ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, October 22, 2017

በኦሮምያ ቡኖ በደሌ የዓማራ እና ትግራይ ተወላጆች መታረዳቸው ዛሬ ተሰምቷል። ከእዚህ ሁሉ ጀርባ 'አስረሰሽ ምች' ባዮች እነማን ናቸው?


  • ዜናዎቹ  (ፎክስ ኒውስ፣ዋሽንግተን ፖስት እና አሶሼትድ ፕሬስ ምን አሉ?)
  • በግጭቶቹ  ሳቢያ 'አስረሰሽ ምች' ባዮች እና 
  • መፍትሄዎቹ 
ጉዳያችን / Gudayachn
ጥቅምት 13/ 2010 ዓም  ( ኦክቶበር  22/ 2017)

የጉዳዩ መነሻ 

በኢትዮጵያ ላለፉት 26 ዓመታት የተደገሰው እና የተፈተለው የጎሳ ፖለቲካ ወደ ከረፋ ደረጃ እየደረሰ ነው።ከእነ ክርፋቱ አብረውት ታቅፈው እሹሩሩ የሚሉት ከባህር ማዶም ሆነ ከአራት ኪሎ እንዲሁም ከአዳማ ከተሞች ንፁሃን ላይ እልቂት እያወጁ ነው።በዛሬው እለት ብቻ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ ዐማራ፣ትግራይ እንዲሁም መጤ  ነህ በሚል ብቻ በአሰቃቂ  አገዳደል ተገድሏል።የቀረው በሽሽት ወደ እምነት ቦታዎች እና ጫካ ሸሽቷል።

1ኛ/ ዜናዎቹ  (ፎክስ ኒውስ፣ዋሽንግተን ፖስት፣ ኢኤንኤን እና አሶሼትድ ፕሬስ ምን አሉ?)

የዛሬውን ዜና  ፎክስ ኒውስ ዜና እንዲህ ይነበባል  ''በኢትዮጵያ በቀጠለው ፀረ መንግስት ተቃውሞ በኦሮምያ ክልል 11 ሰው ተገደለ ሁኔታው ወደ ብሔር ግጭት እያመራ ነው'' ሲለው ዋሽንግተን ፖስት ትናንት ምሽት ላይ " የአሜሪካ ወዳጅ ሀገር ኢትዮያ የጎሳ ፖለቲካ ያሰጋታል።ድብቁ የእሩቅ ገጠራማ ቦታዎች ጦርነት በመቶዎች የሚቆጠሩ ገድሎ መቶ ሺዎችን አሰድዷል'' በማለት ገልጧል።
አሶሼትድ ፕሬስም በዛሬው ዘገባው በበኩሉ 11 ሰዎች በኦሮምያ ክልል መገደላቸውን ከገለጠ በኃላ የኦሮምያ ክልል መንግስት ቃል አቀባይ በኦሮምያ ቡኖ በደሌ 8 የኦሮሞ ተወላጆች እና 3 የአማራ ተወላጆች መገደላቸውን የኦሮምያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ለጥፈው መነበቡን ይገልጣል። 

አሶሼትድ ፕሬስ በመቀጠል እንዲህ ይላል '' 100 ሚልዮን ሕዝብ ያለባት ሀገር ላይ የጎሳ ፖለቲካ መሰረት ያደረገ ፖለቲካ መንግስት በማራመዱ በሶሻል ሚድያ ሳይቀር መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ እየተወቀሰ ነው'' (''Reports of the latest killings in the Oromia region came amid widespread social media accusations against the government for running an ethnic- based administration on this east African nation of more than 100 million people.'' Associated Press)
አፍቃሪ ህወሓት እንደሆነ የሚታማው ኢኤንኤን የስፖርት ፕሮግራም አቁሞ ዛሬ በሰበር ዜናው ባልተለመደ መልኩ  ''መጤዎች በሚል ዓማራ ናችሁ እየተባልን እየተገደልን ነው ፣ ሕዝብ በእየጫካ እየተበተነ ነው አንገታቸው እየተቆረጠ ተጥሏል'' የሚል መልዕክት በቴሌቭዥን ሰበር ዜናነት አሰምቷል።ለመሆኑ ከእዚህ ሁሉ ጀርባ የፖለቲካ ትርፈኞች እንደሆኑ እያሰቡ 'አስረሽ ምቺው' የሚሉት እነማን ናቸው?
  
