ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, November 9, 2017

አርአያነት ያለው የአቡነ ሕርያቆስ ሐዋርያዊ ጉዞ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 10/ 2017 እኤአቆጣጠር (ጉዳያችን ልዩ ሪፖርት)

  • የሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አገልግሎት አስፈላጊነት፣
  • ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን ለመትከል የነበረው ውጣ ውረድ፣
  • አርአያነት ያለው የአቡነ ሕርያቆስ ሐዋርያዊ ጉዞ ወደ ደቡብ አፍሪካ

አቡነ ሕርያቆስ ጆሃንስበርግ ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ሲሰጡ (ፎቶ ከማኅበራዊ ድረ ገፅ)

የሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አገልግሎት አስፈላጊነት 


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት አድማሷ ከሀገር ቤት እስከ ባህር ማዶ ልጆቿ በሚገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ ለማዳረስ በሊቃነ ጳጳሳት፣አገልጋይ ካህናት እና የወንጌል ሰባኪዎች አማካይነት ጥረት ታደርጋለች።በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አገልጋይ ካህናት እና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሚሰጡ ልጆቿ በውጭ ሃገራት በሚደረጉ ጉባኤያት ላይ በመገኘት ከሚሰጡት አገልግሎት በተለየ የሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉዞ በጥቂቶች ዘንድ ካልሆነ በቀር በብዛት አይታይም። እዚህ ላይ በውጭ የሚገኘው ሲኖዶስ ስር  መቀመጫቸውን ስቶኮልም ስዊድን ያደረጉት የአውሮፓ፣ምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ አረጋዊው አባት አቡነ ኤልያስ፣ ከሀገር ቤት ደግሞ በአሜሪካ የነቃ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት አቡነ አብርሃም እና ሌሎች የሉም ለማለት አይደለም። ሆኖም ግን ምዕመናን በተለይ በባህር ማዶ ያሉቱ የሊቃነ ጳጳሳት ወቅቱን የጠበቀ ጉብኝት እና በአጥብያ እና ሃገረ ስብከት ያሉትን አገልግሎቶች ቅኝት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ለእዚህም ምክንያቱ ከአባቶች ከሚገኘው ቡራኬ ጋር በአጥብያ ቤተ ክርስቲያኑ ወይንም በሀገረ ስብከቱ ያሉት ያልተፈቱ ችግሮች እንዲፈቱ እና መመርያ እንዲሰጥባቸው እንዲሁም በጊዜ ብዛት እየተለመዱ ያሉ የተሳሳቱ አስተዳደራዊ ስህተቶችም ሆኑ ስርዓተ ቤተ ክርስቲያን በቶሎ እርማት እንዲያገኙ ይረዳል።

የሊቃነ ጳጳሳት በቅርብ ምዕመኑን የማግኘት ፋይዳው ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ብቻ ሳይሆን ከእዚህም በዘለለ በርካታ ጥቅሞች ቢኖሩትም ምዕመናን በተለይ በሐገር ቤት ስር ባሉ አጥብያዎች  የሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳት አህጉረ ስብከታቸውን በሚገባ ሲጎበኙ እና ምእመናንን ሲያፅናኑ አይታዩም።የእዚህ አይነቱ ሁኔታ በሀገር ቤት በቤተ ክህነት ውስጥ ያለው ቢሮክራሲያዊ አሰራር በእራሱ ለምዕመናን ብቻ ሳይሆን ለሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላትም ሃገረ የስብከታቸውን ሊቀ ጳጳስ ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረድ ሲገጥማቸው ይስተዋላል።

ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን ለመትከል የነበረው ውጣ ውረድ 


የሊቃነ ጳጳሳት በቀላሉ ለምዕመናን አለመገኘታቸው ምን ያህል የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንደሚጎዳ እራሴ የማስታውሰው አንድ አብነት ለማንሳት እወዳለሁ።

ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ  ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቦታ እንድታገኝ ከፍተኛ ጥረት ላይ የነበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች የጁባ ከተማ ከንቲባን ያነጋግራሉ።በወቅቱ ለስራ ወደ ጁባ የሄዱ ወጣቶች በግለሰብ ቤት ውስጥ ሆነው በጋራ የፀሎት ቤት ነበራቸው።የጁባ ከንቲባም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  በነፃ መሬት ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ነገር ግን ከማንኛውም ሊቀ ጳጳስ አንድ ደብዳቤ ተፈርሞ ብቻ እንዲያመጡ ይነግራቸዋል። በወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ለማግኘት ልጆቹ ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ።አዲስ አበባ ቤተ ክህነት እንደመጡ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገሪማን አንዲት ደብዳቤ እንዲፅፉላቸው ይጠያቃሉ። ሆኖም ግን አቡነ ገሪማ የምስራቅ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስን አናግሩ ይሏቸዋል።የምስራቅ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ በወቅቱ የነበሩት ለወራት ሀገር ውስጥ የሉም። ከተመለሱም በኃላ አንዲት ደብዳቤ ለማግኘት (ያውም ሊቃነ ጳጳሳቱ መስራት የሚገባቸውን ሥራ ልጆቹ እየሰሩ) በርካታ እልህ አስጨራሽ ውጣ ውረድ እንደነበረ እና በመጨረሻ ከሁለት ዓመታት ልፋት በኃላ መሳካቱ እና አሁን ቤተ ክርስቲያናችን ጁባ ላይ እንደተተከለች አስታውሳለሁ።

እዚህ ላይ የሚያስደንቀው ጉዳይ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን አሰራር ነው። ከጁባ የመጡት ወጣቶች ቤተ ክህነት አንዲት ደብዳቤ ለማግኘት ደጅ እየጠኑ ሳለ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አንድ ቀን ማለዳ  በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ጁባ ገቡ።በገቡበት እለት ለግብፅ ቤተ ክርስቲያን የሚሆን መሬት ከጁባ ከተማ ማዘጋጃ ተረከቡ።በተመሳሳይ ቀን ምሽት ወደ አዲስ አበባ የሚመለሰውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይዘው አዲስ አበባ ገቡ።በኃላ እንደሰማሁት የጁባ ማዘጋጃ ቤት ባለስልጣናት በግብፁ ጳጳስ ተበሳጭተዋል። የተበሳጩት መሬት በማግኘታቸው አይደለም።ለምንድነው  አንድ ቀን ሳያድሩ እና የደቡብ ሱዳንን ባለስልጣኖች እና የሃይማኖት አባቶች ሳያገኙ የተመለሱት በሚል ነው። ይህ ከላይ የተፃፈው የእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ የሚያውቀው እውነት ነው። መፅሐፍ ግን ጳጳሳት መንጋውን ተግተው እንዲጠብቁ ሲያዝ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 20፣28 ላይ እንዲህ ይላል : - "በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።"

አርአያነት ያለው የአቡነ ሕርያቆስ ሐዋርያዊ ጉዞ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 10/ 2017 እኤአቆጣጠር


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በውጭ የሚገኘው ሲኖዶስ ስር  መቀመጫቸውን ስቶኮልም ስዊድን ያደረጉት የአውሮፓ፣ምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ  አቡነ ኤልያስ ረዳት ጳጳስ አቡነ ሕርያቆስ ከመስከረም 21 እስከ ጥቅምት 10/ 2017 ዓም እኤአ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሐዋርያዊ ጉዞ አድርገው ነበር።የአቡነ ሕርያቆስ (ስለ አቡነ ሕርያቆስ ትምህርት እና አገልግሎት ለማንበብ ይህንን ይጫኑ) ጉዞ በተለይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ በሚፈለግበት በደቡብ አፍሪካውያን ሀገር በጣም ጠቃሚ ተግባራት የተከናወኑበት ነበር።ይህ ሐዋርያዊ ጉዞ ለሁሉም አገልጋዮች አብነት ስላለው ይህንን ሪፖርት ማቅረቡ አስፈላጊ ሆነ። በተለይ አቡነ ሕርያቆስ አፍሪካውያንን ከዑጋንዳ እስከ ደቡብ አፍሪካ በአገልግሎት ዘመናቸው ከማወቃቸው አንፃር  ወደፊት ቤተ ክርስቲያን ለአፍሪካ ለምትሰጠው አገልግሎት ትልቅ ሥራ የሚሰሩ አባት እንደሚሆኑ በዑጋንዳም ሆነ በደቡብ አፍሪካ በአገልግሎታቸው ሲጠቀሙ የነበሩ ምዕመናን ደጋግመው የሚያነሱት ጉዳይ ነው። አቡነ ሕርያቆስ በአሁኑ ወቅት የኦስሎ፣ ኖርዌይ ቅዱስ ገብርኤል አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እና የአቡነ ኤልያስ ረዳት ጳጳስ ናቸው።
አቡነ ሕርያቆስ በሐዋርያዊ ጉዞ ካገለገሉባቸው ጉባኤዎች ውስጥ (ፎቶ ከማኅበራዊ ድረ ገፅ)

አቡነ ሕርያቆስ ሃያ ቀናት ባልሞላ የሐዋርያዊ ጉዞ አገልግሎታቸው በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል።ከእነዚህም ውስጥ : -

1ኛ/ በጆሐንስበርግ ጽርኀ አርያም ቅድስት ሥላሴ የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ የተሰጠው የመስቀል ዓመታዊ በዓል፣ የመስከረም ብዙኀን ማርያም፣የመስከረም ቅድስት አርሴማ ዓመታዊ በዓላት እና የዕለተ ሰንበታት የቅዳሴና የስብከተ-ወንጌል አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ ለአካባቢው ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ ትብለው የታሰቡ የሚከተሉት አገልግሎቶችም ተከናውነዋል።

ሀ/ ለጆሐንስበርግ ጽርሐ አርያም ቅድስ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔ አባላት፣ የሰ/ት/ቤት፣ የስብከተ ወንጌል ክፍል ፣ የልማት ክፍል ኮሚቴዎች፤ ለደርባን ቅዱስ ገብርኤል ሰ/መ/አስተዳደር  ጉባዔ አባላት እና ለሳሶልበርግ ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ-ክርስቲያን ሰ/መ/አስተዳደር ጉባዔ አባላት በአንድ ላይ በጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ የአስተዳደር ሲሚናር ሰጥተዋል። ሲሚናሩ

  • ሰለ የቤተ ክርስቲያን ራእይ/ርእይ (Vision) 
  • ሰለ ዕቅድና ፕላን፣ 
  • ስለ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሆነ በማህበራዊ ኑሮ የሚገጥሙ ግጭት መንሥኤዎችና መፍትሔዎቻቸው፣ 
  • ስለ ዓመታዊ ዕቅድና በጀት እና
  • ሪፖርት አዘገጃጀት አስመልክቶ በአርእስት የተከፋፈለና ያተኮረ ነበር።
ለ/ የሳሶል በርግ ቅ/ልደታ ለማርያም አዲሱ ቤተ-ክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ሕንፃ-ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተባርኮ ጽላቱ ገብቶ ቅዳሴ ቤቱን አክብረዋል።

ሐ/ ወደ ደርባን ከተማም ሐዋርያዊ ጎዞ በማድርግ በከተማው መካከል በሚገኘው በደ/ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተ/ቤተ-ክርስቲያን የሁለት ቀን የወንጌል ጉባዔና የቅዳሴ አገልግሎት ሰጥተዋል።

መ/ ለጆሀንስበርግ ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ ካህናት ስለ ክህነት ዓላማ፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት ለመሾምም ሆነ ከክህነታቸው ለመሻር ስለሚያበቋ ቸው ነገሮች፣ ሰለ ክብረ ክህነት ወዘተ ሲሚናር ተሰጥቷል።

ሠ/ ለሰ/ት/ቤት "የሀብታተ ኦ/ተ/ ቤተ-ክርስቲያን ዘኢትዮጵያ" ሴሚናር ተሰጥቷል። ከሌሎቹ ልዩ የሚያደርጋትን የቤተ ክርስቲያናችንን የፊደል፣የትምህርት፣የዝማሬ/ዜማ የፍልስፍና፣ የቴክኖሎጂ፣ የሕግ፣ የፈውስ ወዘተ ሀብቷን እንዲያስተውሉትና ቤተ-ክርስቲያናቸውን በሚገባ እንዲያውቋት በማሰብ የተካሄደ ሲሚናር ነው።


ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ያሬዳዊ ዜማ ሲያቀርቡ (ፎቶ ከማኅበራዊ ድረ ገፅ)

ከጽርሐ-አርያም ቅ/ሥላሴ ቤ/ክ ሰበካ መ/ አ/ጉባዔ ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይየተነሱ ቁም ነገሮች ውስጥ መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ/ም ከጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባዔ ጋር ሰዓታት የፈጀ ስብሰባ አካሂደው ምክር ለግሰዋል።

በስብስባው ላይ ከጠየኳቸውና ሰፊ ማብራሪያ ከተተሰጠባቸው እንዲሁም የኦስሎ ቅዱስ ገብር ኤል ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤተ-ክርስቲያንን ልምድና ተሞክሮ ካካፈሉባቸው ነጥቦች መካከል የቤ/ክርስቲያኑን አባላት አመዘጋገብና አያያዝ በተመለከተ፣ የቤ/ክን መተዳደሪያ ሕግ በተመለከተ፣ ቤተ-ርስቲያኑ የገዛውን ሕንፃ አስተዳደር በተመለከት፣ የቤተ-ክርስቲያኑን ሕጋዊ ሰውነት፣ የሂሳብ ኦዲት ማስደረግን /ማስመርመርን በተመለከተ ከመንፈሳዊ አገልግሎት በተጨማሪ የሰጧቸው አገልግሎቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ።

ባጠቃላይ አቡነ ሕርያቆስ ጵጵስና ሲመታቸው ከተፈፀመ ገና ወራትን ያስቆጠረ ቢሆንም ባሉበት አጥብያ ሳይሆን በስራቸው በረዳትነት የተሾሙበትን ሃገረ ስብከት ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ለማገልገል ሐዋርያዊ ጉዞ ማድረጋቸው እጅግ አርአያነት ያለው እና አገልግሎቱን ባገኙት ምእመናንም ዘንድ ከፍተኛ ደስታን የፈጠረ ነበር።ቤተ ክርስቲያናችን ምዕመናን ዘመኑን የዋጁ እንዲሆኑ መንገዱን ለሚያመላክቱ አባቶቻችንን እረጅም እድሜ ይስጥልን።


ጉዳያችን GUDAYACHN 
www.gudayachn.com 

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...