ህንፃ ቤተ ክርስቲያኑ በቀይ ቀለም የሚታየውን ቦታ ሁሉ ይሸፍናል።
ጉዳዩ ምንድነው?
የኢትዮጵያውያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ በኖርዌይ በእዚህ ሳምንት ለየት ያለ በጎ ጉዳይ ተከስቷል። ይሄውም በኦስሎ ከተማ ውስጥ ከከተማው እምብርት በቅርብ እርቀት ላይ የሚገኝ ካቴድራል ለሽያጭ ቀርቧል።ማስታወቂያው የወጣው ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ነበር።ቀደም ብሎ በኦስሎ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ገብርኤል፣አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ መልክ የቤተ ክርስቲያን ህንፃ ኮሚቴ አሁን ቤተ ክርስቲያን በኪራይ ከምትገለገልበት ህንፃ የእራሷ ህንፃ እንዲኖራት እየሰራ ባለበት ጊዜ ነው ያለፈው ሳምንት በኖርዌይ የቅርብ ታሪክ ያልተሰማ የቤተ ክርስቲያን ሽያጭ ዜና የተሰማው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኦስሎ ላይ ይህንን ህንፃ ገዛች ማለት ምን ማለት ነው?
አንዳንዶች ኢትዮጵያውያን በውጭ ሃገራት አብያተ ክርስትያናትን መግዛታቸው ለዘላለም ውጭ የሚቀሩ አድርገው ስለሚቆጥሩ የሚመስላቸው ስለሆነ ነው ብለው ያስባሉ።ጉዳዩ ግን ይህ ማለት አይደለም።በየትኛውም የዓለም ጫፍ የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ግዥ ነገ ቤተ ክርስቲያናችን በአንድነት እና በህብረት የምትኖርበት ጊዜ በመላው ዓለም ባሏት ንብረቶቿ ከክርስቶስ ወንጌል በተጨማሪ እንደ ሀገር ያለን ተፅኖ ያድጋል። ይህ በኦስሎ ለሽያጭ የቀረበው ህንፃ በከተማው እምብርት ካለው ቅርበት አንፃር ለመጪው ትውልድም ሆነ አሁን ያለው ትውልድ ከሃይማኖት የራቀውን የሰሜን አውሮፓ ህዝብን በሃይማኖትም ሆነ በባህላችን በቀላሉ ለመድረስ የሚያስችለን፣ የኢትዮጵያን ስም ከፍ የሚያደርግ እና እዚህ ላይ ለመጥቀስ ጊዜ እና ቦታ የማይበቃቸው በርካታ ጥቅሞች አሉት።
ከ 700 ካሬ በላይ ስፋት ያለው ቤተ ክርስቲያን የምድር ክፍሎች እና ደረጃውን የጠበቀ አዳራሽ አለው
አሁን የጨረታው ሂደት ምን ላይ ይገኛል?
የቤተክርስትያኒቱ የህንፃ ኮሚቴ የጨረታውን ማስታወቂያ ከሰማ ጀምሮ በርካታ ስራዎች ለመስራት ሞክሯል። በእጁ ያለውን የተቀማጭ ገንዘብ ጋር በተጨማሪ ከባንክ ብድር ለማግኘት፣ ከምእመናን ጋር ተከታታይ ስብስብሰባ ባለፈው እሁድ እና ዛሬ ምሽት በቤተ ክርስቲያን ከማካሄዱ በላይ በመጪው እሁድም ተመሳሳይ ምክክር ያደርጋል።
ጨረታው መቼ ነው?
ጨረታው የሚደረገው በመጪው ሳምንት ውስጥ ነው።
አሁን ያለው ችግር ምንድነው?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ህንፃውን እንዳትገዛ እንቅፋት የሆነባት ከጨረታው መነሻ ገንዘብ ማለትም 16 ሚልዮን የኖርዌይ ገንዘብ (2.5 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር ገደማ ) ውስጥ በብድር እና ቤተ ክርስቲያን ካላት ተቀማጭ ተደምሮ በጨረታው በበቂ መንገድ ተወዳድሮ የቤተ ክርስቲያን ንብረት ለማድረግ ጨረታው ከሚጠይቀው ገንዘብ 45% ገደማ የሚሆነውን ለማሟላት በኖርዌይም ሆነ በአውሮፓ እና አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ኖርዌይ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የእራሷ ህንፃ መኖር ምን ማለት እንደሆነ ተገንዝበው እግዚአብሔር ባመለከታቸው መልክ አስፈላጊውን ርብርብ እንዲያደርጉ ተማፅኖ ቀርቧል።
ይህ ጉዳይ የማይመለከተው እና የሚመለከተው አለ?
