።

በዛሬው ስብሰባ ከተገኙት  ውስጥ 

ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት የሆኑም ሆኑ እስካሁን በተለያየ ምክንያት አባል ያልሆኑ  ኢትዮጵያውያን  በደስታ ወይንም በሃዘን ጊዜ ብቻ ዕርዳታ ለመጠየቅ ከመምጣት የማንነታችን መገለጫ እና ቤታችን ወደ ሆነው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በመቅረብ ድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባ መረዳት ይገባል።አንድን ነገር ቀርቦ በመመልከት የሚስተካከለውን እንዲስተካከል ማገዝና በምንም አይነት የአመለካከት ጥግ ላይ ቢሆኑ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ የጋራ የኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያዊነት መገለጫ ብቻ መሆኑን ተረድቶ መስራት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል። 

በአዲስ ጉልበት መልካም የስራ ዘመን ለአዲሱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እንመኛለን።


ጉዳያችን GUDAYACHN

www.gudayachn.com

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...