መነሻ
በ20ኛው ክ/ዘመን ውስጥ አለማችንንም እንዲሁም ኢትዮጵያን ያመሱት ሁለቱ ዋነኛ ርዕዮት ዓለሞች ውስጥ የካፒታሊስት እና የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለሞች ቀዳሚዎች ነበሩ። አውሮፓን መሻገር የጀመረው የኢንዱስትሪ አብዮት ካፒታሊዝምን፣ በአስራዘጠነኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ በጀርመን እና ፈረንሳይ እውቅና ያገኘውን እና በኃላም እኤአ 1917 ¨ሰራተኛው የተቆጣጠረው¨ የተባለው የቀድሞዋ የሶቪየት ሕብረት ¨የቦልሸቪክ¨ አብዮት እስከ እኤአ 1980ዎቹ መጨረሻ ድረስ መላው ዓለምን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅኖውን በማሳረፍ የብዙ አገሮችን ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ቅርፅ ለመቀየር ችሏል።
በኢትዮጵያም በ1933 ዓም ፋሽሽት ጣልያን ከኢትዮጵያ ከተባረረች በኃላ ኢትዮጵያ በቀጥታ የገባችው ለአመታት ከኢንዱስትሪው አብዮት ተለይታ እንደመኖሯ ለዘመናዊ ትምህርት፣ለኃይል ማመንጫ እና ለመንገድ ስራዎች ነበር።በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ወደ ባህር ማዶ ለትምህርት የሄዱ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ከሰለጠኑት አገሮች የእድገት ደረጃ ጋር ሲያነፃፅሩ የኢትዮጵያ ሁኔታ ማነሱ ብቻ ሳይሆን የለውጥ አስፈላጊነቱ አንገብጋቢው የወቅቱ ጥያቄ ሆነ።ስለሆነም የባእዳኑ የርዕዮተ ዓለም ፍትግያ ኢትዮጵያን ለማሳደግ በሚል ብርቱ ምኞት ታጅቦ ወደ አገራችን ገባ። ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የሶሻሊስት አስተሳሰብ በበቂ ሁኔታ ውይይት ተደርጎበት ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሳይፈተሽ እና ሳይቃኝ በወቅቱ የውጭ አገራት መፃህፍትን ማንበባቸው እና ዘመናዊ ትምህርት መቅሰማቸው ብቻ ታሳቢ እየተደረገ በወጣቱ ኢትዮጵያዊ ዙርያ አገሪቱን ከ1933 ዓም ጀምሮ ሲመራ የነበረውን የዘውድ ስርዓት ማስወገድ የሚል ብቸኛ ዓላማ እንዳነገበ የጠራ የርዕዮተ ዓለም መንገድ ሳይኖረው ግብታዊው አብዮት የካቲት፣1966 ዓም ፈነዳ።
በ1966 ዓም የፈነዳው አብዮት ከአገር ውጭ እና በአገር ውስጥ የነበረው ነባራዊ ሁኔታ እና ሂደት በሚገባ መጠናት ያለበት እና በለውጡ ሂደት ላይ የንጉሡ እና የቤተሰቡ ትክክለኛ ሃሳብ ሁሉ ወደፊት ታሪክ በባለሙያዎቹ በሚገባ ሲፈተሽ የምንረዳው ይሆናል።ንጉሡ ቀደም ብለው አራተኛ ክ/ጦር መኮንኖች ተሰብስበው እየዶለቱ መሆናቸውን እያውቁ ¨ተዉ አትንኩ እኛው ያሳደግናቸው ናቸው¨ ያሉበት ሁኔታ እና አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ንጉሡ ስልጣናቸው እንዲገደብ እና አገሪቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ትተዳደር የሚል ሃሳብ አቅርበው ነበር የሚሉት በበቂ ማስረጃ መረጋገጥ ያለባቸው ታሪኮች ሁሉ ወደፊት ለትውልዱ መተላለፍ ያለበት የታሪክ ባለሙያዎች የቤት ስራዎች ናቸው።
የደርግ ፈድራሊዝም ?