ይህ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በየትኛውም እምነት ያለ ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ቅርስ ለመጪው ትውልድ መኖር አለበት ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን በሃይማኖት ያልተለያዩ በአስተዳደር ጉዳይ ብቻ በተለያዩ አባቶች ስር ብትሆንም ቤተ ክርስቲያን አንድ ስትሆን የሁላችን ሀብት ነው ብሎ አርቆ የማሰብ አዕምሮ የተሰጠው እና ንብረቱ መቸም ቢሆን መቼ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ንብረት መሆኑን የሚያምን አርቆ አሳቢ ሁሉ ቅሌን ጨርቄን ሳይል ሊረባረብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ስለሆነም ትልቅ የኢትዮጵያዊነት ህብረት በመላው ኖርዌይ፣አውሮፓ እና መላው ዓለም የምንኖር ኢትዮጵያውያን የምናሳይበት አንዱ መገለጫችን ነው። በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ መድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የአይሁድ ምኩራብ ሆኖ ያገለገለ ነበር።ቤተ ክርስቲያኑ ለሽያጭ ሲቀርብ ጥንታዊ የሆነ ቤተ ክርስቲያን ካልገዛው በዘመናዊ መልኩ ነን የሚሉ ቤተ ክርስቲያኖች እንዳይገዙት ግብፆችም ሆኑ አይሁዶቹ ኢትዮጵያ እንድትገዛው ድጋፍ አድርገዋል። ይህም ለሰው ልጅ ቅርስ ሁሉ ከመጨነቅ የመነጨ ነበር።ቤተ ክርስቲያኑ በ1990ዎቹ መጀመርያ አጋማሽ እንደተገዛ ሲኤንኤን ሳይቀር ´´ዎርልድ ሪፖርት´´በተሰኘ ፕሮግራሙ ላይ ልዩ ዘገባ ሰርቶ እንደነበር የእዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ ያስታውሳል። አሁንም ይህ በአውሮፓ የሉተር ማዕከል በሆነች ሀገር ዋና ከተማ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የእራሷ ህንፃ መያዝ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከገባን ምንም አይነት ልዩነት ኢትዮጵያውያን ለቤተ ክርስቲያኑ እንዳይረባረቡ ሊያግዳቸው አይችልም።
የቤተ ክርስቲያኑ አንድኛው ክንፍ የሚገኘው መስኮት
በኖርዌይ፣አውሮፓ፣አሜሪካ እና በመላው ዓለም ያሉ ምእመናን ባሉት ጥቂት ቀናት (ከመጪው ሳምንት መጨረሻ በፊት ምን ያድርጉ?
ጉዳዩን በትክክል ከተገነዘብነው ይህ ጉዳይ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞችን ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሩ እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑት ሁሉ ሊረባረቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ ተቋም (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን) ኦስሎ እምብርት ላይ
ይህንን የሚያህል ህንፃ ገዛች ማለት ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የልጆቻችን ሀብት እና መኩርያ ነው።ከእዚህ በተጨማሪ ቋሚ
ኤግዚብሽን በመክፈት የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻ ማስተዋወቂያ አንድ ሁነኛ ማዕከላችን መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ስለሆነም
ምእመናን የጉዳዩን ክብደት በሚገባ ከተገነዘቡ በኃላ በሚከተሉት መንገዶች በፍጥነት ማገዝ ይችላሉ።
1/ የህንፃ ኮሚቴውን በብድር ሂደቶች ወይንም ለእዚህ ተግባር የሚያግዙ ድርጅቶች ካሉ በቀጥታ በባለቤትነት እንዲያግዙ በመርዳት፣መረጃ በመስጠት፣ወዘተ
2/ እግዚአብሔር ፀጋውን የሰጣቸው እነርሱ እና እግዚአብሔር በሚያውቀው እራሱ ከሰጣቸው ላይ በቀጥታ ገንዘብ በመለገስ እና
3/ ከእዚህ ሁሉ በፊት ደግሞ እግዚአብሔር ፈቃዱ እንዲሆን ጊዜ እና ሰዓት ሰጥተው በመፀለይ ናቸው።
ከእዚህ በታች የቤተ ክርስቲያኒቱ ህንፃ ኮሚቴ የባንክ ሂሳብ ቁጥር እና ፔይ ፓል ማያያዣ ከፍተው መመልከት ይችላሉ። በሊንኩ ላይ ከባንክ ሂሳብ ቁጥር በተጨማሪ የኮሚቴ አባላት ሙሉ ስም እና አድራሻ ስለተያያዘ ማናቸውንም ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ይችላሉ።ስልኮቹ በሙሉ የሞባይል ስልኮች ሲሆኑ የኖርዌይ መግቢያ ኮድ ከፊት 0047 ማስገባት አይዘንጉ። የህንፃ ኮሚቴ በተመለከተ አስፈላጊ መረጃ ለማግኘት ይህንን ሊንክ ይጫኑ : -
ይህንን ሊንክ ይጫኑ - http://www.eotcnor.no/የሕንፃ-ኮሚቴ/ያግኙን/
የአቡነ ሕርያቆስ መልዕክት
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment