ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, November 14, 2017

ኢትዮጵያዊነት፣ የጎሳ ፖለቲካ እና መፍትሄዎቹ (የጉዳያችን ልዩ ዳሰሳ)




ጉዳያችን / Gudayachn

መግቢያ  

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት አገር ነች።ከዓለም መፈጠር ጋር አብራ የሚስተካከል ታሪክ ያላት እንጂ ዘመኗን ቆጥሮ እና ለክቶ መወሰን ከባድ ነው።ለእዚህም ጥንታዊ የታሪክ ቅርሶች እና የፅሁፍ ማስረጃዎች እማኞች ናቸው።ከፅሁፍ ማስረጃዎች ውስጥ ጥንታዊ የሐይማኖት መፃህፍትን መጥቀስ ይቻላል።ሁለቱ የዓለማችን ትልልቅ እምነቶች ቅዱሳን መፃፍህፍቶች መፅሐፍ ቅዱስ እና ቁርአን ከትበው የሚያስነብቡን የኢትዮጵያን ጥንታዊነት ነው።ለምሳሌ መፅሐፍ ቅዱስን ብንመለከት  በምዕራፍ አንድ ላይ ስለአለም አፈጣጠር ከተናገረ በኃላ በምዕራፍ ሁለት ላይ የማንንም አገር ስም ሳይጠራ የሚጠራት ብቸኛ የዓለም አገር ከእስራአልም በቀዳሚነት፣ ኢትዮጵያ ነች።

ኢትዮጵያ ዓረቦች ወደ አፍሪካ ከመግቦታቸው በፊት ግብጽ ይኖሩ በነበሩት ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ደግሞ ኔቶር(ሀገረ እግዝአብሔር) ከዚያ አቢሲኒያ (በንጉሥ አቢስ ስም) ከዚያ ኢትዮጵያ (በንጉሥ ኢትዮጵ ስም) በእነዚህ ስሞች እይተጠራች ኖራለች፡፡ባጭሩ ኢትዮጵያ እያልን የምናወራው ዛሬ በልዩ ልዩ የዘመን አስተሳሰብ እንደ እየሳቢያችን አጥብበን የምናያት አገር ሳትሆን ስለ ዓለም አመጣጥ የምትናገር አገር ነች።እኛ በዘመኑ የጎሳ አስተሳሰብ እራሳችንን ለማሳነስ ብንሞክር ፀባችን ከዓለም ታሪክ እና ከሰው ልጅ ህልውና ጋር መሆኑን ልብ ማለቱ ተገቢ ነው።

በአፍሪካ ነፃነታቸውን ጠብቀው ለመኖር ከቻሉ ሁለት አገሮች አንዷ፣አሁን ዓለም የሚተዳደርበት ዓለም አቀፍ ሕጎችን በዓለም ዲፕሎማሲ እኩል ተከራክራ በቀድሞው የዓለም ማኅበርም ሆነ በአሁኑ የተባበሩት መንግሥታት ምስረታ ላይ ፊርማዋን ያስቀመጠች በጎሳ ስም ሳይሆን ኢትዮጵያ በሚለው ጥንታዊ ስሟ ነው።ኢትዮጵያ  በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ ስትሆን፣ በቆዳ ስፋት ደግሞ አስረኛ ናት።አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ዕድሜያቸው ከአንድ ምዕተ ዓመት የሚያንስ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በንጉሠ ነገሥታት እና ንግሥተ ነግሥታት የተመራች ሀገር ነች የሰለሞናዊው ሥርወ-መንግሥት የአመጣጡን ዘር ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ አስረኛው ዓመተ ዓለም ድረስ ይቆጥራል።ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ብለን ስንጠራ የእነዚህ ዘመናት ሁሉ መገለጫዋን ኢትዮጵያን ነው እንጂ በተናጥል የአንድ ብሔር ስም አይደለም። 

እንዴ ኤውሮፓውያን አቆጣጠር በ1885 ዓም በበርሊን ጉባኤ  የአውሮፓ ሀያላት ሀገሮች አፍሪካን ሲከፋፍሏት፣ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃለች። ከተባበሩት መንግሥታት በፊት የነበረው የዓለም ማህበር ''የሊግ ኦፍ ኔሽን'' አባል ኢትዮጵያ ነበረች። ከአጭር የኢጣልያ ወረራ ጊዜ በኋላም ከየተባበሩት መንግሥታት ከአፍሪካ መሥራች ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ነች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን ሲያገኙ፣ ሰንደቅ አላማቸውን በኢትዮጵያ ቀለሞች ማለትም በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ላይ ነው የመሠረቱትባት ሀገር ነች ኢትዮጵያ።የኢትዮጵያን ተምሳሌትነት ዛሬ ድረስ የአፍሪካ፣የካሪባን እና የእሩቅ ምስራቅ አገሮች ከህሊናቸው አልጠፋም።

በዓለም ዙርያ በሚገኙ ታላልቅ ዩንቨርስቲዎች ውስጥ የሚገኙ ምሁራን ስለ ፍልስፍና ሲነሳ፣ስለጥንታዊ ታሪክ ሲወራ፣ስለ አፍሪካ የነፃነት ታሪክ ሲወሳ ሁሉ የኢትዮጵያን ምሳሌነት ሳይጠቅስ የሚያስተምር ምሁር የለም።የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከላት ያላቸው ዩንቨርስቲዎች በጀርመን፣እንግሊዝ፣ሩስያ እና በቅርቡ ደግሞ በካናዳ ዩንቨርሲዎች በትምህርት ክፍል (ዲፓርትመንት)  ደረጃ ከፍተው ያጠናሉ። በዓለም ካሉ አገራት ለየት ባለ መልኩ በመላው ዓለም የሚኖሩ ምሁራን እየተሰበሰቡ የኢትዮጵያ የጥናት ጉባኤ በዓለም ባሉ ከተሞች በእየ ዓመቱ ይደረጋል።ለምሳሌ የዘንድሮው በዋርሶ፣ፖላንድ ዩንቨርሲቲ መደረጉ ይታወቃል። ይች አገር ኢትዮጵያ ዓለም ይፈልጋታል።ለዓለም ቅርሱ ነች።ዓለም ማንነቱን የሚያጠናባት ቤተ መዘክሩ ነች።በውስጧ የምንኖር ዜጎች እንደፈልገን እንደጥበታችን እና ስፋታችን የምንጥላት እና የምናነሳት አገር አይደለችም። 

ኢትዮጵያ ቀደም ባለው ታሪክ ነገሥታቱ የመጡበትን አካባቢ ጀግንነት ከማውራት ባለፈ የመጡበትን ሰፈር ከኢትዮጵያዊነት ጋርም ሆነ ከጎሰኝነት ስሜት ጋር ሲያቀላቅሉት እና ሲያገዳድሩት አልተስተዋሉም።እርግጥ ነው በታሪካችን የክርስትና ሃይማኖት የበላይነት በየትኛውም የታሪክ ሂደት አንፃር ተንፀባርቁአል።የንጉሡ ወዳጅ ወይንም ባለሟል ለመሆን ከመጣበት ዘር ይልቅ ሃይማኖቱ ሲማርካቸው ተስተውሏል።ለእዚህም አይነተኛ ማሳያ የሚሆነው ከአውሮፓ እና ደቡብ እስያ የፈለሱት በታሪክ 9 ቅዱሳን ተብለው የሚጠሩት እና የነቢዩ መሐመድ ቤተሰቦችን ወደ ኢትዮጵያ መሰደድ መመልከቱ በቂ ነው።የቀደሙት ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ እና ኃላፊነት ይሰማቸው ነበር እንጂ በአካባቢ ጉዳይ እና ስሜት ተገዢ አለመሆናቸውን መረዳት ይቻላል። መነኮሳቱ በመልክ ነጮች፣በባህል ልዩዎች ይሁኑ እንጂ በራሳቸው ሃይማኖታዊ መንገድ ከመረመሩ በኃላ በፈለጉት ቦታ እንዲኖሩ የፈለጉትን እንዲሰሩ ፈቅደውላቸው ነበር። መነኮሳቱም ገዳማትን ገድመው ግዕዝ ተምረው ብዙ መፃህፍትን ፅፈው ለማለፍ ችለዋል።እነ አቡነ አረጋዊን ከሮም የደብረ ዳሞ ገዳምን ገድመው ለመኖር እና በሀገሪቱ ሙሉ መብት እንዲኖራቸው የተደረጉት ከእዚሁ ጎሳን እና ዘርን ከማያማክለው የመንግስት ስሪት በሚመነጩ ባህርያት በተካኑ የኢትዮያ መሪዎች ውሳኔ ነው። አሁን ያለው ኢትዮጵያን የምንለካበት ልኬት ምን ያህል የወረደ እና የተሳሳተ ትናንሽ ስሜቶች ተገዢ እንደሆነ ለመረዳት እራሳችንን በቀደሙት የእዚች አገር መሪዎች አስተሳሰብ ተገብተን ማሰብ መጀመርን ይጠይቃል። 

 የጎሳ ፖለቲካ ያቆሰላት አገር 


(ማሳሰቢያ - ከእዚህ በታች በሚኖረው ፅሁፍ ''የብሔር ፖለቲካ'' የሚለው ለአገር ስለሆነ  ''ብሔር'' የሚለውን ቃል  አልጠቀምም። ''ርዕሰ ብሔር'' ማለት የአገር መሪ እንጂ የጎሳ መሪ ማለት እናዳልሆነ ሁሉ ማለት ነው። 

የጎሳ ፖለቲካ አለማችን አዲስ ክስተት አይደለም።የአምባገነኖች መሸሸጊያ ጉረኖ ዘረኝነት እና የዘር መርዝ መንዛት ነው። አዶልፍ ሂትለር የጦርነት ጥማቱን ለማርካት ጀርመንን ህዝብ የተለየ ህዝብ አድርጎ ማቅረብ ነበረበት። ¨እናንተ ጀርመን ህዝቦች 'አርያን'ዘሮች ¨ እያለ ይሸነግል ነበር።ሰዎች በባህሪያችን ብልህ የመሆናችንን ያህል ጅልነትም አያጣንም።አንድ አውሬነት የተጠናወተው ግለሰብ የአካባቢ ጉዳይ አንስቶ በቀላሉ የሚነዳን አይነቶች።ሁኔታዎች ስህተት መሆናቸውን የምንረዳው እና የምንነቃው ወደ ትክክለኛ ከብዙ የሰው ልጅ እልቂት በኃላ ነገሩ ዘግንኖ ወደ አእምሮአችን ተመልሰን ስንንቃ ነው።

 ሁለተኛው አለም ጦርነት እልቂት አቶ አዶልፍ ሂትለር ''ጀርመን ሆይ! ¨አንተ እኮ አርያን ዘር ነህ¨ ብሎ ነው አለም ጥፋት እሳቱን የለኮሰው። ሞሶሎኒም ኢጣልያ ህዝብ ኢትዮዽያን መውረር እንዳለበት ለማሳመን ¨ታላቋ ሮማ ህዝብ ሆይየምትለዋን ዘረኝነት ቃል መጠቀም በቂው ነበር። አምባገነኖች ዘር ፖለቲካቸው ሲናድ ይደነግጣሉ፣ይርዳሉ።ስለ እዚህ ዘረኝነትን ይንከባከቡታል::ወደ ስልጣን ለመወጣጫነትም ጥሩ የመጫወቻ ካርድ አድርገው ይጠቀሙባታል።

 የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ትውልድ የለውጥ እንቅስቃሴ ሃሳቦችን ብልጭ በማድረግ ስለ ርዕዮተ ዓለም ብዙም ጠልቆ የማያውቀውን ወታደሩ አጠገቡ ያገኘውን ርዕዮት እንዲጨብጥ አድርጎታል፡፡በእዚህ እንቅስቃሴ ስር የተንቀሳቀሱት ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል የፓርቲዎቹ አደረጃጀት  ስር ነቀል ለውጥ የሚያቀነቅኑ እና የማርኪዝም ፍልስፍናን እንደ ዋነኛ መተንተኛ ሰነድ የሚጠቀሙ ነበሩ።ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ህወሓት፣ ህግሐኤ (ህግድፍ) ለዚህ ዋቢ ናቸው፡፡ ኢሕአፓ እና መኢሶን ኢትዮጵያን የሚረዱበት እና ለመለወጥ የሚሞክሩት አግባብ የመደብ ቅራኔና  ዋነኛ አንጓ  በማድረግ ነበር፡፡በሌላ በኩል ህወሓት እና ኦነግ የብሔር ቅራኔውን በማስቀደም የብሔረሰቦች መብት መከበር የችግሩ መፍትሄ መሆኑን ያስቀምጣሉ፡፡ ነገር ግን ኦነግ የኤርትራን ጉዳይ ሙሉ ቅኝ ግዛት (Classical colonialism) መሆኑን ገልጾ የኦሮሚያ ጉዳይ ግን የውስጥ /የአቢሲኒያ ቅኝ ግዛት በመሆኑ ኦሮሚያን ከቅኝ ግዛት ነፃ ስለማድረግ እንደሚታገል ይገልፃል፡፡የዚህ አስተሳሰብ ድባብ ዛሬም ድረስ ከዚህ አካባቢ በተገኙ የተወሰኑ ምሁራን ላይ ይንፀባረቃል፡፡ የብሔረሰብን ጉዳይ በዋነኝነት በተመሳሳይ መልኩ የያዘው ህወሓት ስለጎሳ ጉዳይ አብዝቶ የማንሳቱን ያክል ኦነግ ስለ ጎሳ ሲያነሳ ደግሞ አይጥመውም።ምክንያቱም ጉዳዩ የስልጣን ሽምያ እና ጎሳን ሁሉም የሚጠቀመው ለስልጣን መወጣጫ ስልት በመሆኑ ነው።በሌላ በኩል በወታደሩ የተመሰረተው የኢሠፓ (ኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ) ሌላው  መሠረቱን ግራ ዘመም እና ፍፁም ፈላጭ ቆራጭ ቢሆንም በጎሳ አስተሳሰቦች ውስጥ ያልጠነከረ ይልቁንም ለሀገራዊ አንድነት እና ማንነት የሚሰጠው ልዩ ትኩረት ከቀኝ ዘመሞች የተወሰደ መሆኑ ነው፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ 1967ዓም ከነበረችበት ሁኔታበብዙ የተለዩ አዳዲስ ክስተቶች አሉባት።የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆኑ አንድ ትውልድ አልፎ አዲስ ትውልድ ተተክቷል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 30 ሚልዮን  በሶስት እጥፍ ወደ 90 ሚልዮን ተተኩሷል፣የባሕር በሯ ተዘግቷል፣ወጥ የነበረው የመንግስት ስሪት በጎሳ እና ቋንቋ ላይ በተመሰረተ አስተዳደር ተቀይሯል፣ከተሞች በመጠን ሰፍተዋል።በከተማ የሚኖረው ሕዝብ ከገጠሩ ጋር ሲነፃፀር ግን በእነኝህ ሁሉ ሶስት አስር አመታት በኃላም 90 በመቶ ወደ 85 (83) በመቶ ነው ዝቅ ያለው።የህዝቡ የኑሮ ደረጃ አቆጣጠር 1970 ዎቹ ነፃነታቸውን ከተቀዳጁት የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች ለምሳሌ እንደ ናይጀርያ፣ጋና ጋር  አንፃርም ገቢው ዝቅተኛ የሚባል እና ከእጅ ወደ አፍ ነው።በአፍሪካ ቀንድ የነበረን አማላይነት በምድር ጦር፣በአየር ኃይል እና በባህር ኃይል  የበላይነት ነበረን ።ዛሬ ግን በሕዝብ ብዛት እና ዙርያችንን ያሉት የትናንሽ ደካማ ሃገራት መኮልኮል አጉልቶ ካሳየን የበላይነት ባለፈ መድረስ የሚገባንን ደረጃ አለመድረሳችንን ለማረጋገጥ ብዙ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም።

ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የገጠማት ተግዳሮቶችን በሶስት  መልክ ማስቀመጥ ይቻላል።እነርሱም 
የውስጥ ቁርሾ፣
- ፍፁም አምባገነናዊ አገዛዞች እና 
- ቀጥተኛ እና እጅ አዙር የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነቶች ናቸው።

የውስጥ ቁርሾው በተቻለ መጠን የሚቀልባቸው መንገዶች እንዳይኖሩ እልህ የተጋባው የአምባገነንነት እርምጃዎች በእሳት ላይ ቤንዚን የማርከፍከፍ ያክል ብዙዎች ሳያስቡት ቁርሾውን ለማባባስ ሰበብ እንዲሆኑ ሆነዋል።ደርግ የእርስ በርስ ጦርነቶቹ በተቻለ መጠን ለማቅለል ከውስጥ የነበረበትን የህዝብ ድጋፍ ማጣት ስልጣንን ለሕዝብ በማስረከብ ሊያቀለው አልፈለገም።ይልቁንም ጦርነቶቹ የሰራዊቱን በሥራ መጠመድ ማምጣቱ የታያቸው ወገኖች እንደ መልካም እድልም ተመለከቱት።ለእዚህ ማሳያ የሚሆነን የበዓሉ ግርም ''ኦሮማይ'' መፅሐፍ ላይ የነበረውን የቀይ ኮኮብ ዘመቻ ማስታወሱ ነው።ጋዜጠኛው በዓሉ ግርማ ጦርነቱ በቶሎ እንዳያልቅ እና ሰራዊቱ እንዳያርፍ የሚፈልጉ መኖራቸውን ያሳየበት ፅሁፍ አምባገነኖች ሁል ጊዜ ከብሄራዊ ጥቅም ይልቅ የስልጣን ጥቅም እንድሚበልጥባቸው ያሳያል።

መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ 

ኢህአዲግ/ወያኔ ዘመን ደግሞ የውስጥ ቁርሾው በደርግ ዘመን ከነበረው የህዝብን ስልጣን ለሕዝብ የማስረከብ ጥያቄን የመመለስ ሙግት ብቻ ሳይሆን ''መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ማኅበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት ላይ አደገኛ ጥላ አጠላ።የጎሳ ግጭቱ ከክልሎች የመሬት ግጭት አልፎ እስከ መንደር የከብቶች መሰማርያ ሜዳ ድረስ ኢትዮጵያውያን አጋጨ። ይህ ስርዓት በተለይ ቁጭ ብሎ ህብዝ ከህዝብ ጋር ለማጋጨት የሚሰሩ የደህንነት ሰዎች ያሉት መሆኑ ኢትዮጵያ ምን አይነት አደገኛ ሁኔታ ላይ መሆኗን ያሳያል። 

የእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ በአንድ ወቅት ከስርዓቱ አገልጋይ ግለሰብ የቦረና ጉጂን ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ለማጋጨት እንዴት እንደተሳተፈ የተናገረውን ቃል በቃል ከግለሰቡ መስማቱን ያስታውሳል። በመሆኑም ከአሉባልታ ባለፈ ኢህአዴግ/ህወሃት የኢትዮጵያ ህዝብን በመንደር ለማጋጨት ሙሉ ኃይሉን የሚጠቀም ለመሆኑ እማኝ መሆኑን ይገልጣል።በእነኝህ የጎሳ ግጭቶች የተነሱ ፀቦችን ለማስቆም ዋናው ችግር ''የመንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' መሰረት ያደረገውን የፌድራል  ስርዓት በትክክለኛ የመሬት አቀማመጥ እና የህዝቦች ታሪካዊ አሰፋፈር መሰረት ያደረገ የፌድራል ስርዓት መቀየር መሆኑ እየታወቀ ኢህአዲግ/ወያኔ የተጋጩትን የጎሳ አባላት መዳኘትን እንደ ትልቅ ግብ እየቆጠረ በዜና እወጃው ላይ በስኬት ዜናነት ማውራቱን ቀጥሏል። ባጭሩ ባወጣው የጎሳ ፌደራሊዝም ስርዓት እና ሆን ብሎ ባጠመዳቸው የማጣያ መረቦች ተጠቅሞ  ህዝብን ካጋጨ በኃላ መልሶ እራሱ በፌድረሽን ምክር ቤት እያየሁት ነው እያለ ያፌዛል።የችግሩ መፍትሄ ግን የተሳሳተው ፖሊሲ እና የተንኮል ሥራ እንጂ የተጣሉትን ለመዳኘት የሚደረግ የማስመሰል ሽር ጉድ አይደለም።

1983 ዓም ተከትሎ “የብሔር ብሔረሰብ መብት” የመፍትሄው ማዕከል  ነው ተብሎ ብዙ ተነግሮለታል፡፡ሆኖም ግን ያለፉት 25 ዓመታት ያሳዩን ከሃያ አምስት አመታት በፊት የነበረውን ሳይንሳዊ ትንተና ነው።የጎሳ ፖለቲካ እና ፌድራሊዝም የግጭት እና የብጥብጥ ምንጭ መሆኑን። ይህ ጎሳ ተኮር ግራ ዘመም አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ታሪክ እና ባህላዊ/ እሴታዊ ማንነቶች ከፍተኛ ንቀት ያለው  ከመሆኑም በላይ ለእነኝህ እሴቶች ዋጋ የሚሰጡትን ሁሉ  እና አስተሳሰብ ተባባሪ የነበሩትን ሁሉ  ከማግለል ጀምሮ በተለያዩ ዘዴዎች ማፈን፣ ማሳደድ እና መጨቆን እንደ ዋና ስልት ይመለከተዋል፡፡

በቪየና ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፓሎጂ ትምህርት ክፍል ተመራማሪ የሆኑት / ወንድወሰን ተሾመ እውነተኛ በሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች አማራጭ መንግሥት ሆነው አገሪቱ በሕግ እና ስርዓት እንድትመራ የማድረግ ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡  “ጠንካራ ተቃዋሚ፣ የዴሞክራሲ መወላወል ባለባቸው መንግሥታት ውስጥ ቁጥጥር እና ተጠያቂነትን ስለሚፈጥሩ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት ዋናውን ሚና ይጫወታሉ” በማለት ያስረዳሉ ፡፡
ኢህአዴግ/ህወሃት ሀገሪቱን እንደ ተቆጣጠረ በጥቂቶች ዘንድም ቢሆን ጥቂት ተስፋ አሰንቆ ነበር፡፡ በተለይም በ1994 ዓ.ም የወጣው አዋጅ ቁጥር 82/1994 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ ፈቃድ የሚያትት በመሆኑ፡፡ አዋጁ ማንኛውም እድሜው ከ18 አመት በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የፖለቲካ ፕሮግራም እና የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ ካለው በአንቀጽ 4.1 መሠረት የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

የኢሕአዴግ/ህወሃት የመድበል ፓርቲ ውሳኔ ላይ ጥያቄ መነሳት የጀመረው ብዙም ሳይቆይ ነበር፡፡ለይስሙላ ያወጣው ሕግ በተለይ የሀገራዊ /ህብረ ብሔራዊ/ ፓርቲዎችን መደራጀትን በአይነ ቁራኛነት የተመለከተ እና ውስጥ ለውጥ በጥላቻ  የማደናቀፍ ተግባራት የተሞላ ነበር፡፡ በሕጉ መሰረት አንድ ቡድን ሀገራዊ ፓርቲ ለመመስረት 1500 መስራች አባላት ኖሮት ከአራት ክልል የተገኙ ከያንዳንዱ ክልል ቢያንስ ከ15% በላይ እንዲሁም ከፍ ሲል 40% ያልበለጡ መስራቾች መፈረም አለባቸው።ይህ ሁሉ ግን ዛሬ ተረት ሆኗል።መደራጀት አይደለም ሃሳብን ገልጦ አንዲት መስመር መፃፍ ዋጋው አንዲት ጥይት በሆንበት ዘመን ላይ እንገኛለን።

ዶ/ር ወንድወሰን ተሾመ በቪየና ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፓሎጂ ትምህርት ክፍል ተመራማሪ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2008 ዓም በዓለም አቀፉ ሰብአዊ ሳይንስ የምርምር መፅሄት ላይ የኢትዮጵያን የኢህአዴግ/ህወሃት የጎሳ ፖለቲካ በሚገልፅ ያወጡት የጥናት ፅሁፍ ገፅ 11 ላይ እንዲህ የሚል ይገኝበታል።

'' የጎሳ ፈድራሊዝም የህወሃት 'ከፋፍለህ ግዛ' ፖሊሲ ሲሆን የተዋቀረበት ዋናው ምክንያትም ስርዓቱ የራሱን ስልጣን ለማስጠበቅ ነው።ሁኔታው ግን አገሪቱን እንዳትከፋፈል ያሰጋል'' ያላል።
''...Ethnic federalism is the ''divide and rule'' policy of the TPLF designed to strengthen its own position and it might lead the country into disintegration'' International Journal of Human Sciences, 2008, 11p).
ethnic federalism is the “divide and rule” policy of the
TPLF designed to strengthen its own positio
n and it might lead the country into
disintegration

የኢትዮጵያ የቅርብ ወቅታዊ ተግዳሮት ምንድን ነው?

ሁለተኛው አለም ጦርነት አንስቶ እስከ 1980 ዎቹ አቆጣጠር ተጋግሎ የቆየው የቀዝቃዛው ጦርነት ኢትዮጵያ ወደራሷ የችግር ፈቺነት አቅም ሳያሸጋግር ''ለመንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' አስረክቧት ቀዘቀዘ።ቀድሞ በምዕራባውያን ትምህርት የተዋከበው የእድገት ስልት ቀጥሎ በመጣው በደርግ ሶሽያልስታዊ አስተሳሰብ ተተራምሶ ከዛሬ 24 አመት ገደማ ደግሞ ''መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' ቅርፁም ሆነ ይዘቱ ትውልድ አሻጋሪ እንዳይሆን ሆነ።

ዛሬ የምዕራባውያን ''ሌክቸር'' መሰል አመራርም ሆነ የሶሻልስቱ አለም የማያላውስ ቀጭን ትዛዝ የኢትዮጵያ እራስ ምታቶች አይደሉም።የአካባቢ የአረብ መንግሥታት ግፊት ግን የቅርብ እና ከባድ የኢትዮጵያ ተግዳሮት ነው።ከኢህአዲግ/ወያኔ በፊት የነበሩት መንግሥታት በማዕከላዊነት ይዘውት የነበረውን የሀገር ጉዳይ በጎሳ ስለሸነሸነው ለአካባቢ ''ኢትዮጵያን አረብ ማድረግ አለብን'' እንቅስቃሴዎች እጅግ አመቺ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።ኢትዮጵያን አረባዊ የማድረጉ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በጥቁር ህዝቦች ላይም የተሞከረ እና የታቀደ ይልቁንም እስልምናን ከሃይማኖት ይልቅ ፖለቲካዊ ጥቅሙን ብቻ ነቅሶ የመንቀሳቀስ አላማ የያዘ ነው።ኢትዮጵያን አረባዊ (እስላማዊ ሀገር ) በማድረግ ሂደት ላይ በጉልህ የተሳተፉ ውስጣዊ ኃይላት አሉ።እነርሱም-

1/ የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስት  እናፅፈኛ አጋርተብዬ የጎሳ ድርጅቶቹ


2/ኢህአዲግ/ወያኔን እንቃወማለን የሚሉ ግን የመገንጠል አላማን እንደማስፈራርያ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ናቸው።


ለምሳሌ ዑጋዴን ነፃነት ግንበር እና በኦሮሞ ሕዝብ የሚገዘቱ ግን ማኅበረሰቡን የሚጎዱ ተግባራት የተሰማሩ እና ወደ ስልጣን ለመንጠላጠያነት በስልትነት ብቻ የሚጠቀሙበት ናቸው።

እነኝህ ኃይሎች ከእራሱ ከኢህአዴግ/ህወሃት ጋር  የተለያዩ ይምሰሉ እንጂ ያጣላቸው የበላይ ለመሆን የሚደረግ ግፍያ ካልሆነ በቀር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው።ለምሳሌ ትግራይን የመገንጠል አላማ ይዞ በፕሮግራሙም አካቶ ይንቀሳቀስ የነበረው ህወሓት ዛሬም መንግስት ከሆነ በኃላም የቀድሞ የጎሳ ስሙን ካለመቀየሩም በላይ ለስልጣን ያበቃቸው አጋር ድርጅቶቹ ባብዛኛው በአንድም ሆነ በሌላ ኢትዮጵያን አረባዊ (እስላማዊ) ለማድረግ ከሚሹ ኃይላት በተገኘ የስልጠና፣የቁሳቁስ እና የገንዘብ ድጋፍ የተመሰረቱ ናቸው።ይህንን  ድጋፍ ዛሬም ድረስ እያገኙ ነው።

እነኝህ በተለያየ የጎሳ ድርጅቶች ስም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አላማቸውን ለማስፈፀም የሚሞክሩት እና የሚተገብሩት በአፈሙዝ ነው።ይህ ማለት በሌላ አገላለፅ መጭውም የፖለቲካ መድረክ የሚስተናገደው በአፈሙዝ ስልጣን ላይ የሚወጣ የሚደመጥበት ነው ማለት ነው።አሁንም ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አልታደልንም ማለት ነው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ የሚታዩት ኃይሎች

በአሁኑ ወቅት በእኔ እይታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ  3 ናቸው። እነርሱም-

/ የጠነከረ  የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች

እነዚህ ኢትዮጵያን በእራሳቸው የጎሳ ዘውግ እንደ አዲስ ሰባብረው ለመስራት እና እነርሱ በፈጠሯት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻመኖር የሚፈልጉ፣ለምሳሌ ህወሓት፣ኦብነግንኦነግ መጥቀስ ይቻላል።ኢትዮጵያ የእነርሱ የማቴርያል እና የጎሳቸውን ዝና ያገናል ብለው እስካሰቡ ድረስ የራሳቸውን መንግስት ለመፍጠር ቅድመ ሁኔታ የሚያመቻቹ ናቸው።

/ ለዘብተኛ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች 

 እነኝህ ኢትዮጵያን እንደ አዲስ መሰባበር እና ለመስራት ብዙም አዋጪ አይደለም የሚሉ -
- የጎሳ ፖለቲካ አለመስራቱን ሲመለከቱ ወይንም ደግሞ ከእድሜ ማርጀትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ከፅንፈኛው የጎሳ ፖለቲካ ወደ ለዘበው የጎሳ ፖለቲካ የሚደረገው የማረፍያ ቦታ ነው። ለምሳሌ አንድ አባባል እንጥቀስ
ኢትዮጵያዊ ለመሆን መደራደር እንፈልጋለን አቶ ሌንጮ ለታ በወቅቱ የኦነግ / ሊቀመንበር (ሳሌም መጽሔት፣ ነሐሴ 1984) እዚህ ላይ አቶ ሌንጮ ኢትዮጵያ ሲሉ ፍትህ የጎደለባት ሕግ የታጣባት ወይንም አንድ ብሔር የነገሰባት ከሚል ፅንሰ ሃሳብ ነው ለማለት ይቸግረኛል። እንደዚህ አስበው ቢሆን ኖሮ የጎደለውን ፍትህ በኃይልም ይሁን በምርጫ ማስተካከል አለብን ብለው በተናገሩ ነበር። እራስን ከትልቁ ስብስብ አውጥቶ መነጋገር በራሱ ስህተት ነው።አንድ ሰው የአንድ ቤተሰብ አባልነቱን ካመነ በኃላ ነው ስለ ቤተሰቡ የውስጥ ጉዳይ ልነጋገር የሚችለው።አይደለሁም ካለ ግን ነገሩ ሁሉ እዝያ ላይ ያከትማል።

ለምሳሌ ሀገር ቤት ያሉ እንደነ ኦፍዴን (ኦሮሞ ፌድራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) እና የመድረክ አባል ድርጅቶች ከለዘብተኛ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ይመደባሉ።የእዚህ ለዘብተኛ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ዋነኛ ስልት በሁለት ይከፈላል። አንደኛው እና ሁሉንም ሊያስማማ የሚገባው መሰረታዊ የጎሳው መብት እንዲከበር እንደ ኢትዮጵያዊነትም ተከብሮ መኖር የሚል ሲሆን፣ሁለተኛው ስልት እና የተወሰኑ አባላቱ ይዘው የሚንቀሳቀሱት አደገኛ አካሄድ ደግሞ የጠነከረ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ ለሆኑት መንገድ ጠራጊ መሆን ነው።ይህ አሳዛኝ እና አደገኛ አካሄድ ነው።አደገኛነቱ ለእራሱ፣ወከልኩት ላለው ጎሳ እና እንደ አገር ደግሞ ለኢትዮጵያም ነው።ፖለቲካ የማታለል ሥራ አይደለም።ቁርጠኘንት፣ለአላማ መታመን፣እና ግልፅ ግብ ይፈልጋል።በእዝህኛው ክፍል ላይ የሚታየው አካሄድ ግን በአገር ቤት ቢሮክራሲው ውስጥ ሁሉ ተሰግስጎ የጎጥ ፖለቲካ ማራመድም ነው እና ጉዳቱ ቀላል አይደለም። 

የአንድነት ኃይሎች

እነኝህ ኃይሎች የብሔር ጭቆና ነበርም የለምም የሚል አስተሳሰብ ያላቸው አንድነት የሚገኙበት ነው። ያለፈውን በደል በማሰብ ብቻ መጪው ማስተካከል አንችልም ለወደፊቱ ግን ኢትዮጵያን ሳንሰባብር  የእያንዱ ግለሰብ እንደ ግለሰብ እና ቡድን እንደ ቡድን መብቱ ይጠበቅ፣ለእዚህም እንስራ፣የሕግ የበላይነት ሲመጣ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ ያገኛሉ።ቤትህን ለመስራት ቤትህን ማፍረስ የለብህም የሚስተካከለውን በማስተካከል ወይንም በኅብረት እስከሆነ ድረስ እንደገና መስራትም የሚቻለው አሁንም በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ነው።የሚሉ ናቸው።ከእነዚህ ውስጥ የአገርህን አድን የጋራ ንቅናቄን መጥቀስ ይቻላል።

እነኝህ የአንድነት ኃይሎች አሁን ላለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥያቄ ምላሽ የሚሆኑ የሚሏቸው  መርሆዎች አሏቸው።በተለያዩ መድረኮች ከሚያንፀባርቁት ሃሳቦች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል። እነርሱም :

- በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ሁሉም የጎሳ ፖለቲካ ችግር ይፈታል

ያለፈውን ታሪክ ዛሬ ላይ ሆነን መልሰን ማስተካከል አንችልም።

- የአሁኑም ሆነ መጪው ትውልድ ስለአለፈው ነገር ሁሉ ተጠያቂ አይደለም።

እመንም አትመንም ሊባል አይችልም።የእራሱን አመለካከት መያዝ ይችላል።

ይልቁን አስፈላጊው ጉዳይ ለነገዋ ኢትዮጵያ ሳንሰባብራት እንዴት በአንድነት እንኑርባት የሚሉት ይጠቀሳሉ።

እነኝህ ኃይሎች ዋነኛ የወቅቱ አደጋ የኢህአዲግ/ወይኔ ስርዓት ነው ብለው ያምናሉ።እርሱ ሲወገድ የተጋረጠው አደጋ ይገፈፋል ብለው ይናገራሉ።

የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች መሰረታዊ ችግሮች


ባለፉት ዘመናት የተደረጉትን ታሪካዊ ሁኔታዎች ዛሬ 21ኛው /ዘመን ላይ ሆኖ ለመገምገም የሚፈልግ ነው።የዛሬ 600 አመት አፄ ዘርያቆብ ለምን እንዲህ አላሰቡም? እንዴት እንዲህ ይላሉ? እያለ በወቅቱ የነበረውን ስነ-ልቦና የማኅበረሰቡን ባህል፣እምነት እና ወግ ሳያጠና እንዲሁ ለዛሬ የኢትዮጵያ እሷነት መነሻ ሰበብ ሲፈልግ ከድሮ ታሪክ ጋር እያዛመደ መማሰን ሙያ ብሎ ይዞታል

የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ትልቁ ግቡ ስልጣን እንጂ ቆመንለታል ያሉት ጎሳ አይደለም።ቆመንለታል ያሉት ሕዝብ አጥንቱን ከስክሶ ለስልጣን እስክያበቃቸው ድረስ የአዞ እንባ ያነቡለታል።ስልጣን ላይ ሲወጡ ግን ስልጣናቸውን ማደላደል ብቻ ቀዳም ስራቸው ይሆናል።
 / መራራ ከአንድ ዓመት በፊት ላይ ኢሳት ብዙ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች መገንጠልን እንደ ዋና ግብ አርገው ይናገራሉ ይህ ለምን ይሆናል ብለው ያስባሉ? ተብለው ሲጠየቁ የመለሱት ምላሽ እዚህ ላይ አይነተኛ አስረጅ ይሆናል።

ዶ/ር መራራ ሲመልሱ: ''አይመስለኝም የምኒልክ ቤተመንግስት ከደረሱ ሃሳባቸውን ይቀይራሉ ብዬ አስባለሁ። ህወሃትም እኮ እንዲህ ይል ነበር ምንሊክ ቤተ መንግስት ሲገባ ሁሉን ትቶታል" ብለዋል።

ይህ በህዝቦች ደም መቀለድ ነው።መገንጠልን እና የጎጥ ፖለቲካን እንደማስፈራርያ ''አያጅቦ መጣብህ'' እያለ ሕፃን ልጅን እንደሚያስፈራራ ሰው ይጠቀሙበታል ማለት ነው።እዚህ ላይ ማስረጃው እራሱ ህወሃት ነው።ዛሬ ላይ ሕወሃትን የትግራይ ገበሬ እንዴት ነው የሚገልጠው? አብረውት መሬት ይተኙ የነበሩ የጎጣችን ጉዳይ ነው በረሃ ያወረደን ሲሉ የነበሩ ቤተ መንግስት ሲገቡ እና ሱፍ መልበስ ሲጀምሩ ምነው ዘወር ብለው ለማየት ጊዜ አጡ? የጎጥ ፖለቲከኞች እንዲህ ናቸው።''ከኢትዮጵያ ጋር መደራደር እንፈልጋለን'' ሲሉ የነበሩት አቶ ሌንጮ አሁን የት ናቸው?  በእሳቸው ፖለቲካ ተስቦ እስር ቤት የገባው ምስኪን ኢትዮጵያዊ ወንድሜስ የት ነው? የጎጥ ፖለቲካ ውጤቱም ግቡም ከእዚህ የዘለለ አይደለም።

የጎሳ ፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ ደግሞ ዛሬም ሆነ ነገ እንቅፋት ይሆኑኛል የሚለው ''ደንቃራ'' ከፊቱ ይታዩታል። እርሱም- በረጅም ዘመናት የተገነባው ያለፈው እና አሁን በሕዝቡ ልብ ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊነት ነው።ይህ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ባለፈ ማንነት፣ታሪክ፣ባህል እና እምነት ላይ የተመሰረተ ነው።ስለዚህ ዛሬ ሰበብ አስባብ ፈልጎ ያለፈ ማንነትን የሚንዱ ናቸው ያላቸውን የህዝብ ግጭቶችን፣በነበሩበት ጊዜ ጀግና ያስብሉ የነበሩ 21ኛው /ዘመን ግን ክፉ ተግባራትን እና ፈፅመው የሌሉ ታሪኮችን በመፍጠር የኢትዮጵያዊነት መሰረቶች እንዲናዱ ይሞክራል።

ለምሳሌ የብሔር ብሔረሰቦች ጉዳይ እና ፌድራሊዝም አስተዳደሮች በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ባልተፈጠሩበት ዘመን ለምን አልታወጁም ነበር? የሚመስል ''ውኃ ቀጠነ'' ንግግር ኢትዮጵያዊነትን ይሳደባል፣ያናንቃል።ይልቁን ፌድራልዝም በአለም ሳይታወቅ እነ አባ ጅፋር የራሳቸውን ግዛት በራሳቸው ያስተዳድሩ እንደነበር ግን በጋራ ከማዕከላዊ መንግስት ጋር በሚያገናኛቸው ጉዳይ ላይ አብረው ይሰሩ እንደነበር አያስተውልም።በዚህ ክፍል ውስጥ የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስትን ጨምሮ በፅንፈኛ የእስልምና እምነት የፖለቲካ አላማቸውን ለማሳካት እስከሚፈልጉት ኃይሎች ድረስ የባለፈውን ታሪክ በዛሬ መነፀር እያዩ ህዝብን ማደናገር እና የዛሬውን ትውልድ በማያውቀው ጉዳይ አበሳውን ሲያሳዩት መመልከት የተለመደ ነው።

አሁን ባለንበት ዘመን በእዚህ አስተሳሰብ ሺዎች ተገድለዋል፣ሌሎች አያሌ ሺዎች ከመኖርያቸው ተፈናቅለዋል።ከእዚህ ሲዘል ደግሞ ማስረጃ ለሌለው ተረት ሁሉ ሃውልት ይሰራ ባይ ነው። የእዚህ አስተሳሰብ አራማጆች ዋና ግባቸው ''እኛ ስልጣን ላይ ከሌለን እና የምንፈልገውን ካልፈፅምን ጭር አይልም'' ባዮች ናቸው።ለእዚህ እኩይ ተግባር የሚተባበራቸው ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይል ጋር ለመተባበር ዝግጁ ናቸው።ኢትዮጵያዊነት፣አንድነት እና ህብረት ሲጠነክር ይደነግጣሉ።ምክንያት የእነርሱ አስተሳሰብ በጠንካራ ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ፊት ሞገስ እንደሌለው እና እነርሱንም ወደ ስልጣን ኮርቻ ላይ እንደማያፈናጥጣቸው ይረዳሉና።

አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት  ፖለቲካዊ ችግር  መፍትሄዎቹ 


1/ የባለፈው በጎውን ይዘን፣ ክፉውን ወቅሰን እና ስላለፈው በሌለበት ጉዳይ ያሁኑን ትውልድ ውቀስ አቁመን ለወደፊቱ ልብ ሰብ መጀመር  

ከሁሉ በፊት መረዳት የሚገባን ጉዳይ አለ።ኢትዮጵያ በአንድ ምሽት በቤተ-ሙከራ ውስጥ የተሰራች ሀገር አይደለችም።የብዙ ዘመናት የህዝቦቿ አብሮ የመኖር፣የመተሳሰብ፣የመሰደድ፣የጦርነት፣የሰላም ሁሉ ውጤት ነች።እኛ የተለያየ ጎሳ የኢትዮጵያ ልጆች ባለፈው ታሪካችን ብዙ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች አሉ።ብዙ የዛሬ ማንነታችን ላይ አሻራ ያላቸው ማንም በቀላሉ እንዲነቅላቸው የማይፈቀዱለት የጋራ ታሪክ አለን።በአንፃሩ ደግሞ የሚያሳዝኑ ታሪኮች ባለቤትም ነን።ዛሬ የሚያስፈልገን ያለፈው አንድ የሚያደርጉንን አጉልተን ባለፈው ለተሰሩት ስህተቶችን በትምህርትነት ወስዴግን ግን አሁን ያለውን ትውልድ ባልነበረበት ጉዳይ መውቀሱን ተተን  ወደፊት ስህተቶች እንዳይደገሙ  አርመን መኖር ብቸኛ አማራጫችን ነው።ከእዚህ በዘለለ ባለፈ አሳዛኝ ታሪክ ሊሽር የሚችለው በዛሬው ትልውድ በጎ የታሪክ ተግባር ነው ብለው ማመን መሰረታዊው ገዢ አስተሳሰብ መሆን አለበት

አሁን ሕዝብም የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያላቸውን ግልፅ አስተያየት እና ይህ እይታቸው የነገውን የሀገራችንን መፃኢ ዕድል ማሳያ እንደሆነ አመላካች ነው።ኢትዮጵያ ነገ እንዴት እንድትሆን እንደሚፈልጉ ሁሉ የባለፈው ዕይታቸውም በግልፅ መቀመጥ ያለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።የጎጥ ፖለቲካ ከሃያ አራት አመታት በላይ ዕድል ተሰጥቶታል በቃህ መባል አለበት።ይህ ማለት ማንም ጎሳ በፈለገው  ቋንቋ የመናገር፣በፈለገው መንገድ ባህሉን ማሳደግ፣የእራሱ የሆነ በአገሪቱ ሕግ የሚመራ የእራሱ የመገናኛ ብዙሃን የመክፈት (አሁን እድሉን ያላገኙትን እንደ ትናንሽ ቁጥር ያላቸውን ጨምሮ)፣ በሂደት ደግሞ አገሪቱ ሁለት እና ሶስት ብሔራዊ  ቋንቋ እንዲኖራት ማድረግ ወዘተ በዲሞክራሲ መንገድ የተመረጠ መንግስት ምክር ቤት የሚወስነው ሕዝብ በነፃ የመገናኛ ብዙሃን የሚወያይበት እና በፍቅር የምስማማበት ወይንም ለብዙሃኑ ፍላጎት የሚገዛበት ነው።ይህ ዝርዝር ጉዳይ ነው።አሁን ላይ ሆነን ብዙ ማለት የለብኝ ይሆናል።ግን የጎሳ ፖለቲካ እነኝህን መብት የሚያስከብር የሚመስላቸው የዋሃን ስላሉ እነኝህ መብቶች በኢትዮጵያዊ ጥላ ውስጥ የሚፈቱ እንጂ በጎጥ ፖለቲካ የሚፈቱ አይደሉም ለማለት ነው። 

2/ የጎሰኛነት ስሜት እንደ ኩፍኝ በሽታ ነው ይለቃል።
የሃገራዊ ስሜት ን የተዳፈነ ፍም ነው።
ገራዊ ስሜትን ማዳበር ያስፈልጋል

በአንድ የተወሰነ ርዕዮተ አለም ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አስተሳሰብም ሆነ በመንደርተኝነት ላይ የተመሰረተ ሥራ የአንድ ሰሞን ግርግርታ ናቸው።የኩፍኝ በሽታ በትክክል በምሳሌነት ይመስላቸዋል።ኩፍኝ የአንድ ሰሞን በሽታ ነች።ካልታከመች አደገኛ ነች።ከታከመች ግን የትም አትደርስም።በዘመነ ደርግ ስለሶሻሊዝም ስህተት ለአንድ የቀበሌ ጥበቃ መናገር እስከሞት የሚያደርስ ፍርድ ሊያሰጥ ይችላል።በወቅቱ ገዳዩ ስለመግደሉ ''ትክክለኛነት'' እርግጠኛ ነበር።ከአመታት በኃላ 'ኩፍኙ' አልፉ ሲመለከተው ግን ስህተቱ ይታየዋል።የጎጥ ስሜት እና መሰረቱ እርሱን ያደረገው የፖለቲካ ዘውግም ይሄው ነው።ዛሬእሞትለታለሁያለውየሰፈርስሜት ነገ በኢትዮጵያዊነት እስኪማረክ ብዙ ይባልለታል።ያኩራራል።ያስደስታል።በሂደት ግን መማርያ ይሆናል።እንደ አቶ ሌንጮ ቀስ ይላል ወይንም ድምፁን አጥፍቶ ይቀራል።
የሃገራዊ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ግን ጥብቅ የሆነ ማኅበራዊ፣ስሜታዊ እና ዘመናዊ እሴቶችን ይዞ ከውስጥ እየፈነቀለ ጥላቻ ላይ በረዶ ይከልስበታል።እናም  ዘለቄታዊውን የጋራ ቤታችንን ኢትዮጵያን እንጂ ጎሳዊ ስሜት ይዞ መሄድ አያዋጣም።ስልጣን ከሆነም በኢትዮጵያዊ እውነተኛ ስሜት መነጋገር አንድ ነገር ነው።በወጡበት ጎጥ ስም እየማሉ ወጣቶች እና ሕፃናት ላይ እንዲሁም የሌላ ጎሳን በጥላቻ ዘይት እየቀቡ ሕዝብ ማፋጀት ግን ለጊዜው የተሳካ ቢመስል ውሎ አድሮ የህሊና ቁስል ነው።

3/ጎሰኘነት የጎሳን ስሜት ለመኮርኮር ይጥራል።ሃገራዊ ስሜት ግን 
ለምን ይኮረኩራል።ሕዝብ ለሀገራዊ ጉዳይ ጋ እንዲሰጥ መስራት።

በጎሳ ላይ የተመሰረተ ሁል ጊዜ እጁም፣እግሩም መላ ሰውነቱ የጎሳውን ውሎ፣ብሶት፣ትልቅነት ወዘተ አግንኖ ለማቅረብ ይጥራል።ስራው ሁሉ የጎሳውን ስሜት ለመኮርኮር ነው።ሃገራዊ ስሜትን የሚያንፀባርቅ ግን አቅርቦቱ ሁሉ ሃገሩን አልፎም አካባቢውን ከፍ ሲል ደግሞ ዓለምን ይኮረኩራል።የሚነሱት ጉዳዮች የሌሎችን ሃገራት ጥቅም እና ጉዳት ስለሚመለከት ትኩረት ይስባል።እርግጥ ነው የጎሳ ጥቅም የሌሎችን የሚነካባቸው ብዙ መንገዶች ይኖራሉ።በሀገራት ደረጃ ስናየው ግን ብሔራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረውን ቅድምያ የሚሰጡባቸው ብዙ መንገዶች አሉ።የጎሳ ፖለቲካ  ከማበጣበጥ እና ከመከፋፈል ባለፈ የሚያመጣው  ፋይዳ የለም። ስለሆነም ሃገራዊ ጉዳዮችን ማጉላት የጎሳ ስሜቶችን ማኮሰስ የሚችል ትውልድ መነሳት አለበት።ይህ ማለት ከአንድ ጎሳ  በመወለዳቸው ብቻ በደረሰባቸው በደል ድምፃቸውን ያሰሙትን ሁሉ መኮነን ማለት አይደለም።ከተበደሉት ጋር አብሮ መጮህ ነገር ግን የተነገረውን በደል አስታከው በጎሳው ስም የግል የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት የሚጥሩትን መከላከል አስፈላጊ ነው።



4 / በረጅም ጊዜ የጎሳ ለቲካ እየከሰመ እንዲሄድ የሚያደርጉ 



     ምክንያቶችን ማዳበር እነርሱም: -    

1/ የከተሞች መስፋፋት እያደገ መሄዱ፣
2/ የኢንዱስትሪ መስፋፋት የሚፈጥረው ህብረት እና አንድነት ስለሚኖር፣
3/ የሃይማኖታዊ እና ማኅበረሰባዊ ግንኙነት መጠናከር እያደገ መሄድ እና
4/  የጎሳ ፖለቲካ የሚያመጣው እልቂት እና ግጭት ሕዝብ እየተማረ ስለሚመጣ የሚሉት ይጠቀሳሉ።

በመጨረሻም ኢንጅነር ይልቃል ስለ ጎሳ ፖለቲካ (ጥያቄው የብሔር ፖለቲካን ነው) ሲጠየቁ የተናገሩትን ልጥቀስ-

’'የግለሰቦች መብት ከተከበረ የቡድን መብት ይከበራል።ባህሌ፣ቋንቋዬ፣እምነቴ  እኔ ውስጥ አለ። በቋንቋዬ መናገር የእኔ መብት ነው፣የሙያ ማኅበር መመስረት የእኔ መብት ነው።የእኔ መብት ያልሆነ የቡድን መብት አይኖርም።የግለሰብ መብት ከተከበረ የማይከበር የቡድን መብት የለም።የወለጋን ሕዝብ ለማስተዳደር ከጎጃም ማምጣት የለብንም።የፌድራል አስተዳደሮች የራሳቸውን ቋንቋ መምረጥ እንዳለባቸው የታወቀ ነው።ዛሬ የአንድ ሰፈር ሰው የሌላ ሰፈር ሰው የሚወክልበት ሁኔታ የለም።ይህንን ዘመን አልፈነዋል''

//////////////////////////------///////////////////------/////////////////////////------/////////////////////////------/////////////////
ይህ ፅሁፍ  በኦስሎ፣ኖርዌይ የመወያያ መድረክ ላይ ከሁለት  ዓመታት በፊት በጸሐፊው  ቀርቦ ነበር።በእዚሁ ጉዳያችን ገፅ እና ሌሎች ድረ ገፆች ላይም ከጉዳያችን ገፅ ላይ ከወጣ በኃላ  ተወስዶ ከሁለት ዓመት በፊት ወጥቶ ነበር።


 ጌታቸው በቀለ 
ኦስሎ፣ኖርዌይ 
getachwb221@gmail.com 


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...