ሰኔ 21፣1966 ዓም ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ በሚል ስያሜ ስልጣን የያዘው አካል ለ17 አመታት ያህል ኢትዮጵያን አስተዳደረ።ይህ ስርዓት መሰረታዊ የፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ለውጥ በኢትዮጵያ ላይ ከማምጣቱም በላይ በስልጣን አስተዳደር አዳዲስ አሰራሮችን በወረቀት ደረጃም ቢሆን ማምጣቱ አልቀረም።የገጠር መሬት ይዞታ ወደ ገበሬው የሚያዞረው የየካቲት 25፣1967 ዓም አዋጅ እና የሐምሌ 19፣1967 ዓም ትርፍ የከተማ ቤቶች ይዞታን የሕዝብ የሚያደርገው አዋጅ ከመሰረታዊ ለውጦች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው።
ደርግ በብሄር ብሔረሰቦች ጉዳይ ከህወሓት የሚለየው ህወሓት በየዓመቱ በብሄር በሄረሰብ ስም ጭፈራ እና ድግስ ሲያሳምር፣ደርግ ግን የብሔር ብሔረሰቦች ኢንስቲትዩት መስርቶ በኢትዮጵያ ያሉትን ብሔር ብሔረሰቦች ታሪክ፣ባህል እና ትስስር ያጠና ነበር።ይህ ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ መኖራቸው በመሃል አገር ሕዝብ በብዛት የማይታወቁ በዳር አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ፣ባህል እና ውርስ የሚያሳይ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆነ በጋዜጠኛ ብዙ ወንድም አገኘሁ የሚዘጋጅ እና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዘወትር ሐሙስ የሚተላለፍ ¨ ተጉአዥ ካሜራችን¨ የተሰኘ ፕሮግራም ያስተላልፍ ነበር።በአስተዳደር በኩልም ለኢትዮጵያ እንግዳ ከሆነው ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ለውጥ ባሻገር ደርግ ያመጣው አዲስ ነገር ¨የእራስ ገዝ¨ የሚል የአስተዳደር ዘይቤ ነበር። የእራስ ገዝ የተሰጣቸው የአስተዳደር ቦታዎች ከሚጠቀልላቸው ውስጥ ድሬዳዋ፣ጋምቤላ፣አሰብ እና ኤርትራ የሚጨምር ሲሆን በእነኝህ ቦታዎች ያሉት የተለዩ መብቶች ከጠቅላላው የደርግ መንግስት አስተዳደር ግዛቶች አንፃር የተለየ አይነተኛ እና እውነተኛ መብቶች ማግኘት ቢያስቸግርም በመርህ ደረጃ ግን የተቀመጡ መብቶች ነበሩ።ጃምሮው ግን የደርግ ፈድራሊዝም ጅማሮ ብለን ልናልፈው እንችላለን።
የህወሓት ጎጥን መሰረት ያደረገው ፌድራሊዝም ሞት
ህወሓት በ1967 ዓም አፉን ያሟሸው ስለ ጎሳ ፖለቲካ በማውራት ነው።እዚህ ላይ ስለ ብሔር ብሔርሰብ መናገር እና ስለ ጎሳ ማውራት ይለያያል።ህወሓት ቋንቋን መሰረት ያደረገው ማንፈስቶው በ1967ዓም ሲያወጣ ወዳጅ እና የምታገልለት ያለው የትግርኛ ተናጋሪውን ኢትዮጵያዊ ሲሆን ¨ጠላት¨ብሎ የሚፈይደው ደግሞ በዋናነት የአማርኛ ተናጋረውን የአማራ አማርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን ነው።
ህዳር 29፣1987 በህወሓት አጠራር ታሪካዊ፣በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መከፋፈል ቀን ተብሎ የሚታወቀው እና በአንቀፅ 29 ላይ ከተጠቀሰው የመገንጠል መብት ጨምሮ ኢትዮጵያን በቋንቋ የሚከፋፍል የፈድራል አስተዳደር መታወጁ ኢትዮጵያ ቀደም ብላ የማታውቀው እንግዳ የሆነ አስተዳደር በህወሓት ተጣለባት። ይህ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ የሚኖረው አሉታዊ ተፅኖ አደገኛ መሆኑ ቢታወቅም አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች ተፅኖ ፈጣሪ መንግሥታት ከዳር ቆመው ከማየት ባለፈ ኢትዮጵያ በጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ማለፍ ትልቅ ተሞክሮ እያሉ መመፃደቅ ጀመሩ።አንዳንድ ዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ ምሁራን ግን ጎሳን መሰረት ያደረገው አስተዳደር ውሎ አድሮ ለኢትዮጵያ ትልቅ አደጋ እንደሚያስከትል እና እራሱ ህወሓትን ይዞት የሚሄድ ጎርፍ እንደሚሆን የትነበዩም ነበሩ። ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ከውጭ የተጫነ አስተሳሰብ የሚያስከትለውን አደጋ እንደሚከተለው ይገልፀዋል።
