ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, March 25, 2015

አቡነ እንጦስ ከኖርዌይ መልስ ከእንግሊዝ እንዲወጡ መገደዳቸው ተሰማ


አቡነ እንጦስ 

 በሀገር ቤት ቅዱስ ሲኖዶስ ስር የሚገኘው የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ከእንግሊዝ እንዲወጡ መገደዳቸው ተሰማ።ሊቀ ጳጳሱ ከለንደን ደብረ ፅዮን ማርያም ጋር በተያያዘ ከምዕመናን ጋር በተነሳ አለመግባባት ጉዳዩ እስከ ፍርድ ቤት የደረሰ የሕግ ጉዳይ እንዳለባቸው ይታወቃል።

የለንደን ደብረ ፅዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከአመታት በፊት ከፍተኛ የምዕመናን ትብብር በታየበት መልኩ ለከተማዋ ''አይን'' በሚባል ቦታ በከፍተኛ ገንዘብ መገዛቱ ይታወቃል።ግዥው ከተፈፀመ በኃላ ግን የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ ሆነው የቆዩት አባ ግርማ ከብዙ ምዕመናን ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ለቤተ ክርስቲያኑ ግዥ እስከ 90ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ በማውጣት አስተዋፅኦ ያደረጉ ምዕመናንን ጨምሮ  ከቤተ ክርስቲያን እንዲወጡ መደረጋቸውን ብዙዎች በምሬት ይገልፃሉ።

በቅርቡ የእንግሊዝ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከአንድ ዓመት በላይ በውጭ በድንኳን ፀሎት ሲያደርጉ የነበሩ ምዕመናን ከያዝነው አቢይ ፆም ጀምሮ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ፀሎት እንዲያደርጉ ወስኗል።ሆኖም ውሳኔው ተግባራዊ አለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል።በተለይ አባ ግርማ በሀገር ቤት እና በውጭ በሚገኙ አባቶች መካከል ልዩነትን በማስፋት የሚወቀሱ አባት ናቸው።

ከእዚህ በፊት በሀገር ቤት ያሉትን አባቶች እና ሲኖዶስ ከአንድ አባት ቀርቶ ኢ-አማኒ የማይጠበቅ ፀያፍ ስድብ ሲዘነዝሩ የተመለከቱ ሰዎች ዛሬ እራሳቸውን ሀገር ቤት ካሉ አባቶች ጋር አስጠግተው በውጭ ያሉ አባቶችን ሲነቅፉ መስማታቸውን ይናገራሉ።ለምሳሌ ከሶስት ዓመታት በፊት በስዊድን መድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅነት በተዘጋጀው የአውሮፓ ዓመታዊ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ አባ ግርማ ከለንደን መጥተው በምዕመናን ፊት  ሀገር ቤት የሚገኙትን አባቶች ሲወቅሱ፣ፈፅመው አብረው እንደማይሰሩ እና እራሳቸውን በስደት ወደ አሉ አባቶች አስጠግተው ሲናገሩ በአባቶች መካከል ልዩነት የማስፋት ተልኮ የያዙ ናቸው ብለው ብዙዎች እንዲያስቡ አድረገው ነበር።ትናንት በስፋት የተሰማው የአቡነ እንጦስ ከእንግሊዝ እንዲወጡ መገደድ ምክንያቱ በጠራ መልኩ አይገለፅ እንጂ ከቪዛ ጋር በተያያዘ ነው የሚሉ እና ''እንዳይመለሱ'' የሚል ፓስፖርታቸው ላይ ተመቷል እስከሚለው ድረስ የሚናፈሰው ዜና ጉዳይ እስካሁን አልታወቀም።በተለይ ከአንድ ሳምንት በፊት በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ለምዕመናን ሳይነገር የተወሰኑ ሰዎች በስልክ ተጠራርተው ከተቀበሏቸው በኃላ ''በሰዓታት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ከፈቱ'' ተብሎ ሲነገር በብዙዎች ዘንድ ግርምትን ፈጥሮ ነበር።ለእዚህም መገረም ምእመናን ሶስት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ።

የመጀመርያው ምክንያ በኦስሎ ከተማ ውስጥ ከአስራ አምስት አመታት በላይ የዘለቀ የቅዱስ ገብርኤል እና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በአቡነ ኤልያስ ቡራኬ ለምዕመናን አገልግሎት እየሰጠ እና በቅርቡም ከአንድ ወር በኃላ እስከ አንድ ሺህ ሕዝብ ይይዛል ተብሎ በሚገመተው በከተማዋ በሚገኘው ትልቁ ካቴድራል ''ማየሽቷ ሺርከን'' ለመዞር በዝግጅት ላይ መሆኑ እና ምዕመናን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የህንፃ ዲዛይን የጠበቀ ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ለመስራት በከፍተኛ ዝግጅት ላይ ሆነው ሳለ በከፍተኛ ሚስጥር ለጥቂት ሰዎች በተደረገ የ''ቫይበር'' እና ፌስ ቡክ ጥሪ ሌላ ቤተ ክርስቲያን ለመክፈት በሚል ምዕመናንን ለመክፈል መሞከር ለምን አስፈለገ? የሚል ሲሆን ሁለተኛው አቡነ እንጦስ መጋቢት6/2007 ዓም በኦስሎ በተገኙበት ወቅት ምዕመናን አሁን ስለሚመሰርቱት ቤተ ክርስቲያን ብዙ የማያውቁት ጉዳይ እንዳለ ለማስረዳት የሞከሩ ምዕመናንን የሁሉም አባትነት ስሜትን በያዘ መልኩ ለማናገር ፈቃደኛ አለመሆናቸው፣ 


ሶስተኛው ገና ''በድቁና በአግባቡ ማገልገል አለብኝ አሁን ይህ አይገባኝም'' ያላቸውን ወጣት ''ሊቀ ሕሩያን'' (የምርጦች አለቃ) የተሰኘውን የቤተ ክርስቲያን ማዕረግ እና ''ቅስና'' ሰጥቻለሁ ማለታቸው በብዙ ምዕመናን ዘንድ ግራ መጋባትን ፈጥሯል።በተለይ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንፃር አንድ ቤተ ክርስቲያን ሲከፈት ቀድሞ የነበረው ሊቀ ጳጳስ ጋር ተመካክሮ፣ተከባብሮ እና ተፈቃቅዶ እንጂ በግፍያ እና በአመፅ መሆን እንደሌለበት የታወቀ ነው።በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በአንድ ሲኖዶስ ስር ያሉ ሊቃነ ጳጳሳትም ቢሆኑ አንዳቸው አንዳቸው ሃገረ ስብከት ለአገልግሎትም ቢሆን ሲሄዱ የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ ፍቃድ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል።

ኢትዮጵያውያን በእምነትም ሆነ በማናቸውም ጉዳይ ህብረታቸውን የበለጠ ማጠንከር፣ የምዕመናንን አንድነት የሚሸረሽሩ ማናቸውንም ድርጊቶች በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መግታት እና አጥፊዎችን በማኅበራዊ ተግሳፅ ማረም ተገቢ እንደሆነ የብዙዎች እምነት ነው።ከአቡነ እንጦስ ጋር ተያይዞ የተነሳው ከእንግሊዝ እንዲወጡ የመገደድ ሂደትም ሆነ የለንደን ደብረ ፅዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ዞሮ ዞሮ የሚጋፋው የኢትዮጵያዊነትን እና የክርስትና ክብርን ስለሆነ ጉዳዩን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መመልከት ተገቢ ነው።በነገራችን ላይ የእንግሊዝ ፍርድ ቤት በለንደን ደብረ ፅዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ በመጪው ዓርብ ችሎት እንደሚቀመጥ ለማወቅ ተችሏል።


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
መጋቢት 16/2007 ዓም (ማርች 25/2015)