ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, July 2, 2016

የሃይማኖት አባቶች በአዲስ አበባ በፈረሱት ቤቶች ዙርያ ዝም ሊሉ አይገባም። (የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)

ቤታቸው ፈርሶ ሜዳ ላይ የተበተኑ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ላፍቶ ሰኔ/ 2008 ዓም 
  • ለእዚህ ያህል ሕዝብ ላለቀሰበት፣ለሞተበት እና ለተሰደደበት ጉዳይ የሃይማኖት አባት ስሜቱ ተነክቶ ጉዳዬ ብሎ መግለጫ አለመስጠት፣ሄዶ አለማፅናናት፣ በዳዮችን በግልፅ አለመውቀስ ትልቅ የሞራል ውድቀታችን አንዱ ማሳያ ነው።


በአዲስ አበባ ከገርጂ እስከ ቡራዩ በሺህ የሚቆጠሩ ቤቶች በስርዓቱ ፈርሰዋል።በተለይ ሰሞኑን ከላፍቶ ቀርሳ ኮንቶማ ከ30 ሺህ ሕዝብ በላይ ቤት እየፈረሰ ነው።በእዚህ ሂደት ሁለት ቀሳውስት ጨምሮ አብያተ ክርስትያናት የመፍረስ ዕጣ ተፈርዶባቸው ምናልባት ሰዓታት እየጠበቁ ነው አልያም ፈርሰዋል።የኢሳት ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ከስፍራው ያነጋገራቸው አዛውንት አናግሮ የገለፁለትን በፌስ ቡክ ገፁ አርብ ሰኔ 24/ 2008 ዓም እንደሚከተለው ገልፆታል 

´´ ከላፍቶ ቀርሳ ኮንቶማ አንድ አባት አናግሬ መጨረሴ ነው። ስሜት ይረብሻል። እውነት በመዲናችን፡ በአፍሪካ መናገሻ፡ በአዲስ አበባ እንዲህ ዓይነት ግፍ ሲፈጸም መስማት ያማል። አባት እንደሚሉት የ3 ቀናት አራስ እቤቷ እንዳለች ላይዋ ላይ ቤት አፍርሰው ህይወቷ አልፏል። ሁለት ቄሶች በፖሊስ ጥይት ተገድለዋል። 2 ህጻናት በግርግር በአከባቢው በሚገኝ ወንዝ ገብተው ሞተዋል። በርካታ ወጣቶች በድብደባ ብዛት አቅላቸውን ስተው ህክምና ተነፍገው በፖሊስ ጣቢያ ስቃይ ላይ ናቸው።´´


አዲስ አበባ የሚታተመው አዲስ አድማስ በቅዳሜ ሰኔ 25/2008 ዓም ´´20 ሺ ቤቶች በሚፈርሱበት ክ/ከተማ የሰዎች ህይወት አልፏል´´ በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ ላይም የድርጊቱን ግፍ በትትክክል የሚያሳይ ነው።ባጠቃላይ ጉዳዩ ፀሐይ የሞቀው ዜና ነው። ሕዝብ እያለቀሰ ነው።መሬቱን እየተነጠቀ ንብረቱን ሳያወጣ በላዩ ላይ ቤቱ ሲፈርስ እሪ! እያለ ነው።ይህንን ግፍ ለመቃወም የሃይማኖት አባቶች ሚና ቀላል አይደለም።በእዚህ የጭንቅ ሰዓት ሕዝብ የሃይማኖት አባቶቹን ሲመለከት ይፅናናል።የሃይማኖት አባቶች በቦታው ላይ በመገኘት የሚከተሉትን ተግባራት መስራት ይችላሉ።

1/ በቦታው ተገኝቶ በፈረሱት ቦታዎች ሕዝቡን በሃይማኖት ሳይለዩ ማፅናናት፣

2/ ተግባሩን መኮነን ይህም በቃል እና በፅሁፍ ለሚመለክተው ባለስልጣናት መግለፅ ይህንንም ለሚድያ መግለፅ እና 

3/ ሜዳ ላይ ለተበተኑት አፋጣኝ እርዳታ እንዲደርስ የአዲስ አበባ የሃይማኖት አባቶችን ማስተባበር እና ማድረስ የሚሉት ቀዳሚ ናቸው።

ባጠቃላይ እነኝህ ተግባራት እጅግ በጣም አስፈላጊ እና ወሳኝ ተግባሮች ናቸው።ይህንን ማድረግ ከስርዓቱ ግልምጫ ያስከትል ይሆናል። ሆኖም ግን ሕዝብ የማዳን ሥራ ነው እና ሌላ ምንም አይነት አማራጭ መንገድ የለውም።ከሁሉም የሚገርመው ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈርስ እየተነገረ እና ሁለት ቄሶች መሞታቸው እየታወቀ ዝም መባሉ ነው። የዝምታው ጥግ የት ነው? ድሃ ተበደለ ፍርድ ጎደለ ብሎ መጮህ የማን ሥራ ነው? ዛሬ ያልጮህንለት ሕዝብ ነገ ሰው በላው ስርዓት ወደ እራሳችን ሲመጣ (ይህ አይቀርምና) የትኛው ሕዝብ ከእኛ ጋር ይቆማል? ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው እና ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።ለእዚህ ያህል ሕዝብ ላለቀሰበት፣ለሞተበት እና ለተሰደደበት ጉዳይ የሃይማኖት አባት ስሜቱ ተነክቶ ጉዳዬ ብሎ መግለጫ አለመስጠት፣ሄዶ አለማፅናናት፣ በዳዮችን በግልፅ አለመውቀስ ትልቅ የሞራል ውድቀታችን አንዱ ማሳያ ነው።

ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...