¨ከአገዛዞች መቀየር በኋላ በየአገሮች በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት አቀነባባሪነት የሚወጡትና ተግባራዊ የሚሆኑት ፖሊሲዎች በሙሉ የቴክኖክራቶች ጫወታዎች እንጂ በምድር ላይ የሚታየውን የህዝቦችን ችግር መፍታት እንዳልቻሉ ነው የምናየው። በታሪክ ውስጥም ቴክኖክራሲያዊ የኢኮኖሚ ሞዴል የአንድን አገር ህዝብ ችግር የፈታበት ቦታና ጊዜ የለም። ቴክኖክራቶች ስለቁጥር እንጂ ስለ ሰው ልጅና ስለስልጣኔ ብዙም ስለማይገባቸው ተግባራዊ የሚያደርጉት ፖሊሲ በሙሉ ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል እንጂ በፍጹም ሊፈታው አይችልም። በተጨማሪም የአገራችን የተወሳሰበ ችግር በአንድ ትልቅ ፕሮጀክትና ወይም ደግሞ እዚህና እዚያ በሚተከሉ ትናንሽ ፕሮጀክቶች ሊፈታ እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል። ኢኮኖሚያዊ ክንውን ከህብረ-ብሄር ግንባታ ጋር እስካልተያያዘ ድረስ ትርጉም ሊኖረው በፍጽም አይችልም። ስለሆነም ሰፊውን ህዝብ ያስቀደመና ለሁሉም የሚያመች ቆንጆ አገር ለመገንባት ከዚህ ከተክኖክራሲያዊ ሞዴል ባሻገር ማየትና ማለም ያስፈልጋል። በዚህ መልክ ብቻ ወደ ተፈለገው ዕውነተኛው ነፃነት ማምራት ይቻላል። የተከበረችና የምትፈራ አገርም መገንባት ይቻላል.....አምባገነንነትን እቃወማለሁ፣ ነፃነትን አመጣለሁ ለሱም ጠበቃ የቆምኩ ነኝ የሚል ኃይል ሁሉ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተስፋፋው የተዛባ ስርዓትና ለብዙ ህዝቦችም ነጻነት ጠንቅ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ እንዴት ዕውነተኛ ነፃነት ሊመጣ እንደሚችልና ተግባራዊም እንደሚሆን ማስረዳት ያስፈልጋል¨ ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ፣ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ፣ ጥር 14፣2014።
ከላይ የተጠቀሰው የዶ/ር ፈቃዱ በቀለ ፅሁፍ ላለፉት 40 አመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለፈበትን ውጣ ውረድ የሚያመለክት ነው። ቀደም ብሎ በሶሻሊዝም ስም ቀጥሎ በዓለም ባንክ አይዞህ ባይነት የጎሳ ፖለቲካ የተፈራረቀባት ኢትዮጵያ የእራሷን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ አስተዳደር ሲፈራረቅባት ይሄው አሁን ላለንበት የህውሃት የጥፋት ድግስ ደረጃ አድርሶናል።ህወሓት ይህንን ያደረገው ሕዝቡን ከፋፍሎ ለመግዛት ካለው እቅድ መሆኑ የታወቀ ነው።ዶ/ር ወንድወሰን ተሾመ በቪየና ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፓሎጂ ትምህርት ክፍል ተመራማሪ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2008 ዓም በዓለም አቀፉ ሰብአዊ ሳይንስ የምርምር መፅሄት ላይ የኢትዮጵያን የኢህአዴግ/ህወሃት የጎሳ ፖለቲካ በሚገልፅ ያወጡት የጥናት ፅሁፍ ገፅ 11 ላይ እንዲህ የሚል ይገኝበታል።
” የጎሳ ፈድራሊዝም የህወሃት ‘ከፋፍለህ ግዛ’ ፖሊሲ ሲሆን የተዋቀረበት ዋናው ምክንያትም ስርዓቱ የራሱን ስልጣን ለማስጠበቅ ነው።ሁኔታው ግን አገሪቱን እንዳትከፋፈል ያሰጋል” ያላል። (ጉዳያችን፣ጥር፣2015)።
”…ethnic federalism is the ”divide and rule” policy of the TPLF designed to strength its own position and it might lead the country in to disintegration” International Journal of Human Sciences (2008, 11p).