2ኛ/ በግጭቶቹ  ሳቢያ 'አስረሰሽ ምች' ባዮች 
       
'አስረሽ ምቺው' ባይ ቁጥር አንድ 

በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለንበት ሰዓት ሁለት ኃይሎች በኢትዮጵያውያን ህብረት እና ፍቅር ስጋት ላይ ወድቀዋል።ይህ በግልጥ መታወቅ ያለበት ነው።ይህንን ጉዳይ ተደባብቀን እና አለባብሰን ማለፍ መፍትሄ አይሆንም።እነኝህ በኢትዮጵያውያን ህብረት ስጋት ያደረባቸው ኃይሎች የመጀመርያዎቹ በውጭ በፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔር አቀንቃኝነት የሚታወቁት ናቸው።እነኝህ ክፍሎች ሰሞኑን የተነሳው በኦሮምያ የተነሳው ህወሓት ከስልጣን ይውረድ ጥያቄ እኛ ያልወጠወጥነው ነው በሚል ስሜት እኛ ይህንን አመፅ  አናውቀውም አላስተባበርንም በሚል ከእዚህ በፊት የቀናት የስራ ማቆም አድማ ይጠሩ የነበሩ የዛሬው የጠነከረ የህዝብ ህብረት ግን እንዳስከፋቸው በግልጥ ሳያፍሩ ከባህር ማዶ ሆነው ተናግረዋል። ሌላው ቀርቶ ከኦሮምያ ክልል ወደ ጣና የዘመቱ ወዶ ዘማቾችን ጉዳይ የምንተፍረት ያህል '' ወዶ ዘማቾቹ በአካባቢ ጥበቃ ላይ  ለመስራት ነው ሌላ መልዕክት አይደለም '' የሚሉ ቃላት በጃዋር  ፌስ ቡክ ገፅ ላይ እስከመፃፍ ተደርሷል።

በጎሳ በቆሰለች ሀገር ውስጥ ከኦሮምኛ ተናጋሪ ወጣቶች የዐማራ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ጣና ድረስ መሄዳቸው በምን መልኩ ነው የአካባቢ ጥበቃ እንጂ የፖለቲካ አንድነት አይደለም የሚያስብለው? ይህ ለአንድ በፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ላለፈ ቀርቶ ለማንም ተራ ሰው በጎሳ ግጭት ለተወጠረች ሀገር ፖለቲካዊ መልክቱ እና አንድነቱ መገለጫ እንደሆነ ግልጥ ነው። የሚንሶታው ሰው ግን የአካባቢ ጥበቃ ጋር አያያዘው። በእርግጥ ከእዛ በማስከተል ''ፍቅር በፍቅር ሆነ'' የሚሉ መልክቶች ከገፁ ላይ አንብበናል። 

የህዝብ አንድነት የሚፈጠርበት ቀዳዳ ሁሉ ለማስፋት ለምናፍቅ ሕዝብ ግን አብሮ የኖረ ሕዝብ ያገናኘው የአካባቢ እንክብካቤ ነው ብሎ መፃፍ  በጦር የመውጋት ያህል ያማል።ይህ ማለት የህዝብ አንድነት የሚያሰጋቸው እና እነርሱ አመፁን ለመምራትም ዕድል የማይሰጣቸው ብቻ ሳይሆን በቅራኔዎች እና ያለፉ ታሪኮችን በማውራት በሚፈጠር ግጭት የፖለቲካ ኃይል የማሰባሰብ ዕድል እንዳላቸው የሚያስቡ የዛሬው እልቂት ሲፈፀም ቁጥር አንድ ተደሳቾች ናቸው። እነርሱ ማን ናቸው? ለሚለው ጥያቄ በውጭ ሀገር በፅንፈኝነት በኦሮሞ ስም የሚንቀሳቀሱ ብቻ ሳይሆኑ እራሳቸውን አዳማ እና ናዝሬት ላይ ተቀምጠው በንፁሃን ደም የፖለቲካ ቁማር የሚጫወቱ ናቸው።

'አስረሽ ምችው' ባይ ቁጥር ሁለት 

በቁጥር ሁለት የእዚህ አይነቱ ግጭት  በማራገብ ብቻ ሳይሆን ከ26 ዓመት በፊት የጎሳ ፖለቲካው ውጤት ምን እንደሚያመጣ የሚያውቀው እና ላለፉት 26 ዓመታት በተለይ በዐማራነት እየተመረጠ ሕዝብ ሲገደል፣ መሬታቸው እየተነጠቀ ሲባረሩ በፓርላማ የተጠየቁት አቶ መለስ ጨምሮ ሕግ እና ስርዓት ከማስከበር ይልቅ  ከጉርዳ ፈርዳ ሕዝብ ተሰደደ፣ ተገደለ ለምን? ተብሎ ሲጠየቁ አቶ መለስ ለፓርላማ በሰጡት መልስ '' ጉርዳ ፈርዳ ምስራቅ ጎጃም ስለመሰለ ነው፣ዛፍ እየቆረጡ ስላስቸገሩ ነው'' የሚል እንደ ነበር የምናስታውሰው ነው። ህወሓት በመንግሥትነት ተቀምጦ አባላቱ የመከላከያ እና ደህንነት ቁልፍ ቦታ ይዘው ሕዝብ በጎሳ እንዲያልቅ ሲደረግ ምንም የሕግ ማስከበር ሥራ አለመስራታቸው ብቻ ወንጀለኛ ያደርጋቸዋል።
  
 ከላይ ቁጥር አንድ እና ሁለት ላይ የተጠቀሱት አስረሽ ምችው ባዮች ተመጋጋቢዎች ናቸው።ሁለቱም የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ናቸው። ሁለቱም ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በማንኛውም መንገድ ለጥቅማቸው ይደራደራሉ። ሁለቱም ኢትዮጵያዊ እሴቶች መጥፋት ላይ ይስማማሉ።ሁለቱም ለስልጣን ካልበቁ ኢትዮጵያ ''ብትንትኗ''  ይውጣ ባዮች ናቸው። ሁለቱም በሙስና በቀጥታም  በተዘዋዋሪ መንገድ ኢትዮጵያን  መዝብረዋል።ስለሆነም እርስ በርስ ይመጋገባሉ።

መፍትሄዎቹ  

ከመፍትሄው ውስጥ ቀዳሚው ነጥብ ይህ የጎሳ ግጭት በሁለቱ ተመጋጋቢ ክፍሎች  እንዳይዛመት ማድረግ ነው።በመቀጠል በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በጎሳ መለያየት ስልጣኑን ለማቆየት የሚሞክረውን ህወሓትም ሆነ ወደ ስልጣን መወጣጫው መንገድ በጎሳ ግጭት እና ህዝብን ከህዝብ በመለየት ነው ብሎ የሚያምነው መንተላጠያውንም ኦህዴድ ስር አድርጎ የመሸገው ክፍልን አምርሮ መቃወም እና እስከመጨረሻ ድረስ መታገል የግድ መሆኑን መረዳት ይገባል። 

እነኝህ ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ክፍሎችን ታግሎ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ጤናማ መስመር ለማምጣት የሚፈልጉ ኃይሎች ደግሞ ሁለቱም ከላይ የተጠቀሱት ክፍሎች ውስጥም መኖራቸውን መረዳት እና እነርሱንም  አበረታቶ ወደ ኢትዮጵያ የፍቅር ማዕድ ማምጣት እና በሁለቱ ክፍሎች ውስጥ ያለውን የጥፋት ደዌ እንዲታገሉ ማብቃት ሌላው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ በህወሓት ውስጥ የሚገኙ የጦር ሰራዊቱ አባላት ህወሓት የሚሰራውን ሸፍጥ የሚያውቁ ለለውጥ እንዲነሱ እና የህዝብ አደራ እንዳለባቸው ማስታወስ እና ለለውጥ ማገዝ እንዲሁም በኦህዴድ ውስጥ የተሰገሰጉ እና ከባህር ማዶ ሆነው ፀረ ኢትዮጵያዊ ዘመቻ ላይ የተጠመዱትን መሰረታዊ ባህሪ እና ማንነት የሚያውቁ ነገር ግን በኦህዴድም ውስጥ ሆነ በባህር ማዶው ፅንፈኛ ፀረ ኢትዮጵያዊነት ኃይል ዙርያ ያሉትን አሁንም ከማያዋጣ ብቻ ሳይሆን የባዕዳን እንዲሁም አንዳንድ ፅንፈኛ የመካከለኛ ምስራቅ ሀገሮች ተንኮል ያለበት መሆኑን እንዲገነዘቡ እና ለጋራ ሀገር እኩል መብት እንዲቆሙ በፍቅር መቀበል ያስፈልጋል።

ባጠቃላይ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው የፖለቲካ መልክ ውስብስብ እየሆነ መምጣቱ ቀድሞውንም የተገመተ ነው።አሁን እየሆነ ያለውም እንዳይሆን ስደቀምበት ከነበረው የተለየ አይደለም።ይህ ማለት ግን ቀላል ጉዳይ ነው ማለት አይደለም። የብዙ ስም ያሉ ዝምተኞች ወደ መሃል እየመጡ ሕዝብ ሊያስተምሩ፣ልያነቁ እና ሊሰሩ የሚገባቸው ቁልፍ የህብረት እና የፍቅር ተግባራት ላይ የበለጠ መትጋት ያስፈልጋል።ምንም መገራገጭ ቢገጥም በሕዝብ ደም የፖለቲካ ቁማር የሚጫወቱት ለፍርድ መቅረባቸው አይቀርም። ሕዝብ እነማን ምን እየሰሩ እንዴት እንዳጋደሉትም ፈልፍሎ ማወቁ አይቀርም። ስለሆነም ለማይቀር ፍርድ በሕዝብ ደም ከመታጠብ እራስን ማቀብ እና ለጋራ ህልውና መስራቱ የወቅቱ ጥያቄ ነው።በተለይ በከተሞች የሚኖረው ሕዝብ የበለጠ እልቂት እንዳይፈጠር ቀድሞ በእነማን ላይ መነሳት እንዳለበት ማወቅ እና መነሳት አለበት።በከተሞች የሚደረጉ የትግል መርሆዎቹ ለገጠሩ እንደ ማገር የሚሆኑ የጋራ ሃሳቦች ስለምፈልቁ ገጠሩን ማስደመሙ እና የተንኮለኞች ሰለባ እንዳይሆን ብርታት ይሆነዋል። 


ጉዳያችን GUDAYACHN 
www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...