ህወሓት ህዳር 29፣1987 ዓም የጎሳ ፈድራሊዝም ሲታወጅ (ቀድሞ የታወጀ ቢሆንም ለይስሙላ ቢደረግም ) አንድ ምንነቱን በአግባቡ ያልተረዱ ተሳታፊ ጋቢያቸውን መሬት ሲጥሉ እና ሲዘሉ ያሳይ እንጂ በወቅቱ አደጋው የታያቸው ሁሉ ይህ ጋቢ ጥሎ መዝለል ነገ ሕዝብ ከህዝብ አጋጭቶ ኢትዮጵያን አደጋ ላይ እንዳይጥል ስጋት ያደረባቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን ነበሩ።የተፈራው አልቀረም ላለፉት 24 አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ጎሳ ከሌላው መጋጨት እና መጋደል የተለመደ የኢትዮጵያ ዜና መሆን ጀመረ።በኢትዮጵያ የህወሓት የጎሳ ፈድራሊዝም በፈጠረው አለመረጋጋት እና የህዝብ መፈናቀል ሳብያ የተሰደደው፣የሞተው እና ንብረቱን ያጣው ኢትዮጵያ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው።ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ህወሓት የሌላውን ሕዝብ የእርስ በርስ ግጭት በስርዓቱ ሳብያ ይፈጠር እንጂ አደጋው ለስልጣኑ የሚያሰጋው አልመሰለውም ነበር። ይልቁንም ህወሓት ሕዝብ ሲጋጭ እርሱ አስታራቂ እየሆነ የመኖር ሕልም እንጂ እሳቱ ዞሮ የስልጣን ምህዋሩን ያናጋዋል ብሎ አስቦ አያውቅም።የሆነው ግን ቀድሞ የተፈራው እና የተተነበየው ሆነ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ህወሓት የጎሳ ፖለቲካውን እያወደሰ ነፍጠኛ ያለውን እየገፋ የሚኖር አድርጎ ቢያስብም ሕዝብ ግን የጎሳ ፖለቲካውን በአራሱ እያፈረሰ ህወሃትን በመቃወም በተፃራሪ መንገድ ቆመ።ህወሀትም ሲመፃደቅበት የነበረው ጎሳን መሰረት ያደረው ፈድራሊዝም በያዝነው ዓመት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የህወሃትን የጎሳ ፖለቲካ በእራሱ ማፍረስ ጀምሯል።እስካሁን የኦሮምያ፣የአማራ፣የጋምቤላ እና የሱማሌ ክልል ጎሳን መሰረት ያደረገ ፈድራሊዝም ሙሉ በሙሉ በመሬት ላይ የፈረሰ ሲሆን ህወሓት እነኝህን ቦታዎች በወታደር ኃይል ለመምራት እየሞከረ ሲሆን ይህ አካሄድ ስርዓቱን ወደ ፍፁም ፋሽሽታዊ ስርዓትነት ለመቀየሩ ብዙዎች ይስማማሉ።በእዚህ ዓመት ብቻ ህወሓት የጎሳ ፖለቲካን ለማስፈን ከአንድ ሺህ በላይ ኢትዮጵያንን በጥይት መግደሉ ምን ያህል ለስልጣኑ እንደሚንገበግብ እና የጎሳ ፈድራሊዝም የሚለው የስልጣን ማቆያ መሳርያ ብቻ መሆኑን ያመላከተ ክስተት ሆኗል።
ዛሬ ላይ የህወሓት የጎሳ ፖለቲካ ኢትዮጵያን ለ25 ዓመታት ያመሰው የጎሳ ፖለቲካ መሬት ላይ ሙሉ በሙሉ ፈርሷል።የቀረው የህወሓት የእጅ ቦርሳ ላይ የሚገኝ ወረቀት እና በሚቆጣጠረው የቴሌቭዥን ጣቢያ ላይ ብቻ ቀርቷል።ህወሓት ይህንን ሊክድ ይሞክራል።እውነታውን ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ እየተመከተ ነው።አሁን ያለንበት ጊዜ የህወሓት አገር አጥፊ የጎጥ ፖለቲካን ሕዝብ አልቀበልም ብሎ ተአስቶ ያፈረሰበት ጊዜ ነው።አሁን ኦህዴድ ቢሮ የለም፣ዛሬ ብአዴን አብዛኛው አባሉ ከህዝብ ጎን ቆሟል።ጋምቤላ በህውሃት ወታደሮች በደረሰው እልቂት የአንድ ቡድን ተገዢ መሆን በቃኝ ብሏል። ለእሩብ ክ/ዘመን ኢትዮጵያን ያመሰው የህወሓት ጎጥን መሰረት ያደረገ ፌድሬሽን መሬት ላይ ፈርሷል።ህወሓት እጅ ወረቀቱ ብቻ ቀርቷል።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment